Thursday, July 20, 2023

ዘመን ፣ ምልክት እና እርሾ

 (ሠኔ ፳፭/፪ሽ፲፭ ዓ.እ)  ቆሮ ፪፡ ፲፥ ፩-ፍ፡ም፤ ጴጥ ፩፡ ም. ፭፥ ፩-ፍም፤ ግብ፡ ሐዋ ፳፥ ፳፰-ፍ፡ም፤ መዝ. ፸፫(፸፬)፥  ፲፯-፲፰፤ ማቴ፡ ም. ፲፮፥ ፩-፲፫ ። 

የእርሻ ዑደትንና የወቅቶች መፈራረቅን የሚከተለው የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የግብረ አምልኮ ካሌንደር ከሠኔ 25 እስከ መስከረም 25 ያለውን ጊዜ የክረምት ዘመን ብሎ ይጠራዋል።  ከሠኔ 26 እስከ ሐምሌ 18 ያለውን ጊዜ ደግሞ “የክረምት መግቢያ” ይባላል። ስለዚኽም ዛሬ የሰማናቸው ምንባቦች በሙሉ ስለዝናብ፣ ደመና፣ ዘር ስለ መዝራት ያነሣሉ። የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የገበሬዎች ቤተ ክርስቲያን ኾና ስለኖረች ሥርዓተ አምልኮዋ ከግብርና ሥራ ጋር የተስማማ እንዲኾን የተሠራ ነው። 

የወንጌል ምንባባችን ጌታ ኢየሱስ በጣም ካዘነባቸው ጊዜዎች አንዱን አሳይቶናል። ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ቀርበው ከሰማይ ምልክት እንዲያሳያቸው ጠየቁት። በዚኽ ጊዜ የተሰማውን ሐዘን ሲገልጥ ወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስ “በመንፈሱ እጅግ ቃተተ” “ἀναστενάξας τῷ πνεύματι αὐτοῦ ይላል (ማር 8፡ 12)። በነቢዩ ኢሳይያስ (65፡2) የተነገረው “መልካም ባልኾነው መንገድ ሐሳባቸውን እየተከተሉ ወደሚኼዱ ወደ ዓመፀኛ ሕዝብ ቀኑን ሁሉ እጆቼን ዘረጋኹ!... ''እኔ ከአንተ ይልቅ ቅዱስ ነኝና ወደ እኔ አትቅረብ!' ይላሉ። እነዚኽ በአፍንጫዬ ዘንድ ጢስ፣ ቀኑንም ኹሉ የምትነድ እሳት ናቸው” ይላል። እጅግ ጥልቅ ሐዘን ነው ። የእግዚአብሔርና የሰው የተግባቦት መሥመር በሰው ኃጢኣት መሰበሩን በግልጥ ያሳያል። እግዚአብሔር ይሠራል፤ ሰው ግን የእግዚአብሔርን ሥራ ያይ ዘንድ ዓይኖቹ ተጋርደዋል። ጌታ ኢየሱስ ልቡ እጅግ ስለተሰበረ ጥያቄ ይጠይቃቸዋል፣ “በመሸ ጊዜ 'ሰማዩ ቀልቷልና ብራ ይኾናል ትላላችኹ። ማለዳም፣ 'ሰማዩ ደምኖ ቀልቷልና ዛሬ ይዘንባል' ትላላችኹ። የሰማዩን ፊትማ መለየት ታውቃላችኹ። የዘመኑንስ ምልክት መለየት አትችሉምን?” ሦስት ነጥቦችን እናንሳና ራሳችንን እንመልከት።

1. ዘመን:- በዚኽ ቦታ ላይ ዘመን ተብሎ ወደ አማርኛ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል καιρῶν የሚል ነው። ትርጉሙም የእግዚአብሔርን የሥራ ክንውን እንጂ ተራ ሰዓት ቆጠራ አይደለም። እዚኽ “ዘመን” ተብሎ የተገለጸው ጊዜ ከእግዚአብሔር አኳያ ሲታይ የሚኖረው ትርጉም ነው። ሰው እግዚአብሔር እንዲኽ ይሠራል ብሎ ለእግዚአብሔር የሥራ ዝርዝር አውጥቶ መቀመጥ ይፈልጋል። በዚኽም ምክንያት እግዚአብሔር በተሻለው፣ በሚበልጠው፣ ለዘለዓለም ሕይወት በሚኾነው መንገድ እየሠራ ያለውን ሥራ ሳይመለከት ይቀራል። ብዙ ጊዜም ሲቃረነው ይገኛል። ፈሪሳውያን እግዚአብሔርንና አሠራሩን እንደሚያውቁ እርግጠኞች ነበሩ። ስለኾነም፣ እያዩ ሳያዩ፣ እየሰሙም ሳይሰሙ ቀርተዋል። የእግዚአብሔርን አሠራር ባለማስተዋላቸው ጻድቁ ሰው አሳድደው ገድለውታል። በሥጋ የተገለጠውን የእግዚአብሔርን አሠራር ማስተዋል ስለተሳናቸው ለብዙ ዓመታት የጠበቁት ዕድል አምልጧቸው እነርሱም፣ ከተማቸውም ጠፍተዋል። ስለዚኽ፣ እንደእነርሱ የጥፋት መንገድን ላለመከተል የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ዘወትር ራሳቸውም መጠየቅ አለባቸው። እያንዳንዱ የቤተሰብ ኃላፊም እግዚአብሔር በቤተሰቤ ውስጥ ምን እየሠራ ነው? ብሎ ቆም ብሎ ማጤን አለበት።  እያንዳንዳችን ምእመናንም እግዚአብሔር በእኔ ሕይወት ውስጥ ዛሬ የት ነው? በየቀኑ ራሳችንን በመፈተሽ አሠራሩን መፈለግ፣ ማግኘት፣ መከተል አለብን። ብዙ ጊዜ ልክ እንደፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ትኩረታችን እግዚአብሔር እንዲያደርግ የምንፈልገው ነገር እንጂ እርሱ ፈልጎ እያደረገ ያለው ነገር አይደለም። ስለዚኽም፣ ከእርሱ ሥራ ጋር መተባበር ያቅተናል። ከእርሱ ጋር አንድ በመኾን ሕይወትን መልበስ ያቅተናል። ፈሪሳውያንን “ትቷቸው ኼደ!” እኛንም ለፈቃዳችን ትቶን እንዳይኼድ ራሳችንን እንመልከት። እግዚአብሔር እኛን የማኖር ግዴታ የለበትም።                        

