Thursday, July 10, 2014

እንዲኽም ተደርጓል


“የአዲስ አበባ የወንጀለኛ ምርመራ ክፍል የተመርማሪዎችን ጀርባና እግር በመግረፍ ጥፋትን አለውድ በግድ የሚያሳምን፤ ጥፊና ስድብ የሞላበት፤ በማወናበድ ቃል የሚቀበልበት፡፡ እንደ ኦፔራሲዮን ክፍል የሰው ሕይወት ማጉላሊያ መሣሪያዎች የሞሉበት፤ ከሰብአዊ ርኅራኄ ውጪ የሆነ ከፍተኛ ተግባር የሚፈጸምበት ክፍል ነው፡፡ ከዚህም በቀር የፈለጉትን የሚያጠቁበት የባለሥልጣኖች መፎከሪያ ቤት ነው፡፡ ይህ መሥሪያ ቤት ለአንድ አገር ሕዝብ ከሚሰጠው አገልግሎት ይልቅ የሚፈጽመው ሕገወጥ ተግባር የበዛበት በመሆኑ የሚወጣው የሥራ ማስኬጃ ገንዘብ የትም እንደጠፋ የሚቈጠር ነው፡፡ ለውስጥ እግርና ጀርባ መግረፊያ ጅራፍ፤ ከጩኸት የሚከላከል የማፈኛ ኳስ፤ ለእጅና ለእግር መጠፈሪያ ብረት፤ ለማንጠልጠያ መሰላል፤ ለነኝህ ለመደብደቢያ መሣሪያዎች የሚወጣው በጀት መንግሥትን በገንዘብ በኩል ይጎዳዋል፡፡ በደል ባላደረሱትም ሰዎች ሕይወት ላይ በሚፈጸመው ድብደባ በሕግ ያስጠይቀዋል፡፡

የወንጀለኛ ምርመራ ክፍል በደል ይህ ብቻ አይደለም፡፡ የፍርድ ቤቶችን፤ ሐኪሞችን፤ ፖሊስ ጣቢያዎችንና የዐቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤቶችን በግዳጅ ሕገወጥ ድርጊት እንዲፈጽሙ የሚገፋፋ ነው፡፡ ይህንን ለመግለጥ የተገደድኩት በእኔ ላይ የተፈጸመውን ግፍና እንደእኔም ባልፈጸሙት ወንጀል ድብደባና መጉላላት የደረሰባቸውን ሰዎች ጭምር መኖራቸውን በማመን ነው”

ይህንን የገለጡት ያልወሰዱትን የአንድ ባለሥልጣን ገንዘብ ወስደሀል ተብለው ያለውድ በግድ እንዲምኑ የተደረጉት የክብር ዘበኛ መምሪያ ሻምበል አዛዥ ሻለቃ አሥራት በነበሩ ናቸው፡፡ ሻለቃ በወንጀል ምርመራው ክፍል ባለማቋረጥ በተፈጸመባቸው የድብደባ ወንጀልም ምክንያት ሞትን በመመኘት ባሉበት እስር ቤት ሆነው በተላከላቸው የምግብ ሽፋን ታንቀው ሕይወታቸውን ለማሳለፍ ሞክረው ነበር፡፡ ነገር ግን በሰውነታቸው መዳከም ምክንያት ኃይል በማጣታቸው ከሞት መትረፋቸውን ገልጠዋል፡፡   

“የወንጀል ምርመራው ክፍል በእኔ ላይ መረጃ ባለማግኘቱ ተጨማሪ መሣሪያው በሆነው በጠንቋይም ሊያስፈራራኝ ሞክሯል፡፡ እኔ ግን የምርመራ ዘዴውን ደካማነት ከመታዘብ በስተቀር በውሸት ቀንድ አውጥቶ ሰይጣን መስሎ ለመጣው ሰው ፍንክች አላልኩም፡፡ እርግጥ የተዳከመውን ሰውነቴን በበለጠ ስላጉላላው ጎድቶኛል፡፡ ይህም ደግሞ ከጅራፉ ስላበለጠብኝ ተመስገን ለማለት አስችሎኛል” ሲሉ ሻለቃ አሥራት ይናገራሉ፡፡

