Monday, February 13, 2012

የት አባቴ ኼጄ ልረፍ?

ሞባይሌን ተመለከትሁት የሳምንቱ ቅዳሜ አስራ አንደኛው ሰዐት ካለፈ ሠላሳ ደቂቃዎች መሆናቸውን ነገረኝ፡፡ የመጨረሻዋ ባለጉዳይ ገባች፡፡ መሥርያ ቤቴ ለደንበኞቹ ያዘጋጀውን ቅጽ መሙላት ጀመርሁ፡፡

“ስም”
ተናገረች፡፡ ፊቷ ላይ የፓውደር የከተራ በዓል በደመቀ ሁኔታ እየተከበረ አየሁት፡፡ ስሟን ሞላሁ፡፡ መሥሪያ ቤቴ ያዘጋጀውን ባለ ሦስት ገጽ ቅጽ ሞልቼ ጨረስሁ፡፡ ደስ ብሏት ከቢሮዬ ወጣችልኝ፡፡ እፎይ! ግልግል፡፡ ጠረጴዛ ላይ ጎብጦ ቀኑን ሙሉ ባለ ጉዳዮች በአምሳለ ጢስ ከብበውት የዋለው ትከሻዬ ላይ ቆረጠመኝ፡፡ ለነገሩ በቀን የአራት መቶ ሰው ቅጽ ሞልቼ ባይደክመኝ ይገርማል፡፡ የወጣልኝ ልማታዊ ሠራተኛ ነኝ፡፡

ረኀብ ሆዴን እንደ ድመት ይቧጥጠኝ ጀመር፡፡ ከቢሮዬ ምንጥቅ ብዬ ወጣሁ፡፡ እራቴን የመሥራት ጥንካሬው ስላልነበረኝ ጁስ ቤት ገብቼ አምባሻና ጭማቂዬን ላስኩና (መቼም በላሁ አይባል ነገር) በየወሩ የደመወዜን ግማሽ ወደምሰዋላት ቤቴ ማዝገም ጀመርሁ፡፡ ሰፈራችን መግቢያ ላይ ከክሊኒኩ ጎን ሦስት ሰዎች የሆነ ማስታወቂያ እየተከሉ ነው፡፡ አነበብሁት፤ “የዛሬው ትውልድ ቤተክርስቲያን Today’s Generation Church” ይላል፡፡ ግቢዬ በር ላይ ስደርስ የግማሽ ደመወዜን መሥዋዕት ተቀባይ እማማ እልፍነሽን አገኘኋቸው፡፡ ነጭ በነጭ ለብሰዋል፡፡ የሆነ ትራስና ጋቢ ነገር በቅርቡ ከገጠር ያመጧትንና አሁን በነጠላ የጠመጠሟትን ልጅ እግር ዘመዳቸውን በፌስታል አስይዘዋል፡፡ ትዝ አለኝ፡፡ ነገ ገደል አፋፍ ላይ የተሠራው ቤተክርስቲያን ወርኀዊ በዓል አለ፡፡ ወደዚያው እያዘገሙ እንደሆነ ገባኝ፡፡

በነገራችን ላይ እሱን ቤተክርስቲያን ለምን እዚያ ገደል ላይ ማነጽ እንዳስፈለገ ሁሌም እንቆቅልሽ ይሆንብኛል፡፡ ቤተክርስቲያን ጠፍቶ ነው እንዳይባል ከእርሱ በተቃራኒ አቅጣጫ በሁለት መቶ ሜትር ያህል ርቀት ላይ ሌላ ጥንታዊ ትልቅና በእምዬ ምኒልክ ጊዜ ከሰፈሩ ጋር አብሮ እንደተተከለ የሚነገርለት ቤተክርስቲያን አለ፡፡ አንድ ወቅት ስጠይቅ “ጠበል ፈልቆ ስለተገኘ ነው፡፡” የሚል ምላሽ አግኝቻለሁ፡፡ “ታዲያ ጠበሉን በጥንታዊው ቤተክርስቲያን ጥበቃና አገልግሎት ሥር ማድረግ አይቀልም ነበር?” ብዬ ስጠይቅ “ምነው ጥያቄ አበዛሽ?” የሚል የድምጽ ቁንጥጫ ቀመስሁ፡፡ ድምጻዊ ቁንጥጫው ወደ ዱላዊ ተግሣጽ ከማደጉ በፊት “ዝምታ ወርቅ ነው፡፡” የሚለውን ምሳሌያዊ አነጋገር ከድሮ የአማርኛ ደብተሬ ላይ አስታውሼ ራሴን አዳንሁ! (መማር ደጉ!)   
 
“እንደምን ዋሉ እማማ እልፍነሽ?
“ደኅና፡፡ ዚሃር መስጌን፡፡ ምነው ባክሽ ምነው ሌሊቱን ሙሉ መብራቱን ስታቃጥዪው ማደርሽ?
ውይይይይይይ! እኚህ ሴትዮ! የሚያከራዩዋቸውን ቤቶች 24 ሰዐት በመቆጣጠራቸውና በየሦስት ወሩ ኪራይ በመቀጠላቸው ወደፊት “ሞዴል ኪራይ ሰብሳቢ” ተብለው እንደሚሸለሙ ጥልቅ እምነት አለኝ፡፡
“የውልዎት እማማ እልፍነሽዬ በዚህ ሳምንት ትንሽ ፈተና አለችብኝ፡፡ ለዚያ ነው፡፡ ትንሽ ላጥና ብዬ፡፡ እስከ ስድስት ሰዐት…”
አላስጨረሱኝም፡፡ “ኤዲያ! ኤዲያ! ምነው እልፍነሽ!”

ዓይኖቻቸው ቆዳዬን እንደቅርፊት ከላዬ ላይ ገሸለጡት፤ ከፌስታል ነጻ የሆነ እጃቸውን በጄኪቻንኛ ይሁን በጄትሊኛ ባይገባኝም ፊቴ ላይ አወነጫጨፉብኝ፡፡ ቀድሞውንም ያልያዝሁትን መንገድ በቶኖች በሚለካ ትሕትና ለቀቅሁላቸው፡፡ ጋቢያቸውንና ነጠላቸውን በቁጣ ተጎነጻጽፈውብኝ ከባዱ ሰውነታቸው ወደፊት እየገፋቸው ኼዱ፡፡ እፎይ… ቤቴ ገባሁ፡፡ ጫማዬንና ልብሶቼን ገና ከበር ማውለቅ ጀምሬያለሁ፡፡ አንሶላ በመግለጥ ጊዜዬን ማባከን አልፈለግሁም፡፡ ከሁለት ወራት በፊት በአዲስ አበባ ምሕረት አልባ ብርድ ስሰቃይ ያየችኝ እናቴ የገዛችልኝን ወፍራም አልጋ ልብስ እንደጋዜጣ ተጠቀለልሁበትና በደረቴ ተዘረጋሁ! ከእኛ ግቢ ቀጥሎ ካለው ቡና ቤት “አድራሽ መላሽ አገልጋዬ” የሚለው የዘሪቱ ዘፈን ይሰማኛል፡፡ ዕንቅልፍ ይወስደኝ ጀመር፡፡ እፍፍፍፎይ!

“አላህ ወአክበር!” 
ከቤተክርስቲያኑ ጎን ያለው መስጊድ ደማቅና ማስጠንቀቂያ መሰል የኢሻ ጸሎት አዛን ሙእሚኖቹን ከያሉበት እኔን ግን የበለጸጉ ሀገራት እንኳ ሊለግሱኝ ከማይችሉት እንቅልፌ ጠራን፡፡ ተበሳጨሁ፡፡ ተነጫነጭሁ፡፡ ስግደቱ እስኪያበቃ ድረስ ነጎድጓዳማው ድምጽ ማጉያ አካባቢውን ተቆጣጠረው፡፡ ወይ መከራ! ዓይኖቼን መግለጥ ቢያቅተኝም መተኛት አልቻልሁም፡፡ ቶሎ መጠናቀቁን ተስፋ ማድረግ ጀመርሁ፡፡ “ኢስላም ማለት ሰላም ማለት ነው፡፡” የሚለው የእናቴ ጎረቤት የሼህ በድሩ አስተምህሮ ብልጭ አለብኝ፡፡ “ሼህ በድሩ ዘመዶችዎ እዚህ እኔን የሰላም እንቅልፍ እየነሡኝ እንደሆነ አላዩልኝም፡፡” 

ጸሎቱ ረዘም ላለጊዜ ቀጥሎ ከቆየ በኋላ ዝምታ መልሶ ሰፈነ፡፡ ቦብ ማርሌይ ከጎረቤቴ ቡና ቤት ሆኖ በለስላሳው “Don’t worry about a thing; every little thing is gonna be alright” ይለኝ ጀመር፡፡ “አልሐምዱሊላህ! አሁን መተኛት እችላለሁ፡፡” ብዬ ራሴን አጽናናሁትና ድጋሚ የዕንቅልፍ ቪዛ ለማግኘት የትራሴን ኤምባሲ ደጅ መጥናት ጀመርሁ፡፡ እ…ፎ…ይ…!

