Sunday, May 27, 2012

ከቅዱስ አውጉስጢኖስ ኑዛዜዎች

አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ሆይ!


ሰማይና ምድርን ትመላለህና እነርሱ ሊይዙህ ይችሉ ይሆን? ወይስ ሊይዙህ ስለማይቻላቸው ሞልተህ ትፈስ ይሆን? ሰማይና ምድርን መልተህ ተትረፍርፈህ ስትፈስስ ወዴት ትፈስ ይሆን? ወይስ ሁሉን የምትይዝ አንተ በርግጥ በምልዐትህ ሁሉን ትይዛለህና በምንም ልትያዝ አትችልም? በምልዐትህ የምትገኝባቸው ሸክላዎች አንተን አይዙህም- ቢሰበሩም እንኳ አንተ አትፈስምና፡፡ በእኛ ላይ ስትፈስም አንተ የምትወርድ አይደለህም- እኛ ወደላይ ከፍከፍ እንላለን እንጂ፡፡ አንተ የምትበተን አይደለህም- እኛን ትሰበስበናለህ እንጂ፡፡ 


ግን ነገሮችን ስትመላ በአንተነትህ ሙሉ ትመላቸዋለህን? ወይስ ሁሉም ነገሮች ተሰብስበው ሊይዙህ አይችሉምና አንዱ ነገር አንዱን የአንተነትህን ክፍል ይይዝ ይሆን? ሌሎቹስ ነገሮች ያንኑ ክፍል በዚያው ሰዐት ይይዙ ይሆን? ነጠላ ነገሮች በነጠላነታቸው አንድነትህን ይይዛሉን? ታላላቅ ነገሮች የበለጠ አንተነትህን፣ ታናናሽ ነገሮች ደግሞ በአነስተኛ መልኩ አንተነትህን ይይዙ ይሆን? ወይስ አንተ በሁሉ ምሉዕ የሆንህና ነገር ግን ምንም በምልዐት ሊይዝህ የሚችል የሌለ ነህ?

እንግዲህ አምላኬ ምንድነው? “ከአምላካችን በቀር አምላክ ማነው? ከጌታችን በቀርስ ጌታ ማነው?” ተብሎ የተነገረለት ጌታዬ ምንድነው?

የሚተካከለው የሌለ ልዑል፣ የሚመስለው የሌለ ሥሉጥ፣ ሁሉን ማድረግ የሚችል፣ ምሕረቱ ተነግሮ የማያልቅ መሐሪ፣ በፍርዱም እንከን የሌለበት ጻድቅ፣ ኅሊና የማይደርስበት ረቂቅ፣ በሁሉ የሚገኝ፣ ፍጹም ኃያልና ፍጹም ውብ፣ ደጋፊ የማይሻ ጽኑዕ፣ ሁሉን የሚለውጥ እርሱ ግን ፈጽሞ የማይለወጥ፣ የማይታደስ፣ የማያረጅ ነገር ግን ሁሉን የሚያድስ ትዕቢተኞችን ሳያውቁት የሚያስረጃቸው፣ ሁሌም የሚሠራ፣ ሁልጊዜም በዕረፍቱ ፍጹም፣ ሁሉን የሚሰበስብ ግን አንዳችም የማያስፈልገው፤ ሁሉን የሚመግብ፣ ሁሉን የሚይዝና ሁሉን የሚጠብቅ፤ ፈጣሪ፣ መጋቢ፣ ተንከባካቢ፤ ሁሉ ገንዘቡ የሆነ ፈላጊ፡፡ 

No comments:

Post a Comment