“በመጀመሪያው ቀን ማታ የስቃዬ የመጀመሪያ የሆነው ግርፋት ተጀመረብኝ፤ እጅና እግሬን አስረው ዘቀዘቁኝ፡፡ ዓይኔን ሸፈኑኝ፡፡ አፌ ውስጥ እንዳልጮህ ማፈኛ ኳስ ነገር አገቡብኝ፡፡ ከዚያ በኋላ ውስጥ እግሬን ይገርፉኝ ጀመር፡፡ እንዲህ ያለው ኑሮ የሚተዳደሩትን ሰው ሲሰቃይ ደስ የሚላቸውን ኢየሱስ ክርስቶን የገረፉትን የአይሁዶችን ወንድሞች በዓይኔ ለማየት ጓጉቼ ነበር፡፡ ነገር ግን እንዳላይ ሆንኩ፡፡ የአንደኛውን ቀን ግርፋት አዲስ በመሆኔ ተቋቋምኩት፡፡  እንደገና በማግሥቱ ከዚሁ ባላነሰ ግርፋት ተፈጸመብኝ፡፡ በዚህ ላይ በጌታ እንዳፌዙት አይሁዶች ፌዛቸውና ስድባቸው አይጣል ነው፡፡ አሁንም የሦስተኛውን ቀን ግርፋት ለመቀበል ገባሁ፡፡ የቆሰለው እጄ ደም የሚወርደው እግሬ ጠገግ ጠገግ ሳይል፡፡ “አውጣ፤ ተናገር” የሚለው የግርፋት ምርመራ ባለማቋረጥ ሊፈጸምብኝ ሲል መርማሪው መኰንን “የሚገርፉ ሰዎች ችግር ስለሌለብን ዛሬ የሚገርፉህ ሌሎች ናቸው ስለዚህ እንድታውቀው” አለኝ፡፡ ግርፊያው ቀጠለ፡፡ ስታምን ምልክት ስጥ ተብዬ ስለነበር፡፡ ገራፊዎቹ አዲሶች እኔግን ያው እኔ ስለሆንሁ ያላቋረጠው የሦስት ቀን ስቃይ ጠናብኝ፡፡ የሚፈልጉትን የውሸት እውነት አመንኩ” ሲሉ ሻለቃ አሥራት የደረሰባቸውን መከራ ለመናዘዝ በቅተዋል፡፡

ሻለቃ ይህ ሁሉ ሊደርስባቸው የቻለው ለምንድነው? እንደሚከተለው ያብራራሉ፡፡ “ግንቦት 6 ቀን 63 ዓ/ም/ በጊዜው የነበሩት የክብር ዘበኛ ዋና አዛዥ ከጽ/ቤታቸው ሲሠሩ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ገደማ ላይ የግል ገንዘባቸው የሆነው 21 ሺህ ብር ከካዝናቸው መጥፋቱን ጠርተው ነገሩኝ፡፡ እኔ የማውቀው ነገር የለም አልኳቸው “በምርመራ እንኳን ይኸና ሌላም ከፍ ያለ ጉዳይ እንደሚገኝ አታውቅም?” አሉኝ፡፡ እርግጥ ይገኛል፤ ነገር ግን ያልተወሰደ ገንዘብ በታምር ይገኛል? ብዬ ጥያቄያቸውን በጥያቄ መለስኩላቸው፡፡



