Thursday, January 26, 2012

ላምና አሳማ


አንድ ገበሬ አንዲት እርሱና ቤተሰቡ የሚወዷት ላምና አንድ አሳማ ነበሩት፡፡ ለአሳማው ያላቸው ፍቅር ግን የላሚቱን ያህል አይጠናባቸውም ነበር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን አሳማው ላሚቷን እንዲህ ይላት ጀመር፡- 
“እንዴት ነው ግን ሰው ሁሉ አንቺን እጅግ አድርጎ ሊወድሽ የቻለው? ሰዎች አንቺ ወተት፣ ቅቤ፣ አይብ ስለምትሰጪ እጅግ ቸር ቸር ናት ይሉሻል፡፡ ኤዲያ! እኔ ከዚያ የበለጠ እሰጥ የለ እንዴ? ሽንጡና ጭቅናው የማን ሆነና ነው? ግን ያንቺን ያህል አልወደድም፡፡ ለምን? ለምን?
ላሚቷም መለሰች፡- “ምናልባት እኔ የምሰጠውን የምሰጠው በሕይወት እያለሁ ስለሆነ ይሆን?

ከሞትን በኋላ የምሰጠው ስጦታ እምብዛም አይደል፡፡ ይልቁንም በሕይወት ሳለን ከሕይወታችን ላይ የምንሰጠው ማለትም በሕይወት እያለን የምናፈቅረው የበለጠ ዋጋ አለው፡፡ 

