Saturday, October 6, 2012

ዕረፉ፡፡ እኔም አምላክ እንደኾንሁ ዕወቁ፡፡ (መዝ. 46፡ 10)


ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ጳጳስ በሚቀድሱበት ቤተክርስቲያን ውስጥ አንዲት ድብርት ፊታቸው ላይ ጎጆዋን የሠራችባቸው የሚመስሉ ክርስቲያን እናት ከፊት ለፊታቸው ተመለከቱ፡፡ በቅዳሴ ላይ እያሉ ድብርት የተከናነበውን የሴትየዋን ፊት ያስተዋሉት ጳጳስ በቅዳሴው ፍጻሜ ሴትየዋን ወደኋላ ቀረት ብለው እንዲያናግሯቸው መልእክት ላኩባቸው፡፡ ሴትየዋ እንደተባሉት ጳጳሱን ለማነጋገር ወደኋላ ቀረት አሉ፡፡ “እንደምን አሉ እናቴ? ምነው የከፋዎት ይመስላሉ፡፡” ሴትየዋ ደንገጥ ብለው “አይ እንደው ነው… እንደው ዝም ብዬ ነው፡፡ ድካሙ እርጅናው ይኾናል፡፡” ሲሉ መለሱ፡፡ ጳጳሱ ግን በዚህ መልስ አልረኩም፡፡ ይልቁንም ፊታቸው ውስጣቸውን የሚያስጨንቃቸውና የሚያበሳጫቸው ነገር እንዳለ እንደሚያሳብቅ በመጠቆም ችግሩን እንዲያካፍሏቸው አበረታቷቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ሴትየዋ ወደ ጳጳሱ ዘንድ ይቀርቡና “አባቴ፣ ጸሎት ሰለቸኝ፡፡ ታከተኝ፡፡ እንደዛሬ ሳይታክተኝ የማልደግመው የጸሎት መጽሐፍ የለም፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት ጀምሮ ግን የጸሎት መጽሐፌን ስከፍትና ስዘጋው ካልኾነ በስተቀር መኻል ላይ ስለምን እንደጸለይሁ እንኳ አላውቀውም፡፡ ይህም እጅግ ሲበዛ አታክቶኛል፡፡ እርግፍ አድርጌ ልተወው ነው፡፡” ሲሉ ራሳቸውን ይገልጣሉ፡፡ ጳጳሱም ሴትየዋን በጥሞና ካዳመጡ በኋላ “እናቴ፣እስኪ ጠዋት ከዕንቅልፍዎ ሲነቁ እዚያው መኝታዎ ላይ አንድ አስራ አምስት ደቂቃ ያህል ይቆዩና አካልዎን ዘና አድርገው የትንፋሽዎን ምልልስ፣ የልብዎን ምት፣ የደም ሥርዎችዎን ንዝረት፣ በዙሪያዎ ያለውን አየር በጸጥታ ያዳምጡ፡፡” የሚል መልስ ሰጧቸው፡፡ ሴትየዋ ምንም እንኳ የጳጳሱ መልስ ግራ ቢያጋባቸውም “የካህን ቃል እንዴት እምቢኝ ይባላል!” በሚል ሐሳብ ትእዛዝ እሺታቸውን ገልጸው ኼዱ፡፡


ከኹለት ሳምንታት በኋላ   
ጳጳሱ ቅዳሴያቸውን ፈጽመው ከቤተክርስቲያኑ ውስጥ አረፍ ብለው ሳለ አንዲት ፊታቸው በደስታ የበራ እናት ወደ እርሳቸው ይቀርቡና “አባቴ እግዚአብሔር አብዝቶ ይባርክዎ! ያሉኝ ነገር ሠርቷል፡፡ በዕድሜ በጸጋ ይጠብቅልኝ፡፡” ሲሉ ምርቃት ያወርዱ ጀመር፡፡ ጳጳሱ ሴትየዋን ሊያስታውሷቸው አልቻሉም፡፡ ግራ ተጋብተው “የትኛው ነገር ነው እናታችን?” ሲሉ ይጠይቋቸዋል፡፡ ሴትየዋ ችግራቸው የነበረውን ነገርና ጳጳሱ የሰጧቸውን ምክር መልሰው ተረኩት፡፡ በንግግራቸው ፍጻሜም “ለካ እግዚአብሔር እንደዚህ ቅርብ ነው!” አሉ፡፡ ጳጳሱ በጽሙና ካዳመጡ በኋላ “ጥሩ ነው፡፡ ግን ከዚህ የመንፈሳዊ ሕይወት ውጣ ውረድዎ ምን ተማሩ?” የምትል አጭር ጥያቄ አቀረቡላቸው፡፡ የሴትየዋ መልስም እንዲህ የሚል ነበር፡- “በመጀመሪያ ደረጃ ጸሎት እግዚአብሔርን ለማዳመጥ ራስን በእግዚአብሔር ፊት ማቅረብ ነው፡፡ ጸሎት ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር ማለት እንጂ ለእግዚአብሔር መናገር ማለት አይደለም፡፡ እኛ ዝም ካላልን እግዚአብሔር አይናገረንም፡፡ ቢናገረንም ደግሞ አንሰማውም፡፡

እውነት ግን ጸሎት ለብዙዎቻችን ምንድነው?
ሰሞኑን የገዛሁት “መንፈሳዊ ብልጽግና፤ ጣዕመ ጸሎት” የተሰኘ መጽሐፍ ውስጥ ቀጥሎ ያቀረብሁላችሁን ውብ አንቀጾች አግኝቻለሁ፤ በእኔ ግምት ለብዙ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ሳይጠቅም አይቀርም፡-
ጸሎት ማለት “ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር” ማለት ነው የሚለው ትርጉም ብዙዎችን ያስማማል፡፡ ነገር ግን የጸሎት ልምዳችን ከዚህ ትርጉም የራቀ ነው፤ ማለትም የለመድነው ለእግዚአብሔር መናገር እንጂ ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር አይደለምና፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ለመነጋገር እግዚአብሔርን ማግኘት አለብህ፤ እግዚአብሔርን ለማግኘት ደግሞ ለእግዚአብሔር መገኘት አለብህ፡፡
ከእግዚአብሔር ጋር ስትነጋገር አንተ ብቻ ተናግረህ አትቀመጥም፤ እግዚአብሔርም ሲናገር ትሰማለህ፡፡ እግዚአብሔርን መፈለግ፣ እግዚአብሔርን ማግኘት፣ እግዚአብሔርን ማዳመጥ (መልስን መቀበል) የሌለበት ንግግርን የጸሎት ልምዳችን አድርገን ብዙ ዘመን ተመላልሰናል፡፡ ይህ ልምምዳችን ጸሎትን ከከንፈር ቃል የማያልፍ ልማዳዊ ድርጊት ከማድረጉም በላይ ጸሎትን በአባትና በልጅ መካከል የሚደረግ የፍቅር ግንኙነት ሳይኾን በግድ የሚፈጸም አሰልቺ ሥራ አስመስሎታል፡፡ ከዚህም የተነሣ ጸሎቱ ለሕይወታቸው ልዩ ትርጉም ባለማምጣቱ የብዙዎች የጸሎት ሕይወት ሞቷል፤ አንዳንዶችም አስጨናቂ ሸክም ኾኖባቸዋል፡፡ ብዙዎች በትግል ውስጥ ናቸው፤ ምናልባት በጣም ጥቂቶች እንደሚነድ ጧፍ ሌሊቱን ብቻ ሳይኾን ቀኑን ጭምር በጸሎታቸው አብርተውት ይውላሉ፡፡ እነዚህ ወደ ጣዕመ ጸሎት የደረሱ ናቸው፡፡ የተሳሳተ የጸሎት ልምድህ ወደ ትክክለኛ የጸሎት ሕይወት ሲለወጥ ሕይወትህ መለወጡ ጥርጥር የለውም፤ ጸሎትህ የሚለወጠው ደግሞ ስለ ጸሎትህ ያለህ ግንዛቤ (መረዳት) ሲለወጥ በመኾኑ ጸሎትን ከላይ እንደተገለጸው ተረዳው፡፡
ጸሎት ለዘለዓለም በፍቅር የሚወድህ አባትህን የምታይበት የእምነት ዓይንህ ከእርሱም ጋር የምትነጋገርበት የፍቅር ቋንቋህ ነው፡፡ ስለዚህ በጸሎትህ ከማንም በላይ የሚወድህ አባትህን ፊቱን ለማየት ናፍቅ እንጂ ከቃላት ጋር አትታገል፡፡ ጸሎትን ወደ ሰላምህ ጫፍ ወደ ዕረፍትህም ከፍታ የምትደርስበት የልጅነት ሥልጣን መገለጫ መኾ እጅግ ያስደስትሃል፡፡ ስለዚህ በጸሎትህ ወደ ክብሩ ለመድረስ በመናፈቅ ትጋ፤ ከቃልህ በፊትም በልብህ ፈልገው፡፡‹1›

