Thursday, February 19, 2015

ኢትዮጵያዊነት፤ በደም ላይ የበቀለ ጽጌረዳ

ኧርነስት ሬናን የተባለ የ19ኛው ክፍለ ዘመን ሰው ሀገርን ሲበይነው “The nation is the culmination of a long past of endeavors, sacrifice and devotion….[It is] a large scale solidarity, constituted by the feeling of the sacrifices that one has made in the past and of those one is prepared to make in the future.”

የካቲት 12፣ ለዚኽ አባባሉ አማናዊ ምስክር ናት፡፡ የካቲት 12 ፋሺስቱን ግራዚያኒንና መኰንኖቹን በቦምብ ያቆሰሉት አብርሃ ደቦጭናሞገስ አስገዶም ሰሜነኞች ነበሩ፡፡ (በዘመናችን አማርኛ “ኤርትራውያን” ይባላሉ፤ እነርሱ ግን ራሳቸውን “ኢትዮጵያውያን” እንጂ “ኤርትራውያን” ብለው አልጠሩም፡፡ ኤርትራ የሚለው ስያሜም ጣልያን ከአድዋ ጦርነት በኋላ በጉልበት ለያዘው የምሥራቅ አፍሪካ ክፍል ያወጣው ስም እንጂ ኢትዮጵያውያን ቦታውን በዚኽ ስም ጠርተውት አያውቁም ነበር) ይኽን ጥቃት ለመፈጸም የተባበሩት ደግሞ ከኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ነገዶች የተወለዱ፣ በፋሺስት ተረግጦ መኖርን አንቀበልም ያሉ ኢትዮጵያውያን ነበሩ፡፡ ጥቃቱን ሲያቅዱም ኾነ ሲፈጽሙ በነፍሳቸው ተወራርደው ነው- በፋሸስቱ አገዛዝ ቢያዙ የሚደርስባቸውን አሰቃቂ ቅጣት ያውቁታልና፡፡ ጥቃቱ በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ከተፈጸመ በኋላ አዲስ አበባ የሞት ፍርድ ተበየነባት፡፡ ሀገሪቱን በቋንቋ ከፋፍሎ ኤርትራ፣ አማራ፣ ሐረር፣ ኦሮሞና ሲዳማ፣ ሶማልያ ብሎ ሠይሞ “እናንተ በፍጹም አንድ ሕዝብ አይደላችኹም፤ አንድ ማንነትም የላችኹም” ብሎ ሲለፍፍ የከረመው ፋሺስት ከልዩ ልዩ ነገዶች ተውጣትተው የከተሙባትን አዲስ አበባን በእሳት ሲያጋያት፣ ሰዎችን በአካፋ ሲጨፈጭፍ፣ ሲሰቅል፣ ሲረሽንና ሲያሥር ያ የሰበከው ልዩነት ትዝም አላለው፡፡ 

እነዚኽ ኹለት ነጥቦች ስለ ኢትዮጵያዊነት የሚናገሩት ነገር አላቸው፡፡ አንደኛ፣ ኢትዮጵያዊነት እነአብርሃ በአንድነት ነፍሳቸውን ያስያዙለት የነጻነት፣ የባለ ሀገርነት፣ የሀገርነት እሳቤ ነው፡፡ ኹለተኛ፣ ኢትዮጵያዊነት ማለት ከእነዚኽ ከልዩ ልዩ ነገዶች የተውጣጡ ሴቶች፣ ወንዶች፣ ሕጻናት፣ አረጋውያን ሲታረዱ በአዲስ አበባ አፈር ላይ ኮለል ብሎ የፈሰሰው ደማቸው የመሰከረው አንድነት ነው፡፡

ለዚኽነው ያ ትውልድ ተብዬው “ኢትዮጵያዊ የሚባል ሕዝብ የለም” ሲል የዘመናችን ደቀ መዝሙሮቻቸው ደግሞ “ኢትዮጵያዊ የሚባል ማንነት የለም” ሲሉን እንባችን በዓይናችን የሚሞላው፡፡ ኢትዮጵያ የሚለውን ከታሪካዊ ሕዝብ መጠሪያነት ወደ ተራ የፌዴሬሽን ስምነት በጉልበት ሲቀይሩት እምቢኝ ያልነውም የምንለውም ለዚኽ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ አለ፤ ኢትዮጵያዊ የሚባል ማንነትም አለ፤ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገርም አለች ብለን ሙጭጭ የምንለውም ለዚኽ ነው፡፡

ነፍሴ ከእነዚኽ ነፍሳቸውን አንድ አድርገው ከተወራረዱት ሰዎች የተነሣች ናት፡፡ በደም ሥሮቼ ውስጥ የሚዘዋወረው ደምም በየሜዳው ተዋህዶ ከፈሰሰው ደማቸው የተቀዳ ነው፡፡ ስለዚኽ፣ ደማቸው የፈሰሰለት የይርጋ ጨፌ ልምላሜ፣ የኤርታሌ ንዳድ፣ የባሮ ፀጥታ፣ የቢዘን ገዳም፣ የአዱሊስ ወደብ፣ የዳኽላክ ደሴቶች የእኔ የኢትዮጵያዊው ነው፡፡ የኮንሶን እርከኖች ያበጁት፣ ኦዳን ቅቤ የቀቡት፣ የአሹራን ገንፎ ያገነፉት፣ የመውሊድን ድቤ የደለቁት፣ አኵስምን ያነጹት፣ ላሊበላን የገነቡት የእኔ የኢትዮጵያዊው እጆች ናቸው፡፡ “ሆ መሬዎ!” ብሎ የኢሬቻን ዝማሬ ያፈለቀው፣ ጌረርሳውን ያሳመረው፣ በአራራይ የተንቆረቆረው፣ መንዙማን ያወረደው የእኔ የኢትዮጵያዊው ጉሮሮ ነው፡፡ የነገሥታት ጭካኔያቸው ያሠቃየኝ፣ ዘመቻቸው የገደለኝ፣ ጥበብ አልባነታቸው ያደከመኝ፣ የክፉ ቀን ረኀብ ያረገፈኝ እኔ ነኝ፡፡ እኔ ኢትዮጵያዊው፡፡ በአንድ የጎሣ ሣጥን ልወሰን የማልችል፣ የኹሉ የኾንኹ አንዱ ብቻ ግን ሊይዘኝ የማይችል፣ በእናንተ ብያኔ “ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ” የምትሉት የጎሣ ሣጥን ለትልቁ ኢትዮጵያዊነቴ የማይበቃኝ፣ ለመኖሬ ዕውቅና የማትሰጡኝ ወንድማችኹ ኢትዮጵያዊ፡፡