Tuesday, June 10, 2014

ፈረንሳይኛ ዋጋው ስንት ነው?

የዚኽ ጽሑፍ መነሻው በአዲስ አበባ መስተዳድር ባሉ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የፈረንሳይኛ ትምህርት እንዲሰጥ መወሰኑን ከኹለት የዜና ምንጮች መስማቴ ነው፡፡ ከአንዳንድ ምንጮች እንደሰማኹት ደግሞ ፈረንሳይኛን በሀገሪቱ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ኹሉ እንዲሰራጭ የማድረግ ዕቅድ በመንግሥትና በኤምባሲው ተይዟል፡፡ እውነቱን ልንገራችኹና ዜናውን ስሰማ ልስቅ ቃጥቶኝ ነበር፡፡ ይኽን ውሳኔ የሰጡትን ሰዎችም የሚሠሩትን የማያውቁ የዋኀን፣ ወይም ለአንዳች ቡድናዊ ወይም ግላዊ ጥቅም ሲሉ የሀገር ሀብት ማባከን የማይገዳቸው ጨካኞች እንደኾኑ አድርጌ እንድመለከታቸውም አሳስቦኛል፡፡ ቀጥሎ የዚኽን ውሳኔ ስሕተትነት በዝርዝር ለመሞገት እሞክራለኹ፡፡  

የቋንቋ ትምህርትና ሀገራዊ ምጣኔ ሀብት
እንደኢትዮጵያ ባሉ ድኻ ሀገራት አንድን ቋንቋ በትምህርት ቤቶች ውስጥ ለማስተማር ቢያንስ ኹለት ዐበይት ምክንያቶች ያስፈልጋሉ፡፡ አንደኛ የቋንቋው ምጣኔ ሀብታዊ (ኢኮኖሚያዊ) ጠቀሜታ ነው፡፡ ማለትም፣ ቋንቋው በማኅበረሰቡ ውስጥና በማኅበረሰቡ አካባቢ ካሉ ሌሎች ጎረቤት ማኅበራተ ሰብ ጋር ለሚኖረው ምጣኔ ሀብታዊ መስተጋብር የሚጫወተው ሚና መታሰብ አለበት፡፡ በዚኽ ረገድ ፈረንሳይኛን ስንመዝነው በአፍሪቃ ቀንድ አካባቢ በሚደረግ የገበያ ልውውጥ እዚኽ ግባ የሚባል ስፍራ የለውም፡፡

በአንጻሩ፣ በቅርቡ የጋራ የንግድ ቀጠና ከመመሥረት አልፈው በአሥር ዓመታት ውስጥ በአንድ ገንዘብ ለመገበያየት ደፋ ቀና እያሉ የሚገኙት ኬንያ፣ ታንዛንያ፣ ኡጋንዳ፣ ሩዋንዳና ቡሩንዲ ኪስዋሒሊን በዐቢይ ልሳነ ምሥያጥነት (lingua franca) ይጠቀማሉ፡፡ የሀገራቱን የጋራ ግብይት በማሣለጥ ረገድ ቋንቋው ከፍ ያለ ሚና እንደሚጫወት ለማወቅ የማኅበራዊ ሥነ ልሳን ባለሙያ መኾንን አይጠይቅም፡፡ ስለዚኽም የምሥራቅ አፍሪካ አካል የኾነችው ኢትዮጵያ የዚኽ ገበያ ተጠቃሚ እንድትኾን ልጆቻችን ፈረንሳይኛ ሳይኾን ኪስዋሒሊን ቢማሩ ይሻላቸዋል፡፡ ለፈረንሳይኛ የምናወጣውን ገንዘብ ለኪስዋሒሊ ብናወጣው ቢያንስ ነገ እዚኽ ደጃፋችን ላይ እየተመሠረተ ካለው ገበያ እንደልብ መገበያየት የሚችል ሕዝብ እንዲኖረን ያደርጋል፡፡  