አንቀጸ ብፁዓንን የሕይወት መመሪያው አድርጎ እንደኖረ የሚነገርለት የሕንዳውያን የነጻነት ታጋይ ማኅተማ ጋንዲ ጸሎትን እንደሚከተለው አብራርቶት ነበር “Prayer is not asking. It is a longing of the soul. It is daily admission of one's weakness. It is better in prayer to have a heart without words than words without a heart.” (“ጸሎት የነፍስ ናፍቆት እንጂ ጥያቄ አይደለም፡፡ ይልቁንም ደካማነትን በየዕለቱ ማመን ነው፡፡ በጸሎት ጊዜ ቃላት ያለልብ ከሚቀርቡ ልብ ያለቃላት ቢቀርብ ይሻላል፡፡”) ሶረን ኪርከጋርድ የሚባል ፈላስፋም እንዲህ ብሏል፡- “The function of prayer is not to influence God, but rather to change the nature of the one who prays.” (ይህንን እናንተ እያስተነተናችሁ ተርጉሙት!)

ግብዣ፡-
ከሚከተሉት ጥቅሶች አንዱን ውሰዱና ለጥቂት ደቂቃዎች በጽሙና አስተንትኑ፡-



“ቅሩብ እግዚአብሔር ለየዋኀነ ልብ” (ልባቸው ገር ለኾነ ሰዎች እግዚአብሔር ቅርብ ነው፡፡) (መዝ. 33፣ 18)
“እግዚአብሔር እረኛዬ ነው፡፡ የሚያሳጣኝ የለም፡፡” (መዝ 22፣ 1)
“ነአኵቶ ለገባሬ ሠናያት” (መጽሐፈ ቅዳሴ)
“ነፍሴ እግዚአብሔርን ታከብረዋለች፡፡ መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ደስ ይላታል፡፡” (ሉቃ. 2)






[1] መነሻ መጽሐፍ
ያሬድ ዮሐንስ፡፡ መንፈሳዊ ብልጽግና ቁጥር 1፡ ጣዕመ ጸሎት፡፡ አዲስ አበባ፣ 2004፡፡

2 comments:

  1. Dear Mehari.
    You said it well, that is what is happing in my life specially after coming to Europe, I sometime take prayer as a burden, even though I know why I should pray...I would dig every reason to pass it or make it short....and I am seeing the reult in detioration of the spritual zeal and a long build personality. What do you think the practical solution is ?

    ReplyDelete
    Replies
    1. Dear Anonymous, thank you for reading this blog and taking time to share your feelings.

      Although I am neither equipped theologically nor experienced spiritually to be any kind of spiritual director, based on my readings and personal experiences I suggest to try to do the same thing as the lady described above: to try to listen to God in silence rather than talking or reading some prayer book.

      Particularly, it will be very useful for a person to have moments of silence after reading a prayer book, if one prays with that. Primarily, prayer is not talking, rather it is LISTENING to the Lord who loves us.

      Because of our over simplified culture of prayer, we have forgotten so many things our forefathers used to enjoy in prayer. Prayer is a moment we shall enjoy in the presence of our loving father. But, for most of us, I think, it is just reading some prayer book. We usually forget that, that prayer book was first authored by a person who was in a spiritual ecstasy in the presence of the Lord with him.

      It was not in vain that our fathers tell us St. Ephraim saw Our Lady when he was 'sitting' in his place after his pastoral activities. To me that sitting was not simply sitting. It was a moment of settlement in body, in mind and in spirit. It was a moment to feel the presence of the Lord around him. It was a moment to remember His love for creating us and recreating us through His suffering on the Cross. The journey of His amazing love to the cross which starts in the womb of virgin Mary.

      Hence, take a moment of silence and contemplate this love of His which is all around you. Feel the air you are breathing. Feel your body you exist in. Feel your heart beat. Feel your lungs. Are not they miracles?!

      Prayer is not starting to read one prayer book and finishing it after sometime. No! It is first opening oneself before the all-knowing Lord and feeling His presence firstly. After that, giving Him thanks. Then, asking for forgiveness for my weaknesses. Lastly, offering oneself before the Lord to do and to walk only according to His Holy will. God is always with us even when we are not with ourselves.

      In addition to the Amharic book I used above, You may find the following books useful:

      God of Surprises by Fr. Gerard Hughes
      Nine Faces of God by Fr. Peter Hannan
      Confessions by St. Augustine
      Introduction to the devout Life by St. Francis de Sales
      http://meharigebremarqos.blogspot.com/2011/12/st-francis-de-sales.html

      If you don't have time to read all of them the first one will be enough to give you guidance. In addition to all that, the following links will help you to have a daily prayer of silence and scripture:

      www.sacredspace.ie
      www.prayasyougo.org

      May the Lord be with you,





      Delete