Tuesday, November 15, 2022

“አባት ልጁን ይወዳል ሁሉንም በእጁ ሰጥቶታል።” ዮሐ. 3፡ 37

መዝሙር፦ ትዌድሶ መርዓት  

ምንባባት፦ ኤፌ 5፡ 21 ፤ ራእ 21፡ 1 ሐዋ 21፡ 31 መዝ 127፡ 2 ዮሐንስ 3፡ 25   

ዛሬ የሰማናቸው ምንባቦች በሙሉ (ከሐዋርያት ሥራ በስተቀር) “ሙሽራ” “ሙሽሪት”፣ ባል፣ ሚስት የሚል ቃል አላቸው። የዕለቱ መዝሙርም “ትዌድሶ መርዓት” (ሙሽሪቱ ታወድሰዋለች [ሙሽራዋን]) ይባላል። ዮሐንስ መጥምቅ “ሙሽራዪቱ ያለችው እርሱ ሙሽራ ነው” ሲል፣ ዮሐንስ ባለራእዩ “ወደዚኽ ና፣ የበጉን ሚስት ሙሽራዪቱን አሳይኻለኹ” የሚል ድምፅ ከመሪው መልአክ መስማቱን ይነግረናል። ቅዱስ ጳውሎስም “ክርስቶስ ቤተክርስቲያንን እንደወደዳት… ስለእርሷ ራሱን አሳልፎ እንደሰጠ” ሲል ሰምተነዋል። ስለዚኽ ሙሽርነት ለመነጋገር ግን መነሻው ነጥብ ከላይ የጠቀስነው እውነት ነው። “አባት ልጁን ይወዳል፤ ኹሉንም በእጁ ሰጥቶታል።” ሦስት ነጥቦችን እናንሣ፦  

  1. የሙሽርነት መጀመሪያ 

እግዚአብሔር አብ ልጁን በፍጹም ፍቅር፣ በፍጹም ልግስና ይወድዳል። ስለዚኽም እርሱ በአባትነቱ፣ በእግዚአብሔርነቱ ያለውን ኹሉ አምላክነቱን፣ ብርሃንነቱን፣ ሕይወትነቱን ያለ አንዳች ንፍገት፣ በፍጹም ልግስና ሰጠው። አብ ለወልድ ያልሰጠው አንዳችም ነገር የለም፤ እውነተኛ አባት ነውና። ከልግስናው ብዛት የተነሣም በልጁ በኩል የእርሱን ሕይወት የሚወርስ ፍጥረትን መፍጠር ወደደ። ወድዶም በቃሉ ካለመኖር ወደ መኖር አመጣት፤ ከእርሱ ሕያውነት የተነሣ ከዘለዓለም ሕያው በኾነው ልጁ በኩል የእርሱን ሕይወት ወርሳ የምትኖር፣ የሰው ልጅ ራሷ፣ ጉልላቷ የኾነላት ፍጥረትን በአንድ ልጁ አበጀ። በልጁ፣ ለልጁ ስላበጃት፣ የልጁን ሕይወት ወርሳ የምትኖር ስለኾነችም የልጁ ትዳር፣ የልጁ ሙሽራ ተባለች። እግዚአብሔር ለልጁ ሙሽርነትን ሰጠ። ልጁም የፍጥረት ሙሽራ ተባለ። ይኽ እግዚአብሔርና በፍጥረት መካከል እንዲኖር እግዚአብሔር ከዘለዓለም የወሰነው ትዳር የሰው ልጅና እግዚአብሔር በሚኖራቸው ግንኙነት ይገለጣል፤ የሰው ልጅ የፍጥረት ጉልላት፣ የፍጥረት ራስ፣ የፍጥረት ተወካይ ነውና። የዚኽ ትዳር መነሻ ነጥቡ ሙሽሪት አይደለችም፤ የሙሽራው አባት ለልጁ ያለው ፍቅር ነው። የዚኽ ትዳር ጽናቱም ሙሽራው ወልድ አባቱ እርሱን በወደደበት ፍቅር የአባቱ ስጦታ የኾነችው ሙሽራውን መውደዱ ነው። የዚኽ ትዳር ፍጻሜውም ሙሽሪት በተወደደችበት ፍጹም ለጋስ ፍቅር ተመልታ በፍጹም ልግስና መልሳ የወደዳትን ለመውደድ ራሷን ስትሰጥ ነው። የዚኽ ትዳር ዓላማው መረዳዳት፣ ከዝሙት መራቅ፣ ልጅ መውለድ አይደለም። ፍጹም ፍቅር ብቻ ነው።        

  1. ሙሽርነት፣ ጫጉላና መስቀል

መጽሐፍ ቅዱስ ከዘፍጥረት እስከ ራእይ የሚነግረን ይኽንን በሰው ልጅና በእግዚአብሔር መካከል ያለውን ትዳር ነው፤ “የእግዚአብሔርና የሰው ልጅ ፍቅር እስከመቃብር” ልንለው እንችላለን። ግን መቃብር ላይ አያበቃም። እስከ ትንሣኤ፤ እስከ ዕርገት ድረስ ደርሶ የሰው ልጅ በሥላሴ መንበር ተቀምጦ ለዘለዓለም ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ሲባል እንጂ። ሙሽሪት “መች መጣሽ ሙሽራ መች ቆረጠምሽ ሽምብራ” እንዲሉ የተፈጠረችበትን፣ የተጠራችበትን ዓላማ ትታ ሕይወትን ለፍቅር ሳይኾን ለመኖር ብቻ ፈለገችው። ክፉና ደግን በራሷ ፍላጎት ከእርሷ አንጻር ብቻ ወስና ራሷ የራሷ ብቸኛ አፍቃሪ ኾና መኖር ፈለገች። አፍቃሪዋን ፍቅርን ገፋችው። ከኑሮዋ ጋር አመነዘረች። ፍቅርን ገፍታለችና ኑሮዋ ፍቅር ተለየው። ሕይወቷም የተሰጣት ከፍቅር ነበረና ፍቅርን ስትገፋው ሕይወት ተለያት። ሞተች። እንደሸንኮራ እየመጠመጠችና እያጣጣመች ለብቻዋ እስከመጨረሻው እንጥፍጣፊ ልትልሰው የተመኘችው መኖር የሚባል ነገር እያደሩ መሞት ኾነባት። ክፉና ደግን ከሚያሳውቀው ዛፍ በበላሽ ቀን ትሞቻለሽ ተብላ ነበረ። አልሰማችም፤ ገና በጫጉላዋ አመነዘረች፤ ስለዚኽም ከሙሽርነት ሰገነቷ ወደቀች፤ ጭቃ ነበረችና ወደ ጭቃ ተንከባለለች፤ ሙሽሪቱ ሞተች። ፍቅሩ የተገፋ ሙሽራ ምን ማድረግ ይችላል? “ሙሽራዬ ቀረች፤ ከዳችኝ፤ የሚገባትን አገኘች” እያለ ይቀመጥ ይኾን? ቅዱስ ጳውሎስ እንዲኽ ይለናል፦ “ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደወደዳት … በውኃ መታጠብና ከቃሉ ጋር አንጽቶ እንዲቀድሳት ስለእርሷ ራሱን አሳልፎ ሰጠ። እድፈት ወይም የፊት መጨማደድ ወይም እንዲኽ ያለ ነገር ሳይኾንባት ቅድስትና ያለነውር ትኾን ዘንድ ክብርት የኾነች ቤተክርስቲያንን [ሙሽሪትን] ለራሱ ሊያቀርብ ፈለገ።” ኤፌ 5፡ 21

የእርሷ ታማኝነት ማጣት፣ የእርሱን መታመን ሳያስቀር፣ የእርሷ ማፍቀር አለመቻል የእርሱን አፍቃሪነት ሳያስቀረው የአባቱን ዘለዓለማዊ ስጦታ ከተጣለችበት ያነሣት ዘንድ ከወደቀችበት ድረስ ወረደ። ሞት በሚባል በሽታ ተይዛ ቢያገኛት ከእርሷ ከመለየት አብሯት መሞትን መረጠ። በመስቀል ላይ ተቸንክሮ ጫጉላውን ፈጸመ። እነሆ ሙሽራው ሙሽሪትን እንደሚወድድ ማንም ሊጠራጠር አይችልም። እስከሞት ድረስ ጨክኖላታልና። መስቀል የጌታ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያንን ያገባበት የጫጉላ አልጋ ይባላል። (ውዳሴ መስቀልን ተመልከት)። 

ስለዚኽም ዛሬ ቤተክርስቲያን በኼደችበት ኹሉ ከፍ አድርጋ ትይዘዋለች፤ የመወደዷ ምልክት፤ የቃል ኪዳኗ ማኅተም ነውና። እነሆ ሙሽራው ሙሽራዪቱን ከሞተችበት አነሣት፤ አዲሲቱ የእግዚአብሔር ከተማ አደረጋት፤ “የድካምኽን ፍሬ ትበላለኽ” “ፍሬ ፃማከ ተሴሰይ፤ ብፁዕ አንተ ወሠናይ ለከ፤ ብእሲትከ ከመ ወይን ሥሙር ውስተ ጽርሐ ቤትከ” ተብሎ የተነገረለትም ተፈጸመ። እስከ መስቀል ድረስ ደክሞ ሥጋውን አብልቶ፣ ደሙን አጠጥቶ፣ ከስማ የነበረችውን ዛፍ አለመለማት። ሥጋውን ሥጋዋ ደሙንም ደሟ አድርጎላት “ይኽቺ ሥጋ ከሥጋዬ ናት” የሚላትን “ፍሬ” አፈራ። እርሷም ወይን ደሙን ጠጥታ እንደወይን ቆንጅዬ ኾና ለሚቀበሏት ኹሉ በእግዚአብሔር ክብር ተሞልታ ከእግዚአብሔር ዘንድ ትወርድላቸዋለች። እርሷን የሚያገኟት በመካከልዋ የሚኖረውን እግዚአብሔርን ያገኙታል። እግዚአብሔር በአንደበቷ ይናገራል፤ “እግዚአብሔር ይፍታሕ” በሚል ቃሏ እግዚአብሔር ከኃጢኣት እሥራት ይፈታል። እነሆ ዓለሙን ለማዳን ትኖራለች። ጥያቄ፦ በእኔ ኑሮ የሚድን ሰው ይኖር ይኾን?        