የአፍሪካውያንን ቋንቋ አንፈልግም አንፈልግም ከተባለም፣ ላለፉት 23 ዓመታት ሲቀነቀን በኖረው የዘውግ ፖለቲካ የተፈጠሩትን በልሳነ ዋሕድነታቸው (monolingual) የተነሣ ከክልላቸው ተሻግረው መሥራትም ኾነ መኖር እየተሳናቸው የመጡትን ወጣቶቻችንን በሀገሪቱ የትኛውም ስፍራ ተዘዋውረው እንዲሠሩ ለማስቻል ገናን የሀገሪቱን ቋንቋዎች እንዲማሩ ማድረግ ይገባል፡፡ ለፈረንሳይኛ የምናወጣውን ገንዘብ የሀገራችን ወጣቶች አፋቸውን ከፈቱበት ቋንቋ በተጨማሪ ሌላ ቋንቋ እንዲማሩ ብናደርግ  (ለምሳሌ፣ በአማርኛ አፉን የፈታውን ወጣት ኦሮምኛንና ትግርኛን፣ በሶማልኛ አፉን የፈታውን ወጣት ኦሮምኛን ወይም አማርኛን፣ ለአፋሯ ወጣት ኦሮምኛንና ትግርኛን፣ በኦሮምኛ አፉን የፈታውን ወጣት አማርኛና ወላይትኛ፣ በትግርኛ አፉን የፈታው አማርኛና አፋርኛ፣ ወዘተ.) ሀገሪቱ ወጣቶቿን በፈለገቻቸው ቦታ ኹሉ ለማሠማራት ትችላለች፡፡ ልጆቻችንም አባቶቻችን ሲያደርጉት እንደኖሩት እንደልባቸው በሀገሪቱ እየተዟዟሩ መገበያየት ይችላሉ፡፡ ባቢሎን ኾነንም አንቀርም፡፡ የሀገር ውስጥ ግብይቱን ለማፋጠንና ክልሎቻችንን ይበልጥ ሚዛናዊ በኾነ ምጣኔ ሀብት ለዘለቄታው ለማስተሣሠር ይኽ እጅግ በጣም አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡
  
የቋንቋ ትምህርት እና ሀገራዊ ጂኦፖለቲካ
ቋንቋዎችን በትምህርት ቤት ውስጥ በትምህርት ዓይነትነት ለማስተዋወቅ ከምጣኔ ሀብቱ ጉዳይ በተጨማሪ መታየት የሚገባው ዐቢይ ነጥብ የቋንቋው ፖለቲካዊ ፋይዳ ነው፡፡ ለምሳሌ፣ በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን ትምህርት ሀገራችን ውስጥ ድክድክ ማለት ሲጀምር የምዕራብ አውሮፓን ቋንቋዎች (ፈረንሳይኛ፣ ጣልያንኛ፣ እንግሊዘኛ) መማር ከፍ ያለ ስፍራ ነበራቸው፡፡ የዚኽም ምክንያቱ ዙሪያዋን እንደጥንብ አንሣ ከብበዋት ከነበሩት ቅኝ ገዢዎች ጋር መደራደር የሚችሉ፣ የቅኝ ገዢዎቹን ቋንቋዎች የሚያውቁ ዲፕሎማቶችን ለሀገሪቱ ማፍራት ማስፈለጉ ነበር፡፡


በፖለቲካውም ሚዛን ቢኾን ግን ዛሬ ፈረንሳይኛን በመንግሥት ትምህርት ቤቶቻችን ውስጥ ለማስተማር ወጪ ማውጣት ፋይዳው እዚኽ ግባ የሚባል ኾኖ አይገኝም፡፡ አንድ ወዳጄ “ፈረንሳይኛ የአፍሪካ ኅብረት ቋንቋ ነው፡፡ አዲስ አበባ ደግሞ የአፍሪካ ኅብረት መዲና ነች፡፡ ስለዚኽ ፈረንሳይኛን በመንግሥት ትምህርት ቤት ውስጥ ማስተማር ይገባል፡፡” የሚል ነጥብ አንሥቶ ነበር፡፡ ይኽ ግን በኹለት ምክንያት ሚዛን የሚደፋ አመክንዮ አይኾንም፡፡ አንደኛ፣ የአፍሪካ ኅብረትን ስብሰባ ሊካፈሉ የሚመጡት መሪዎችና አጃቢዎቻቸው እንጂ “ፈረንሳይኛ ተናጋሪ” የሚል ስም የተለጠፈላቸው ሀገራት ሕዝብ አይደሉም፡፡ እነዚኽን እፍኝ የማይሞሉ መሪዎች በሚያርፉበት ሆቴል ለማገልገል ሲባል ልጆቻችንን በሙሉ ፈረንሳይኛ ለማስተማር ገንዘብ ማውጣት አለብን ማለት ፍጹም የዋኅነት ከመኾን አይዘልም፡፡ ኹለተኛ፣ እነዚኽ “ፈረንሳይኛ ተናጋሪ” (Francophone) የሚል ስያሜ የተለጠፈባቸው ሀገራት ይኽን ስያሜያቸውን እነርሱ እንዳላወጡትም መገንዘብ ያሻል፡፡ በእነዚኽ ሀገራት አብዛኛው ሕዝብ የሌሎች አፍሪካዊ ልሳናት ተናጋሪ እንጂ ፈረንሳይኛ ተናጋሪ አይደለም፡፡ ፈረንሳዮቹ ራሳቸውም ይኽንን አበጥረው ያውቁታል፡፡ ለምሳሌ፣ ኬንያ፣ ታንዛኒያና ኡጋንዳ ለስሙ “እንግሊዘኛ ተናጋሪ” (Anglophone) ተብለው ይጠራሉ፡፡ እውነታው ግን ኪስዋሒሊ ተናጋሪ መኾናቸው ነው፡፡ እንግሊዘኛ የሚናገረው የሀገሪቱ ሕዝብ ቁጥር ከጠቅላላው የሀገሪቱ ሕዝብ አኳያ ሲታይ መጠኑ አንሶ ይታያል- ያውም ኪስዋሒሊና እንግሊዘኛን እየደባለቀ የሚያወራውንም ጨምረን፡፡ ለእኔ፣ እነዚኽ ስሞች “የእንግሊዝ ቅኝ ተገዢ የነበረ”፣ “የፈረንሳይ ቅኝ ተገዢ የነበረ”፣ “የፖርቱጋል ቅኝ ተገዢ የነበረ”፣ ወዘተ. ላለማለት በቀድሞ ቅኝ ገዢዎች የተፈጠሩ ዲፕሎማሲያዊ ስድቦች ይመስሉኛል፡፡ አልያ የራሱ ቋንቋ ያለውን ሕዝብ በምን ምክንያት በሰው ቋንቋ መጥራት ይደፈራል?

