Monday, March 18, 2013

ኹለቱ የኑሮ መርሖች


በዓለም ላይ ስኖር የቀረቡልኝ ኹለት አማራጭ የመኖሪያ መንገዶች አሉ፡፡ አንደኛው መሥመር መነሻው « እኔ » ነኝ፡፡ እኔን ተጠቃሚ ለማድረግ፣ የእኔን ፍላጎቶች ለማሟላትና አንድም ሳይሟላ የሚቀር ፍላጎት እንዳይኖረኝ ምኞቶቼን ኹሉ እውን ለማድረግ በሚደረግ ሩጫ ይጀመራል፡፡ የመነሻ መሥመሩ ሌላው መጠሪያ «የለኝም/ ይጎድለኛል» ይሰኛል፡፡

ሩጫው በዚኽ መሥመር ይጀመርና ፍላጎቶቼን ለማሟላት የሚያስችሉ የሚመስሉኝን ነገሮች ኹሉ ለመሰብሰብ እሮጣለኹ፡፡ አባርሬ እይዛለኹ፡፡ አሳድጄ እጨብጣለኹ፡፡ እሰበስባለኹ፤ እሰበስባለኹ፤ እሰበስባለኹ፡፡ በሰበሰብኋቸው ነገሮች ደስ ይለኛል፡፡ ግን ጥቂት እንደቆየኹ የሰበሰብኹት ነገር ኹሉ ይሰለቸኛል፡፡ ስለዚኽም ሌላ አዲስ ነገር ለመሰብሰብ ሩጫዬን እቀጥላለኹ፡፡ ደስታዬን ዘላቂ ለማድረግ ሰውንም፣ ፍጥረትንም በቁጥጥሬ ሥር ለማዋል እጥራለኹ፡፡ ምንም ነገር ከእኔ ቁጥጥር ውጪ እንዲኾን አልፈቅድም፡፡ ከቁጥጥሬ ውጪ ሊኾኑ የሚሞክሩ ነገሮች ቢኖሩ እንኳ ሲደክመኝ ወንበር እያቀረበ፣ ሲርበኝ መና እያወረደ፣ ሲጠማኝ ውኃ እያፈለቀ፣ ቀን ሐሩር እንዳይመታኝ በደመና፣ ሌሊት ጨለማ እንዳያስፈራኝ በእሳት ዓምድ እንዲመራኝ የምጠብቀው አምላክ አበጃለኹ፡፡

ይህ አምላኬም ጾሙን በቀበላና በፋሲካ እያጀብኹ እስከ ጾምኹለት፣ ለቤተ መቅደሱ አሥራት በኵራቱን እስከ ሰጠኹለት፣ ጠዋት ጠዋት እየተነሣኹ የውዳሴ ቀለቡን እስከሰፈርኹለት፣ በዓላቱን ሞቅ ደመቅ አድርጌ እስካከበርኹለት፣ ድረስ ከእኔ ጋር እንደሚኾን እርግጠኛ ነኝ፡፡ የምፈልገውን ኹሉ እንደሚያሟላልኝም እተማመናለኹ፡፡ እንዴ! የኔ አምላክ ነዋ! «አባቶቼ ያመለኩት!» እኔ እርሱ የሚፈልገውን አደርጋለኹ፤ እርሱ ደግሞ እኔ የምፈልገውን ኹሉ ያደርጋል፤ ወይም ይፈቅድልኛል፡፡ ታዲያስ! ሕይወት ሰጥቶ የመቀበል ገበያ አይደለች እንዴ!


ኹሉ ለፈቃዴ ይታዘዝልኝ ዘንድ የሰብሰብኋቸውንና «አሉኝ» ብዬ የምላቸውን ነገሮች ደግሞ ሰዎች ኹሉ እንዲያዩልኝ እፈልጋለኹ፡፡ የውዳሴ ዝናብ ይጠማኛል፤ የአድናቆት መሥዋዕት ሽታው ውል እያለ ዕረፍት ይነሣኛል፡፡ በዚህ የተነሣም የማኅበራዊ ኑሮ መፈክሬ «ዕንቁልልጬ!» ይኾናል፡፡ ሌሎች የላቸውም እኔ ግን አለኝ ብዬ የማስበውን ነገር ከፍ አድርጌ « እንቁልልጬ !» እያልኹ ባለኹበት አካባቢ ኹሉ የበላይነቴን፣ የተሻልኹ መኾኔን ማረጋገጥ እሻለኹ፡፡ በዚኽም ሌሎች እኔን እንዲያደንቁ፣ እንዲያወድሱ፣ እንዲያነግሡ እጣራለኹ፡- «መንግሥቴ ቀርባለችና ወደ እኔ ተመልከቱ! የሀብቴን ብዛት፣ የክብሬን ድምቀት እዩ! ስገዱልኝም!»

