Thursday, March 29, 2012

ትምህርት ምን ያደርግልናል?


ቀጥሎ የቀረበላችሁ ጨዋታ ከባለ ቅኔው መንግሥቱ ለማ አባት ከአለቃ ለማ ኃይሉ የተገኘ ነው፡፡ ሙሉ ጨዋታቸውን “ትዝታ ዘአለቃ ለማ” ከተሰኘው መጽሐፍ ታገኙታላችሁ፡፡ የዚህ ጡመራ መታሰቢያነቱ እነርሱ ከሚያውቁት ውጪ ሌላ ዕውቀት ያለ ለማይመስላቸው፣ “መመራመር ብርቁ” ለሆኑ የዐውደ ምሕረትም ሆነ የዐውደ ዕውቀት “አስተማሪዎች” ይሁንልኝ፡፡  



ደጃች ኃይሉ የሸደሆ ገዥ፣ ደጃች ወንዴ ደግሞ የመቄት ገዥ ነበሩ፡፡ ደጃች ኃይሉ የተማሩ ሲሆኑ፣ ደጃች ወንዴ ግን አልተማሩም      ነበር፡፡ ደጃች ከጣቢሽ የተባሉት ደግሞ ሁለቱንም ግዛቶች በአንድነት ይገዙ ስለነበር የሁለቱም ደጃቾች የበላይ ነበሩ፡፡

ሁለቱ ደጃቾች ወደ ደጃች ከጣቢሽ ይሄዳሉ፡፡ ቤተክርስቲያኑ ጊዮርጊስ ነው፡፡ ሁለቱም በቤተክርስቲያን ተገኝተው ይጸልያሉ፡፡ ደጃች ኃይሉ ዳዊት አውጥተው ዳዊታቸውን ይደግማሉ፡፡ መልኩንና ይህን የመሰለውን ሁሉ በመጽሐፍ ይደግማሉ፡፡ ደጃች ወንዴ ደግሞ ትምህርት የሌላቸው ናቸውና “ቅዱስ ጊዮርጊስ የአባቴ አምላክ! ፈጥረህ የት ትጥለኛለህ?” እያሉ ያለ መጽሐፍ በቃል ይጸልያሉ፡፡ በኋላ ሁለቱም ተያይዘው ደጃች ከጣቢሽ ወዳሉበት ይወጣሉ፡፡ ከዚያ ደጃች ወንዴ “ደጃች ኃይሉ፣ መማር ለምን ይበጃል?” አሉ፡፡ ተንኮለኛ ነህ ለማለት ነው፡፡

ደጃች ኃይሉም “ቅዱስ ጊዮርጊስ ፈጣሪዬ! ከማለት ያድናል፡፡” ሲሉ መለሱላቸው ይባላል፡፡

Wednesday, March 21, 2012

አባቴን ሺኖዳን መሸኛዬ

መዝሙረ ፍጥረታት
ቀጥሎ የቀረበላችሁን መዝሙር የደረሰው አባት ለፍጥረታት በነበረው ልዩ ፍቅር የሚታወቀው ቅዱስ ፍራንቸስኮስ ይባላል፡፡ የተወለደው በአሥራ ሁለተኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ሲሆን በአሥራ ሦስተኛው ክፍለ ዘመን በነበረው የቤተክርስቲያን እንቅስቃሴ ታላቅ ሚናን ከተጫወቱ ሰዎች አንዱ ነው፡፡

የዚህ የፍራንቸስኮስ ብሔረ ሙላዱ ጥንተ ነገዱ እንደምን ነው? ቢሉ እነሆ እጅግ በጣም በአጭሩ ይህን ይመስላል፡-
በ1182 ዓ.ም. (አንዳንዶች 1183ም ይላሉ) አሲሲ በምትባለው ዛሬ ጣልያን ውስጥ በምትገኘው ቦታ አንድ ፒየትሮ በርናርዶን የሚባል ሀብታም የጨርቅ ነጋዴ ወንድ ልጅ ተወለደለት፡፡ ይህ ልጅም ክርስትና ሲነሣ ጆቫኒ (ዮሐንስ) የሚል ስም ተሰጠው፡፡ አባቱ ግን ፍራንቸስኮስ ብሎ ሰየመው፤ የዚህም ምክንያቱ አባትየው ፈረንሳይን እጅግ አጥብቆ የመውደዱ ነገር እንደነበር ይነገራል፡፡

