Sunday, December 8, 2013

ይቅርታ፣ ብሔር የለኝም፡፡ (Sorry, I don't belong to a single ethnic group.)



በየሬድዮ ጣቢያው ላይ ብሔር፣ ብሔር፣ ብሔር፣ ብሔር… እየተባለ የሚለፈለፍበት ሰሞን ስለኾነ ጥቂት “ስለብሔር” ጉዳይ አንድ ሰው ያጫወቱኝን ገጠመኛቸውን መሠረት አድርጌ፣ ትንሽ የእውነት ቅመም ጨምሬበት ሐሳቤን ላካፍላችኹ እወድዳለኹ፡፡

አንድ ጉዳይ ይገጥማቸውና መታወቂያ ለማውጣት ቀበሌ ይኼዳሉ፡፡ ወንበሩ ላይ የተሠየመው ሰው ቅጽ እየሞላ ጥያቄ መጠየቅ ይጀምራል፡፡
“ስም”
“እገሌ እገሌ”
“የአያት ስም”
“እገሌ”
“የተወለዱበት ዘመን”
ሰውየው ተናገሩ፡፡
“ብሔር”
ይኼኔ ሰውየው “የለኝም፡፡” አሉ፡፡
“እንዴት የለዎትም”
“አሃ! የለኝማ! የለኝም፡፡”
“ለምንድነው የማይኖርዎት”
“ኦሮምኛ፣ አማርኛ የምታቀላጥፈው እናቴ የተወለደችው ከኦሮሞ እናትና ከጉራጌ አባት ነው፤ ግእዝ፣ አገውኛና አማርኛ የሚናገረው አባቴ ደግሞ እናቱ አገው ሲኾኑ አባቱ ደግሞ ጎንደር ተወልደው ያደጉ የትግራይ ሰው ናቸው፡፡ እኔ የተወለድኹት ደብረ ዘይት፣ ያደግኹት አዲስ አበባ ሲኾን ሐረሪዎች ዘንድ ብዙ ዓመታት በመኖሬ አደሪኛ እናገራለኹ፡፡ እና የእኔ ብሔር ምን ሊባል ነው?”

Monday, October 28, 2013

የእሑድ ብቻ ሃይማኖት


ሰሞኑን እግር ጥሏቸው እጄላይ ከወደቁ ጽሑፎች መካከል አንደኛው ዲትሪች ቦንሆፈር ስለተባለ፣ አይሁዳውያን በናዚ ጥቃት በሚደርስባቸውና የጀርመን ብሔራዊት ቤተክርስቲያንም ከሒትለር ጋር ባበረችበት ዘመን አካኼዷ ትክክል አለመኾኑን ወቅሶ አይሁዳውያንን ይረዳ ስለነበረ ሊቅ ነው፡፡ ስለዚህ ሰው የተጻፈው ይህ ጽሑፍ በውስጡ ከያዛቸው መልእክቶች ኹሉ ገንኖ የተሰማኝን እንዲህ እንካፈል፡-


እውነተኛ ክርስትና የእሑድ ብቻ ሃይማኖት አይደለም- የምንተነፍሰው አየር፣ የልባችን ምት፣ በሥሮቻችን ውስጥ ያለ ደም፣ የህልውናችንም መሠረት ነው እንጂ፡፡ ይኹን እንጂ እውነተኛ ክርስትና፣ እውነተኛ ደቀ መዝሙርነት፣ ክርስቶስን በእውነት መከተል ዋጋ ያስከፍላል፡፡ በ2000 ዓመታት ታሪኳ ቤተክርስቲያን ክርስቶስን የተከተለችባቸው ጊዜያት ነበሩ፡፡ ክርስቶስን የመከተል ቋንቋ እየተናገረች እውነታው ሲታይ ግን የዓለም ተከታይ ኾና የተገኘችባቸው በርካታ ጊዜያትም አሉ፡፡ አንድ ሰው ቤተክርስቲያን ውስጥ ኾኖ ቤተክርስቲያኗን ከጥፋት መንገዷ እንድትመለስ ቢጮኽ ያ ሰው የቤተክርስቲያን ጠላት ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ ቤተክርስቲያኒቱ እጅግ የሚያስፈልጋት ሰው ግን እርሱ ነበር፡፡ ታሪክ እንደሚያስረዳው ቤተክርስቲያን የዓለምን ዕውቅና የፈለገችባቸው ጊዜያት ነበሩ፡፡ ዕውቅናውን ባገኘች ጊዜ ግን ወንጌልን አሳልፋ ሰጥታ፤ በዚህም ተስፋዋን ጥላ ነበር፡፡

ቤተክርስቲያን ወንጌልን ስትተው ማዕከሏና የወደፊት ህልውናዋ የኾነውን መልእክቷን ታጣለች፡፡ ቤተክርስቲያን በወንጌል ላይ እምነት ስታጣ ለባህል መልእክት ባርያ ትኾናለች፡፡ እነዚህ ችግሮችም ቀስ በቀስ የቤተክርስቲያኗን የወደፊት ህልውና መሠረት ይገድሉታል፡፡ እግዚአብሔር ግን በአንድ ቅርንጫፍ ብቻ የሚኖር አይደለም፡፡ ወንጌል እያስገመገመ እንደሚኼድ ግሩም ወንዝ ነው፡፡ ሊበራሊዝም አያግደውም፤ ጭቆና አያፍነውም፤ ቢሮክራሲ አያንቀውም፤ የአገልጋዮች ስንፍናም አይገድለውም፡፡ አንድ ቤተክርስቲያን እውነተኛውን ወንጌል መመልከትና እርሱንም ከመስበክ ፈቀቅ ስትል እግዚአብሔር ሌላ ቤተክርስቲያን፣ ሌላ ትውልድ፣ ሌላ ሕዝብ ያስነሣል፡፡ አንድ ታሪካዊ ቅርንጫፍ በባህል ሲዋጥ እግዚአብሔር ሌላውን ቅርንጫፍ ስለ እውነት ያስነሣል፡፡         


Source:- <http://www.cbcroseville.org/sermons/text/The_Cost_of_Discipleship-1.pdf>

Thursday, June 13, 2013

የቤቲ ጉዳይ፤ ሦስቱ ዐዳዲስ የኢትዮጵያ አማልክት?