በኢትዮጵያችን ተጨማሪ ቋንቋዎች በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ይካተቱ ከተባለ መመረጥ የሚገባቸው ቋንቋዎች በሀገሪቱ ጂኦፖሊቲካ ውስጥ ጕልሕ ሚና ሊጫወቱ የሚገባቸው ሊኾኑ ይገባል፡፡ ከዚኽ አኳያ ደግሞ ለመካከለኛው ምሥራቅ ባለን የምጣኔ ሀብት፣ የባህልና የፖለቲካ ትሥሥር የተነሣ ከፈረንሳይኛ ይልቅ ዐረብኛ ተመራጩ ቋንቋ መኾን አለበት፡፡ ከግብፅና ሱዳን ጋር ያለን ጣጣ፣ ከሳዑዲዎችና የመኖች ጋር ያለን ድንበርተኛነት፣ እነርሱ በሀገራችን ላይ ያላቸው ልዩ ፍላጎት፣ ወዘተ. ፈረንሳይኛን ሳይኾን ዐረብኛን ይጠራል፡፡ ከወደ ደቡብና ደቡብ ምዕራብ ለሚኖረን ግንኙነት ደግሞ እንግሊዘኛና ኪስዋሒሊ ናቸው፡፡ እንግዲኽ ለፈረንሳይኛ አመክንዮአዊ ስፍራ ከወዴት እናግኝ? (“ጂቡቲስ?” ብሎ የሚጠይቀኝ ካለ ለጂቡቲ እኽልና ውኃዋን፣ ከጫቷ ጋር ከሰፈርንላት መች አነሳትና የቅኝ ገዢዎቿን ቋንቋ እናጥናላት መልሴ ነው፡፡ እስከዛሬ ፈረንሳይኛ አለመማራችንስ ከጂቡቲ ምን አጎደለብን? ጂቡቲያውያንን በአፋርኛ፣ በሐረሪ፣ በአማርኛና በሶማልኛ እንጂ በፈረንሳይኛ እናውቃቸዋለን እንዴ?)    

ዐረብኛና ኪስዋሒሊ ካልተፈለጉም ቢያንስ ወደ ሀገራችን ቋንቋዎች መለስ እንበልና ያለንን አማራጭ እንመልከት፡፡ ባለፉት 23 ዓመታት ቀን የተቀነቀነው የዘውግ ፖለቲካ (Ethnic politics) ስብከት በሀገራችን ልዩ ልዩ ነገዶች መካከል እየፈጠረ ያለውን ማኅበራዊ-ፖለቲካዊ (sociopolitical) ንቃቃት ለመፈወስና ፖለቲካዊ ኁባሬው የበረታ ኢትዮጵያዊ ማኅበረሰብ ዳግም ለመፍጠር ከላይ በምጣኔ ሀብታዊ ፋይዳ ሥር ያነሣኹት ተማሪዎች አፍ ከፈቱበት ቋንቋ(ዎች) በተጨማሪ አንድ ተጨማሪ ቋንቋ እንዲማሩ ማድረግ ማኅበራዊ-ፖለቲካዊ ፋይዳው እጅግ ብዙ ነው፡፡ ፈረንሳይኛ ለልጆቻችን ለማስጠናት የሀገሪቱን ገንዘብና ጉልበት ከመከስከስ ኦሮምኛን፣ ትግርኛን፣ ሶማልኛን፣ ወላይትኛን፣ ወዘተ. ለማስተማር መድከም የሀገሪቱን ልዩ ልዩ ነገዶች በማቀራረብ የዘመኑ የጎጥ ፖለቲካ በሀገሪቱ ልዩ ልዩ ነገዶች መካከል የፈጠረውን ቁርሾና ስንጥቃት ለመፈወስ የማይናቅ ሚና ይጫወታል፡፡        
ለተማሪዎቻችንስ የትኛው ይቀርባቸዋል?
ዐረብኛ፡ ከአማርኛ፣ ከትግርኛ፣ ከሐረሪ፣ ከሥልጢ፣ ከጉራጊኛ፣ ወዘተ. ጋር አንድ የቋንቋ ቤተሰብ (ሴማዊ) ስለኾነ፣ እንደ ኦሮምኛ፣ አፋርኛ፣ ሶማልኛ፣ አገው ላሉ ኩሻዊ ቋንቋዎች ደግሞ የቅርብ ቤተሰብ (አፍሮኤዥያዊ) ስለኾነ ለኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ከፈረንሳይኛ ይልቅ ዐረብኛን ማጥናት በእጅጉ ይቀልላቸዋል፡፡ ኪስዋሒሊም ቢኾን የዐረብኛና የባንቱ ድቅል ስለኾነ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች በቀላሉ ሊማሩት ይችላሉ፡፡ ይኽ ደግሞ ቋንቋውን በቀላሉ ተማሪዎች የራሳቸው እንዲያደርጉት፣ ሥሉጥ እንዲኾኑበት መንገድ ይከፍትላቸዋል፡፡     