እናቴን መጣች፡፡ ካቀረቀርሁበት ወረቀት ላይ ቀና አድርጋ ሳመችኝና “ምነው ልጄ ከሳሽ?” አለችኝ፡፡ ፊቴን እየደባበሰችም “የአዲስ አበባ ብርድ አቆርፍዶሽ የለ እንዴ? ወይኔ ልጄን! ቆይ አሁን ቆንጆ እራት አዘጋጅልሻለሁ፡፡” እያለች ወደ ማድቤት ገባችና የሚጣፍጥ ምሥር ወጥ ዝንጥፍጥፍ ባለ የነጭ ጤፍ እንጀራ ላይ አድርጋ ወደእኔ መጣች፡፡

“አበባዬ እስኪ ይህቺን ላጉርስሽ፡፡ አንቺ መቼም እዚህ ወረቀት ላይ አንዴ ከተተከልሽ የሚነቅልሽ የለም፡፡” አምላክ እናቶችን የፈጠረበት እጁ በእውነት ፍቅር ነው፡፡

እንጀራውን በወጥ አጥቅሳ ጉርሻዋን ከሰማመረቻት በኋላ እጇን ወደኔ ዘረጋች፡፡ ወይኔ! የምሥሩ ወጥ ሽታ የጽጌረዳን መዓዛ ያስንቃል! አቦ አሁን የእናት ጉርሻ ከሌላ ሰው ጉርሻ ጋር እኩል ጉርሻ ይባላል? ስሕተት ነው፡፡ እንዴ! ሌላ ሰው የፈለገውን ያህል ጠቅልሎ ቢያጎርስ ጉርሻው እንጀራ በወጥ ከመሆን አይዘልም፡፡ ምናልባት ከዘለለም አሳንቆ የመግደያ መሣሪያ ሊሆን ይችላል፡፡ የእናት ጉርሻ ግን እንደዚህ አይደለም፡፡ ወጡ ሽሮም ይሁን ዶሮ እናት የምታጎርሰው እንጀራ በወጥ አይደለም- ፍቅር በፍቅር እንጂ፡፡ በተለይ ደግሞ ወጡ እንደዚህ እንደኔ እናት ምሥር ወጥ ትክትክ ብሎ የተከሸነ ከሆነማ በቃ! አፌን ወደጉርሻዋ ቀረብ አደረግሁ፡፡

ምን ያደርጋል! የጎረቤታችን ቡና ቤት ዲጄ ከአንድ የጥቁር ፈረንጅ ጋር በመመሳጠር “Can’t touch this!” ብሎ ጮኸብኝና እርሱ ላይበላው የእናቴን ጉርሻ ነጠቀኝ፡፡ ጠላታችሁ ብን ይበል! ብንን ብዬ ተነሣሁና በድንጋጤ ጆሮዎቼን እኮረኩር ጀመር- ዲጄው ጆሮዬ ውስጥ የገባ መስሎኝ፡፡ ውይ ሐበሻ! አሁን እናቴ እኔን አንድ ሴት ልጇን በሕልሜ እንኳን ብታጎርሰኝ ምናለበት?! አቦ ሐበሻ ምቀኛ ነው፡፡ እንደ ዐረብ ሀገር ስደተኛ እኅቶቼ ከሀገረ እንቅልፍ በጥረዛ መባረሬ ካልቀረ ምናለ የእናቴን ጉርሻ እንኳ እስክጎርስ ቢጠብቀኝ ኖሮ፡፡
*                                           *                          *                                   *                    *
“እንዲህ ቢሆን ኖሮ! እንዲያ ቢሆን ኖሮ!
ኖሮ እያሉ ኖሮ
ከመኖር አማርሮ”
አሁን ያለሁበትን ሁኔታ በዘመናchin Journalists አማርኛ ስገልጸው “ዲጄው የሙኒትን ዘፈን እጅግ ከፍ ባለ ድምጽ በማጫወት ላይ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡” ልል እችላለሁ፡፡ አብረውት ያሉት የቡና ቤቱ ታዳሚዎችም ባልተገራ ጉሮሮ በጃምቦ-ጀትኛ ያጓሩ ጀምረዋል፡፡ ለነገሩ የጠጡት ጃምቦ ብዛትም ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ታዋቂ ዘፈኗ እኛ ሰፈር አካባቢ እንዲህ ያለ ያለመዜም አሰቃቂ አደጋ እንደደረሰበት ራሷ ሙኒት ብትሰማ ኖሮ ከድንጋጤዋ ብዛት የተነሣ ቦሌ አካባቢ የሚገኘው አማርኛዋ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከሀገር ይኮበልልባት ነበር፡፡ ደግነቱ ቴዎድሮስ ታደሰ “ነገር ካልሰሙት መቼም አይቆጭም፡፡” ብሏል፡፡