ቅዱስ ፍራንቸስኮስ የባዕለ ጸጋ ልጅ ሊያገኘው የሚችለው እንክብካቤና ምቾት ሁሉ ሳይጎድልበት ስላደገ ገንዘብ እንደውኃ መርጨት፣ መዝናናትንና መሽቀርቀርን ማዘውተር ተለይቶ የሚታወቅባቸው የወጣትነት ጠባዮቹ ነበሩ፡፡ ታሪኩን የጻፉልን አበው እንደሚናገሩት የወጣትነት ዘመኑን የመጀመሪያ ዓመታት ያየ ማንም ሰው “ፍራንቸስኮስ ቅዱስ ይሆናል፡፡” ብሎ አይጠብቅም ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ያኔም ቢሆን ለድኾች እጅግ የምታዝን ርኅርኅት ልብ ባለቤት እንደነበረው ሳይጠቅሱ አያልፉም፡፡

Tuesday, March 13, 2012

ጾም ምንድናት?



ዛሬ የማካፍላችሁን ትምህርት ያገኘሁት “ማር ይስሐቅ” ከተሰኘው ባለፈው ጊዜ ስለ ንስሐ፣ ፍቅርና ፈሪሃ እግዚአብሔር ከተማርንበት መጽሐፍ ነው፡፡ ጊዜው የጾም ወቅት ስለሆነ በእኛ በምሥራቃውያን ክርስቲያኖች ዘንድ ደግሞ የጾም ትውፊት እጅግ ይከበራል፡፡ ይህም ጥሩ ልምምድ ነው፡፡ ነገር ግን ጾምን የምንጾመው አባቶቻችን ሥርዓቱን ስለሠሩት ብቻ የምንፈጽመው ግዴታ አድርገን መሆን የለበትም፡፡ አንዳንዶቻችን “ጾም ሳይገባ እንብላ! እንጠጣ!” ብለን የምናካሒደው የቀበላ ሰሞን የግጦሽ ዘመቻ፣ አንዳንዶቻችን ደግሞ ጾም ላለመጾም የምናካሒደው የምክንያት ድርደራና የቅድስተ ቤተክርስቲያንን ትእዛዝ ያለመፈጸም ሽሽት ጾምን ጥቅሟን እንደማናውቅ ይመሰክርብናል፡፡ አንዳንዶቻችን ደግሞ አንደበቶቻችንን ለመቆጣጠር አንዳችም ጥረት ሳናደርግ፣ በምላሳችን የሰዎች ቁስል ላይ ጥዝጣዜን እየጨመርን፣ ፍርድ እያጓደልን፣ ሠራተኞቻችንን እየበደልን፣ ጉቦ እየበላን፣ ሚዛን እያጭበረበርን፣ “በርበሬ ነው፡፡” ብለን ሸክላ እያቀረብን፣ “ቅቤ ነው፡፡” ብለን ሙዝ እየሸጥን፣ በንግድ ስም በአልጠግብ ባይነት ከሚገባን በላይ ትርፍን በመፈለግ ድኃውን እየመዘበርንና እያስጨነቅን ለተወሰኑ ሰዐታት ከምግብ በመከልከላችን ብቻ ጾምን በጥሩ ሁኔታ እየጾምን እንደሆነ እናስባለን፡፡[i] ባጠቃላይ ስናየው ይህ ሁሉ የሚያመለክተው ወደአንድ አቅጣጫ ነው- የጾምን ምንነትና ጥቅም አለማወቃችንን፡፡ 

ስለሆነም ጥቅሙን ዐውቀን ስለምን እንደሆነ እንድንረዳ ስለጾም ምንነት ከአበው ትምህርቶች ጥቂት ፍርፋሪ ብንቀማምስ ለነፍሳችን ጥሩ ስንቅ ይሆነናል፡፡ ቀጥሎ የምናነበውን ትምህርት የምናገኘው “ማር ይስሐቅ” ላይ ነው፡፡ እርግጥ ነው “ማር ይስሐቅ” የተጻፈው በዐቢይነት የመነኮሳትን ሕይወት ለመምራትና ለማረቅ መኾኑ አይካድም፤ ይህ በራሱ ግን ያልመነኮሱና የማይመነኩሱ ሰዎች ሊያገኙበት የሚችሉትና ሊያገኙትም የሚገባቸው ትምህርት የለም አያሰኝም፡፡ በተለይም ደግሞ ክርስትና ራስን የመግዛት ሕይወት ስለሆነ ከመነኮሳት ኑሮ በርግጥ ብዙ የምንማረው ይኖረናል፡፡ ልንማርም ይገባናል፡፡ መጽሐፍ “ተሰአሎ ለአቡከ፤ ወይነግረከ፡፡” (ዘዳግ. 32፣7) (አባትህን ጠይቅ ይነግርህማል፡፡) ይል የለምን?