ባለፈው ሰሞን ሳልከፍተው የቆየኹትን የፌስ ቡክ ገጼን ስከፍት በርከት ያሉ ጽሑፎች “ቤቲ” የምትባል ወጣት (አንዳንዶቹ ወጣትነቷንም የሚራጠሩ ነበሩ፡፡) ስለሠራችው “ጉድ” (ብትሹ በእንግሊዘኛ ብትሹ በአማርኛ አንብቡት፡፡) የሚያትቱ፣ የሚሞግቱ ነበሩ፡፡ በርከት ያሉ ሰዎችም ድንጋጤያቸውን፣ ሐዘናቸውን ገልጸዋል፡፡ “ኢትዮጲያዊነታችን በዓለም አደባባይ ተዋረደ!” ብለው ተብከንክነዋል፡፡ ቪኦኤም፣ ዶቼ ቬሌም ጉዳዩን አነሣሥተውታል፡፡ የሬድዮ መርሐ ግብሮችም አብዝተው አራግበውታል (በተለይ ታድያስ አዲስ)፡፡ ብዙዎቹ መብከንከኖች ሲጨመቁ ዛላቸው አንድ ነው- “ቤቲ ኢትዮጵያን ወክላ በኼደችበት የቴሌቪዥን ትርኢት ውስጥ እንደ ውሾችና ድመቶች የዐደባባይ ሩካቤ ፈጽማ አዋረደችን፡፡ ድሮም ስማችን አላማረም፤ አኹን ደግሞ ይባስ ብላ ኢትዮጵያ የጋለሞቶች ሀገር አሰኘችን፡፡ ኢትዮጵያዊት መምህርት ኾና እንዴት እንዲኽ ባህላችንን ታረክሳለች?!” የሚል ቁጭት፡፡ 

ቁጭታቸውን ልረዳው ብሞክርም ድንጋጤያቸውን ግን ልረዳውም፣ ልካፈለውም አልቻልኹም፡፡ እንዲያውም አደረገች የተባለውን ነገር ስሰማ ውስጤ ፈጽሞ አልደነገጠም፡፡ ያልተጠበቀ ነገርም አልኾነብኝም፡፡ ለምን?

ተወደደም ተጠላም ልጅቱ የዚኽ ማኅበረሰብ ውጤት ናት- የሥጋችን ቁራጭ፣ የአጥንታችን ፍላጭ፡፡ ማኅበረሰብ ደግሞ ከዕለተ ልደታችን ጀምሮ በእንቅስቃሴዎቻችን ኹሉ አእምሯችንን በባህሉ እየቀረፀ የምንወድደውን እንድንወድድ፣ የምንጠላውን እንድንጠላ፣ የምናከብረውን እንድናከብር፣ የምንንቀውን እንድንንቅ አድርጎ ዳግም ይወልደናል፡፡ በመኾኑም “ቤቲ ኢትዮጵያዊት ናት፡፡” ሲባል ቤቲ ኢትዮጵያውያን ስለራሳቸው ማሰብ የሚሹትን መልካም መልካሙን ብቻ ይዛ የምታውለበልብ የባንዲራ ማማ ናት ማለት ሳይኾን የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ (ቢያንስ ያሳደጋት ከተሜው ኢትዮጵያዊ ማኅበረሰብ) አአምሮዋን በቀረፀበት መንገድ የምታስብ ፍጥረት ናት ማለት ነው፡፡

ጊርት ሆፍስቴድ የተባለ ሰው “ባህል የአእምሮ ሶፍትዌር ነው፡፡” ይላል፡፡ በሌላ አባባል የሰው ልጅ ሲወለድ ዐዲ ሐርድዌር ኾኖ ይወለድና ማኅበረሰቡ በአንድም በሌላም መንገድ የማኅበረሰቡ አባል የሚያደርገንን “ሶፍትዌር” ይጭንብንና በባህሉ ያጠምቀናል፡፡ ከልሙጥ ሰውነት ወደ ማኅበረሰቡ ልዩ አባልነት ዳግም ይወልደናል፡፡ ይኽን “ሶፍትዌሩንም” በየጊዜው “አፕዴት” ያደርገዋል፡፡

ብዙ ጊዜ “ባህል” ሲባል ነባርና የኾነ የጥንት ዘመን ላይ የነበሩ “ክቡራን አበው” የተፈጠረና “ሳይከለስ ሳይበረዝ” ኖሮ እኛ ዘንድ የደረሰ፣ እኛም ሳንበርዝና ሳንከልስ ወደ መጻኢው ትውልድ የምናስተላልፈው “ቅዱስ” ነገር ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ ይኽ ግን የባህልን ምንነት ካለማወቅ የሚሰጥ የጨዋ አስተያየት ነው፡፡ ባህል ማለት የአንድ በሕይወት ያለ ማኅበረሰብ የአኗኗር ዘይቤ እንጂ በሙዳይ የተቀመጠ ጨሌ ማለት አይደለም፡፡ የማኅበረሰቡ ሥርዓተ ዕሴት (value system) በተለዋወጠ ቁጥር ሲለዋወጥ የሚኖርና ሲለዋውጥ የሚያኖር እውነታ ነው፡፡ ለዚኽ ነው የቤቲ ድርጊት ያላስደነገጠኝ፡፡ በእኔ አመለካከት፣ ልጅቱ የኾንነውን እንጂ ያልኾንነውን አላሳየችንም፡፡ እዚኽ ላይ “እንዴት ብትደፍር ነው? ኢትዮጵያ የኩሩዎች፣ የደናግል (የእነ ፍቅር እስከመቃብሯ “ሰብለ ወንጌል”ና የአደፍርሷ “ጺወኔ”)፣ የሃይማኖተኞች ሀገር አይደለችምን!” ብሎ የሚቆጣ ሰው ይኖር ይኾናል፡፡

እርግጥ ነው ኢትዮጵያ እንደተባለው ኩሩዎች፣ ደናግል፣ ብሉይ ከሐዲስ አስተባብረው የሚያመልኩ ሃይማኖተኞች ኖረውባት ይኾናል- ድሮ፡፡ ዛሬ ግን ኢትዮጵያ (በተለይም ደግሞ እኔ የማውቃት ከተሜዋ ኢትዮጵያ) እነርሱ እንደሚሏት አይደለችም፤ ስትኾንም ዐይቻት አላውቅም፡፡ እኔ የማውቃት ኢትዮጵያ ለሦስት አማልክት የምታጥንና የምታፈነድድ እንጂ ባለ አንድ አምላክ አይደለችም ነው፡፡ እነሆ ሦስቱን አማልክት ልጠቁማችኹ፡፡

Tuesday, May 14, 2013

ለምን አስተማራችኹኝ?