አሁን ዲጄው ከድምጽ ማጉያው ጋር ተቧድኗል፡፡ ታዳሚዎቹ ደግሞ በአንድ ላይ ሆነው በባዶ ጉሮሮ እየተፎካከሩት ይገኛሉ፡፡ እንቅልፌን አባረሩብኝ፡፡ “ምነው ጉሮሯችሁ እንደ አክርማ ከሁለት በተሰነጠቀ!” ብዬ ልራገም አማረኝ፡፡ ግን ያን የመሰለ የእናቴን ጉርሻ ሊቀበል የነበረ አፌ እንዲህ ያለ መራራ ነገር አይመጥነውም ብዬ ተውሁት፡፡ ደግሞ የእናቴ መንፈስ ሰምቶኝ ሰዎቹን በሙሉ ጉሮሮ አልባ ቢያደርጋቸውስ? 
እነሆ በአንድ ሌሊት እንቅልፌን ለሁለተኛ ጊዜ ተነጠቅሁ፡፡ ወይ ነዶ! የብስጭቴ ብዛት ውስጥ እግሬ ድረስ ዘልቆ ስለተሰማኝ ነው መሰለኝ ልቤ በኃይል ትመታ ጀመር፡፡ ውስጥ እግርና ልብ እንዴት ይገናኛሉ? የሚለው ጥያቄ ለሥነ ሕይወት ተማሪዎች፣ ተመራማሪዎች ወይም ተማራሪዎች የቤት ሥራ ይሁናቸው፡፡  
ሞባይሌን አየሁት፡፡ ከሌሊቱ 7፡13 ደቂቃ ይላል፡፡ ነገ 4፡00 ላይ የምፈተነው ፈተና አለኝ፡፡ ምንም እንኳ የምማረው ለሁለተኛ ዲግሪዬ ቢሆንም ቅሉ ውጤቴ ላይ ቀልድ አላውቅም፡፡ ምክንያቱም አሁን ከምሠራበት መሥሪያ ቤት አሰልቺ ልማታዊ ስብሰባና አቆርቋዥ የቢሮ ፖለቲካ ልላቀቅ የምችለው ይህቺን ዲግሪዬን ስይዝ ብቻ እንደሆነ ጠንቅቄ አውቃለሁ፡፡ እርግጥ ነው ሰሞኑን አብዛኛውን ከዕንቅልፌ፣ ጥቂት ጥቂት ደግሞ ከሻይ ሰዐቴም፣ ከቢሮ ወሬ ሰዐቴም፣ ከታክሲ ላይ ቆይታዬም እየቀነጣጠብሁ ጥሩ ስቸክል ከርሜያለሁ፡፡ ትምህርቱ ደግሞ ደስ ይላል፡፡ A ማምጣት እንዳለብኝ ከራሴ ጋር ተስማምተናል፡፡ ዛሬ ሌሊት እስከ 9፡30 ድረስ ተኝቼ ከዚያ በኋላ ያሉትን ሰዐታት ለመጠቀም አስቤ ነበር፡፡ እድሜ ለጎረቤቶቼ እነሆ ለሊቷ ዓይኔ እያያት ሔደች፡፡ ራሴ ይወቅረኝ ጀመረ፡፡ እማማ እልፍነሽ መውጣታቸውን ማየቴ አደፋፈረኝና የመጣው ይምጣ ብዬ መብራቱን አበራሁት!
እንደምንም ራሴን አበረታታሁትና ከአልጋዬ ወርጄ ፊቴን ታጠብሁ፡፡ ወረቀቶቼን ከቦርሳዬ ውስጥ አውጥቼ አልጋዬ ላይ ቁጭ አልሁ፡፡ አንድ ሰዐት ያህል እንዳነበብሁ ዓይኔ ይቆጠቁጠኝ ጀመር፡፡ ዕንቅልፌ እንዳያሸንፈኝ ብዬ ከአልጋዬ ወረድሁና ቆሜ ማንበብ ጀመርሁ፡፡ ብርዱ ሊሰማኝ ሲጀምር አልጋ ልብሱን ለብሼ አልጋ ላይ ቁጭ አልሁ፡፡ የዲጄው ሙዚቃ እየቀነሰ ሔዷል፡፡
*                                  *                           *                                   *
የድሮ ትምህርት ቤታችን ውስጥ ነን፡፡ አባዬ የገዛልኝን አዲሱን ሮዝ ቀሚሴን ለብሻለሁ፡፡ የዓመቱ መጨረሻ ነው፡፡ ሁላችንም ወላጅ አምጥተናል፡፡ የመረብ ኳስ ዳችን ላይ የክፍል ዴስኮቻችን ወጥተው ወላጆቻችንና እኛ ተደርድረንባቸዋል፡፡ ከየክፍሉ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ የወጡ ተማሪዎች እየተሸለሙ ነው፡፡ የኛ ክፍል ተራ ደረሰ፡፡ የአካባቢ ሳይንስ ቲቸራችን መነጽራቸውን አስተካከሉና
“ከሦስተኛ ኤ ተማሪ ምሥራቅ ቢተርፍ ሦስተኛ!” በማለት ጮሁ፡፡
ወላጆቻችን አጨበጨቡ፡፡
ወንዳታ! ሦስተኛ አልወጣሁም ማለት ነው፡፡ አባባ ደግሞ ከአንድ እስከ ሁለት ከወጣሽ የቦሊ ቦሊ ኳስ እገዛልሻለሁ ብሎኛል፡፡
ጓደኛዬ ምሥራቅ ሽልማቷን ተቀብላ ተመለሰች፡፡ ሱዚና ገመድ ዝላይ የሚችላት የለም፡፡ ቦሊ ቦሊ ግን እኔ እበልጣታለሁ፡፡
“ተማሪ ደቻሳ ግርማይ ሁለተኛ!” የስ! አንደኛ ነው የወጣሁት ማለት ነው!
ደቻሳ ስዘልል አየኝና አኮረፈ፡፡ ስለበለጥኩት ነው፡፡ ግን ሽልማቱን ሔዶ ወሰደ፡፡
“ተማሪ በፍቅር አዘዘ አንደኛ! አጨብጭቡላት!” ሰዉ ሁሉ አጨበጨበልኝ፡፡ ምሥራቅ ግን አላጨበጨበችልኝም፡፡ እኔ ግን አጨብጭቤላት ነበረ፡፡
አባዬ ዕቅፍ አድርጎ ሳመኝና “ሒጂ ሽልማትሽን ውሰጂ፡፡” አለኝ፡፡
“አባዬ የቦሊቦሊ ኳሴን ትገዛልኛለህ አይደል?”
“እሺ፡፡ እሱ በኋላ ይደርሳል፡፡ አሁን ሒጂና ተሸለሚ፡፡”
ዳይሬክተራችን በቢጫ ወረቀት የተሸፈነ ነገር ይዘዋል፡፡ ለኔ ነው፡፡ ፈገግ ብለው እያዩኝ ነው፡፡ አካባቢ ሳይንስ አስተማሪያችንም እያጨበጨቡልኝ ነው፡፡ መድረኩ ጋር ልደርስ ነው፡፡ ከኋላዬ የነበረው ጭብጨባ በድንገት ጸጥ አለና “ተንሥኡ ለጸሎት!” የሚል ትእዛዝ ሰማሁ፡፡ ወደኋላዬ ዞር አልሁ፡፡

