Tuesday, December 25, 2018

ቃል ለምን ሥጋ ኾነ?


“አምላክ ለምን ሰው ኾነ” ለሚለው ጥያቄ አብዛኛው ሰው የሚሰጠው መልስ “ከኃጢኣታችን ሊያድነን” የሚል ኾኖ ይታያል፡፡ ይኽ መልስ ግን በአምላክ ሰው መኾን የተገኘውን ውጤትና አምላክ ሰው የኾነበትን ምክንያት የሚያደበላልቅ ደካማ መልስ ነው፡፡ አምላክ ሰው የኾነው በሰው ልጅ ኃጢኣት ምክንያት አይደለም፡፡ ከመጽሐፍ ቅዱስም፣ ከሐዋርያትም፣ ከቀደሙት አበውም “አምላክ ሰው የኾነበት ምክንያት የሰው ልጅ ኃጢኣት ስለሠራ ነው” የሚል ትምህርት አላስተማሩም፡፡ የክርስትና አስተምህሮ ፍጥረትን ካለመኖር ወደ መኖር ካመጣው ከእግዚአብሔር ሞልቶ ከሚፈስሰው የማይለወጥ የእግዚአብሔር ፍቅር እንጂ ከኃጢኣት አይጀምርም፡፡   
  
አምላክ ሰው የኾነው ዓለም ሳይፈጠር ጀምሮ የሰውን ልጅ የመለኮቱ ባሕርይ ተካፋይ ለማድረግ የነበረውን ዕቅድ ሊፈጽም ነው፡፡ ቅዱስ ሄሬኔዎስና ቅዱስ አትናቴዎስ በመጽሐፎቻቸው እንዳሰፈሩት የሰው ልጅ የእግዚአብሔር ልጅ ይኾን ዘንድ የእግዚአብሔር ልጅ የሰው ልጅ ኾነ። እርሱ በባሕርዩ የኾነውን ኹሉ እኛ በጸጋ እንኾን ዘንድ እኛን ኾነ። የአብ ብቸኛ ልጁ ከእመቤታችን ተወልዶ ወንድማችን ስለኾነልን ወንድሞቹም ስለተባልን በእርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ተባልን። "አብ እንዴት ያለውን ፍቅር እንደሰጠን እዩ!" (1ኛ ዮሐ 3፣ 1)። በወልድ ውሉድ፣ በቅዱስነቱ ቅዱሳን፣ በክርስቶስነቱ ቤተ ክርስቲያን ተሰኘን። ይኽ ለእኛ የተሰጠው ሕያውነትም በእኛ ብቻ ወስነን እንድናስቀረው አይደለም የተሰጠን፣ በእኛ በኩል ፍጥረት ኹሉ የእግዚአብሔርን ጸጋ እንዲለብስ የጸጋ መስኮቶች እንድንኾን ነው እንጂ።  
 
ፍጥረት ኹሉ የተፈጠረው በእርሱና ለእርሱ ነውና እርሱ የፍጥረት ራስ በመኾን ፍጥረትን የመለኮቱ ባሕርይ ተካፋይ ለማድረግ ዓለም ሳይፈጠር፣ ዘመን ሳይቆጠር በፊት ወስኖልናል፡፡ የሰው ልጅ በኃጢኣት መውደቅ እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ያቀደውን ከአእምሮ በላይ የኾነ ስጦታ እንዳይሰጥ አልከለከለውም፡፡ ከእግዚአብሔር ተለይተን እርስ በርሳችንም ተለያይተን የኖርንበት የኃጢኣታችንን ግንብ መናዱ የቃል ሥጋ መኾን ካስገኘልን ውጤቶች አንዱ ነው እንጂ አምላክ ሰው የኾነበት ምክንያት አይደለም፡፡ ከዛሬ አንድ ሺሕ ስድስት መቶ ዓመት በፊት የቁስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳሳት የነበረው ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የቲቶን መልእክት ባብራራበት ድርሳኑ ላይ ይኽን አስመልክቶ እንዲኽ ብሏል፡- 

መዳናችን ሐሳብን በመቀየር አኹን የተደረገ  አይደለም፤ ከመጀመሪያው የታቀደ ነበር እንጂ፡፡ ጳውሎስ ይኽንን በተደጋጋሚ ያረጋግጣል፤ ልክ በሮሜ 1፣1 ላይ “ለእግዚአብሔር ወንጌል ተለየ” ሲል እንደሚያደርገው፡፡[1] ደግሞም “አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ ይመስሉ ዘንድ ወስኗልና” እንዲል (ሮሜ 8፣ 29)፡፡ በዚኽም ጥንተ ታሪካችንን ያሳየናል፡፡ የወደደን አኹን አይደለም ገና ከመጀመሪያው አፈቀረን እንጂ፡፡
 
ቅዳሴ ማርያምም “ፍቅር ሰሐቦ ለወልድ ኃያል እመንበሩ ወአብጽሖ እስከለሞት” (ፍቅር ኃያል ወልድን ከዙፋኑ ሳበው እስከሞትም አደረሰው) እንዲል፡፡ 


[1] ይኽ ሐረግ የሚገኝበት ዐረፍተ ነገር “አስቀድሞ ተስፋ ለሰጠው” የሚል ሐረግ አለው፡፡ ዮሐንስ አፈወርቅም በዚኽ አባባሉ እርሱን እየጠቆመ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment