Tuesday, October 27, 2015

ተጨማሪ የፌደራል መንግሥቱ የሥራ ቋንቋን በተመለከተ



የደቡብ አፍሪካ መንግሥት 11 የሥራ ቋንቋዎች እንዳሉት ይናገራል፡፡ ይኽ በሕግ ደረጃ (de jury) ተቀመጠ እንጂ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ እውነተኞቹ (de facto) የሥራ ቋንቋዎች እንግሊዘኛና አፍሪካንስ የተሰኘው የደች ድቅል ቋንቋ ናቸው፡፡ ሕጉም ቋንቋዎቹ በሀገሪቱ ውስጥ ለመኖራቸው ዕውቅና ከመስጠት የዘለለ ሥራ ሲሠራ አይታይም፡፡ በዩኒቨርሲቲዎች፣ በከፍተኛ ፍርድ ቤቶች፣ በፓርላማ፣ በትምህርት ቤቶች ገንኖ የሚገኘው የሥራ ቋንቋ እንግሊዘኛ ነው፡፡ ሕዝቡም በዚኽ ላይ ቅሬታ ያለው አይመስልም- ቢያንስ እኔ እንደታዘብኹት፡፡ እንዲያውም ወደ ኋላ ተመልሰን በሀገሪቱ ፀረ አፓርታይድ ትግል ታሪክ ውስጥ ከፍ ያለ ስፍራ የሚሰጠውን የሶዌቶን ዐመፅ ብንመረምር የዐመፁ አንድ ዐቢይ መንሥኤ “በእንግሊዘኛ ካልተማርን” የሚለው የጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን ጥያቄ እንደነበር እንመለከታለን፡፡

ይኹን እንጂ፣ የደቡብ አፍሪካ ሕዝብ ለቋንቋዎቹ ግድ የለውም ማለት አይደለም፡፡ ሕዝቡ ቋንቋዎቹ ዕውቅና እንዲነፈጉ አይፈልግም- ለአንድ ቋንቋ ዕውቅና መንፈግ ለቋንቋው ተናጋሪዎች ህልውና ዕውቅና የመንፈግ ምልክት ነውና፡፡


በዚኽ ረገድ በ125ኛው አንቀጹ ላይ አማርኛን በብቸኝነት የሀገሪቱ ብሔራዊ ቋንቋ አድርጎ የደነገገውን የንጉሠ ነገሥቱን ሕገ መንግሥት የ1966ቱ አብዮት ሲንደው ኢትዮጵያ አንድ እርምጃ ወደፊት ተራምዳለች፡፡ ደርግ 16 ቋንቋዎችን የሚጠቀም የመሠረተ ትምህርት ዘመቻ ሲያውጅም ኾነ ኋላ ላይ በ1980ው ሕገ መንግሥት አማርኛን “ከብሔራዊ ቋንቋነት” ወደ “የሥራ ቋንቋነት” ሲቀይረው ዋና ግቡ ለሌሎች ሀገራዊ ቋንቋዎች ዕውቅና መስጠት ነው፡፡ ፕሬዚደንቱ ሲሾም በሚፈጽመው ቃለ መሓላም የሀገሪቱን ቋንቋዎችና ብሔረሰቦች በእኩል እንደሚያገለግል ቃል እንዲገባ ያስገድድ ነበር፡፡ ምንም እንኳ ኢሕአዴግ ራሱን የብሔረሰቦች መብት ብቸኛው ዋስ ጠበቃ አድርጎ ለማቅረብ ቢሞክርም ለሀገሪቱ ቋንቋዎች ዕውቅና በመስጠትም ኾነ የሥራ ቋንቋን በማወጅ ረገድ የ1987ቱ የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት ከ1980ው የኢሕዲሪ ሕገ መንግሥት የሚለይበት ምንም ዐቢይ ነገር የለም፡፡ ምናልባት የ1987ቱ ሕገ መንግሥት ጉልሕ መለዮው ሀገሪቱን በዐበይት ቋንቋዎች ከልሎ እያንዳንዱ ክልል የራሱን የሥራ ቋንቋ እንዲወስን ዕድል መስጠቱ ነው፤ ይኽን በ1980ው ሕገ መንግሥት አናይም፡፡