ወዲያው ለጄኔራል ይልማ ሺበሺ ቴሌፎን ደወሉ፡፡ እሳቸውም መጡ፡፡ ከቢሮዋቸው ስብሰባ ካደረጉ በኋላ የእኔ ጠረጴዛ ኪስ ሁሉ ተበረበረ፡፡ ወዲያው አብረዋቸው ከመጡት መኰንኖች ጋር ልብሴን ለውጬ ወደ ወንጀለኛ ምርመራ ክፍል ተወስጄ 10 ቀን ያለ ሌሊት ልብስ ሰነበትሁ፡፡ የተወሰደው እርምጃ ሁሉ “ያለአግባብ በመረዳዳት” መሆኑን ተረዳሁ፡፡፡ በዚህም መሠረት የውሸት እውነት እንድናገር በ3ኛው ቀን ግርፋት አምኜ ስለነበር ከስብሰባው አዳራሽ ምንጣፍ ውስጥ ነው አልኳቸውና ይህንኑ ለጄኔራል አበበ ወንድሙ ታረጋግጣለህ አሉኝ፡፡ እሳቸውም ወዲያው መጡ፡፡ “ብዙ ስቃይ ሳያጋጥምህ ቶሎ ማመንህ ጥሩ ነው” አሉኝ፡፡ እኔ ግን ሞት የቀረኝ መሆኔን አላወቁልኝም፡፡ በእሳቸው መሪነት ሄድን ለአዛዡም ተገኝቷል ይምጡ  ተብሎ ተደወለላቸውና መጡ፡፡ ገባንና ምንጣፉን ገለጥኩት፤ ምንም የለም፡፡ ሁሉም ተናደዱ፡፡ ተመልሼ መኪና ውስጥ ገባሁ፡፡ ጉዞ እንደቀጠልን ይኸ ሌባ ተጫወተብን፤ አዋረደን አሉኝ፡፡ እግርፋቱ ክፍል ገባሁ፤ ታሰርኩ፡፡ ቢገርፉኝ ሰውነቴ እንደማይችል ተረዳሁና ከቤቴ ማዶ ጫካ ውስጥ ቀብሬዋለሁ አልኳቸው፡፡ ቦታውን ታውቀዋለህ አሉኝ፡፡ አውቃለሁ አልኳቸው፡፡ ወደ እስር ቤት ተመለስኩ፡፡ በዚህ ሌሊት እግሬ ወሀ በመቋጠሩ አሞኝ አደርኩ፡፡ በዚህ ዕለት ነው ሕይወቴን ላጠፋ ተገድጄ የነበረው፡፡

እንደገና 5 የሚሆኑ መኰንኖች መጥተው ገንዘቡን ስጥ ጭንቅ ከሚበዛብህ አሉኝ፡፡ እኔ በሕይወቴ ላይ ስቃይ ስለበዛብኝ ነው ወስጃለሁ ያልኩት እንጂ አልወሰድኩም ብዬ መለስኩ፡፡ እንደገና ከሌላው የግርፋት ጊዜ የተለየ ዝግጅት ተደርጎ በመጀመሪያ በመሰላል ላይ ተሰቀልኩ፡፡ እጅና እግሬ ታሰረ፡፡ ለ1 ሰዓት ያህል ተጉላላሁ፡፡ በዚያ ስቃይና ድካም ወርጄ ግርፋቱ ቀጠለ፡፡ የምሆነውን አጣሁ፡፡ በዚያን ዕለት አልሞትኩም ብዬ አልዋሽም አሰኘኝ፡፡ በመጨረሻ እንደዕቃ ተሸክመው ወሰዱና እስር ቤት ጣሉኝ፡፡ እግሬ በመቁሰሉ ምክንያት መርገጥ አቅቶኝ እነሱ ደግሞ ለሚቀጥለው ግርፊያ እንዲረዳን እርገጥበት እያሉ አስቸገሩኝ፡፡ ጣጣው ብዙ ነው ብዙ ሆነው መጥተው ለሚያቀርቡልኝ አወናባጅ ጥያቄ የምሰጠው መልስ ራሴን እስከ ማዞር አድርሶኛል፡፡

የአባለዘርህን ፍሬ አጥፍተን መንገድ ዳር እንድትለምን ሳናደርግህ የቀረን እንደሆነ፤ የሚልም ዛቻ ተሰንዝሮብኛል፡፡ ከዚህም በቀር ፍርድ ቤት ቀርቤ ውሳኔ እንዳላገኝ ወይም በቀጠሮ እንዳልለቀቀቅ በየጊዜው እየሔዱ የምርመራ ቀጠሮ ይሰጠን በማለት የምቀርብበትን ጊዜ ያስተላለፉብኝ ጊዜ ብዙ ነው፡፡ ባለቤቴ በወለድ ገንዘብ ተበድራ ጠበቃ ብትገዛም በጠበቃው ላይ ያለው ተጽዕኖ በመብዛቱ ውጤት አላገኘልኝም፡፡ የምርመራው ክፍል በማደንዘዣ መርፌ ቃሌን ለመቀበልም ሞክሮ ነበር፡፡ ነገር ግን ምንም ውጤት ለማግኘት አልቻሉም፡፡ ታመሃል ተብዬ በድብቅ ፖሊስ ሆስፒታል አስገብተውኝ ተኛሁ፡፡ ከአንድ ኮሎኔል (ዶክተር) በስተቀር ሌላ ሐኪም ገብቶ እንዳያክመኝ ተደረገ፡፡ የሚሰጠኝ መድኃኒት ግን ቪታሚን ብቻ ነው፡፡ ጠበቃዬ መጥቶ እንዳያነጋግረኝ በመደረጉ የምርመራውን ክፍል በደለኛነት አረጋግጫለሁ፡፡ በቀጠሮ ፍርድ ቤት ቀርበው ታሟል ብለው ነገሩ፡፡ የሐኪም ማስረጃ ያምጣ ተባሉ፡፡ ይዘውኝ ምኒልክ ሆስፒታል ሔዱ፡፡ ያለምንም ምርመራ ከፖሊስ ሆስፒታል የተጻፈውን የዶክተሩን ማስረጃ ፖሊሱ ለዚህኛው ዶክተር ሰጥቶት በሌላ ወረቀት ላይ ያንኑ ገልብጦ መለሰለት፡፡ ያንን ለፍርድ ቤት እንደማስረጃ አድርገው አቀረቡት፡፡