  1. የጫጉላ አልጋዋን ተሸክማ የምትዞር ሙሽራ

አኹን እርሷም “በዘለዓለም ፍቅር ወድጄሻለኹ” የተባለችበት ፍቅር ተገልጦላታል። ስለዚኽም፣ ያለፈውን አሮጌውን ለመኖር መኖር የሚባልን ጣዖት አሽቀንጥራ ጥላ ለፍቅር ትኖራለች። በጥምቀት “እክሕደከ ሰይጣን” ብላ አሮጌውን ኑሮ ያስተማራትን የድሮ መምህሯን ትረግማለች። “አአምነከ ክርስቶስ” ብላ በመስቀል ቀለበት ከታሠረላት ሙሽራዋ ኢየሱስ ጋር አንድ ልትኾን መስቀሏን ዕለት ዕለት በፍቅር ትሸከማለች። መከራዋ የፍቅሯ መግለጫ ነውና መከራውን ትታገሠዋለች፤ “እግዚአብሔር በመከራችን ኹሉ የትዕግሥትን ፍጻሜ ይሰጠን ዘንድ ስለነፍሳችን ትዕግሥት እንማልዳለን!” እያለች ጽንዐት አጥታ ከፍቅሯ ሸርተት እንዳትል ስለ ጽንዐት ትማልዳለች። መስቀሏን እንዳትዘነጋ መስቀሉን በፍቅር በስስት ትስማለች። የመስቀል ስጦታዋን ከፍ አድርጋ “አሜን አምናለኹ፤ ይኽ በእውነት ሥጋኽ እንደኾነ አምናለኹ” ብላ ትቀበላለች። መስቀላቸውን የተሸከሙትን ከፍ አድርጋ ሥዕል ሥላ፣ መታሰቢያ ቀን ቆርጣ ታስባቸዋለች። በተለይ በዚኽ ጊዜ በዚኽ የመስቀል ኑሮ እውነተኛ ምሳሌ የኾነችውን ቅድስት ድንግልን የመከራ ኑሮዋን፣ ጨቅላ ልጇን ይዛ ሀገር ለሀገር መንከራተቷን፣ ስደቷን፣ እንግልቷን ታስባለች። እመቤታችን በመከራዋ እንደጸናች እንድትጸናም “እርሱን በማመን ያጸናን ዘንድ” “ድንግል ሆይ! ከሚያስብ ኹሉን ከማይዘነጋ ከልጅሽ ዘንድ አሳስቢ!” “ቅድስት ሆይ! ለምኚልን!” ከሚለው ጸሎቷ እንድንሳተፍ ትጋብዘናለች። 

ለመኖር የሚኖረውን ሟቹን አሮጌውን ሰው አስወግደን በሥጋም በመንፈስም የቤተክርስቲያን አባላት ስንኾንም ሙሽርነቷን እንሳተፋለን፤ ከእርሷ ጋር “ሙሽራዪቱ”፣ “ዐዲሲቱ የእግዚአብሔር ከተማ” እንባላለን። የአንድ ልጁ ወንድሞች በመኾን “የእግዚአብሔር ልጆች” እንደተባልን፤ የአንዲቱ ሙሽሪት አባላት በመኾን ደግሞ እያንዳንዳችንም የቤተ ክርስቲያን የሙሽርነት ሕይወት የሚገለጥብን “ሙሽሮች” እንኾናለን። እግዚአብሔር ፈጣሪያችን እስከመጨረሻዪቱ ሕቅታ ድረስ የምንኖርለት ባላችን ይኾናል፤ “ፈጣሪሽ ባልሽ ነው” ተብሎ ተጽፏልና (ኢሳ 54፡ 5)። 

ሁሉን ለልጁ ለሰጠ ለእግዚአብሔር አብ፣ አባቱ እርሱን በወደደበት ፍቅር በወደደን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ፣ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ከቤተክርስቲያን ክብር ምሥጋና ይኹንለት። ለዘለዓለም። አሜን።         


No comments:

Post a Comment