Monday, November 30, 2015

ከበደ ሚካኤል

የቅኔ ውበት የተሰኘ የግጥም መድበል አላቸው፡፡ ብርቱ ገጣሚ፣ መንፈሳዊና ትሑት ሰው እንደነበሩ በአካል ያውቋቸው የነበሬ ይመሰክራሉ፡፡ በጣልያን ወረራ ጊዜ ፋሽስቶች የተማሩ ኢትዮጵያውያንን እየለቀሙ ሲያጠፉ ነፍሳቸውን ለማትረፍ ከቻሉ ጥቂቶች መካከል አንዱ ነበሩ፡፡ ከነበሩት ጥቂት የተማሩ ሰዎች መካከል ስለነበሩም ፋሽስታዊውን ሥርዓት በፕሮፓጋንዳ ክፍሉ ውስጥ የማገልገል ግዴታ ተጥሎባቸው ነበር፡፡ በዚኽም የተነሣ፣ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም አምርረው በባንዳነት ከሚወቅሷቸው ሰዎች መካከል አንዱ ኾነዋል፡፡

እርግጥ ነው ከበደ ሚካኤል በፋሽስቱ አገዛዝ ውስጥ እንዲሠሩ ከተደረጉ ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ እንደነበሩ ማስተባበል አይቻልም፡፡ ይኹን እንጂ፣ እርሳቸው በዚኽ ደስተኛ ነበሩ የሚያሰኝ ምንም ማስረጃ ግን በእኔ በኩል አላውቅም፡፡ ይልቁንም “እኔና ቹሊ” የሚል በፋሽስታዊው አገዛዝ ላይ ምሬታቸውን የሚገልጽ ተውኔታዊ ግጥም አላቸው፡፡ በሦስተኛው ክፍለ ዘመን (ቅ.ል.ክ./BC) ሮም ሳትወርረን በፊት እኛ ካርቴጃውያን ወርረን ማስገበር አለብን በማለት ሮምን ወርሮ ያስጨንቅ የነበረውን የአፍሪካዊውን የጦር ጀግና የሐኒባልን(Hannibal) ታሪክም በተውኔት መልክ አዘጋጅተው አቅርበውታል- ብዙ ሰው የሚያውቀው ባይመስለኝም፡፡ ከዚኽም በተጨማሪ፣ እርሳቸው ከንባብ ትጋታቸው የተማሩትን ለኢትዮጵያ ወጣቶች በቀላሉ ለማቅረብ በነበራቸው ትጋት 26 መጻሕፍትን አዘጋጅተው አቅርበው ነበር- ደርግ በግፍ ሲያስመርራቸው ሰብስበው ያቃጠሏቸው ሌሎች በርካታ ያልታተሙ መጻሕፍት እንደነበራቸውም ይነገራል፡፡ ይኽን ስመለከት ሰውየው የፋሽስት ዘመን አገልግሎታቸውን በደስታ የሚፈጽሙት ነበር ለማለት እቸገራለኹ፡፡ ሰው ለማይወድደው ሀገር እንዲኽ ይደክማል?  

የንባባቸው ስፋት የሚገርም ነበር፡፡ በወቅቱ የነበረውን ምዕራባዊ ፍልስፍናና ሥነ ጽሑፍ በስፋት ያነበቡ ሰው ነበሩ፡፡ በትምህርት ላይም ጽኑ እምነት ነበራቸው፡፡ ኢትዮጵያ የጃፓንን ፈለግ በመከተል ማኅበራዊ ዕሴቶቿን ሳትተው ወደ ሕገ መንግሥታዊ የዘውድ ሥርዓት እንድትመጣ ይመኙ ከነበሩ የዘመናቸው ልሒቃን መካከልም አንዱ ነበሩ፡፡ ለዚኽም ሲሉ ጃፓን እንዴት ሠለጠነች? የሚል መጽሐፍ እስከ መጻፍ ደርሰዋል፡፡ የምዕራባውያንን ታሪክና ፍልስፍና እጅግ በቀላል ቋንቋ ለኢትዮጵያ ወጣቶች በማቅረብ ረገድ የተሳካላቸው ነበሩ፡፡ ታላላቅ ሰዎች፣ የሥልጣኔ ዐየር፣ ሥልጣኔ ምንድነች?፣ የዕውቀት ብልጭታ የሚሉ ሥራዎቻቸው በሙሉ ግባቸው የኢትዮጵያን ወጣቶች ከምዕራባዊው ሥልጣኔ ጋር ማስተዋወቅ ነበር፡፡

ገጣሚነታቸው በአማርኛ ሥነጽሑፍ ውስጥ ደምቆ ከሚነሣላቸው ሰዎች መካከል አንዱ ናቸው፡፡ በዚኽም የተነሣ፣ የአማርኛ ሥነ ግጥም ሊቁ ብርሃኑ ገበየኹ ባለ ስድስት ቀለም (በተለምዶ "የወል ቤት" እየተባለ የሚጠራውን) የአማርኛ ግጥም ምጣኔ “የከበደ ቤት“ ሲል ሰይሞላቸዋል- ብዙዎቹ ግጥሞቻቸው በዚኽ ምጣኔ የተበጁ ናቸውና፡፡ ጥቂት ስንኞችን እነሆ፡-

የተማረ ሆኖ ዕውቀቱን የማይገልጥ፣
ባለጸጋ ሆኖ ገንዘቡን የማይሰጥ፣
ድኻ ሆኖ መሥራት የማይሻ ልቡ፣
ሦስቱም ፍሬ ቢሶች ለምንም አይረቡ፡፡

በቅርብ ያዩዋቸው ሰዎች ከበደ ሚካኤል ቤተክርስቲያን መኼድ የሚወድዱ፣ በጣም ትሑትና መንፈሳዊ ሰው እንደነበሩ ይናገራሉ፡፡ ባለቤታቸው በሞት ከተለዩዋቸው በኋላ እንደባሕታዊ አንዲት አፓርትመንት ውስጥ ተዘግተው በጽሙና ኖረዋል፡፡ ከግጥሞቻቸው መካከል አንዱም ለቅድስት ድንግል ማርያም የተጻፈ ውብ ውዳሴ ነው፡፡ በ1990 ዓ.ም. አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ላደረጉት አስተዋጽዖ የክብር ዶክትሬት ሰጥቷቸዋል፡፡ ከዚያ በፊትም ከጃፓን፣ ከሜክስኮ፣  ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ሶቭየት ኅብረት፣ ጣልያን እንዲኹም ከንጉሠ ነገሥት ኃይለ ሥላሴ ሽልማቶችን አግኝተዋል፡፡ ከበደ ሚካኤል በ1998 ዓ.ም. በ82 ዓመታቸው ከዚኽ ዓለም ውጣ ውረድ ተገላግለዋል- የ17ኛው ክፍለዘመን ሊቅ አባ ባሕርይ “ዘሞተሰ ብፁዕ ውእቱ” እንዲሉ፡፡  

No comments:

Post a Comment