Wednesday, September 24, 2014

ወደ ናፖሊዮን ሣልሳይ የቀረበ የቅኝ ተገዢነት ጥያቄ



ቀጥሎ የቀረበው ደብዳቤ በ1859/1851

አገው ንጉሤ ከተሰኘው የኢትዮጵያ መስፍን ወደ ፈረንሳይ ንጉሥ ናፖልዮን ሣልሳይ የቀረበ ወደ ናፖሊዮን ሣልሳይ የቀረበ የቅኝ ተገዢነት ጥያቄ ነው፡፡ በግእዝ የተጻፉትን ዐረፍተ ነገሮች ወደ አማርኛ በቅንፍ ተርጉሜላችኋለኹ፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክና በኢትዮጵያ ነገሥታት (የነበሩትንም ያሉትንም ይመለከታል፡፡) ላይ ትንሽ ይቆዝሙ፡፡ 



ተጽሕፈት በሐውዜን አመ 1ኅዳር እምልደተ እግዚእነ በ%80)9 ዓመትበሐሳበ ሮማ፡፡ ወበኢትዮጵያ በ%80)1  ዓመት አመ&4 ለጥቅምት፡፡ (በሮማውያን አቆጣጠር ኅዳር1ቀን 1859፣ በኢትዮጵያውያን አቆጣጠር ደግሞ ጥቅምት 24 ቀን 1851 ዓመተ ምሕረት በሐውዜን ተጻፈች፡፡)

ንጉሠ ነገሥት ሆይ!
ካገሬ ሥራት አስቀድሜ ለጣቃዬ ያክስቴ ልጅ እርሱም ከፈረንሳዊ አገር ሲመለስ መርከብ በመሰበር በባሕር መሞቱ ልቤን የሚያሳዝነኝን ባደረጉለት መልካም ