Tuesday, April 8, 2014

ዐረፍተ ነገሯ ስትመዘዝ፤ የመብራት ኃይል ጉዳይ (Anayzing the Sentence of the Deputy Prime Minister)

ይኽን ጽሑፍ ከጻፍኹ ትንሽ ቆየት ብሏል፡፡የጻፍኹትም አንድ መጽሔት ውስጥ ያነበብኹት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ተብሎ ይጠራ የነበረውን ተቋም ከኹለት መከፈል የሚያትት ዜና ላይ አንድ ሐሳቤን የቆነጠጠችኝ ነገር ከተመለከትኹ በኋላ ነው፡፡
እንደመጽሔቱ ዘገባ ሠራተኞቹም በአዲሱ አወቃቀር ውስጥ ለመካተት እንዲችሉ በእንግሊዘኛ የተዘጋጀ ቅጽ እንዲሞሉ ተጠይቀዋል አሉ፡፡ ይኼ ሲያሻው እጨለማ ውስጥ የሚያሳድረንን፣ ሲያሻው ሥራ አስፈትቶ የሚያውለንን ብልጭ ድርግም የሚያስቀርልን ከኾነ እሰየው! እልልልል! እንኳን እኹለት ለምን ሃያ ኹለት ቦታ አይከፍሉትም!


እኔን የቆነጠጠኝ መከፈሉ ሳይኾን ሠራተኞቹ እንዲሞሉት የታዘዙት ቅጽ በእንግሊዘኛ የተዘጋጀ መኾኑ ነበር፡፡ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ደብረ ጽዮን ጋር ባደረጉት “ውይይት” ላይ ሠራተኞቹ፣ ቅጹ ለምን በእንግሊዘኛ ኾነ የሚል ጥያቄ አንሥተው እንደነበር መጽሔቱ ያትታል፡፡ ሚኒስትሩም፣ “እነርሱ (ሕንዶቹ) ወደ አማርኛ ከሚመጡ እኛ ወደ እንግሊዘኛ ብንኼድ ይቀለናል የሚል ነው፡፡” ማለታቸው እንደተሰማ ይጠቁማል፡፡


መቼም ነገሩን ላይላዩን ላየው ሰው የሚኒስትሩ መልስ ቀላልና ወጪ ቆጣቢ ይመስላል፡፡ ነገር ግን ውስጡን በማኅበራዊ ሥነ ልሳን (Sociolinguistics) ትምህርት፣ በተለይም ደግሞ ከቋንቋ ፖለቲካና ከቋንቋ አመለካከት (language attitude)  አኳያ፣ ስናየው ሚኒስትሩ ተናገሩ የተባለው ዐረፍተ ነገር የያዘው ፍቺ እጅግ ብዙ ኾኖ እናገኘዋለን፡፡

ሥውርና ገሃድ ፖሊሲ


በቋንቋ ፖለቲካ ትምህርት ውስጥ የቋንቋ ፖሊሲዎች ከሚከፈሉባቸው መንገዶች አንዱ ሥውር (Covert)ና ክሡት (Overt) የሚለው ነው፡፡ ክሡት የሚባሉት የቋንቋ ፖሊሲዎች በገሃድ የሚነገሩ፣ በጽሑፍ የሚሠፍሩና በዐዋጅ የሚታወጁ ሲኾኑ ሥውር የሚባሉት ግን በዐዋጅ ያልታወጁ፣ በጽሑፍም ያልሰፈሩ፣ በገሃድም ያልተነገሩ ነገር ግን በልዩ ልዩ መልኮች ተፈጻሚነትን የሚያገኙና በመፈጸምም ህልውናቸውን የሚያረጋግጡልን የቋንቋ ፖሊሲዎች ናቸው፡፡ ለምሳሌ፣ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አማርኛ የፌደራል መንግሥቱ የሥራ ቋንቋ መኾኑን ያውጃል፡፡ ይኽ እንግዲኽ ክሡት የቋንቋ ፖሊሲ ይባላል፡፡ በዚኽ ክሡት ፖሊሲ የተነሣም የትኛውም የፌደራል መሥሪያ ቤት የሚጠቀመው የሥራ ቋንቋ አማርኛ እንዲኾን ይገደዳል፡፡
በሌላ በኩል፣ አንድ ስሙን በማልጠቅሰው የግል ባንክ ለመቀጠር ከሒሳብ አያያዝ ትምህርት በተጨማሪ የኦሮምኛ ቋንቋ መናገር መቻል ግድ እንደሚል ሰምቻለኹ፡፡ ምንም እንኳ ባንኩ በግልጽ የሰፈረ “ኦሮምኛ ቋንቋን የማይችል ሰው እዚኽ ድርጅት ውስጥ ሥራ ማግኘት አይችልም፡፡” የሚል ደንብ ባያወጣም፣ የመወዳደሪያ መስፈርቱ ላይም ባይሰፍር- ኦሮምኛ የማይችሉ ሰዎች በሥራ ውድድር እንዳያልፉ፣ ኦሮምኛ የሚችሉ ተወዳዳሪዎች ደግሞ ሥራውን እንዲያገኙ በማድረጉ ብቻ ሥውር የቋንቋ ፖሊሲ አለው ይባላል፡፡ ይኽ ሥውር ፖሊሲም በሕዝቡ ዘንድ እየታወቀ ሲኼድ ኦሮምኛ የማይችሉ ሰዎች ፈጽሞ ወደ ባንኩ ኼደው ሥራ አይወዳደሩም፣ እንደማያልፉ ያውቁታልና፡፡