Monday, January 16, 2012

ሰባቱ ሴቶችና ክርስቲያኖች


ሰሞኑን እየተመለካከትኋቸው ከነበሩ መጻሕፍት መካከል አንዱ “Apostolic Fathers”[i] በሚል ርእስ  ጥንታውያን ክርስቲያኖች የጻፉዋቸው ተብለው ከሚታመኑ ጥንታውያን ጽሑፎች መካከል ጥቂቱን በመድበል መልክ የያዘ ነበረ፡፡ ቀሌምንጦስ ዘሮም ለቆሮንቶስ ምእመናን የጻፈው መልእክት፣ ሁለተኛው ቀሌምንጦስ በመባል የሚታወቀው ስብከት፣ አግናጥዮስ ምጥው ለአንበሳ[ii] በየሀገሩ ተበትነው ለሚገኙ የአንዲቱ ቤተክርስቲያን ልጆች የጻፋቸው ደብዳቤዎች፣ ፖሊካርፐስ ምጥው ለእሳት[iii] ለፊልጵስዩስ ምእመናን የጻፈው መልእክት፣ ሰማዕትነቱን የተመለከቱ ክርስቲያኖች የጻፉለት “ገድለ ፖሊካርፐስ”[iv]፣ “መልእክተ በርናባስ”[v] ፣ “መልእክት ወደ ዳዮግኔጠስ”[vi] ፣  “የሔርማስ እረኛ”[vii] ይገኙበታል፡፡ ሁሉንም ጽሑፎች እዚህ ለማስተዋወቅ አስቸጋሪ ነው፡፡ ነገር ግን እንዲያው በጥቅሉ ጽሑፎቹ ቤተክርስቲያን እንዲህ እንዳሁኑ በልጆቿ ኃጢኣት ሳትሰቃይና ሳትከፋፈል የነበሩትን የመጀመሪያዎቹን ክርስቲያኖች ለሰማዕትነት በናፍቆት የሚቃጠል ክርስቲያናዊ መንፈስ፣ አንዳቸው ሌላቸውን ለማነጽ የነበራቸውን የሞራል ብቃት እንዲሁም የአነዋወር ዘይቤዎቻቸውን የሚያመላክቱ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ እግረ መንገዳችንንም የዛሬዋን ቤተክርስቲያን በትናንት መነጽር እንድንመለከታት፣ የዛሬዎቹን “ክርስቲያን” ተብሎ የመጠራት ታላቅ ስጦታ የተሰጠንን እኛን የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ሰዎችን በጥንታውያኑ ሚዛን እንድንለካ ጥሩ የአስተንትኖ መንገድ ይከፍታሉ- የሚጓዝ ፈቃደኛ እግረ ኅሊና ካለ፡፡ ስለ አጠቃላይ ይዘቶቻቸው ይህን ያህል ካልሁ ዘንዳ ለእኔ እጅግ ውብ ሁነው የታዩኝን ሁለት አናቅጽ ከሁለት ጽሑፎች ላይ ልውሰድና “እንብላ”፡፡
የመጀመሪያው “የሔርማስ እረኛ” ከተሰኘው ጽሑፍ የተቀነጨበ ነው፡፡ ይኸውም ክርስትና ራስን ለእግዚአብሔር መቀደስ ነውና ለእግዚአብሔር ራሳቸውን በቀደሱ ሰዎች ጡብነት የተሠራችውን ቤተክርስቲያን የተሰኘች ግንብ ደግፈው ስለሚይዙት ሰባት ጠንካራ ሴቶች ይናገራል፡፡ 
አሁን ስለ ተግባራቸው አድምጥ፡፡ ከእነርሱ መካከል ጠንካራ እጆች ያሏት የመጀመሪያዋ እምነት ትባላለች፡፡ በእርሷም የእግዚአብሔር ምርጦች ሁሉ ይድናሉ፡፡ የሠራተኛ ልብስ የለበሰችውና ወንድ የምትመስለው ራስን መግዛት ትባላለች፡፡ የእምነት ልጅ ናት፡፡ ከክፉ ቢታቀብ ዘለዓለማዊ ሕይወትን እንደሚወርስ አምኖ ከክፉ ሁሉ ይርቃልና እርሷን የሚከተላት ሁሉ በሕይወቱ ይባረካል፡፡
“ሌሎቹስ እነማን ናቸው?”
እውነተኝነት፣ ዕውቀት፣ የዋኅነት፣ ትሕትናና ፍቅር ይባላሉ፡፡ እርስ በርሳቸውም የእናትነትና የልጅነት ተዛምዶ አላቸው፡፡ ስለዚህም አንተ የእምነትን ሥራ ሁሉ ስትሠራ በሕይወት መኖር ትችላለህ የሁሉም እናታቸው ናትና፡፡ … እምነት የራስን መግዛት እናት ናት፤ ራስን መግዛትም የእውነተኝነት እናት ናት፤ እውነተኝነት የየዋኅነት፣ የዋኅነትም የትሕትና፣ ትሕትናም የዕውቀት፣ ዕውቀትም የፍቅር እናቶች ናቸው፡፡ ደግሞም የአንዷ ኃይል በሌላዋ ይወሰናል፡፡ በዚሁ የትውልዳቸው ቅደም ተከተልም አንዷ ሌላዋን ስትከተል ትኖራለች፡፡ ስለዚህም ሥራዎቻቸው ንጹሓት፣ ክቡራትና አምላካውያት ናቸው፡፡ በዚህም የተነሣ እነርሱን የሚያገለግልና ሥራዎቻቸውንም ለመማር ጥንካሬን ገንዘቡ ያደረገ የትኛውም ሰውም በእግዚአብሔር ቅዱሳን ግንብ ውስጥ መኖሪያን ያገኛል፡፡
ቀጥሎ ያለውን ደግሞ የወሰድሁት “መልእክት ወደ ዳዮግኔጠስ” ከተሰኘው ክርስቲያኖች ክርስቲያን ካልሆኑ ሰዎች በምን እንደሚለዩ በማሳየት የክርስትናን ልዕልና ከሚሰብከው ጽሑፍ ነው፡፡ 
ክርስቲያኖች ከሌላው የሰው ዘር በሀገር፣ በቋንቋ ወይም በባህል የተለዩ አይደሉም፡፡ የትም ቢሆን ለራሳቸው ብቻ በተለየ ከተማ ውስጥ አይኖሩም፡፡ ወይም ያልተለመደ ዓይነት የአነጋገር ዘዬ የላቸውም፡፡ ከሰው በማይገጥም የአነዋወር ዘይቤም አይኖሩም፡፡ ይህ የሚያስተምሩት ትምህርትም ከብልኆች ሰዎች አእምሮ የተገኘ አይደለም፡፡ አንዳንዶች እንደሚያደርጉት የሰው ትምህርትንም አይሰብኩም፡፡… በሀገሮቻቸው ይኖራሉ- ነገር ግን እንደ ባይተዋር ነው፡፡ እንደዜጋ በሁሉም ነገር ይሳተፋሉ፤ ነገር ግን እንደ ባዕዳን ሁሉን በጽናት ይታገሣሉ፡፡ እያንዳንዷ ባዕድ ሀገር እናት ሀገራቸው ናት፡፡ እያንዳንዷ እናት ሀገርም ባዕድ ናት[viii]፡፡ እንደሁሉም ሰው ያገባሉ፡፡ ልጆችም ይኖሯቸዋል፡፡ ነገር ግን ልጆቻቸውን ለክፉ ነገር አሳልፈው አይሰጡም፡፡ ምግባቸውን ይጋራሉ፤ ሚስቶቻቸውን ግን አይደለም፡፡ በሥጋ ናቸው ነገር ግን እንደ ሥጋ አይኖሩም፡፡ በምድር ይኖራሉ፤ ዜግነታቸው ግና በሰማይ ነው፡፡ የተሠሩ ሕግጋትን ያከብራሉ፤ በግል ሕይወታቸው ግን ከሕግ በላይ ናቸው፡፡ ሁሉን ያፈቅራሉ፤ ግን ሁሉም ያሳድዳቸዋል፡፡ አይታወቁም፤ ነገር ግን ይፈረድባቸዋል፡፡ ለሞት ተላልፈው ይሰጣሉ፤ ነገር ግን ወደ ሕይወት ይመጣሉ፡፡ ድሆች ናቸው፤ ግን ብዙዎችን ሀብታሞች ያደርጋሉ፡፡ ሁሉ ነገር ያስፈልጋቸዋል፤ ነገር ግን ሁሉ ተትረፍርፎላቸል፡፡ ይዋረዳሉ፤ ነገር ግን በመዋረዳቸው ውስጥ ይከብራሉ፡፡ ይታማሉ፤ ነገር ግን ስማቸው ይከብራል፡፡ ይረገማሉ፤ እነርሱ ግን ይመርቃሉ፡፡ ይሰደባሉ፤ እነርሱ ግን ያከብራሉ፡፡ መልካም ሲሠሩ እንደ ክፉ አድራጊዎች ይቀጣሉ፡፡ በአይሁዳውያን እንደ ባዕድ ይጠቃሉ፡፡ በግሪኮችም ይሳደዳሉ፡፡የሚጠሏቸው ግን ለጥላቻቸው ምክንያት የላቸውም፡፡
እኒህን ጽሑፎች ሳነብ ራሴንና ክርስትና በተለይ በእኛ ሀገር ዛሬ የደረሰበትን ደረጃ እየመዘንሁ ነበረ፡፡ በእኔ አእምሮ ሚዛን ያገኘሁት ነገር ግን ብዙም አላስደሰተኝም፡፡ እንዲያውም ካልተሳሳትሁ ክርስትና ክርስቶስን የመምሰል ሕይወት ሳይሆን “ተራ ባህል” ብቻ ተደርጎ የሚወሰድበት ዘመን ላይ እየኖርሁ መስሎኛል፡፡
እርግጥ ነው ኢትዮጵያ “የክርስቲያኖች ሀገር” እንደነበረች ታሪክና ቅርሶች በአንድነት የሚመሰክሩት ሐቅ ነው፡፡ ኢትዮጵያ እንደ ቅዱስ ላሊበላ ያሉ ንጉሥም ቅዱስም የሆኑ መንፈሳውያን ሰዎች የበቀሉባትና በክርስቶስ ፍቅር በእግዚአብሔርም በሰውም ፊት ያማረች እንድትሆን የደከሙላት ሀገር እንደነበረች የእምነታቸው ፍሬዎች የሆኑት ሥራዎቻቸው ዛሬም ሕያዋን ምሥክሮች ናቸው፡፡ ነገር ግን ዛሬ ኢትዮጵያ “የእውነተኞች ክርስቲያኖች ሀገር ናት ወይ?” ብለን ብንጠይቅ የምናገኘው መልስ አዎንታዊ መሆኑን እንጃ፡፡ ቡሩካን አባቶቻችን ከክፉው የዓለም ገዢና ከአገልጋዮቹ ታግለው መሰዊያውን አሳምረው አበጅተውልን ሔደዋል በእግሮቻቸው የተተካን እኛ ግን መሰዊያው ላይ የሚቀርብ የመንፈስ ፍሬ[ix] ያለን አይመስልም፡፡ ለምን?
G.K. Chesterton የተባሉ ሊቅ[x] “ዓለም ላይ ያለው ችግር ምንድነው?” ብለን ስንጠይቅ የምናገኘው መልስ “እኔ ነኝ፡፡” የሚል እንደሆነ ይነግሩናል፡፡