እነሆ! የአንድ ሺህ ስድስት መቶ ዓመቱ አረጋዊ መጽሐፍ ማር ይስሐቅ አንቀጽ 4 ምዕራፍ 6 ላይ እንዲህ ይላል[ii]፡-

ጥያቄ፡- በክርስትና ሕይወት ተጋድሎ ለመጀመር የሚፈልግ ሰው ሥራውን በምን ይጀምራል?
መልስ፡- ይህማ በሁሉ ዘንድ የታወቀ ነው፡፡ ሰው በሥጋው በኩል የምትዋጋውን የኃጢኣትን ጦር ድል ለመንሣት፣  ፍትወትንም ከእርሱ ለማራቅ በሚያደርገው ተጋድሎ በቅድሚያ የምትመጣው የመታገያ መንገድ በጾም ሥጋን ማድከም ናት፡፡ ዕንቅልፍን ቀንሶ በሌሊት ለጸሎት መትጋትም እንዲሁ ጾምን የምታግዝ መሣሪያ ናት፡፡ በዘመኑ ሁሉ እነዚህን የሚጠብቅ ሰው ንጽሕናን ገንዘቡ ማድረጉ አይቀርም፡፡ ጥጋብ የክፉ ሥራ መጀመሪያ እንደሆነች ሁሉ የዕንቅልፍ ብዛትም ሥጋዊ ፍላጎትን ያበረታዋል፡፡ ስለዚህም ከዕንቅልፍ ቀንሶ ጸሎት ማድረግና ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብ ደግሞ በምግባር በትሩፋት ለማደግ ጥሩ መሠረት ይሆናሉ፡፡

ጾም የምግባር የትሩፋትን ሥራ ሁሉ ለመሥራት ታነቃቃለች፡፡ እርሷ እንደ ትጉኅ ገበሬ ራሳቸውን ለክርስቶስ ጠምደው ለሚኖሩ አክሊላቸው ናት፡፡ ዳግመኛም በክርስትና ሕይወት ለሚደረግ ተጋድሎ መጀመሪያ፣ ስለኃጢኣታችንና ስለወገኖቻችን ልናወርደው የሚገባንን እንባ የምናገኝባት የጸሎት ምንጭ፣ የድንግልናና የንጽሕና ጌጣቸው፣ የንጽሕና መገለጫ፣ የወንጌል ሥራ መጀመሪያ፣ አርምሞን የምታስተምር ናት፡፡

ጤነኛ ዓይኖችን ዘወትር ብርሃን ማግኘት እንደሚስማማቸው ሁሉ ትክክለኛ ጾምም ጸሎትን ማዘውተር ይስማማታል፡፡ ሰው ጾም በጀመረ ጊዜ ኅሊናው በጸሎት ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር ይጀምራል፡፡ ከዕንቅልፉ ቀንሶም ይጸልያል፡፡ ሰው አብዝቶ አፉን በጾም ከምግብ የከለከለውን ያህል በዚያው መጠን በትሕትና ሁኖ እያለቀሰ መጸለይን ገንዘቡ ያደርጋል፡፡[iii]  ጸሎታትም ከልቡናው ይታሰባሉ፡፡ ልቡ ጸሎታትን በማሰላሰል ይጠመዳል፡፡ በፊቱ ላይም ትዕግስት ትነበባለች፡፡ ስለኃጢኣቱ ያዝናል፡፡ ክፉ ሐሳቦችም ይርቁለታል፡፡ ከንቱ ንግግርም ትሸሸዋለች፡ 

ጾም የበጎ ምግባራት ግምጃ ቤት ስለሆነች ሰይጣን ከበጎ ምግባራት እንድንርቅ ሊያደርገን ሲሻ በቅድሚያ የሚያደርገው እርሷን እንድንንቅና እንድናቃልል መጋበዝ ነው- ምክንያቱም የጾምን ምንነቷን ዐውቆ ጥቅሟን ተረድቶ የሚጾማት ሰው የበጎ ነገሮች መከማቻ በሆነች ቤት ውስጥ ይኖራልና ከሥጋ፣ ከዓለምም ሆነ ከሰይጣን ለሚመጡለት የክፉ ፈቃድ ጥሪዎች አይገዛም፡፡ በዚህም የተነሣ ጾምን የሚያቃልል ሰው በፈቃዱ በጎውን ነገር ሁሉ ከራሱ አራቀ፡፡ አዳምን “ከእርሷ እንዳትበላ!” ብሎ በማዘዝ እርሷ እኛን ለክፉ ፈቃድ ከመገዛት እንድትጠብቀን እኛም እርሷን በመታዘዝ እንድንጠብቃት ከጥንት ጀምሮ ከፈጣሬ ዓለማት ተሰጥታናለችና፡፡