ወደ ቀደመው ነገራችን ስንመለስ


ሚኒስትሩ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ሠራተኞች ሰጧት የተባለችው መልስ ከቋንቋ ፖለቲካ አኳያ ስትመዘን የመንግሥትን ሥውር ፖሊሲ፣ የሚኒስትሩን ደግሞ የቋንቋ አመለካከት (language attitude) የማሳየት ዐቅሟ የማይናቅ ይኾናል፡፡

“እነርሱ” እነማን ናቸው? እኛስ ማነን?


በዚያች ዐረፍተ ነገር ውስጥ “እነርሱ” የተባሉት የሕንዳዊው አማካሪ ኩባንያ ሰዎች (ምናልባትም ሙሉ በሙሉ ሕንዳውያን) ናቸው፡፡ በዐረፍተ ነገሯ መሠረትም “እነርሱ” ሕንዳውያኑ አማርኛ አጥንተው፣ በአማርኛ ቅጽ አዘጋጅተው እንዲሞላ ከሚያደርጉ ይልቅ “እኛ” ኢትዮጵያውያውኑ በእንግሊዘኛ የምንሞላው ቅጽ ተሰጥቶን ብንሞላው ይቀላል፡፡ ጥያቄው የሚነሣው እንግዲኽ እዚኽ ላይ ነው፡፡ ቅጹን እንዲሞሉት ከተደረጉት ሠራተኞች መካከል ምን ያኽሉ እንግሊዘኛ ያውቃሉ? (ያውም ቅጽ መሙላት በሚያስችላቸው ደረጃ) እነዚኽ ሰዎች ቅጹን ሲሞሉ የማይገባቸው ነገር መኖሩ የሚጠበቅ ነገር መኾኑ ከማንም የተሠወረ አይመስለኝም፡፡ ሌላው ቀርቶ ጠቅላይ ሚኒስትራችን እንኳ የማንዴላ ቀብር ለት ያደረጉትን የእንግሊዘኛ ንግግር፣ አቶ ደመቀ መኮንን በጋዜጠኞች ጉባኤ ተገኝተው በእንግሊዘኛ መልስ ሊሰጡ የሞከሩበትን መንገድ፣ በቅርቡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደቡብ ሱዳን ጁባ ላይ የሰጡትን ጋዜጣዊ መግለጫ ቢቢሲና አልጀዚራ ላይ ያስተዋለ ሰው የእንግሊዘኛ ትምህርት በኢትዮጵያ ውስጥ ያለበትን የቅጥነት ደረጃ መገመት ይሳነዋል ብሎ ማመን ይከብዳል፡፡