ሞኞችና አቆላማጮችም ይከተሉኛል፡፡ በውዳሴና በአድናቆት ክንፎቼም በርሬ፣ በከፍታ ላይ ከፍታ እጨምርና ልቤን «ከእኔ በላይ» ከሚለው ተራራ ላይ አውጥቼ አኖረዋለኹ፡፡ ከዚኽ ተራራ ላይ ኾነው ቁልቁል ሲያዩት አንሦ የማይታይ ነገር የለም! ልብም ቁልቁል በማየትና ከበታቿ ካሉት መብለጧን በማሰብ ስለምትጠመድ ሽቅብ ወደ ሰማይ ለማየት ጊዜ የላትም፡፡ ሽቅብ ካየችማ ሌላ የሚበልጣት ሊመጣ ነው፡፡ ሽቅብ አይቶ ራሱን የሚያሳንስ ማን ሞኝ አለ! «ያለኹት እኔ ነኝ! ከእኔ በላይ ያለውም ነፋስ ብቻ ነው፡፡» እያሉ ቀብረር ብሎ መኖር እንጂ!
ዓለም በእኔ ዙሪያ የምትሽከረከርልኝ! ይመስለኛል፡፡


አእምሮዬ ውስጥ የሚመላለሰውም የ«እኔ» ምሥልና ሐሳብ ብቻ ነው፡፡ ጀግና ስለኾንኹ ሰው ኹሉ ሊፈራኝ ይገባል! ክቡር ስለኾንኹ ሰው ኹሉ ሊያከብረኝ ይገባል! ቆንጆ ስለኾንኹ ሰው ኹሉ በውበቴ ሊነኾልልኝ፣ ውበቴን ሊያደንቅልኝ ይገባል! ከእኔ በላይ ዐዋቂና ሊቅ ላሳር ነው! ትሑት ስለኾንኹ ገልጬ ስለማልናገረው እንጂ « ኢየኀድጋ ለሀገር እንበለ አሐዱ ጻድቅ » (ሀገርን ያለአንድ ጻድቅ አይተዋትም፡፡) የተባለው ለእኔ ነው፡፡ እግዜርንም በቅርብ ዐውቀዋለኹ፡፡ የሚወድድ የሚጠላውን፣ የሚያስኮርፍ የሚያስቀውን ኹሉ ዐውቃለኹ !...    
በአጭሩ « እኔ » የእኔ እግዜር እኾናለኹ፡፡


የዚኽ ሩጫ «ክፋቱ» ታዲያ በራሳቸው እንዲኖሩ እንጂ ለእኔ እንዲገብሩ ያልተፈጠሩትን ነገሮች የኔ ገባሪዎች ለማድረግ በማደርገው ትግል ኹልጊዜም ዘላቂ አሸናፊ መኾን አለመቻሌ ነው፡፡ ለጊዜው ድል ቢቀናኝና ባስገብራቸው እንኳ የኋላ ኋላ የራሳቸውን ፈቃድ መከተላቸው አይቀርም፡፡ ለጊዜው ድል ያደረግኋቸው ቢመስል እንኳ ኋላ ሐዘን ሽንፈትን ተከትላ መምጣቷ አይቀሬ ነው፡፡ አምባገነንነት ቁስልን፣ ቁስልም ዐመፅን አለመውለድ አይችሉምና፡፡

ይኽንን ደግሞ የውስጤ ውስጥ አሣምሮ ያውቃል፡፡ ስለዚኽም የዐመፁ ምንጮች ሊኾኑ የሚችሉትን ነገሮች ለማድረቅ ልዩ ልዩ የመጨቆኛ መሣሪያዎችን ለማካበት ሌላ ሩጫ እጀምራለኹ፡፡ ኹሌም ሥጋት ነው፡፡ ኹሌም ፍርኀት ነው፡፡ ቀጥላ የምትመጣው ሰከንድ ምን ይዛብኝ እንደምትመጣ አላውቅም፡፡ ምናልባት ገመናዬን ገሃድ አውጥታ ክብሬን በወዳጆቼ ፊት ትቢያ የምታለብስ ጠላት፣ ሀብቴን የምትነጥቀኝ ባላንጣ፣ ጤናዬን የምትወስድብኝ በሽታ፣ ውበቴን የምትገፍፈኝ ምቀኛ ልትኾንብኝ ትችላለች፡፡ አምላኬ ደግሞ አንዳንዴ የምፈልገውን ኹሉ ላያደርግልኝ ይችላል፡፡ ከ «እኔ» በስተቀር ማንም የሚያስተማምን የለም፡፡ ለእኔ ያለኹት «እኔ» ብቻ ነኝ፡፡ ይኹን እንጂ ውስጤ እንደሚያውቀው «እኔ» ደግሞ ውስንነቶች አሉብኝ፡፡ የማልችላቸው ነገሮች አሉ፡፡ ትልቁ ውስንነቴ ደግሞ ነገን አለማወቄ ነው፡፡ ነገ የሥጋቴ ምንጭ ነው፡፡ ነገ የፍርኀቴ መነሻ ነው፡፡ ስለዚኽ «ነገ» የሚያመጣውን አደጋ ለመቀነስ ስል ዛሬን ላልተፈጠረ ችግር መፍትሔ በመፈለግ ስባዝን አሳልፈዋለኹ፡፡