የሁላችን አባት አዳም እርሷን ባለመጠበቁ በሰይጣን ድል ተነሣ፡፡ እርሱ በመብላቱ ስለተሸነፈም ቅዱሳን ነቢያት ሁሉ ከሥጋ፣ ከዓለምና ከሰይጣን ክፉ ፈቃዳት ጋር በመጣላት ሕጉን ለመጠበቅ ያደረጉትን መጋደል በጾም ጀምረው ፍጹም ወደሆነው ፈሪሃ እግዚአብሔር ደረሱ፡፡ ክብር ይግባውና ጌታችን በዚህ ዓለም በተገለጠ ጊዜም ሥራውን በጾም ጀመረ፡፡ እርሱን ለመምሰል የፈቀዱ ቅዱሳንም ሁሉ ጾምን የገድላቸው መጀመሪያ አደረጓት፡፡ እርሷ ከልዑል እግዚአብሔር የተሰጠች ጋሻ ናትና ጾምን የሚንቅና የሚያቃልል ሰው ተግሣፅ ይገባዋል፡፡

ትእዛዝን የሰጠ፣ ሕግን የሠራ እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ከጾመ ሕግን ለመጠበቅ ከሚፈቅዱ ሰዎች መካከል ጾምን ሊወድዳት የማይገባው ማን ነው? በዘመነ ብሉይ ጌታ ስላልጾማት የሰው ልጆች ጾም በሰይጣን ላይ ፍጹማዊ የበላይነትን አልተቀዳጀችም ነበር፡፡ በዘመነ ሐዲስ ግን ክብር ይግባውና ለአዳም ካሣ ሊሆነው የመጣለት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አዳም ያልተጠቀመባትን ይህችን ሰማያዊ የጦር ዕቃ ጾምን አንሥቶ ሰይጣንን ተበቅሎልናል፡፡ በዚህም እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ የሐዲስ ኪዳን ገዳማዊ ሥርዓትን ለመጀመር በኵር ሆነ፡፡ ሰይጣንንና ክፉ ፈቃዳትን ለመዋጋትና ድል ለማድረግም በኵር ሆነልን፡፡ እነሆም በሰይጣን ተሸንፎ ወድቆ፣ ተጥሎ ለነበረ እኛነታችን የማሸነፍን አክሊል አቀዳጀ፡፡

ስለዚህም ዛሬ ሰይጣን ከሰው ልጆች መካከል አንዱን እንኳ ለጾም ሲጠመድ ሲመለከተው እጅግ ይፈራል- ጌታ በጾም እንዴት ድል እንደነሣው ያስታውሰዋልና፡፡ ከሊቀ ካህናታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ በተሰጠችን በጾም የሰይጣንና የመሣሪያዎቹ የክፉ ፈቃዳት ኃይላቸው ይደክማል፡፡ አቤት! ጌታ እንዴት ያለ ድንቅ ምክር ሰጠን! ከአጋንንት ጋር ለመዋጋት ለልቡና ጽንዓትን የሚሰጥ እንደዚህ የጦር ዕቃ (እንደ ጾም) የሚበረታ ሌላ የጦር ዕቃስ ወዴት ይገኛል? የሰው ልጅ ክብር ይግባውና ክርስቶን ለማገልገል በመራብ ሥጋው በጾም በደከመ መጠን የዚያኑ ያህል አጋንንትን ጸንቶ ይዋጋል፡፡ ድል ያደርጉኛል ብሎም አይፈራም- የሚዋጋው ድል ከተነሣ ጠላት ጋር ነውና፡፡