የእማማ እልፍነሽ ቤተክርስቲያን ዲያቆን ከሞት ለመቀሰቅስ በሚመስል ጩኸት ሽልማቴን ነጠቀኝ፡፡ እስኪ ምናለ በሕልም እንኳ ብሸለምበት?

“እግዚኦ ተሣሃለነ፡፡” ሌላ ድምጽ ተቀብሎ አካባቢውን አንቀጠቀጠው፡፡ ከመሬቷ በስተቀር ሁሉ ነገሯ ቆርቆሮ የሆነችው ቤተክርስቲያኗ አናቷ ላይ የሰቀሉባትን ይህን አገር ገልብጥ ድምጽ ማጉያ እንዴት እንደቻለችው አላውቅም፡፡ "ቆይ ደግሞ “ለጸሎት ተነሡ!” የሚለው ትእዛዝ ቤተክርስቲያን ውስጥ ላለሰው እንጂ እሥራ ላይ ውሎ ደክሞት ቤቱ አልጋ ላይ ማንንም ሳያስቸግር የተኛ ሰውን ነው እንዴ?" ተነጫነጭሁ፡፡ ወረቀቶቼ አልጋው ላይ ተበታትነዋል፡፡ ደብተሬም መሬት ላይ ወድቋል፡፡ ወይ ነዶ!
ሰዐት አየሁ፡፡ ከሌሊቱ 10፡10 ይላል፡፡