« አሉኝ » ብዬ የቆጠርኋቸው ንብረቶቼ ከእጆቼ እንዳይወጡ ለማድረግ የባርነት ቀንበራቸውን ለማጠባበቅ ምስማሮች ሳበጃጅ ቀኑ ያልቃል፤ ሌሊቱ ይባጃል፡፡ ለደስታ ፍለጋ የጀመርኹት ጉዞ በደስታ ፈንታ ጭንቀትን፣ በእርካታ ፈንታ ጥማትን፣ በዕረፍት ፈንታ መባዘንን ይሰጠኛል፡፡ የማምነው «እኔ» ራሱ ስለማያስተማምነኝ ነገ የሥጋት ባንዲራ እንጂ የተስፋ ጭላንጭል አይደለችም፡፡ ሥጋቴ ፍርኀትን፣ ፍርኀቴም ጥላቻን ይወልዱብኛል፡፡ ነገ ያስጠላል፡፡ ዛሬም የነገ ዋዜማ ስለኾነ አያምርም፡፡ ጥላቻዬ ብስጭትን አርግዛ ትወልዳለች፡፡ «እኔ» በምሬት ሐሩር ይደርቃል፡፡ ደስታ የቀን ቅዠት ይኾናል፡፡ ዘላቂ ሐሴትና ሰላም ከዕለታዊ ኑሮዬ መዝገበ ቃላት ላይ ይጠፋሉ፡፡ የኑሮ ትርጉም የኾነው መስጠት ይርቀኛል፡፡ አንዳችም ነገር መስጠት ይሳነኛል፡፡ ከእምነት መሬት ተነቅሎ፣ የተስፋን ጥላ አጥቶ፣ የፍቅርን ውኃ ተጠምቶ የሚገኘው « እኔ » ራሱ የእርሱና የተከታዮቹ ማክተሚያ ጭንጫ መቃብር ይኾናል፡፡

አኹንም ግን እጅ አልሰጥም፡፡ ይልቁንም የውዳሴ መሥዋዕት እንዳይታጎልብኝ ስል ይኽንን ልምላሜ የሌለው፣ ፍሬ የማይታይበት፣ ውስጡ ለዓይን በሚከፋ፣ ለአፍንጫ በሚከረፋ ብስባሽ የተሞላ ጭንጫ መቃብር ውጫዊው ገጽታው እንዲያምር በወርቅማ ፊደሎች አንቆጠቁጠዋለኹ፡፡ በእብነ በረድ እከድነዋለኹ፡፡ ምን ላድርግ ውስጡማ አንዴ በበሰበሰ እኔነት ተሞልቷል፡፡ ብስባሹ እኔነት ያጎነቆለው ትልም ያንን የበሰበሰ እኔነት ያለዕረፍት እያኘከ ይበልጥ ያበሰብሰዋል፡፡ ከላይ ጌጥ ባኖርኩበት፣ አበባ በከመርኩበት፣ በኮስሞቲክስ በለቀለቅኹት፣ በሱፍ በጠቀለልኹት ቁጥርም ውስጡ ይበልጥ ይደፈናል፤ ይኽ ኹሉ ጥረት ወደ ውስጥ ላለማየት አይደል! ትሉም የበሰበሰው ውስጤ ይመቸዋል፡፡

ለሌሎች ያበጃጀኹት ቀንበር እኔኑ ባርያው አድርጎ ቀፍድዶኛል፡፡ ቀኖቼ በሐዘን ይፈጸማሉ፡፡ ሌሊቴም በሐዘን ያልፋል፡፡ ሀብት እዩኝ እዩኝን፣ እዩኝ እዩኝም ኩራትን ወለደ፡፡ የኩራትን ቀንበር እንደጌጥ ከጫንቃዬ ላይ አኖርኹ፡፡ ኩራትም የሥጋት አባት ኾነና፡፡ ለእኔ ሸጠኝ፡፡ እኔም በዕረፍት አልባ በረኀ፣ በእርካታ ቢስነት ምድረ በዳ አንከራተተኝ፡፡ እኔ ከ « እኔ » ተነሥቶ በ « የእኔ » በኩል አድርጎ « እኔ » ውስጥ ተቀብሮ ሕይወት መስጠት አቅቶት ቀረ፡፡ «ለዚኽ ለኃጢኣት ከተሰጠ፣ ከሕይወት መርገምን ከመረጠ ለሞት ከተሰጠ ከንቱ ኑሮ ማን ያድነኛል?!»


… ይቀጥላል

Inspiration from: Spiritual Exercises by St. Ignatius of Loyola.

No comments:

Post a Comment