ከ2002 ምርጫ ወዲኽ ሀገሪቱ ተጨማሪ የሥራ ቋንቋ እንዲኖራት የሚጠይቁ የፖለቲካ ቡድኖች በርክተዋል፡፡ አንዳንዶቹ ይኽ የሥራ ቋንቋ ኦሮምኛ መኾን አለበት ይላሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ የትኛው ቋንቋ መኾን እንዳለበት በውሳኔ-ሕዝብ (referendum) ይወሰን የሚል ሐሳብ ያቀርባሉ፡፡ ይኹን እንጂ፣ የእነዚኽን ወገኖች ዕቅድና ግብ ከፖለቲካ ፕሮግራሞቻቸው ስንመረምር አንዳቸውም ይኽን ተጨማሪ የሥራ ቋንቋ ከዐዋጁ በኋላ እንዴት ሥራ ላይ እንደሚውል የጠራ ዕቅድ የላቸውም፡፡ ይኽም እነዚኽ ቡድኖች ተጨማሪ ሀገራዊ የሥራ ቋንቋ ዐዋጁን ከትእምርታዊ (symbolic) ፋይዳው በዘለለ የሚፈልጉት መኾኑን እንድንጠራጠር ያደርጋሉ፡፡

“The devil in the detail”

አንድ ቋንቋ የሀገሪቱ የሥራ ቋንቋ ሲኾን ቋንቋውን በአፍ መፍቻነት የማይናገሩትን የሀገሪቱን ዜጎች ከሀገሪቱ ምጣኔ ሀብታዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎ የሚያገልል መኾን የለበትም፡፡ ለዚኽ ደግሞ ሰፊ የትምህርትና የማኅበረሰባዊ ስምምነት ዝግጅት ይጠይቃል፡፡ ለምሳሌ፣ በፌደራል መንግሥቱ ውስጥ ያሉ የፌዴሬሽኑ አባላት በሙሉ በትምህርት ሥርዓታቸው ውስጥ ሊያካትቱት ይገባል፡፡ ይኽም ሰፊና የተደራጀ የሥርዓተ ትምህርት፣ የመጻሕፍት፣ የትምህርት መርጃ መሣሪያዎች፣ የመምህራን ዝግጅት እንዲኹም የተማሪዎችን (የማኅበረሰቡን) የመማር ፈቃደኝነት ይጠይቃል፡፡ የትርጉም ሥራ ዝግጅት ደግሞ ሌላው እጅግ መሠረታዊ ነገር ነው፡፡ መንግሥታዊ ኮሚዩኒኬሽንና ሀገራዊ ሰነዶች በሙሉ በኹለቱም የሀገሪቱ የሥራ ቋንቋዎች መዘጋጀት፣ መሰነድ ይኖርባቸዋል፡፡ ይኽን ለማድረግ ከፖለቲካዊ ቆራጥነት በላይ ምጣኔ ሀብታዊ ዐቅምና ማኅበረሰባዊ ስምምነት (social concensus) ያስፈልጋሉ፡፡ አለበለዚያ “የእገሌ ቋንቋ ተጭኖብን” የሚል ሌላ የብስጭት ትርክት ከመፍጠር ፈቀቅ ማለት አይቻልም፡፡ የኢትዮጵያ አጠቃላይ የፖለቲካ መንፈስ የጋራ ተጠቃሚነትን ሳይኾን ቡድናዊ ተጠቃሚነትን ብቻ ታላሚ በሚያደርግ ዐጭር ዕይታ (short sightedness)፣ በዝቅተኝነት ስሜት፣ በከማን አንሼ ፉክክር የተቃኘ በመኾኑ ይመስላል የተጨማሪ ቋንቋ ጠያቂዎቹ በዚኽ ረገድ ምንም ዕቅድ ይዘው ሲቀርቡ የማይታዩት፡፡ የትኛውንም ቋንቋ ለሥራ ቋንቋነት ከማጨት በፊት በቅድሚያ ሊሠሩ የሚገባቸው ምጣኔ ሀብታዊና ማኅበረሰባዊ መደላድሎች አሉ፡፡ እነርሱን ሳያሟሉ የሥራ ቋንቋ ማወጅ ከንቱ ኩራት ከመፍጠር አያልፍም፡፡ አማርኛን ከአገው ሥርወ መንግሥት ጀምሮ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ቋንቋ ያደረገው ማኅበረሰባዊ መደላድሉ ነው፡፡ በጎንደር ቤተ መንግሥት ኦሮምኛን ያገነነው የጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረው ማኅበረሰባዊ መስተጋብሩ እንጂ ዐዋጅ አይደለም፡፡ 

No comments:

Post a Comment