Thursday, January 23, 2014

ምንባብና መልመጃ

ቀጥሎ ያቀረብኹላችኹ ትናንትና ሌሊት የአማርኛ አስተማሪዬ በሕልሜ መጥተው ያስተማሩኝን ነው፡፡ ከተመቻችኹ ሕልሜን ፍቱልኝ፡፡ “ካልተመቻችኹ በሊማሊሞ አቋርጡ” ያለው ማን ነበር? ሕልሙ እንዲኽ ነበር፡-

እንደምን አደራችኹ ተማሪዎች፡፡
ደኅና እግዚአብሔር ይመስገን መምህህህህህር፡፡
ቁጭ በሉ፡፡
እናመሰግናለን፡፡
አጥንቱን ልልቀመው መቃብር ቆፍሬ
ጐበናን ተሸዋ አሉላን ተትግሬ፣
ስመኝ አድሬያለኹ ትናንትና ዛሬ፣
ጐበናን ለጥይት አሉላን ለጭሬ፡፡
ተሰበሰቡና ተማማሉ ማላ፣
አሉላ ተትግሬ ጐበና (ከሸዋ)፣
ጎበና ሴት ልጁን ሊያስተምር ፈረስ፣
አሉላ ሴት ልጁን ጥይት ሊያስተኩስ፣
አገሬ ተባብራ ታልረገጠች እርካብ፣
ነገራችን ኹሉ የእንቧይ ካብ፣ የእንቧይ ካብ፡፡

ልጆች፣ እነዚኽን ስንኞች ከዚኽ በፊት የኾነ ቦታ ሲነገሩ ሰምታችኹ ይኾናል፡፡ አፍላቂያቸውን ስንቶቻችኹ እንደምታስታውሱ ግን እርግጠኛ አይደለኹም፡፡ አብሽር! ረኪና ሂንጅሩ! (ችግርየለም!) እኔ እነግራችኋለኹ፡፡ የእነዚኽ ውብ ስንኞች መፍለቂያቸው ዮፍታሔ ንጉሤ ይባላል፤ በሀገራችን የቴአትር ጥበባት ነገር ሲነሣ ስማቸው በግንባር ቀደም ከሚጠራላቸው ሰዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ ይኽ ሰው ጎጃም ደብረ ኤልያስ ከቄሰ ገበዝ ንጉሤ ተወልዶ፣ ንባብ ቆጥሮ፣ ዜማ ቀጽሎ፣ ቅኔ ተቀኝቷል፡፡ ገና በ19 ዓመቱ ገደማም “ቀኝ ጌታ” ተብሏል፡፡ ከአባቱ ሞት በኋላ በገጠመው ማኅበራዊ ምስቅልቅል ወደ አዲስ አበባ ተሰድዶ መጣና እዚኽ ቀበና አቦ በድብትርና አገልግሏል፡፡ ቀጥሎም በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት በአማርኛ መምህርነት ተቀጥሮ ይሠራ ነበር፡፡ ኋላም የቅዱስ ጊዮርጊስ ትምህርት ቤት ዲሬክተር ኾኖ ሠርቷል፡፡ የምናብ እግሮቹ ወደ ቴአትሩ ዓለም ያመሩትም በዚኽ የመምህርነት ጊዜው ነው፡፡ ዮፍታሔ በ1920 ዓ.ም. ገደማ የጀመረው የድርሰት ሥራ የአምስት ዓመቱ የፋሽት ወረራ እስኪመጣ ድረስ ይበልጥ እያበበና እየፈካ ኼዶ እንደነበር የሕይወት ታሪኩን ያሰናዳው ዮሐንስ አድማሱ ይገልጣል፡፡ ዮፍታሔ የሀገር ፍቅር በእጅጉ ይሰማው የነበረ ሰው እንደኾነ ቴአትሮቹ ውስጥ ይስተዋል ነበር፡፡ ከላይ በመግቢያነት የሰፈረችው ቅንጭብም ይኽንኑ የሀገር ፍቅሩን ሳትጠቁም አትቀርም የሚል ተስፋ አለኝ፡፡ ይኽንኑ ለማጽናት አንድ ሌላ ቅንጭብ ብጨምርላችኹ አይከፋኝም፡፡ ፋሽስት ቀስ እያለ ኢትዮጵያን ቅኝ የመግዛት ዓላማውን ሊያሳካ ምሥራቅ ኢትዮጵያ ላይ ሲያደባ አካኼዱን የታሰበው ዮፍታሔ (1928) እንዲኽ ብሎ ነበር፡-

ከአገር ዕድሜ ተርፎ የሚቀረው ዕድሜ፣
ሞተ-ነፍስ ይባላል ልናገር ደግሜ፡፡
የፈሰሰ ስንዴ ተርፎ ከስልቻ፣
ለጌታው አይደለም ለዐይጥ መጫወቻ፡፡
ወታደር ገበሬ መጠንቀቅኽ የታል፣
ፍልፈልም ይገፋል፤ ዐፈር ይጎልታል፡፡


ይኹን እንጂ፣ ዮፍታሔ በጭፍን ዐርበኝነት ወይም በአድርባይነት በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚያየውን ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ሳንክ ችላ ብሎ የሚያልፍ ሰውም አልነበረም፡፡ ዮሐንስ አድማሱ[1] ይኽንን ሲመሰክርለት እንዲኽ ብሏል፡- 