የፈረንሳይ ኤምባሲ ትብብር?
ባነበብኹት ዜና ላይ ለዚኽ ትምህርት ጅማሮ የፈረንሳይ ኤምባሲ እገዛ እንደሚያደርግ ይናገራል፡፡ እንዲኽ ዓይነቱ “እርዳታ” ዓላማው “ተረጂዎቹን” ለመጥቀም ይምሰል እንጂ የሩቅ ገበያ ታልሞ የሚሰጥ የለየለት ንግድ መኾኑ በማኅበራዊ ሥነ ልሳን ትምህርት ይታወቃል፡፡ ለምሳሌ፣ ብሪቲሽ ካውንስል እንግሊዘኛ የሚሸጥ የእንግሊዝ የንግድ ተቋም እንጂ እኛን “የእንግሊዘኛ ባለቤቶች” ለማድረግ የተቋቋመ ድርጅት ከመሰለን ተሸውደናል፡፡ አሊያንስ ኢትዮ ፍራንሴዝም ሥራው ፈረንሳይኛን መቸብቸብ ነው፡፡ በ2010 ላይ በራሱ በብሪቲሽ ካውንስል የታተመው “Making it Happen: The Prime Minister’s Initiative for International Education” የተሰኘ መረጃ እንደሚያመለክተው በአንድ ዓመት ብቻ እንግሊዝ እንግሊዘኛን ከማስተማር “ከአንድ ቢሊየን ዩሮ በላይ” ታፍሳለች፡፡ እ.አ.አ. በ1990ዎቹ የተሠራ አንድ ጥናት ደግሞ እንግሊዘኛ ቋንቋ ስድስተኛ የሀገሪቱ የገቢ ምንጭ እንደኾነ ጠቁሟል፡፡ ከኹለት ወይም ከሦስት ዓመታት በፊት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለድኅረ ምረቃ ተማሪዎቹ የእንግሊዘኛ ሥልጠና እንዲሰጥለት ከብሪቲሽ ካውንስል ጋር ተዋውሎ ነበር፡፡ በዚኽ ሥልጠና አ.አ.ዩ. በሚሊየን የሚቆጠር ገንዘብ ለብሪቲሽ ካውንስል እንደከፈለ ሰምቻለኹ፡፡ የብሩን ብዛት አስባችኹ ብሪቲሽ ካውንስል ጥሩ መምህራንን አምጥቶ እንግሊዘኛ እንደውኃ ሲፈስ ታይቷችኹ ከኾነ አኹንም ተሸውዳችኋል፡፡ ተቋሙ ያመጣቸው ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው “አስተማሪዎች” ፈጽሞ የቋንቋ ባለሙያዎች አልነበሩም፡፡ (በነገራችን ላይ፣ በራሳችን ቋንቋዎች የምንማር ሰዎች ብንኾን ኖሮ እንዲኽ በገዛ ገንዘባችን አይቀለድብንም ነበር፡፡)
ይኽ ሽያጭ ሲጀመር ግን ኹልጊዜም በሽያጭ ስም አይጀመርም- እርዳታ፣ ድጋፍ፣ ወዘተ. እየተባለ እንጂ፡፡ በእርዳታ እግራቸውን ያስገቡና ቋንቋው በማኅበረሰቡ ውስጥ ስፍራ እየያዘ ሲመጣ ኦክስፎርድ፣ ማክሚላን፣ ሎንግማን፣ ወዘተ. ለሚባሉ መዛግብተ ቃላትና የሰዋስው ማስተማሪያዎች ገበያ ፈጠራችኹ ማለት ነው፡፡ ትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ ከገባማ አለቀ ሠርግና ምላሽ ነው! የመማሪያ መጻሕፍት ዝግጅት፣ የመምህራን ሥልጠና፣ የአፍፈት (native speaker) መምህራን ቅጥር፣ ወዘተ. በሙሉ ቋሚ የገቢ ምንጭ ይኾናል፡፡ ከዚያ ቋሚ የገቢ ምንጭም ያወጣችኹትን ዕጥፍ ድርብ ታስገባላችኹ፡፡ ስለዚኽ የፈረንሳይ ኤምባሲ “እርዳታ ሰጠን” ብሎ ፈረንሳይኛን ሥርዓተ ትምህርቱ ውስጥ ማስገባት ከጥቅሙ ይልቅ የሚያስከፍለን ይበዛል፡፡