አንድ መጠይቅ ሲዘጋጅ ሊያሟላ ከሚገባቸው ነገሮች መካከል የመጠይቁ ሞዮች በሚገባ የሚረዱት መኾን መቻል አንዱና ወሳኙ ነጥብ ነው፡፡ ስለኾነም፣ ሞዮቹ በማይገባቸው ቋንቋ ፈጽሞ ሊዘጋጅ አይገባውም ማለት ነው፡፡ የሚሞሉት መጠይቅ በትክክል ገብቷቸው ካልሞሉት በሠራተኞቹ ሥራና ህልውና ላይ ሊያመጣ የሚችለው ጣጣ እጅግ ብዙ ሊኾን ይችላል፡፡ ይኽ የትኛውም ጤነኛ አእምሮ ያለው ሰው የሚስተው አይመስለኝም፡፡


እንዲኽ ጣጣው ብዙ የኾነን መጠይቅ ሞዮቹ በማይገባቸው ቋንቋ ማዘጋጀት አንድም፣ በመንግሥት በኩል ያለ የሚመስለውን ሥውር ፀረ-አማርኛ ፖሊሲ (የአማርኛ ቋንቋ ትምህርት የመሰናዶ ተማሪዎች እንዳይፈተኑት መደረጉን ያስታውሷል)፣ አንድም፣ መንግሥት ስለ ሀገርኛ ቋንቋዎች ግድ የሚለው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን የሚባለው በዓል ሲደርስ መኾኑን ነው፡፡ የሚኒስትሩ ዐረፍተ ነገር ደግሞ ሚኒስትሩ ለሀገርኛ ቋንቋዎች ዝቅተኛ አመለካከት አላቸው ሊያሰኝ ይችላል፡፡ አንድም፣ በሌሎች በአውሮጳውያን ቅኝ ሲገዙ የኖሩ ሀገራት ውስጥ ሥር የሰደደው የራስን ቋንቋና ሥልጣኔ የመናቅ በሽታ እርሳቸውንም ተጠናውቷቸው ይኾን ያሰኛል፡፡ አንድም፣ የሥራ ቋንቋውን በይፋ በደነገገ የፌደራል መንግሥት ሥር የሚተዳደር ኮርፖሬሽን ውስጥ በማማከር ሰበብ እንዲኽ ዓይነት ስሕተት ሲፈጸም ሚኒስትሩ ግፋ በለው የሚሉ ከኾነ “ሕግ” የሚባለው ነገር የሚሠራው ለእኛ ለስም የለሽ ዜጎች ብቻ ነው ማለት ነው፡፡ እንዲኽ ከኾነ ዘንድም በዘመናዊት “Republic” ሳይኾን “Justice is the interest of the powerful” ሲል በሚያውጀው በሶቅራጥስ ተቃራኒ በትራሲማከስ (Trasymachus) ዓለም ውስጥ ነን ማለት ነው፡፡

ምን ሊደረግ ይችል ነበር? ምንስ ሊደረግ ይችላል?


ለወደፊቱ፣ እንዲኽ የውጭ ሀገር አማካሪዎችን ወደ ሀገራችን (በተለይ የፌደራል መሥሪያ ቤቶች) በሚያስመጡበት ጊዜ -አማካሪዎቹ ከየትኛውም የዓለም ጥግ ይምጡ፤ የትኛውንም ቋንቋ ይናገሩ- ቅጾቹ በፌደራል መንግሥቱ የሥራ ቋንቋ፣ በአማርኛ (እደግመዋለኹ በአማርኛ!) ተተርጉመው ሊቀርቡ ይገባል፡፡ አንድ ባለ ስድስት ገጽ ቅጽ ለማስተርጎም ከ2000 ብር በላይ አይወጣም፡፡ ሞዮቹ ያልገባቸውን ቅጽ ሞልተው በሠራተኞቹ ላይም ኾነ በመሥሪያ ቤቱ ብቃት ላይ ሊፈጠር የሚችለውን ችግር ግን በ2000 ብር መመለስ ይቻል እንደኾነ አንባቢ ይታዘበው፡፡ ባለሥልጣናቱ ባለሥልጣናት ያደረገን ሕግ ነው ብለው የሚያምኑ ከኾነ ወደዱም ጠሉም ሕጉን ማክበር ይገባቸዋል፡፡ በዙሪያቸው የተሰበሰቡት የፖሊሲና የሕግ አማካሪዎችም ይኽንን ሊያስተምሯቸው ያስፈልጋል፡፡

“በእኛ ሀገር ዕውቀት ከሥልጣን ይመነጫል፡፡” አሉ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም፣ እውነት ብለዋል፡፡

No comments:

Post a Comment