የዕለቱ ምንባቦች ፦
፩ ቆሮ፡ ም. ፲፥ ቍ. ፩-፲፬ ራእየ፡ ዮሐ፡ ም. ፲፬፥ ቍ. ፩- ፮ ግብ፡ ሐዋ፡ ም. ፬፥ ቍ. ፲፱-፴፩ ማቴዎስ፡ ም. ፲፪፥ ቍ.፩-፳፪
መዝሙሩ ፦ “ ወመኑ መሓሪ ዘከማከ ፤ ወኵሉ፡ ይሴፎ፡ ኪያከ ”
የወንጌሉ ንባብ ማሳረፊያው “አሕዛብም በስሙ ተስፋ ያደርጋሉ።” (ይኽ ቃል ከኢሳይያስ 42፡1-6 ድረስ ይገኛል።)
ተስፋ ምንድነው?
ተስፋ በሚታወቅ ነገር ላይ የሚኖር መተማመን ነው።
Ἐλπίς (ኤልፒስ) የሚለው የግሪኩ ቃል መተማመን የሚል ፍቺም ይይዛል። በማይታወቅ፣ ባልተቀመሰ፣ ምልክቱ ባልታየ ነገር ላይ ተስፋ አይደረግም። የማያውቀውን፣ ያልቀመሰውን፣ ምልክቱን ያላየውን ነገር ይኾናል ብሎ የሚተማመን ሰው “የቅዠት ባለቤት” እንጂ “የተስፋ ሰው” አይባልም። ቅዠት የካርል ማርክስ Classless Society ኾነ፣ የፕሌቶ Republic፣ ወይም የአክራሪ ካፒታሊስቶች Free Market Economy እውን የማይኾኑት የቢኾን ዓለም ቅዠቶች እንጂ ተስፋ ስላልኾኑ ነው።
በብሉይ ኪዳን የነበረው የእግዚአብሔር ሕዝብ፣ የእግዚአብሔርን ማዳን ከአባቶቹ ሰምቷል፤ የእስራኤል ለቃልኪዳኗ አለመታመን የእርሱን (የእግዚአብሔርን) ታማኝ አፍቃሪነት ሳያስቀረው ምድረ ርስት ከነዓንን አውርሷቸው እንደነበረ ያውቃል፤ ይኽ በጭላንጭል የሚያውቀው የእግዚአብሔር ታማኝነት የተስፋው ምሶሶ ነበረ። ስለዚኽም፣ በነበረበት ውስጣዊ ፖለቲካዊ ምስቅልቅልና የሮማውያን ቅኝ ግዛት ውስጥ ኾኖም ነቢያቱ “የተቀጠቀጠውን ሸምበቆ የማይሰብረው፣ የሚጤስን ጧፍ የማያጠፋው፣ የእግዚአብሔር ምርጥ ብላቴና፣ እግዚአብሔር የቀባው መሢሑ ይመጣል!” እያለ ተስፋ የሚያደርግ፣ የተስፋ ሕዝብ ነበረ።
ተስፋ ዘላቂ መፍትሔ ላይ ያረፈ ዓይን ነው።
በጥንታዊ ግሪክ ሥነ ጽሑፍ ውስጥ ከማይገኙ ቃላት መካከል አንዱ ተስፋ ነው ይባላል። ምክንያቱም ከአይሁድ እምነት ውጪ የነበረው አሕዛቡ ዓለም ተስፋ የሚባለውን ነገር በፅንሰ ሐሳብ ደረጃ እንኳ ያውቀው ነበረ ብሎ ለመናገር አዳጋች ነው። የዚኽም ምክንያቱ ከሞት የሚሻገር ነገር አለማየታቸው ነው። ንጉሦቻቸውን በወርቅ በተጌጡ መቃብሮች ከብዙ ጌጣጌጥና ንብረት፣ ምግብና መጠጥ ጋር ቢቀብሩም አንዱም ንጉሥ ተነሥቶ የተጣመመ ፍርድ ሲያቃና ወይም ሀገሩን ከጠላት ሲከላከል አላዩም። ስለዚኽም በአብዛኛው ሕዝብ ዘንድ ሞት የመጨረሻው ፍጻሜ፣ የሰው ኑሮ ከንቱነት ማሳያው ነጥብ ነበረ። ከዚኽች ከሚያዩዋትና ከሚያውቋት ውጪ ያለውን ነገር በሥነ ጽሑፎቻቸው