ከፈረንሳይኛ ክፍለ ትምህርት ለሚመረቁ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ተፈልጎ እንደኾነም ሌላ የአስተርጓሚነት ሥራ ይፈለግላቸው፤ ወይም ፈረንሳይኛ መማር የሚፈልጉ ሰዎችን በግልም በቡድንም እንዲያስተምሩ ይፈቀድላቸው (ኮብል ስቶን ይፍለጡ አላልኩም!)- እንጂ የሀገር ሀብት ላይ ረብ የለሽ ጫና የሚፈጥር ሥርዓት መዘርጋት ጦሱ ተመዝዞ አያልቅም፡፡ ለዓለም ዐቀፋዊ ግንኙነት እንግሊዘኛ ከበቂ በላይ ነው፡፡ በእርሱ በቅጡ ማድመጥ፣ መናገር፣ መጻፍና ማንበብ ከቻልን ሌላ የአውሮፓ ቋንቋ አምጥተን የትምህርት ክፍለ ጊዜያችንን የምናጣብብበት አንዳችም አሳማኝ ምክንያት የለም፡፡ በዩኒቨርሲቲዎቻችንም እንደቀድሞው በንዑስ ትምህርትነት (ማይነር) ብቻ ቢወሰን መልካም ይመስለኛል፡፡ እኛ አውሮፓን አደራ ያለን የለ! (በነገራችን ላይ፣ ተማሪዎች ቢያንስ ኹለት መስኮችን ዐውቀው እንዲወጡ ያስችል የነበረው የንዑስ ትምህርት መዋቅር “የሀገር ሀብት ያባክናል!” ተብሎ በትምህርት ሚኒስቴር ቀጭን ትእዛዝ እንዲዘጋ የተደረገው የዛሬ አምስት ዓመት ገደማ ነው፡፡ የአኹን ተማሪዎች በአንድ መስክ ብቻ ያውም በሞጁላዊ ሥርዓት እንደሚማሩ ሳስብ ከልቤ አዝናለኹ፡፡)  
ይኽንን መጻፌ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ሰዎች ይሰሙኛል ብዬ አይደለም -እንደው መቆጨቴን ልንገራችኹ ብዬ እንጂ፡፡ ቢሰሙኝ መልካም ነበር፡፡ እነርሱማ አይሰሙም፡፡ ቢሰሙም የሚሰሙት አለቆቻቸውን ብቻ ነው፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም “እኛ ሀገር ዕውቀት ከትምህርት ሳይኾን ከሥልጣን ይመነጫል፡፡” ብለው ጨርሰውታል፡፡
ከጋሽ ፈቃደ አዘዘ “እየኼድኩ አልኼድም” መድበል ውስጥ “ከበዳ ወደ በዳ” ከተሰኘው ግጥም በቀነጨብኋቸው ስንኞች ነገሬን ላብቃ፡-
ግን ማንስ አዳምጦ?
አረ ማንስ ሰምቶ?
    ኹሉም እጆሮው ላይ፣ በሆዱ ተኝቶ፡፡
                              












No comments:

Post a Comment