ፕሮፌሰር መስፍን ያኔ ልጅ እያሉ በወቅቱ የነበሩትን የትምህርት ሚኒስትር “ለምን አስተማራችኹን” ብለው አፋጥጠዋቸው ነበር፡: አባባላቸው ኹልጊዜም የሚያሳስበኝን የማኅበረሰባችንን ነገር ዳግም አስታወሰኝ፡፡ “ተማር፡፡” አሉኝ፡፡ ተማርኹ፡፡ “አንብብ ፤ማንበብ ጥሩ ነው፡፡” አሉኝ፤ የዐቅሜን ያኽል አነበብኹ፡፡ መማር የተሻለ ደሞዝ እንደሚያመጣ እንጂ ተማሪውን እንደሚቀይር አላስተዋሉትም፡፡ 

መማር ማለት የኾነን ዕውቀት ወይም የምስክር ወረቀትን በባለቤትነት መያዝ ሳይኾን ለእውነት ራስን ክፍት ማድረግና እውነት ሕይወትን እንድትመራ በነጻነት መፍቀድ መኾኑን አላሰቡትም፡፡ እነርሱ የታያቸው በምስክር ወረቀቶች ብቻ የምበልጣቸው የእነርሱ ቅጂ ኾኜ እነርሱ ማድረግ ያልቻሉትን እንዳደርግ ነበር፡፡ ምን ያድርጉ- ልጃቸው አይደለኹ እንዴ! እኔ ምክራቸውን ተከትዬ ኼድኹ፡፡ እነርሱ ባሉበት ቆመው ቀሩ፡፡ (ማለቴ ላይፍ ቢዚ አደረገቻቸው፡፡) 

በመንገዱ ላይ የቀትር ሐሩርን፣ የሌሊት ቁርን፣ የመጸው ነፋስን፣ የበጋ ሙቀትን፣ የበልግ ወበቅን፣ የክረምት ቅዝቃዜን ከነጓዛቸው አገኘኹዋቸው፡፡ አቀበቶቹ አደከሙኝ፤ ቁልቁለቶቹ አዳፉኝ፤ ዛፎቹ አስጠለሉኝ፤ እሾኾቹም ቧጠጡኝ፤ ዕንቅፋቶቹም ጣቶቼን አቆሰሏቸው፡፡ ለምለሙን መስክ እንደልቤ ቦረቅኹበት፡፡ መልኬ ጠየመ፤ ቆዳዬ ሻከረ፤ መዳፌ ጠነከረ፤ ውስጥ እግሬ ደደረ፤ ትከሻዬ ሰፋ፤ ድምፄ ለሰለሰ፤ ዓይኖቼ ርቆ ለማየት በረቱ፡፡ 

ከአድማሱ ወዲያ ያለውን ዓለም አየኹ፤ አምላኬ! ቤትኽ ለካ እንዲኽ ሰፊ ናት! በርቀት ጠቁመው ያሳዩኝ አድማስ አጠገቡ ስደርስ አድማስነቱ አከተመ፡፡ ቀድሞውንም ለካ እነርሱ ከቆሙበት ሲታይ እንጂ አድማስ አልነበረም፡፡ ያሳደጉኝ ሲነግሩኝ፣ ሲያስተምሩኝ፣ ሲመክሩኝ “ያ አድማስ የእኛ አድማስ ነው፡፡ አድማሱ የእውነት ዓለም ድንበር ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ያለው ስፍራም ዘንዶው የሚጫወትበት የጥፋት፣ የሐሰትና የውንብድና ዓለም ነው” ብለውኝ ነበር፡፡ ኼድኹ- አድማሱ ጋ ለመድረስ፡፡ አድማሱ አጠገብ ስደርስ ግን አድማሱ ጠፋ፡፡ ድንበሩ የለም፡፡ ለካ የማየት ዐቅማችን እንጂ ድንበሩ እውነት አይደለም፡፡ ገርሞኝ በሕጻንነት ንጽሕና “ድንበሩ የለም፡፡ ከፈለጋችኹ ኑና እዩ፡፡” ብዬ ነገርኋቸው፡፡ አልሰሙኝም፡፡ ርቀታችን የትየለሌ! እንዴት እንደማመጥ፡፡ ማን ነበር “ጉድጓድ ውስጥ የምትኖር ዕንቁራሪት የሰማዩ ስፋት በጉድጓዱ አፍ ልክ ብቻ ይመስላታል” ያለው? የትውልድ ሀገሬ ለካ ድንበር የላትም፡፡ ጌታ ሆይ! ቤትኽ እንዴት ሰ...ፍ...ፍ...ፍ...ፊ  ናት፡፡ አቤት የግዛታችን ስፋቱ! ይኼ ኹሉ የኛ ነው? ዘመዶቼ ይኽን ቢያውቁ ኖሮ ዓለም እንዲያ አትጠበብብባቸውም ነበር፡፡ መንገዱ ኮ ገና አላለቀም አይገርምም?! ታድዬ! እንኳን ልጅኽ ኾንኹኝ!  

Wednesday, May 1, 2013

ውዴን ያያችኹ ንገሩኝ


ውዴን ያያችኹ ንገሩኝ፤
ነፍሴ በፍቅሩ ታምማለች፤
ልቡናዬ በናፍቆቱ እጅጉን ተንሰፍስፋለች፡፡



 ነፍሴ ሆይ ያው! ያውልሽ!
ከሩቅ ይታያል ውድሽ
በወዳጆቹ ተክዶ
በሠላሣ ብር ተሸጦ
በግፍ ታስሮ ይጎተታል
መስቀሉ ከብዶት ይወድቃል
ደግሞም ይነሣል
          ይ
    ወ
         ድ
             ቃ
                 ል፡፡




ነፍሴ ያውልሽ ውድሽ!
ተደበደበ፤ ተናቀ፤
          ተገፋ፤
ተጣለ፤
ምራቅ……………..ተወረቀ፤
ተ…ጎ…ተ…ተ…፤
ተ…ገፈፈ፤ ታሠረ፤ ተቸነከረ፡፡

ዘውዱ የሾኽ አክሊል፣
ዙፋኑ እርጥብ መስቀል፣
ትከሻው በሸክም ቆስሎ፣
እጁ በችንካር ተቀድዶ፣
እግሩ ጎልጎታ ቆሟል፣
ደሙ እንደውኃ ይወርዳል፡፡


ጀርባው ታርሷል በአለንጋ፤
ጎኑም በጦር የተወጋ፣
ጠረኑ ሽቱና ከርቤ፣
ከበፍታ ልብሱ ዐወደ፣
ከእንግዳ መቃብር ተአንገደ፡፡

ነፍሴ ሆይ ! ያው ያውልሽ፤
በመከራው የወደደሽ፣
በሞቱ የወለደሽ፣
በትንሣኤው ሊያድስሽ፣
ተቀበረልሽ፡፡

Wednesday, April 24, 2013

በእግዚአብሔር ፍቅር



ከእግዚአብሔር ጋር ከመገናኘት የበለጠ ሕይወትን የሚቀይር ነገር የለም፡፡
እግዚአብሔርን እንደማግኘት ብርቱ የኾነ ነገርም የለም፡፡
ይህም ወደኋላ ላይመለሱ በእግዚአብሔር ፍቅር ተይዞ ወደፊት መጓዝ ነው፡፡

እግዚአብሔርን ስታፈቅር

ሐሳብኽ እርሱን ከማሰብ አያርፍም፤ 
የምታደርገው ነገር ኹሉም ለእርሱና ስለ እርሱ ብቻ ይኾናሉ፡፡

ጠዋት ከእንቅልፍኽ የምትነሣበት ምክንያትኽ
የምሽት ተግባራትኽ መንሥኤ
የዕረፍት ቀናትኽን የማሳለፊያ መንገድኽ
የምታነብባቸውን መጻሕፍትና የምትተዋወቃቸውን ሰዎች መምረጫ ሚዛንኽ
የሚያሳዝኑኽና የሚያስደንቁኽን ጉዳዮች መስፈሪያኽ
የሚያስደስቱኽና የምትረካባቸውን ነገሮች መለኪያኽ
እርሱ ብቻ ይኾናል፡፡
ፍቅሩን አጥብቀኽ ፈልግ፡፡ ለፍቅሩ ልብኽን ክፈት፡፡ በፍቅሩ ኑር፡፡
ያኔ ሕይወትኽ በፍቅሩ ይለወጣል፡፡ 

(Source:- Javier Uriarte (SJ). Reprinted from: Review of Ignatian Spirituality) 
Special Gratitude to Abba Groum Tesfaye (SJ)

Friday, April 5, 2013

ዝምታ


ሄሮድስ ትርኢት ሽቶ እስረኛውን ኢየሱስን ጥያቄ ይጠይቀው ጀመር፡፡ የሰይጣን ወጥመዶች መልካቸው ቢለያይም ኹልጊዜም ቢኾን ይዘውት የሚመጡት ፍልስፍና “እኔ”ን በእግዚአብሔር ፈንታ አምላክ አድርጎ ማቆም ነው፡፡ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በጾመ ጊዜ “እስኪ ከዚኅ ቁልቁል ተወርወርና የእግዚአብሔር ልጅ መኾንኽን አስመስክር፡፡” ብሎ በግልጥ ጥያቄ ያቀረበው ሰይጣን አኹን ደግሞ በሄሮድስ አንደበት ተአምራት እንዲያደርግ ይወተውት ጀመር፡፡ ስንት ተአምር በፊታቸው እያደረገ “መሢሕ መኾንኽን እናምን ዘንድ ምን ተአምር ታደርጋለኽ” ብለው የጠየቁት ሰዎች የአራት ቀን ሬሳ አልዓዛርን ከሞት መነሣቱን እያዩና እየሰሙም ሌላ በእነርሱ ቀመር የተዘጋጀ ተአምር እንዲሠራ ይጠይቁታል፡፡

የሄሮድስ “ተአምር ሥራና አሳየኝ” የምትል ጥያቄ ላይ ላይዋን የሰርከስ ፍቅር ትምሰል እንጂ ውስጧ “ክብርኽን ተከላከል፤ ራስኽን አስከብር” በሌላ አማርኛም “እስኪ ከመስቀል ውረድ” የምትል እግዚአብሔርን እርሱ በወደደው ሳይኾን እኔ በቀመርኹለት ቀመር ብቻ እንዲሠራ መመኘት ናት፡፡ ለዚኽች ጥሪ የሚሰጠው መልስ ግን ዝምታ ብቻ ነው፡፡ የእኔ ክብር በፍቅር ለፈጠረኝ ፍቅር የመሚገባ የፍቅር ምላሽ መስጠት ብቻ ነው፡፡ ከዚኽ ውጪ እንኳን ክብር ትርጉምም አይኖረኝም፡፡

ሄሮድስ ምኞቱ በውትወታ አልሳካ ሲለው በንቀት በኩል ሌላ የ”ማንነትኽን አስመስክር” የዕብሪት ጥሪ ያቀርባል፡፡ ጌታ ኢየሱስ ግን በሄሮድስ የንቀት ፊት የእግዚአብሔርን የትሕትና መንገድ ገለጠ፡፡ ለስድብ መልስ የለውም፡፡ ለትርኢት ተብሎ የሚደረግ በጎ ነገርም እግዚአብሔር አይከብርበትም- “እኔ” ጣዖት ኾኜ በእግዚአብሔር ፈንታ ቆሜያለኹና፡፡