“ሰላም ለኵልክሙ!” ቄሱ ቀጠሉ፡፡ ወይ ሰላም! አጠገቤ ቢሆኑ ኖሮ ብዬ ተመኘሁ፡፡
“ለእኔ አሁን ሰላሜ እንቅልፌ ስለሆነ አይበጥብጡኝ! አይጩሁብኝ! ልተኛበት! እኔ እንደእርስዎ በወር ሁለት ሳምንት ሳይሆን በወር አራት ቀናት ብቻ እንዳርፍ የተፈቀደልኝ ግብር ከፋይ ዜጋ ነኝ፡፡ እሑዴን አይሸራርፉብኝ፡፡ እማማ እልፍነሽን ከሆነ እርስዎ ጋር ስለሆኑ በሹክሹክታም ቢናገሩ ይሰሙዎታል፡፡ እኔን ለእንቅልፌ ይተዉኝ፡፡ አሁን ጸሎትዎን ለመካፈልም ሆነ የድምጽዎን መረዋነት ለማድነቅ ጊዜዬ አይደለም፡፡” እላቸው ነበር፡፡ 

ዕንቅልፌ ሲሸሽ ጥሎት በሔደው የድካም ጓዝ ሰውነቴ ደቀቀብኝ፡፡ ትራሱ ቆልምሞኝ ነበረ መሰለኝ አንገቴን በጣም አመመኝ፡፡ አጠገቤ የነበሩትን ወረቀቶች በማንሣት ጥናቴን ለመቀጠል ሞከርሁ፡፡ ከአንድ ሰዐት በላይ ግን መቀጠል አልቻልሁም፡፡ ዓይኖቼ እጅግ ያቃጥሉኝ ጀመር፡፡ ቢያንስ አእምሮዬ በቂ ዕረፍት ካገኘ እስከዛሬ ያጠናሁትን ፈተና ላይ ንቁ ሆኜ እንደምሠራ ራሴን አባበልሁትና የሔደውን እንቅልፌን ለመከተል ቆረጥሁ፡፡ ጠዋት ዕንቅልፍ እንዳይጥለኝም ስልኩን ዐላርም ሞላሁት፡፡ እግረመንገዴንም አሁን 11፡05 መሆኑን አየሁ፡፡ የመስጊዱ ሙአዚን በአረብኛ “ከእንቅልፍ ሶላት ይሻላል!” ሲሉ መጣራት ጀምረዋል፡፡ እኔ ግን ለጊዜው አምላኬን ከጸሎት ይልቅ በሕልም ውስጥ ማየትን መርጫለሁ፡፡ ስለዚህ ልተኛ ነው፡፡ አልጋልብሱን ወደፊቴ ሳብሁትና ተሸፋፈንሁ፡፡
*                                         *                                       *                          *
“ምእመናን ሙሽሮቹ እየገቡ ስለሆነ እልል በሉ! እልል በሉ! እልልልልልልልልልልልልልልልል!”
“በጽሐ መርዓዊ ፍሥሐ ለኵሉ
በሰላም ጻኡ ተቀበሉ፡፡”
ወይ ሰላም! የትልቁ ቤተክርስቲያን ትልቁ ድምጽ ማጉያ በቤተክርስቲያኑ ውስጥ ሁለት ሰዎች ከሁለትነት ወደአንድነት በመምጣት ላይ በመሆናቸው እኔ በምንም ምክንያት ለብቻዬ እንቅልፌን ማጣጣም እንደማልችል ነገረኝ፡፡ ወይ ጣጣ! አሁን እነዚህን ሰዎች ለማጋባት ቤተክርስቲያኑ ውስጥ ያለው ሰው እልል ካለ አይበቃም? ቤታችን ያለን ሰዎች ሁሉ አልጋችን ውስጥ ሆነን እልል ማለት ይጠበቅብናል? ወይስ ቤተክርስቲያኑ ውስጥ የሚደረገውን ነገር በሙሉ እኛ ልንሰማው ያስፈልጋል? እንዴ መስማት ከፈለግን እንመጣ የለም እንዴ የምን ረብሻ ነው?
የእማማ እልፍነሽ ቤተክርስቲያን ካህን ደግሞ “ለእሉ ክልኤቱ ፍጡራን ስብሐተ ፈጣሪ ይደልዎሙ” እያሉ ደመቅ አድርገው ያዜሙ ጀመር፡፡
ሦስቱም ድምጽ ማጉያዎች አንድ ላይ ሲጮሁብኝ ራሴ ዉዉዉ... ይልብኝ ጀመር፡፡
ተኝቶ ከማዳመጥ ውጪ ምንም ማድረግ አልቻልሁም፡፡ ሦስቱንም በደነዘዘ አእምሮ ማድመጥ ጀመርሁ፡፡ አስራ አንድ ሰዐት ተኩል አካባቢ ሙአዚኑ ዝም አሉ፡፡ አሁን የሁለቱ ቤተክርስቲያኖች ድምጽ ማጉያዎች እሪታ ብቻ አካባቢውን ተቆጣጥሮታል፡፡
“ተሣሃልከ እግዚኦ ምድረከ!”
“ሠርዐ ለነ ሰንበተ ለዕረፍተ ዚአነ ፍሥሐ ወሰላም ለእለ አመነ፡፡”
እንቅልፍ በዓይኖቼ ሊዞር አልቻለም፡፡ ይህቺ ሞገደኛ ውስጤ ሒጂና “እኔን ዕንቅልፌን እየነሣችሁኝ እናንተ ሰንበት ለዕረፍት ነው ብትሉ እንዴት ላምናችሁ ይቻለኛል?” በያቸው አለችኝ፡፡ እኔ ግን ዐቅሜን ስለማውቅ ለሌሊት እንቅልፍ ብዬ የቀን ሕይወቴን መቃብር አላወርዳትም ብዬ ተውሁት፡፡