በማንኛውም ኅብረተሰብ ስሜታቸው ሥሥ የኾነ፣ ተሎ የሚሰማቸው፣ የሚሰማቸውም ማንኛውም ነገር ከሥጋቸው አልፎ ነፍሳቸውን ገብቶ የሚበረብራት፣ አይተው፣ ሰምተው ዝም ለማለት የማይችሉ ሰዎች ይገኛሉ፡፡ እንደዚኽ ያሉት ሰዎች ናቸው እንደተልእኳቸውና እንደተውህቧቸው፣ እንደብሩህነታቸው መጠን በያሉበት ኅብረተሰብ ውስጥ የሚጋጥማቸውን ቅራኔ ኹሉ የሚያውጁ፣ ለቅራኔው መፍትሔ የሚሹ፣ “ነስሑ፣ እስመ ቀርበት መንግሥተ ሰማያት” የሚሉ፡፡ እንደዚኽ ዓይነቱን ምግባር ለመፈጸም የሚፋጠኑ፣ ዕድል ፈንታቸው፣ ጽዋ ተርታቸው የኾነ… ዝም ቢሉ፣ ባይናገሩ፣ ባይሠሩ ፍዳው በራሳቸው ላይ መኾኑን ያውቃሉ፡፡ ተናግረው፣ አስጠንቅቀው ግን ፈጻሚ ባያገኙ ከፍዳው ነጻ ናቸው፡፡ በትንቢተ ሕዝቅኤል እንደተባለው፡-

እኔ ኃጢኣተኛውን፡- በርግጥ ትሞታለኽ ባልኹት ጊዜ፣ አንተም ባታስጠነቅቀው፣ ነፍሱም እንድትድን ከክፉ መንገዱ ይመለስ ዘንድ ለኃጢኣተኛው አስጠንቅቀኽ ባትነግረው፣ ያ ኃጢኣተኛ በኃጢኣት ይሞታል፤ ደሙን ግን ከእጅኽ እፈልጋለኹ፡፡ ነገር ግን አንተ ኃጢኣተኛውን ብታስጠነቅቅ፣ እርሱም ከኃጢኣቱና ከክፉ መንገዱ ባይመለስ፣ በኃጢኣቱ ይሞታል፤ አንተ ግን ነፍስኽን አድነኻል፡፡ (ሕዝ. 3፡ 18-21)፡፡
        …የዮፍታሔም መንፈስ የተቃኘው በዚኹ ስልት ነበረ፡፡[2] (ገጽ79)


በቡድን ውይይት የሚሠራ መልመጃ

ዛሬ በእኛ ትውልድ ይኽን ከላይ የቀረበውን፣ ዮሐንስ አድማሱ ትንቢተ ሕዝቅኤልን አጣቅሶ ዮፍታሔን የገለጸበትን ገለጻ የሚጋሩ ነገር ግን ስፍራ የተነፈጋቸው(ወይም ስፍራቸው ከማኅበረሰቡ ዘንድ እንዳይኾን አንድም በማኅበረሰቡ፣ አንድም በጉልበተኞች የተጋዙ፣ የተሰደዱ፣ የተገለሉ) ፣ ዓለማየኹ ገላጋይ ፋክት ላይ “ኑ እንዋቀስ!...የአገልግሎት ዋጋቸውን በልተን በዕዳችን ያስጠየቅናቸው ግለሰቦች አሉ፡፡ ጡጫና እርግጫ የጠገቡት እነርሱ እያሉ እኛ ግልምጫ የሚሸሽ ውርደታም ሕዝብ ኾነናል፡፡ ልጆቻችንን ሰብስበን የእነርሱን በትነናል፡፡ ቤተሰቦቻችንን ሸክፈን የእነርሱን አንከራትተናል፡፡ ቤታችንን አሙቀን የእነርሱን ጎጆ አቀዝቅዘናል፡፡” ብሎ የጻፈላቸው ጸሐፍት አሉ ብላችኹ ታምናላችኹ? ካሉ እነማን ናቸው? 




[1]በነገራችን ላይ፣ ይኽን የዮሐንስ አድማሱን ሥራ ልቅም አድርገው አሰናኝተው ለኅትመት ብርሃን እንዲበቃ ያደረጉት ባለፈው ዓመት መጽሐፉ ሊመረቅ ጥቂት ቀናት ሲቀረው በዕረፍተ ሥጋ የተለዩን ሊቁ ዶ/ር ዮናስ አድማሱ ናቸው፡፡ እግረ መንገዴንም፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስን ይኽን ከባለ ታሪኩም፣ ከአዘጋጁም፣ ከአሰናኙም አኳያ ቢታይ ቅርስ የኾነ ሥራ በምርጥ የኅትመት ጥራት ስላደረሰን እጅግ ከፍ አድርጌ ላመሰግነው እወድዳለኹ፡፡

[2] ዮሐንስአድማሱ፡፡ ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ፤ ዐጭር የሕይወቱና የጽሑፉ ታሪክ (1887- 1939)፡፡ አዲስ አበባ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ፣ 2004፡፡

No comments:

Post a Comment