ጾምን ፈጽመህ ውደደው!                                   
ጾምን የናቀና ያቃለለ ሰው ሌላውን ትሩፋት ከመሥራት ቸል ይላል፤ ይደክማል፡፡ በስንፍና ምልክትነቷም ኃጢኣትን ወደ ሰውነቱ መርታ ታደርሳታለች፡፡ ኃጢኣትም ነፍሱን በመውጊያዋ ታቆሳስላታለች- የጦር ዕቃ ሳይይዝ ወደ ጦር ሜዳ ሔዷልና፡፡ ዳግመኛም፣ ፈተና በሚመጣበት ጊዜ የሚጸናበትን፣ ከፈተና ጦር የሚጠበቅበትን ከእግዚአብሔር ለሰው ልጆች የተሰጠችንን ጋሻ ጾምን አልያዘምና ከሚነሣበት ፈተና የተነሣ የጀመረውን ክርስቶስን የመምሰል ገድል አቋርጦ ይሸሻል፡፡

አንተ ግን ሰማዕታትን ምሰላቸው፡፡ እነርሱ የምስክርነት አክሊል የሚቀበሉበትን (ማለትም ስለክርስቶስ ሲሉ የሚገደሉበትን) ቀን ካወቁ በዚያች ሰማዕትነትን በሚቀበሉባት ቀን አንዳች ምግብ ሳይቀምሱ ሰማዕትነታቸውን በጾም ይቀበሏት፣ ይጠባበቋት ነበር ይባላል፡፡ ከጾሙ ጋርም ጸሎትን አብዝተው ያደርሱ፤ ወደ ሠርግ እንደሚሔድ ሰውም በምሥጋና፣ በደስታና በሐሴት ወደ ሰማዕትነታቸው ይጓዙ ነበር፡፡

ክርስቲያን በመሆን “እናንተ የአባቴ ቡሩካን በወደ እኔ ኑ!” የሚለውን ቃል ለመስማት የታጨን እኛም እንግዲህ ይህንን የሕይወት ቃል ለመስማት ንቁዎች ሁነን ልንኖር፣ ለጠላቶቻችን ለአጋንንትም በሕይታችን ላይ መንገድ እንዳንሰጥ ልንጠነቀቅ፣ ከአካል ክፍሎቻችን አንዱም ቢሆን ክፉ ሥራ የሚያስብበትን ምልክት እንዳንሰጠው ልንጠበቅ ይገባናል፡፡


“ንዑ ኀቤየ ቡሩካኑ ለአቡየ!” የሚለውን የሚያረጋጋ ድምጹን ለመስማት
የበቃን፣ የነቃን፣ የተጋን ያደርገን ዘንድ ልዑል እግዚአብሔርን
በአንድ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ
እንለምነዋለን፡፡
    አሜን፡፡


[i] እንደእኔ አመለካከት ከእንደዚህ ዓይነቱ “ጾም” መሰል ረኃብ ይልቅ አንዳንድ ፖለቲከኞችና የሰብአዊ መብት ታጋዮች የሚያካሒዱት የረኃብ አድማ ሳይሻል የሚቀር አይመስለኝም- የእነርሱ ቢያንስ አንድን ምድራዊ ዓላማ ለማሳካት ሲሉ የሚያደርጉት ነውና፡፡ እግዚአብሔር በነቢዩ ኢሳይያስ አንደበት (ትን. ኢሳ. 58) እንዲህ ዓይነቱን ግፍ እየሠሩ የሚጾም ጾም እንደማይቀበለው በግልጥ ነግሮናል፡፡

[ii] እንደተለመደው ኣማርኛውን ለተነሣንበት ዓላማ እንዲሆን አለዛዝቤዋለሁ፡፡

[iii] አንዳንዶቻችን የምናደርገውን “ቢራ ጾም የለውም ወይስ አለው?” “ዓሳ ጾም የለውም ወይስ አለው?” እያልን የምናደርገውን ጉንጭ አልፋና ጥቅም አልባ ክርክር ትተን እንደነቢዩ ዳንኤል ኃጢኣታችንንና የሕዝቡን ሁሉ ኃጢኣት እያሰብን “ኃጢኣት ሠርተናል፤ በድለንማል፤ ክፋትንም አድርገናል፤ ዐምፀንማል፤ ከትእዛዝኽና ከፍርድኽም ፈቀቅ ብለናል፡፡” በማለት ልንጸልይ ይገባናል (ትን. ዳን. 9፣ 5)፡፡ ሆዳችን ከመራቡ በፊት ልባችን እግዚአብሔርን ለማግኘት መራብ አለባት- ልባችን እግዚአብሔርን ሳይራብ ልማድ እንዳይቀርብን ብቻ የምናደርገው ጾም ለነፍሳችን የሚያተርፈው ነገር እምብዛም ነውና፡፡