ኪዳኑ አለቀ፡፡ ቅዳሴ ቀጠለ፡፡
“ኵሉ ዘገብራ ለጽድቅ ጻድቅ ውእቱ ወዘያከብር ሰንበተ፡፡”
 …
“ጻኡ ንኡሰ ክርስቲያን፡፡”
ሰዐቴን አየሁት፡፡ 1፡15፡፡ ፈተናዬ ሊጀመር ሁለት ሰዐት ከ45 ደቂቃዎች ይቀሩታል፡፡ እነዚህን ሰዐታት እንኳ ብተኛ ንቁ እሆን ነበረ፡፡ ከመንጋጭላዬ የግራ ጎን አንሥቶ እስከመሐል አናቴ ድረስ እየወጋኝ ነው፡፡ ራስ ፍልጠት የሚባለው መሆን እንዳለበት ገመትሁ፡፡ ጨጓራዬም ክፉኛ መገለባበጥ ጀምሯል፡፡ በጊዜ በወተት ካላበረድሁት እንደተለመደው ሳምንት ሊያስተኛኝ መሆኑ ነው፡፡ ወደ ትምህርት ቤት ሔጄ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ትንሽ ብተኛስ? እንዲያውም ከሸምሱ ሱቅ የላስቲክ ወተት እገዛና እሱን መንገድ ላይ ጠጥቼ እሔዳለሁ፡፡ ከአልጋው ላይ በፍጥነት ወረድሁና ማታ በያቅጣጫው የወረወርኳቸውን ልብሶቼን ከያሉበት ጠርቼ ለባበስሁ፡፡ ጫማዬን አስሬ ቀና ስል የማየው ነገር ሁሉ ነጭ ሆነብኝ፡፡ አዞረኝ፡፡ ቶሎ ብዬ ቁጭ አልሁ፡፡
የእማማ እልፍነሽ ዲያቆን “የተቀመጣችሁ ተነሡ!” ሲል ሰማሁት፡፡
ወይ መነሣት!