እንኳ አያዳንቁትም። ሆሜር በተባለው ባለቅኔ የተደረሰው ኦዲሴ የተሰኘ ሥራ ውስጥ አኪሊስ የሚባል ጀግና ገጸ ባሕርይ “በሞት ሀገር ጌታ ከምኾን በምድር ላይ ባርያ ኾኜ ልኑር” ማለቱ ተጠቃሽ ምሳሌ ነው። አሕዛብ የሚያዩት የሰው ልጅ ኑሮ የመጨረሻ ነጥብ ሞት ብቻ ነበረ። ዓይኖቻቸው የሞትን ጨለማ አልፈው ማየት አልተቻላቸውም። ስለዚኽም ከተቻለ ነገን በልቶ፣ ጠጥቶ፣ ተደስቶ፣ ሕይወትን እንደሸንኮራ ምጥምጥ አድርጎ እስከሞት ድረስ ማጣጣም፣ ወይም እንደፈላስፎች በትሕርምትና በተመስጦ ይኽን ፈራሽና በስባሽ ዓለም ጥሎ መመንጠቅና በሐሳብ ዓለም ከመዋኘት የዘለለ ነገር ሊያስቡ አልቻሉም። ተስፋ የሚለው ፅንሰ ሐሳቡ ራሱ ለሐሳባቸው እጅግ ሩቅ ነበረ። ቅዱስ ጳውሎስ “የሚያየውንማ ማን ተስፋ ያደርገዋል?” እንዳለ (ሮሜ 8፡ 24)።
እንደኢሳይያስ ያሉ ነቢያት የእግዚአብሔር ሕዝብ ወደ እንዲኽ ዓይነቱ የአሕዛብ አስተሳሰብ እንዳይዘቅጥ ታግለዋል። የችግሩ መንሥኤ ኃጢኣት፣ የችግሩ መፍትሔም እግዚአብሔር መኾኑን አሳስበዋል። የእግዚአብሔር ሕዝብ ዓይኑን በሞት ጨለማ ላይ ከማፍዘዝ የእግዚአብሔር ቃል ሰምቶ የተስፋ ብርሃንን እንዲያይ ጮኸዋል። ድምፃቸውም ወድደው ለሚሰሟቸው የተስፋ ብርሃን ነበረ። “ፍርድ ጎደለብን!” ብለው ለሚቆጩት “በእውነት ፍርድን የሚያወጣ” እግዚአብሔር የቀባው ንጉሥ መሢሑ ይመጣል። “የእግዚአብሔርን ቃል የሚያቀብለን ካህን፣ መንገድ የሚያሳየን ነቢይ አጣን” ብለው ለሚቆጩት እግዚአብሔር “ደግፌ የያዝኹት ባርያዬ፣ ነፍሴ ደስ የተሰኘችበት ምርጤ፣ በእርሱ ላይ መንፈሴን አድርጌያለኹ” ብሎ በእውነት የተናገረለት እውነተኛ ነቢይ ይመጣል። ከርኅራኄውም የተነሣ “የተቀጠቀጠ ሸምበቆን አይሰብርም፤ የሚጤስን የጧፍ ክር አያጠፋም”
የነቢያቱ ጩኸት ምክንያት ሰው ዓይኑን ከእግዚአብሔር ላይ ካነሣ በምድር ላይ መኖር የሚባለው ነገር ሞት በዜሮ የሚያባዛው ትርጉም የለሽ ሩጫ፣ ወይም መልስ የሌለው አስቀያሚ ዕንቆቅልሽ ስለሚኾን ነበረ።
የእግዚአብሔር ቃል ሥጋ ሲኾን፣ የእግዚአብሔር ልጅ የማርያም ልጅ ሲኾን፣ እግዚአብሔር ሰው፣ ሰውም እግዚአብሔር ሲኾን ይኽ ተስፋ ተፈጸመ። የሰው ልጅ ማኅበረሰባዊ የታሪክ የአዙሪት እሥርቤት ተበጠሰ። የችግራችን ምንጭ የነበረው የእግዚአብሔር መታጣት፣ በእግዚአብሔር ልጅ መገኘት መፍትሔ አገኘ። ዓለም ከመፈጠሩ በፊት እግዚአብሔር ያቀዳት ተዋሕዶ ስትፈጸም፣ ቃል ሥጋ ሲኾን፣ ዘለዓለማዊውን የእግዚአብሔርን ልጅ “ኢየሱስ” ብላ ድንግል እናቱ ስትጠራው ጥያቄያችን ኹሉ ተመለሰ። ሐዋርያት ይኽን እግዚአብሔር ለሰው ልጅ የሰጠውን መፍትሔ ለሰዎች ለመንገር ስለጓጉ መደብደባቸው አላሳሰባቸውም፤ ይልቁንም “ጌታ ሆይ! ለመፈወስ እጅኽ ሲዘረጋ፣ በቅዱስ ብላቴናህ በኢየሱስ ስም ምልክትና ድንቅ ሲደረግ፣ ባርያዎችኽ በፍጹም ግልጥነት ቃልኽን እንዲናገሩ ስጣቸው!” ብለው ጸለዩ (ሐዋ 4፡29)። ሊነገር የሚያጓጓ ዜና ነዋ! የችግሮቻችን ኹሉ መፍትሔ! ኢየሱስ ክርስቶስ “ለበሓማን ኮኖሙ ቃለ፤ ለዕውራን ብርሃነ፣ ወለሓንካሳን ፍኖተ፣ ወለዘለምፅ መንጽሒ” እንዲል የኪዳን ጸሎት።
ተስፋ በጽናት ይገለጻል።
ተስፋ አስተማማኙን ዘላቂ መፍትሔ መተማመን ነው። በዚኽ መተማመን ውስጥ የሚኖር ሰው በፍርኃት፣ በተስፋ መቁረጥ፣ በሐዘን፣ በጥላቻ ሊኖር አይችልም። ቅዱስ ጳውሎስ የቆሮንቶስ ምእመናንን የሚያሳስባቸው ይኽንን ነው። ክርስቲያኖች ወደ ኃጢኣት ሸለቆ ወርደን ስንርመጠመጥ የምንገኘው በምሥጢራተ ቤተክርስቲያን፣ በተለይም በቅዱስ ቁርባን፣ ተዋሕዶን ከሚኖረው ጌታ ኢየሱስ ላይ ዓይኖቻችንን ስናነሣና ዙሪያችንን ማማተር ስንጀምር ነው። የልባችን ዓይኖች ጌታ ኢየሱስ ላይ ከተተከሉ ጨለማ ዙሪያችንን ቢከብበንም እንኳ ከጨለማው ሥራ ጋር አንተባበርም፤ ብርሃን ኢየሱስ ክርስቶስ በልባችን አለና። በጥምቀት የለበስነው ጸጋው፣ በቅዱስ ቁርባን የምንቀበለው እርሱነቱ ሞት ቢከብበን እንኳ ከሙት ሥራ ከመተባበር ያድነናል። ከራሳችን ተርፎም ለሌሎች የተስፋ ብርሃናችን ያበራል። ብርሃናችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእኛ ጋር ነውና።
ስለዚኽም፣ ቤተ ክርስቲያን የጌታ ኢየሱስን ቅዱስ ስሙን ሙጥኝ ትላለች። ለአፍታ ከአንደበታችን ደጃፍ፣ ከልባችን ጓዳ እንዳንለየው ታሳስባለች። ቅዱስ ስሙ የደስታችን ምክንያት፣ የመከራችንም ትርጉም ነው። ጣፋጭ ስሙን ትጠራለች፤ ጽኑ ስሙን ትታመናለች፤ ታማኝ ስሙን ተስፋ ታደርጋለች። ድንግሊቱ ቤተ ክርስቲያን የበጉ ስምና የአባቱ ስም በመንፈስ ቅዱስ ግንባሯ ላይ ተጽፎ ሙሽራዋን በጉን በሄደበት እየተከለች ቅዱስ ስሙን ትዘምርለታለች (ራእ. 14፡1-5)። ክርስቲያን መኾን የጌታ ኢየሱስ ቅዱስ ስሙን ተስፋ ማድረግ ነው።
ስሙ ሕይወት ለኾነው ለእግዚአብሔር አብ፣
ጣፋጭ ስሙ ተስፋ ለኾነን ለአንድ ልጁ ለኢየሱስ ክርስቶስ፣
ቤተ ክርስቲያንን በአብና በወልድ ስም ላተማት ለመንፈስ ቅዱስ
ክብርና ምሥጋና ይኹን። አሜን።
No comments:
Post a Comment