ሄሮድስ ሊዘብት ጌጠኛ ካባ አለበሰው፡፡ ጌታ ኢየሱስ ግን ለዚኽም መልስ አልሰጠም፡፡ ዝምታ ብቻ፡፡ በሰው ልጆች ክፋት ውስጥ የምትሠቃየውን የእግዚአብሔርን በጎነት፣ በሰው ልጆች ጥላቻ የምትገፋውንና የምትሠቃየውን የእግዚአብሔርን የፍቅር ዕቅፍ እያሳየ ዝም አለ፡፡ ውዴ ዝም አለ፡፡

Thursday, March 21, 2013

"ወንጌል ስማ፡፡" ለምትሉኝ


“ወንጌል” ምንድነው? አንድ ከኾነ የነገረ መለኮት ትምህርት ቤት የተመረቀ፣ ወይም የኾነ ማኅበር አባል የኾነ፣ ወይም ደግሞ የኾነ ነገር ሸምድዶ ዲያቆን ወይም ቄስ ወይም ፓስተር የተባለ ሰውዬ ቀሚስ ለብሶ ወይም ከረባት አድርጎ ወይም ዐውደ ምሕረት ላይ አልያም በቲቪ ቆሞ የሚያወራው ነገር ኹሉ ወንጌል ነው? ሰውየው “ወንጌል እሰብካለኹ!” ስላለ ብቻ ጌታ ኢየሱስ ከአብ ዘንድ ይዞልን የመጣውን የምሥራች እንደሚሰብክ በምን እርግጠኞች እንኾናለን? “ወንጌላዊ ነኝ!” “ሰባኬ ወንጌል ነኝ!” ስለተባለ ብቻስ ወንጌላዊ መኾን ይቻላልን? “ክርስቲያን ነኝ!” “ቤተክርስቲያን ነኝ!” ስለተባለ ብቻስ ቤተክርስቲያን መኾን ይቻላልን? የምንገነባው ካቴድራል ወይም የምንለብሰው ቀሚስ አልያም የምንጠቅሰው መጽሐፍ ቅዱስ አልያም የምንኮፈስበት ወንጌል-ጠቀስ ባህል ስላለንና በዓል "በድምቀት ስላከበርን" ክርስቲያን መኾን ይቻላል?  

ወንጌል ስንል የምሥራች ማለታችን ከኾነ ምን ስለኾንን ነው የምሥራች የሚያስፈልገን (ያስፈለገን)? ክርስትና “እንዲኽ ስላደረግኹ እንዲኽ ይሆንልኛል” ከሚል ተራ አስማትና ከሱፐርስቲሽን በምን ይለያል?

እዚህ ላይ በተለይ በየታክሲውና በየፖሉ ላይ ተለጥፎ የማየው “ታላቅ የፈውስና የምናምን ኮንፈረንስ” ወይም “ከእንዲኽ እንዲኽ ዓይነት በሽታ ፈውስ ወደሚገኝበት ታላቁ የምናምን ገዳም የሚደረግ ታላቅ ምናምናዊ ጉዞ!” እየተባለ የሚለጠፈው ማስታወቂያ፣ የቅቤ እምነት፣ የሎሚ እምነት እየተባለ የሚነገረው ነገር፣ እንትን ለሚባል በሽታ ይኽን ያኽል ሊትር ጠበል ጠጡ የሚባለው “የጠበላውያን ምክር”፣ “ታቦቱ አልንቀሳቀስ አለ!” እየተባለ የሚወራው ትርክት፣ እገሌ የተባለ ቦታ አዲስ ጠበል ፈለቀ፣ ተአምር ተደረገ እየተባለ የምንነጉደው ነገር፣ “የቁልቢው ተከተለኝ!” እየተባለ በየመኪናው ላይ የሚለጠፈው ማስታወቂያ (“እኔ የፈለግኹበት ስኼድ አንተ እየተከተልኽ ከዐቅሜ በላይ የኾኑ ችግሮችን እየፈታኽ፣ መና እያወረድኽ፣ ከአደጋ እየተከላከልኽ የዘበኝነት አገልግሎት ስጠኝ፡፡” ለማለት ይመሥላል፡፡) ወዘተ. በአስተዋይ ኅሊና ሊመረመሩ እንደሚገባቸው አምናለኹ፡፡ 

እዚኽ ላይ ፈውስ ለምን ተገኘ እያልኹ ወይም የቅዱሳንን ረድኤት እየተቃወምኹ አለመኾኔን ተረዱልኝ፡፡ እግዚአብሔር በወደደው መንገድ ይፈውሳል፡፡ እዚያ ላይ ተቃውሞ የለኝም፡፡ የእኔ ጉዳይ እግዚአብሔርን ተገማች (predictable) ያደረግንበት መንገድ እንዲመረመር መጋበዝ ነው፡፡ 

በእኔ እምነትና ዕውቀት Predictable የኾነ እግዚአብሔር ሰዎች በአምሣላቸው የፈጠሩት ዕግዜር እንጂ አማናዊው እግዚአብሔር አይደለም፡፡ ሊኾንም አይችልም፡፡ ቤተክርስቲያን የምኼደውና የምጸልየው እኔ የምፈልጋቸው ነገሮች በሙሉ ማለትም ጎጆዬ ወይም ግራ ጎኔ ወይም ትምህርቴ ወይም ምናምኔ እንዲሞሉ ብቻ ከኾነ እየፈለግኹ ያለኹት የአላዲን ፋኖስ ውስጥ ያለውን ጂኒ እንጂ እንዴት ድኾችንም ሀብታሞችንም የሚወድደውን እግዚአብሔርን ሊኾን ይችላል? 

