Tuesday, December 25, 2018

ልበስዎ ለሐዲስ ብእሲ (“ዐዲሱን ሰው ልበሱ”)(ኤፌ. 4፣ 24)


ይኽ ቃል የሚገኘው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በእሥር ቤት ኾኖ ለኤፌሶን ምእመናን በጻፈው መልእክት ውስጥ ነው፡፡ መልእክቱ በዋናነት የኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን ምእመናን እግዚአብሔር በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የገለጠውንና ያለ ዋጋ እንካችኹ ያለውን ፍጹም ፍቅር በማስተዋል፣ ይኽን ፍቅሩ አስተማማኝ የኾነ እግዚአብሔርን በማመን ጸንተው እንዲቆዩ ለማድረግ የተጻፈ ነው፡፡ በሌላ አባባል ክርስቲያን መኾን ማለት ምን ማለት እንደኾነ እንዲያስተውሉ፣ አስተውለውም ክርስትናቸውን አጽንተው እንዲኖሩ የሚያደርግ ትምህርት ያስተላለፈበት ደብዳቤ ነው፡፡ ትምህርቱ ለኤፌሶን ምእመናን ብቻ ሳይኾን በየዘመኑ ለሚነሡ ክርስቲያኖች ኹሉ እጅግ ጠቃሚ መኾኑን አምነውበትም አበው ከቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ እንዲካተት አድርገዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ክርስቲያን የመኾናቸውን ትርጉም የሚዘነጉ ምእመናን ልባቸውን እንዲያነቁበት ላለፉት ኹለት ሺሕ ዓመታት ስትጠቀምበት ቆይታለች፡፡ ዛሬም ትጠቀምበታለች፡፡  

በዚኽም መሠረት፣ ቅዱስ ጳውሎስ ዛሬ እኛን “ዐዲሱን ሰው ልበሱ” ይለናል፡፡ እሺ ብለን ዐዲሱን ልብስ እንልበስ ስንል ግን ዐዲሱን ልብስ ለመልበስ አንድ መስፈርት እንዳለ ይናገራል፡፡ ጥቅሱን ከፍ ብለን ስናነብበው ቁጥር 22 ላይ የሚከተለውን ቃል እናገኛለን፡- “በሚያታልል ምኞት የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው አስወግዱ”፡፡ ዐዲሱን ሰው ከመልበስ በፊት አሮጌውን ሰው ማስወገድ ግድ ይላል፡፡

አሮጌው ሰው ማን ነው?

አንደኛ፣ አሮጌ ነው፡፡ አርጅቷል፡፡ ከፊቱ ሞትና መፍረስ እንጂ ሕይወትና ደስታ አይጠብቁትም፡፡ 

ኹለተኛ፣ የምኞትና የመጎምዠት እሥረኛ ነው፡፡ ልቡ ዕረፍት የለውም፡፡ ከሰዎች ክብርን የመቀበል ሱስ ስለተጠናወተው በሰዎች ዘንድ ያስከብረኛል የሚለውን ነገር ለመያዝና የዚያ ነገር “ጌታ” ኾኖ ለመታየት የማይፈነቅለው ደንጊያ የለም፡፡ በቃኝ አያውቅም፡፡ ኹሌ እንደሮጠ፣ ኹሌ አንዳች ነገር ተከትሎ እንደበረረ ይኖራል፡፡ እርካታ የለውም፡፡ እንዲኽ ዓይነቱ ሰው በሰዎች ዘንድ የሚያስከብረው እስከኾነ ድረስ ክፉ ነገር ብቻ ሳይኾን ደግ ነገርንም ሊያደርግ ይችላል፡፡ ለእርሱ ዋናው ነገር በሰዎች ዓይን ከፍ ብሎ መታየቱ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሲያሠራ፣ ገዳማት ሲዞር፣ ሲጾም፣ ሲጸልይ፣ ባስ ሲልም ደግሞ ዐውደ ምሕረት ላይ ወጥቶ ሲሰብክ፣ ቤተ መቅደስ ገብቶ ሲቀድስ ሊታይ ይችላል፡፡ አንዱንም ነገር ግን ለእግዚአብሔር ክብር አያደርገውም፡፡ በእግዚአብሔር ፈንታ በራሱ ልብ ውስጥ ራሱን አንግሦ፣ ራሱን እያመለከ፣ ራሱን “ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ” እያለ የሚኖር፣ ዓለም በዙሪያው የምትሽከረከርለት የሚመስለው ዕብሪተኛ ሰው ነው፡፡ የሚያደርገው ክፉም ኾነ “በጎ” የሚመስል ድርጊት ኹሉ ከዚኽ የመመለክ፣ የመከበር፣ በሌሎች ላይ ጌታ የመኾን ጥማቱ ይመነጫል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ይኽንን እግዚአብሔርን ያለማመንና በልብ ላይ ያለማንገሥ በሽታ “ኃጢኣት” ሲል ይጠራዋል፡፡ የዚኽ በሽታ ታማሚዎች (ነጻ ፈቃዳቸውን ኃጢኣት የተቆጣጠረባቸው ሰዎች) ኃጢኣተኞች ሲል ይጠራሉ፡፡ ከእነዚኽ አንዱ “ቃየን” ይባላል፡፡ 

ቃየን በእግዚአብሔር ፊት መሥዋዕት አቅርቦ ነበር፤ መሥዋዕቱ ግን ተቀባይነት አላገኘም፡፡ መሥዋዕት ማቅረብ በጎ ሥራ ነበር፡፡ ነገር ግን ቃየን ልቡ እግዚአብሔርን ያነገሠ አልነበረምና እግዚአብሔር መሥዋዕቱን አልተቀበለውም፡፡ መሥዋዕቱን ሳይቀበለው ሲቀር ደግሞ ለምን መሥዋዕቴን ሳይቀበልልኝ ቀረ ብሎ ራሱን ከመመርመር ይልቅ፣ የወንድሙ መሥዋዕት ተቀባይነት በማግኘቱ ተናደደ፡፡ ምክንያቱም መሥዋዕት ያቀረበው እግዚአብሔርን “እንዲኽ ስላደረግኹልኽ በል አንተ ደግሞ እንዲኽ አድርግልኝ” ብሎ እግዚአብሔርን እንደባርያ ለማዘዝ እንጂ እግዚአብሔርን ለማምለክ አልነበረምና፡፡ በእግዚአብሔር ላይ የነበረውን ቁጭት ነው ወንድሙን አቤልን በመግደል የተወጣው፡፡  

እንግዲኽ ቅዱስ ጳውሎስ ይኽን በእግዚአብሔር ጌትነት የማያምነውን፣ ሰብአዊ ፈቃዱን ለእግዚአብሔር ፈቃድ ያላስገዛውን እከብር ባይ፣ ዕብሪተኛ ልቡና ነው “አስወግዱት” የሚለን፡፡ በእውነትም ይኽ የሰውን ልጅ ግላዊም ኾነ ማኅበራዊ ሰላም እንዳይኖረው ያደረገው፣ አምላክ ሳይኾን አምላክ ነኝ ብሎ “ፈቃዴን ፈጽሙልኝ፤ ለግዛቴ ተጋደሉልኝ፡፡ ለክብሬ ሙቱልኝ፡፡” እያለ መከራችንን የሚያሳየን ሐሰተኛ፣ ራስ ወዳድ፣ አሮጌ ሰውነታችን መወገድ አለበት፡፡ ለምን ምክንያቱም አለበለዚያ ዕረፍት፣ ሰላም፣ እርካታ፣ ደስታ የሉምና፡፡ የቤተ ክርስቲያን ሊቅ ቅዱስ አጎስጢኖስ “ጌታ ሆይ አንተ ለአንተነትኽ ፈጥረኸናልና ልባችን በአንተ እስኪያርፍ ድረስ ዕረፍተ ቢስ ኾኖ ይኖራል፡፡” እንዳለው፡፡  

No comments:

Post a Comment