“ያለምንም ሕክምናና ሕመም ሆስፒታል ተኝቼ ወጣሁና እንደገና ወደ እስር ቤት ተመለስኩ፡፡ እኔ የተኛሁበት አልጋ ስንት ሕመምተኛ ሊተኛበትና ሊድን ይችል ነበር፡፡ በእስር ቤት እንዳለሁ ዓባይ ጠንቋይም አምጥተው እንዳምን አድርገዋል፡፡ ደካማ የወንጀል ምርመራ!” በብዙ ትግልና በዋስ ተለቅቄ ሥራ መግባት አለብኝ ብዬ ያለፈውንም ደመወዜን ለመጠየቅ ወደ መምሪያው ሔድኩ፡፡ በነኝህ በሁለት ጉዳዮች ያየሁት ፈተናና የደረሰብኝ የባለሥልጣኖች የውስጥ ለውስጥ ተፅዕኖ ተዘርዝሮ አያልቅም፡፡ በዚህ ደጅ ጥናት ላይ እንዳለሁ የአዛዡን ገንዘብ የሰረቀው ወታደር ተይዞ፤ ወታደሩም በሚገባ አመነ፡፡ ገንዘቡንም ከምን ላይ እንዳዋለው ገለጠ፡፡ ክስ ቀርቦበትም 7 ዓመት እስራት ተፈረደበት፡፡ የእሱ ዜና በፖሊስና ርምጃው ጋዜጣ ላይ ሲገለጥ፤ የእኔ በነፃ መውጣት አለመገለጡ ደግሞ አሳዝኖኛል፡፡

የተሰረቀው ገንዘብ ለአዛዡ እንዲሰጥ ሲደረግ የእኔ ከወንጀል ነፃ መሆን ስላልታያቸው በፋይሌ ላይ እንኳን ያሰፈሩት ጽሑፍ የሚያሳዝን ነው፡፡ ከዚህም አልፈው ዓይኔን እንዲያዩ ባለመፍቀዳቸው በረሃ በበዛበት ወደ አሰብ ሔጄ በ11ኛ ሻለቃ ውስጥ እንዳገለግል ሆኛለሁ፡፡ አሁን ከዚያ ተመልሼ በሠራዊቱ ውስጥ በማገልገል ላይ ነኝ፡፡ በጠቅላላው ያለምንም በደልና ጥፋት 3 ወር በእስራትና በግርፋት፤ ሁለት ወር በሥራ ደጅ ጥናት፤ በጠቅላላው 5 ወር ተጉላልቻለሁ፡፡ የማዝነው ግን የባለሥልጣኖች ብቻ መገልገያ የሆነውና ሕገወጥ ሥነ ሥርዓት ለሚፈጽመው የወንጀል ምርመራ ተብሎ ለሚጠራውና ሕግ በባለሥልጣኖች ላይ የማይሠራ ፤ ባለሥልጣኖች የሚሠሩትም በደል እንዳይገለጥ የሚያግድ መሆኑ ብቻ ነው፡፡

ይሠራል ተብሎ የወጣው ሕገመንግሥት “በኢትዮጵያውያን መካከል ልዩነት አይደረግም” ይላል፡፡ ከዚህ የበለጠ ልዩነት አልነበረም፡፡” ብለዋል፡፡


(ምንጭ፡- አዲስ ዘመን፣ ነሐሴ 19 ቀን 1966 ዓ.ም. ፡፡)

1 comment:

  1. I didn't even change a single word. I took it from the newspaper as it is.

    ReplyDelete