ይቺ እግዚአብሔርን በእኛ ፎርሙላና ሐሳብ ለመለካት የመመኘት መንገድ ድሮ ድሮ በእነ ልፋፈ ጽድቅና በነዐውደ ነገሥት፣ በነፍካሬ ኢየሱስና በሞራ ገለጣ ትገለጥ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ዘመኑን ተከትላ ነቢዩ ኤልያስን  ከምድረ ፍልስጥኤም የነጠቀው ሠረገላ ከሦስት ሺህ ዓመት በኋላ ኢትዮጵያ አምጥቶ ጣለው በሚሉን ሰባክያነ ኤልያስ በጋዜጣና በገጸ ድር መጣች፡፡ 

ዛሬ ኤልያስ መጥቷል ተብለናል፤ ነገ ቴዎድሮስ መጥቷል እንባላለን፡፡ ስላላመንን ነገን እንፈራለን፤ ስለምንፈራም ከፍርኀታችን ለመላቀቅ ስንል ነገን ለመቆጣጠር እንፈልጋለን፡፡ ነገን ለመቆጣጠር ያለው አማራጭ ደግሞ ነገን ራሱን የሚያመጣውን ኃይል መቆጣጠር ይኾናል፡፡ በቁጥጥር ሥር ያዋሉት ነገር አይከብድማ፡፡ "ተማክረው የፈሱት ፈስ አይገማም፡፡" አይደል ተረታችንስ፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሔርን የነገ ዕቅድ ለማወቅ ተአምርና ትንቢት ስናሳድድ እንገኛለን፡፡ 

እግዚአብሔር ዓለሙን በሰው ልጆች በጥላቻ በየቀኑ እየተቸነከረ በፍቅሩ ከሚያስተዳድርበት መስቀሉ እንዲወርድ እንፈልጋለን፡፡ “እስኪ! እውነት አንተ እግዚአብሔር ከኾንኽ ከመስቀል ውረድ!” እንላለን፡፡ ከመስቀል ቢወርድ ምትሐት ነው ልንል፡፡ ሰማይ ከነ ግሡ ምድር ከነግሣንግሡ የእርሱ ተአምር ኾኖ እያየነው ማመን አቅቶን ሌላ ተአምር እንሻለን፡፡ ይህ ነው የእኛ ፎርሙላ፡፡ ይኽ ነው መፈለጊያችን፡፡ ጌታ ኢየሱስ ግን “ክፉና አመንዝራ ትውልድ ተአምር ይሻል፡፡” አለ፡፡   

Monday, March 18, 2013

ኹለቱ የኑሮ መርሖች


በዓለም ላይ ስኖር የቀረቡልኝ ኹለት አማራጭ የመኖሪያ መንገዶች አሉ፡፡ አንደኛው መሥመር መነሻው « እኔ » ነኝ፡፡ እኔን ተጠቃሚ ለማድረግ፣ የእኔን ፍላጎቶች ለማሟላትና አንድም ሳይሟላ የሚቀር ፍላጎት እንዳይኖረኝ ምኞቶቼን ኹሉ እውን ለማድረግ በሚደረግ ሩጫ ይጀመራል፡፡ የመነሻ መሥመሩ ሌላው መጠሪያ «የለኝም/ ይጎድለኛል» ይሰኛል፡፡

ሩጫው በዚኽ መሥመር ይጀመርና ፍላጎቶቼን ለማሟላት የሚያስችሉ የሚመስሉኝን ነገሮች ኹሉ ለመሰብሰብ እሮጣለኹ፡፡ አባርሬ እይዛለኹ፡፡ አሳድጄ እጨብጣለኹ፡፡ እሰበስባለኹ፤ እሰበስባለኹ፤ እሰበስባለኹ፡፡ በሰበሰብኋቸው ነገሮች ደስ ይለኛል፡፡ ግን ጥቂት እንደቆየኹ የሰበሰብኹት ነገር ኹሉ ይሰለቸኛል፡፡ ስለዚኽም ሌላ አዲስ ነገር ለመሰብሰብ ሩጫዬን እቀጥላለኹ፡፡ ደስታዬን ዘላቂ ለማድረግ ሰውንም፣ ፍጥረትንም በቁጥጥሬ ሥር ለማዋል እጥራለኹ፡፡ ምንም ነገር ከእኔ ቁጥጥር ውጪ እንዲኾን አልፈቅድም፡፡ ከቁጥጥሬ ውጪ ሊኾኑ የሚሞክሩ ነገሮች ቢኖሩ እንኳ ሲደክመኝ ወንበር እያቀረበ፣ ሲርበኝ መና እያወረደ፣ ሲጠማኝ ውኃ እያፈለቀ፣ ቀን ሐሩር እንዳይመታኝ በደመና፣ ሌሊት ጨለማ እንዳያስፈራኝ በእሳት ዓምድ እንዲመራኝ የምጠብቀው አምላክ አበጃለኹ፡፡

ይህ አምላኬም ጾሙን በቀበላና በፋሲካ እያጀብኹ እስከ ጾምኹለት፣ ለቤተ መቅደሱ አሥራት በኵራቱን እስከ ሰጠኹለት፣ ጠዋት ጠዋት እየተነሣኹ የውዳሴ ቀለቡን እስከሰፈርኹለት፣ በዓላቱን ሞቅ ደመቅ አድርጌ እስካከበርኹለት፣ ድረስ ከእኔ ጋር እንደሚኾን እርግጠኛ ነኝ፡፡ የምፈልገውን ኹሉ እንደሚያሟላልኝም እተማመናለኹ፡፡ እንዴ! የኔ አምላክ ነዋ! «አባቶቼ ያመለኩት!» እኔ እርሱ የሚፈልገውን አደርጋለኹ፤ እርሱ ደግሞ እኔ የምፈልገውን ኹሉ ያደርጋል፤ ወይም ይፈቅድልኛል፡፡ ታዲያስ! ሕይወት ሰጥቶ የመቀበል ገበያ አይደለች እንዴ!

Tuesday, March 5, 2013

እመርጣለኹ!


እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ከሰጠን ስጦታዎች አንዱ መምረጥ መቻላችን መኾኑን አምናለኹ፡፡ ምርጫችን ላይም ገደብ የለብንም፡፡ እንኳን የምናደርገውን የምናመልከውን ሳይቀር መምረጥ እንድንችል ነጻ ተለቅቀናል፡፡ ለምን ነጻ ተለቀቅን ለሚል ጥያቄ እኔ መልስ መስጠት እንደማልችል ከወዲሁ ልገልጽላችኹ እወድዳለኹ፡፡[i] ምክንያቱም ውብ አድርጎ ፈጥሮ ያቀረበልንን ዓለምን እንኳ ራስን ብቻ ማዕከል አድርጎ የመጓዝ አቅጣጫን በመምረጣችን ምክንያት እነሆ በሥቃይ እንቀቅላታለን፡፡ በሰው ልጅ የተነሣ እነሆ ፍጥረት ይሠቃያል፡፡ የፍጥረት አካል የኾነው የሰው ልጅም በዚህ በምርጫው ካመጣው ሥቃይ ተካፋይ ከመኾን አላመለጠም፡፡ የአብዛኛው ሥቃዮቻችን መነሻም ራሳችንን መውደዳችን ነው፡፡[ii]

“እኔ” የሚባል መሥዋዕት የማይጠግብ አምላክ ባሮች ነን፡፡ በርትራንድ ረሰል የሚባል ፈላስፋ “የሰውልጆች ኹሉ አምላክ መኾን እንሻለን፡፡ እርስበርስ እንዳንግባባ ያደረገንም ይኸው አምላክ የመኾን ጥማታችን ነው፡፡ ከሌሎች ሰዎች ጋር በምንነጋገርበት ጊዜ ኹሉ እኛ አምላክ ሌሎቹ ደግሞ አምላኪዎቻችን እንዲኾኑ እንሻለን፡፡”[iii] ይላል፡፡

Thursday, February 21, 2013

“ከቶ አታጥበኝም!”



ታጥቀኽ ጨርቅን ለማበሻ፣
ልታጥበኝ እግሬን ስትሻ፣
“ከቶ አታጥበኝም!” ብዬ፣
በግብዝነት ተሰናክዬ፣
መስቀሌን ከእኔ እንዳላርቅ፣
   በ“እኔ” ታንቃ ነፍሴ እንዳትማቅቅ::


የጌቴሴማኒን ሐዘን ጭንቀት፣ የጲላጦስን አለንጋ፣
የጭፍሮችን የሾኽ አክሊል፣ የሄሮድስን ቀይ ካባ፣
የመስቀልን ጽዋ ተርታ፣
የጎልጎታን ዕድል ፈንታ፣
ፈርታ…
ሳትካፈል እንዳትቀር የትንሣኤኽን ሰላምታ…

አሜን! ውዴ ሆይ! እጠበኝ፡፡





ገመዴ ባማረው ስፍራ፣ በአንተነትኽ ላይ ትውደቅ፤
ርስቴም መስቀልኽ ኾኖ ዘለዓለም ፏ! ብሎ ይድመቅ፤
ነፍሴ ካለማመኗ፣ ከፍርኀቷ ዕድፍ ትላቀቅ፡፡

አሜን፡፡ አባቴ፡፡
በሂሶጵ እርጨኝ እጠበኝና፣
ዕድሌ በዕድልኽ ይጽና፡፡
                                 

Tuesday, February 19, 2013

አንተ ትሕትና ነኽ፡፡


ሙሴን መሪ ሊያደርገው ከቤተመንግሥት አውጥቶ የበግ እረኛ ያደረገ፣ ሳዖልን ለአህያ ፍለጋ በወጣበት ለንግሥና የቀባ፣ በቤተሰቦቹ ዘንድ ሳይቀር ከቁብ የሚቆጥረው የሌለውን በግ ጠባቂውን ዳዊትን የ12 ነገድ እረኛ አድርጎ የሾመ፣ ከዳዊት ድካም ሰሎሞንን ያኽል ጠቢብ የፈጠረ፣ በበረት ተወልዶ እጅ መንሻ የተቀበለ፣ በግርግም ተኝቶ ሰብአ ሰገል የሰገዱለት፣ በከብቶች ተከብቦ መላእክት የዘመሩለት እርሱ እነሆ ከነመፈጠራቸው እንኳ ለማንም ትዝ የማይሉ፣ እዚህ ግባ የሚባል ቦታ በማኅበረሰቡ ውስጥ የሌላቸውን ዓሣ አጥማጆች ለወንጌል ሥራ ጠራ፡፡ 
አዎን ጌታ ሆይ! አንተ ትሕትና ነኽ፡፡


ጴጥሮስ ገራገሩ የቤተሰብ ኀላፊነቱን ትቶ አዲስ ናዝራዊ ይከተል ዘንድ እንዴት አስቻለው ?

ያዕቆብና ዮሐንስስ አባታቸውን ከነጀልባው ትውት አድርገው ለመጓዝ እንዴት ጨከኑ?

ሌዊስ የቀራጭነት ወንበሩን፣ የተደላደለ ኑሮውን ትቶ ለመኼድ ምን አተጋው?

ጌታ ሆይ ! በልባቸው ስላበራኸው ፍቅርኽ እነርሱ ይህን ኹሉ ትተውታል፡፡ እኔንም በፍቅርኽ ብርሃን አጥለቅልቀኝና እስከ መጨረሻዋ ኅቅታ ድረስ ኹሉን እየተውኹ ልከተልኽ፡፡

በአሳራፊው ቅዱስ ስምኽ፡፡

አሜን፡፡

Saturday, January 26, 2013

ምናባዊ ጥያቄና መልስ ከቅዱሳን ጋር


በአንድ ቤተክርስቲያን ውስጥ በተቀምጫለኹ፡፡ በግቢው አፀድ ውስጥ ኑሯቸውን ከመሠረቱት አዕዋፍና የመቁጠሪያ ጸሎት ከሚያደርሱ አንዲት እናት ዝግተኛ የመቁጠሪያ ድምፅ በስተቀር ፀጥታ ነግሦዋል፡፡ ነፍሴ በፀጥታው ውስጥ ሟሟች፡፡