2. ምልክት:- የእግዚአብሔር አሠራር ምልክቶች አሉት። እነዚኽ ምልክቶችም እውነተኝነት፣ ጭምትነት፣ ጽድቅ፣ ንጽሕና፣ ፍቅር፣ መልካም ወሬ፣ በጎነት፣ ምሥጋና፣ የቅዱሳን ሐዋርያትን ኑሮ መከተል፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ እምነት፣ የውሃት፣ ራስን መግዛት ይባላሉ (ፊልጵ 4፡8፤ ገላ 5፡ 23)። እነዚኽ ባሉበት እግዚአብሔር አለ። እነዚኽ በሌሉበት እንቅስቃሴ ኹሉ ግን እግዚአብሔር የለም። ፍጻሜውም ጥፋት ብቻ ነው። ቤተሰብም ይኹን ግለሰብ፣ ማኅበረሰብም ይኹን ሀገር እነዚኽ ከሌሉት እግዚአብሔር በእርሱ ዘንድ እንደሌለ ይወቅ። ከእግዚአብሔር አሠራር ጋርም ኅብረት እንደሌለው ይረዳ። 

3. እርሾ:- የእግዚአብሔርን አሠራር ለይቶ ማወቅ ከፈሪሳውያን እርሾ ያድናል። እርሾ ጥቂት ኾኖ ሊጡን ኹሉ እንደሚያቦካው የእግዚአብሔር አሠራርን ለይቶ ዐውቆ አለመከተል እንደፈሪሳውያን እግዚአብሔርን በብሔራዊ ኩራታቸውና ሀገራዊ ሕልሞቻቸው አምሳል ለማበጀት፣ እንደሰዱቃውያን እግዚአብሔርን እናመልካለን እያሉ ለጥቅምና ለምቾት እየሰገዱ መኖርን ያመጣል። ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውን እርሾ ካልተጠበቅን የእግዚአብሔርን አሠራር ለማጤን አንችልም። ጌታችን ኢየሱስ ትናንት ደቀ መዛሙርቱን “ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠበቁ!” ያላቸው፣ ዛሬም እኛን “ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠበቁ!” እያለ የሚያስጠነቅቀን ለዚኽ ነው። ከፈሪሳውያን እርሾ የማይጠበቅ ሰው እግዚአብሔር ሕልሙን እንዲያሳካለት ይፈልገዋል እንጂ “ፈቃድኽ በሰማያት እንደኾነች እንዲኹም በምድር ትኹን!” ብሎ የኢየሱስ ክርስቶስን መንገድ አይከተልም። ራስ ወዳድነትን እንጂ ፍቅርን ስለማይከተል መስቀል ጌጥ እንጂ ድል አይኾነውም። በምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ከክርቶስ ጋር አንድ ኾኖ የሚኖር አንድ የመካከለኛው ዘመን ክርስቲያን ግን የፈሪሳውያን እርሾ ከእርሱ እንዲርቅ እንዲኽ ሲል ጸልዮ ነበረ፦ 


ጌታ ሆይ! 

የሰላምኽ መሣሪያ አድርገኝ።

ጥላቻ ባለበት ፍቅርን እንድዘራ

ቂም ባለበት ዕርቅን እንድዘራ 

ጥርጥር ባለበት መተማመንን እንድዘራ

ሐዘን ባለበት ደስታን እንድዘራ 

ጨለማ ባለበት ብርሃንኽን እንድዘራ ስጠኝ። 

ጌታ ሆይ!

ከመጽናናት ይልቅ ማጽናናትን 

ሰዎች ይረዱኝ ከማለት ይልቅ ሰዎችን መረዳትን 

ከመወደድ ይልቅ መውደድን እንድፈልግ 

ጸጋኽን ስጠኝ። 

የምንቀበለው በመስጠት 

ይቅር የምንባለውም ይቅር በማለት 

ሕያዋን የምንኾነውም ከአንድ ልጅኽ ጋር በመሞት ነውና። 

ክብርና ምሥጋና ለቅዱሱ ስምኽ ይኹን! አሜን።  


No comments:

Post a Comment