[i] በኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ዘንድ እኒህ አበው “ሐዋርያውያን አበው” በመባል ይታወቃሉ፡፡
[ii] ለአንበሳ የተሰጠው አግናጥዮስ ማለት ነው፡፡
[iii] ለእሳት የተሰጠው ፖሊካርፐስ ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ፖሊካርፐስ ስለ ክርስቶስ ፍቅርና ስለ ቤተክርስቲያን አገልግሎቱ ሲል ሰማዕትነቱን በእሳትና በስለት ተቀብሏልና፡፡
[iv] The Martyrdom of Polycarp
[v] The Epistle of Barnabas
[vi] Epistle to Diognetus
[vii] The Shepherd of Hermas. በነገራችን ላይ ይህ መጽሐፍ በሐገራችን ተረፈ ጳውሎስ ተብሎ የሚታወቀው ሳይሆን አይቀርም፡፡ መጽሐፉን ገና ስላላየሁት ግን ምንም ማት አልችልም፡፡ የቅዱስ ያሬድ “ወሪድየ ብሔረ ሮሜ” የሚለው ዜማው ግን መነሻው ይህ መጽሐፍ እንደሆነ አይቻለሁ፡፡
[viii] እዚህ ላይ ብጹዕ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ “ክርስትና ከየትኛውም ጎሳና ነገድ በላይ ነው፡፡” ያሉትን አስታውሶኛል፡፡
[ix] ገላ.5፣ 18
[x][x] Hahn, Scott. 2006. Lord, Have Mercy: The Healing Power of Confession. India, Longman and Todd Ltd, [pp 49].