የአሲዚው ቅዱስ ፍራንቸስኮስ፣ የሳሉ ቅዱስ ፍራንቸስኮስና የሎዮላው ቅዱስ አግናጥዮስን አየኹዋቸው፡፡ ከአሲዚው ቅዱስ ፍራንቸስኮስ አጠገብ በደስታ የሚዘልሉ በርካታ እንስሳት ይታዩኛል፡፡ የሎዮላው ቅዱስ አግናጥዮስ ደግሞ ዓይኖቹ በተመስጦ ውቅያኖስ ላይ በርጋታ ይቀዝፋሉ፡፡ የሳሉ ቅዱስ ፍራንቸስኮስ ደግሞ በእጁ መጽሐፍ ይዟል፡፡ 














ያው እንደምታውቁት የመጽሐፍ ነገር አይኾንልኝምና “አባቴ፣ የያዝከውን መጽሐፍ ልየው?” ስል ጠየቅኹት፡፡ “ለአንዲት መንፈሳዊት ልጄ የጻፍኹት ነው፡፡” አለና ሰጠኝ፡፡ ርእሱ “Introduction to the Devout Life” ይላል፡፡ ውስጡን ገለጥ አድርጌ ሳይ የሚከተለውን አገኘኹ፡-

Tuesday, January 22, 2013

ተመልሰኽ ና!



በዚህ ዓለም ስትኖር በልብኽ ውስጥ ያስቀመጥኹት የእኔነቴ ኮከብ አለ፡፡ ይህን ኮከብ ከሑከትና ሩጫ ጨለማ ዘወር ብለኽ፣ በፀጥታና በጸሎት ብርሃን ስትፈልገው ታገኘዋለኽ፡፡ የህልውናኽ አልፋና ዖሜጋ፣ የሕይወትኽ ትርጉም ወደ ኾንኹት ወደ እኔ፣ ወደ አባትኽ ይመራኻልና ተከተለው፡፡ ኮከቡን የመከተል ጉዞኽን ስትጀምር የዚህ ዓለም ገዢ “ማነኽ ወዴት ነኽ? ማን ስለኾንኽ ነው ይህን ጉዞ የጀመርኸው?” የሚሉ ጥያቄዎችን ያቀርብልኻል፡፡

መልስኽ እንዲህ ይኹን፡- “እኔ ዩኒቨርሱን በእጆቹ ያበጃጀው የፍቅር ባርያ ነኝ፡፡ እርሱ በልቡናዬ ያስቀመጠልኝን ኮከብ ተከትዬ እየኼድኹ ነው፡፡ ዓላማዬም ለንጉሤ እኔነቴን እጅ መንሻ ማቅረብ ነው፡፡ ጉዞው ረጅም፣ መንገዱም ውጣ ውረድ የበዛበት እንደኾነ፣ ከእኔ የተሻለ ዐቅም ያላቸውን እንኳን አዳክሞ መግደል የቻለ ከባድ መንገድ እንደኾነ ዐውቃለኹ፤ ግን የጠራኝ እርሱ ኃይሌ ስለኾነልኝ ጉዞዬን እንደምፈጽመው አምናለኹ፡፡ ስሙ መጠጊያዬ፣ ኃይሉ ድጋፌ፣ ፍቅሩ መጽናኛዬ፣ ብርታቱም ምርኩዜ ናቸው፡፡” 

ገዢው ሊያታልልኽ “ተመልሰኽ ና!” ይልኻል፡፡ አንተ ግን በአዲሱ መንገድኽ ኺድ፡፡ ዕለት ዕለት ኮከብኽን ተከተል፡፡ ዕለት ዕለት ንጉሥኽን አግኘው፡፡ ዕለት ዕለት አንተነትኽን ለንግሥናው፣ ለማይነገረው ታላቅና ጥልቅ ፍቅሩ አቅርብለት፡፡ በእውነት ይገባዋልና!

እኔን ኾነኽ





ጌታ ሆይ! ምንኛ ወደድኸኝ! ስለወደድኸኝስ ምንኛ ተዋረድኽልኝ! ይህን ፍቅር ምን አንደበት ሊገልጠው፣ የትኞቹስ ቃላት ሊሥሉት ይችሉ ይኾን! የአንተ ታደርገኝ ዘንድ እኔን ኾንኽልኝ፤ ትፈልገኝ ዘንድ ተገኘኽልኝ፤ በመንግሥትኽ ታሳርፈኝ ዘንድ በድንግል ማኅጸን ኾነኽ ማረፊያ ፍለጋ ከበረት ገባኽልኝ፤ ታነሣኝ ዘንድ ወደቅኽልኝ፡፡ ጌታ ሆይ! በእውነት ሥራኽ ከአእምሮ በላይ ነው! እንደ ቅድስት ድንግል በልብ ይዞ “ዕፁብ ያንተ ሥራ!” እያሉ በምሥጋና ነፍስን በፊትኽ ከማፍሰስ ውጪ ምን መግለጫ ይኖረዋል!

የጣልኹትን እኔነቴን እኔን ኾነኽ ቀደስኸው! ያልቀደስኸው የእኔነቴ ቅንጣት የለም፡፡ ኹለመናዬን ቀደስኸው! ሰው ኾነኽ ሰው መኾንን ቀደስኸው! አቤቱ ስምኽ ይባረክ! የድንግል ማርያም ልጅ ፍጹም አፍቃሪዬ፣ የእነቴ እውነተኛ ወዳጅ ሆይ! ስምኽ ከፍ ከፍ ይበል፡፡ ጌታ ሆይ! በየዕለቱ ይበልጥ አንተን ማወቅን፣ አንተን ማፍቀርንና አንተን መከተልን በልቤ ጨምርልኝና በልቤ በየቀኑ ተወለድ፤ ኑርልኝም፡፡ እንዳረፍኽባት ግርግም ነገሥታቱም፣ እረኞቹም፣ መላእክቱም ወደ እኔ ሲመጡ የሚያገኙት አንተን ብቻ፣ የሚሰሙትም ቃልኽን፣ የሚሰማቸውም ሰላምኽና ፍቅርኽ ብቻ ይኹን፡፡ አባቴ ሆይ! እኔን የሚያገኙኝ ኹሉ አንተን እንጂ እኔን አያግኙ፡፡ በእኔ ውስጥ አንተ ብቻ እንጂ እኔ አይኑር፡፡ መድኃኒት በኾነልኝ ስምኽ! አሜን፡፡