ለጥቂት ደቂቃዎች እዚያው ባለሁበት ተቀመጥሁና መለስ እንደማለት ሲልልኝ ቀስ ብዬ ተነሣሁና በሩን ቆልፌ ወጣሁ፡፡
ክሊኒኩ ጋር ስደርስ የሆነ ነገር መሬት ላይ ወድቆ ተመለከትሁ፡፡ ጎንበስ ብዬ አየሁት፡፡ ጠላታችሁ ወከክ ይበል ልቤ ወከክ አለ፡፡ መቶ ብር! እንዴ! ሌሊቱን ሙሉ በእርሱ ስም እንቅልፍ ሲነሱኝ ያደሩትን ተመልክቶ አምላክ ለካሳዬ የሚሆን ነገር አዘጋጀልኝ፡፡ ብድግ አደረግኋት፡፡ ቀና ስል ግን ሰማይ ምድሩ ተደባለቀብኝ፡፡ ምድሪቷ ከሥሬ ከዳችኝ፡፡ ጸጥታ፡፡
*                             *                                          *                                 *
 “በፍቅር! በፍቅር!”
ነቃሁ፡፡  ክንዴ ላይ ግሉኮስ ተቀጥሎልኛል፡፡ ተርፌያለሁ ማለት ነው፡፡ ነጭ ገዋን የለበሰ ረዥምና ወፍራም ሰው አጠገቤ ቆሞ ይጠራኛል፡፡ በዓይን አውቀዋለሁ፡፡ የክሊኒኩ ነርስ ነው፡፡
“አቤት”
“ምን ሆነሽ ነው፡፡” 
“አዙሮኝ፡፡” 
“ስትወድቂ እኔ ከኋላሽ ነበርሁ፡፡ አንሥቼሽ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ያምሽ ነበር እንዴ?”
ከጨጓራ በስተቀር የማውቀው ሌላ ሕመም እንደሌለብኝና ሌሊት በእንቅልፍ እጦት እንዴት እንደተሰቃየሁ ነገርሁት፡፡ ፊት ለፊቴ የተሰቀለውን የግድግዳ ሰዐት ተመለከትሁት፡፡ 3፡00፡፡ የአራት ሰዐቱ ፈተናዬ ትዝ አለኝ፡፡ እንደምደርስ አሰብሁ፡፡ አሁን ራስምታቱ ቀለል ብሎልኛል፡፡ ጸጥ ብሏል፡፡

“ታድለህ!” ብዬ ልናገር ስል የቤቱ የፍሎረሰንት መብራት እንደጥንዚዛ መጮህ ጀመረ፡፡
“Great! መብራት መጣ ማለት ነው፡፡” አለ፡፡
በዚያው ቅጽበት ከጎረቤት “ኢየሱስ ጌታ ነው! ኢየሱስ ጌታ ነው! እልልልልልልል!” ተባለ፡፡ አዲሷ የሰፈሬ ፕሮቴስታንት ቸርች ምእመናን ናቸው፡፡ ኪይቦርዱ አጉረመረመ፡፡ አስመላኪው ምእመናኑን ለዝማሬ ጋበዘ፡፡ እስከ ሰማይ ድረስ በእነርሱ ምስጋና ምድርን እንደ ብረት ድስት ክድን እንደሚያደርጓት መንፈሳዊ መፈክር አሰማ፡፡ 
“አሜን! ሀሌሉያ! እልልልል!” ተባለ፡፡ ከዚያም አካባቢው ይቀወጥ ገባ፡፡ 

“የነፍሴ ወዳጅ አንተ በፍቅርህ ልቤን ታሳርፋለህ፡፡”
“እልልልልልል…..!”

እያሉ ይዘምሩ ጀመር፡፡ የጭብጫቦውና የእልልታው ሱናሚ የክሊኒኩን የጭቃ ግድግዳ ያናግረው ገባ፡፡ ነርሱ ምንም እንዳልተፈጠረ ሥራውን ቀጥሏል፡፡ ያው በፊዚካል ምናምን እቋቋመዋለሁ ብሎ ይሆናል፡፡ እኔ ግን “ጃፓንን ያየ በሱናሚ አይቀልድም፡፡” ብዬ የመሐሙድን “ዐቅምን ዐውቆ መኖር ጥሩ ነው፡፡” እየዘፈንሁ ከአልጋው ዱብ፡፡ የምሬን ነው የምላችሁ የሃይማኖት ድርጅቶች በሙሉ እኔ እንዳልተኛ በጠላትነት የተሰለፉብኝ መሰለኝ፡፡ እንዴ! እነርሱ ስለ እረፍታቸው የሚያመሰግኑት ሌላ ሰው ዕረፍት እየነሱ ነው እንዴ? 

ከክሊኒኩ ስወጣ አያቴ ዳዊት ሲደግሙ “መኑ ይሁበኒ ክንፈ ከመ ርግብ እስርር ወአእርፍ” ይሉ የነበረው ትዝ እያለኝ ነበር፡፡
በርሬ አርፍ ዘንድ እንደርግብ ክንፍን ማን በሰጠኝ (መዝ. 55፣6)፡፡

No comments:

Post a Comment