Friday, November 26, 2010

ግጥም ስናጣጥም Enjoying Amharic poetry

ገጣሚ፡- ገብረ ክርስቶስ ደስታ           

(መንገድ ስጡኝ ሰፊ፣ ገጽ 62)

የዓለም መራራነት

ያለም መራራነት ነው የሚጣፍጠን
መቸ መጣፈጧ፤
ኮሶውን በማሯ ጠቅልላ ስትሰጠን
        ስትሰጠን እሳቱን
አመድ አስመስላ ሸፍና ረመጡን፡፡
ስትሰጥ ማየ ሕይወት ስትሰጠን መድኃኒት
መርዟ ጨምራበት፡፡
ስትሰጠን እሬቱን ስኳር አስመስላ
እንደጎመን ሠርታ ሳማዋን ስንበላ፡:
                                
                                እሷ ትዞራለች
                                ፀሐይ ትሞቃለች
እኛን በብርድ ላይ በጨለማ ጥላ፡፡
ያለም መራራነት
የሚያቆራምድ ነው፤ የሚያኮራምት፡፡
ስትወስድ ወደኋላ ስትወስድ ወደ ሌላ
ምሥጢር ያላት መስላ፡፡
ከቤተሰብ ማሕል
ሰው ስታስኮበልል፡፡
ስትወስድ ስጦታዋን
ለገጸበረከት ያቀረበችውን፡፡
ሌባ ናት ሰራቂ
ቀጣፊ ነጣቂ፡፡
አቀባባይ ቀልማዳ፤ አታላይ አስመሳይ
ዋሾ ናት ወላዋይ፡፡
ሰው ሊኖር ባለም ላይ መች ተፈጠረ!
መንገደኛ እንግዳ
መሽቶበት የመጣ
ሠራተኛ አገልጋይ ነው የተቸገረ፡፡
ብዙ ነው ልፋቱ
ሲፈጠር፤ ሲመጣ፤ ሲወጣ ከቤቱ፡፡
አይችልም መዝናናት
በደመነፍስ ባሕርይ እንደተቀረጹት፡፡
እንዳህያ እንደጅብ ወይም እንደጦጣ
ወይም እንዳንበጣ
የማይቸገሩት ለምን ያስባሉ?
ከብቶች ይግጣሉ፤ ወፎች ይዘፍናሉ
አበቦች ያድጋሉ፡፡
ውስጡን አላወቁም፤ አልተመራመሩም
ሲመጡ ወዳለም፡፡
የውሸት ሥዕል ናት
                                ለዛዋ እሚጠፋ ቀለሟ እሚጠፋ፡፡
ጠረኗ እሚያባርር፤ ጣሟ እሚከረክር
ቧልቷ የሚያስመርር፡፡
የሰው ልጅ አንድ ባንድ ልታንሸራሽረው
ሁልጊዜ እንግዳ ነው
ማናፈስ ማቅበጧ
ማቻኮል ማሮጧ፡፡
ያለም መራራነት ነው የሚጣፍጠን
                                መቸ መጣፈጧ! 





የግጥም ልክፍተኛው ወዳጄ ሲሳይ ጫን ያለው ሬድዮ ፋና ላይ “ግጥም እናጣጥም” የሚል ድንቅ ዝግጅት ይዞላችኋል፡፡


By the way,
I got the pictures from the internet.
The man on the photograph is Gebrekirstos himself. The title of the painting below the poem is Patriots. <the3rdman.com>








8 comments:

  1. Thought this article relevant to your post.
    I like your pic on the bus and the cappucino.
    http://www.ethiopia.org/index.php?option=com_content&view=article&id=540:gebre-kristos-desta&catid=5:ethiopian&Itemid=79

    ReplyDelete
  2. ሐገሬ ታማብኝ
    ሠዎች በወለዱት
    በማይድንም ህመም
    በማየሽርም ደዌ
    ሐገሬ ታማብኝ እምየ በጸና፣
    ባይም ብመለከት
    ለዛዋን አጥታ
    አይሆኑትን ሆና፤
    እኔማ ዘንድሮ
    ሠማዩን በማየት
    ሳንጋጥጥም አለሁ
    አንገቴን ሳቀና፣
    እያልኩት አምላኬን
    ትዝብትህ አብቅቶ
    ሐገሬን ሚታገድ
    ታምራትም አዉርድ
    መኖርዋን ታዉቃለህ አንተኑ ተማምና፤፤

    በፋሲካዉ ዘርፉ
    ነሃሴ 03፤2004 ዓ.ም.
    fasizer@yahoo.com

    ReplyDelete
  3. የዝምታ ድምፀት
    የዝም አይነቅዝም ስሌት
    ከአባባል ያለፈዉ
    የሃሳቡ ንረት
    ለኛ ያልተሰማን
    ትርጉሙ ያልገባን
    የጩኸቱ ልኬት
    በፀፅታዉ ያለዉ
    የዝምታዉ ግመት
    ሠባት ሠማይ አልፎ
    በዛ ሊደመጥ ነዉ
    ዕዉነትም ባለበት
    የዝምታዉ ድምፀት
    ትርጉም ሠዋሰዉ በቅኔ ተዋዝቶ
    በሚዘረፍበት

    በፋሲካዉ ዘርፉ
    ነሃሴ 03፤2004 ዓ.ም.
    fasizer@yahoo.com

    ReplyDelete
  4. የነፍሴን እጣ አልበሉት
    ሥጋየን ቢያበሰብሱት
    ዘመኔን ቢያሳጥሩት
    ላይቀጠል ቢቆርጡት
    የሕይወት ግርዶሽ አዉጀዉ
    ቢያደርጉብኝ የቀትር ምሽት
    የአሸናፊነት ጉዞየን በመንገድ ላይ ቢቀጩት
    የኑሮ ሕልሜን ቀጥቅጠዉ
    ከራሳቸዉ ቢጨምሩት
    ሥጋቸዉን ቢያደልቡት
    የሥጋየን ብቻ እንጅ
    የነፍሴን ዋጋ አልወሰዱ
    የነፍሴን እጣ አልበሉት


    በፋሲካዉ ዘርፉ
    ሰኔ 08 2000 ዓ.ም.
    fasizer@yahoo.com

    ReplyDelete
  5. ውበትህ ልዩ ነው


    ውበትህ ልዩ ነው
    የለም የሚመስልህ
    አሰራርህ ልዩ
    ብዙ ነው ጥበብህ
    ሰምቼ ነበረ ብዙ በጆሮዬ
    አይኔ አይታሀለች
    የኔም በተራዬ
    ታዲያ ለማሞገስ
    ቃላት አጣሁና
    አንተ ለማወደስ
    ዝም ብዬ ብዳክር
    የሚመጥን ሀሳብ
    ቢጠፋኝ ብቸገር
    እንዲያው ሁሉን ጥዬ
    እጆቼን አነሳሁ
    ፊቴን አንጋጥጬ
    ይገባሃል ብዬ!

    ReplyDelete
  6. God bless you brother,let us get connected.Bekele

    ReplyDelete
  7. Thank you, Belachew. It is beautiful.

    ReplyDelete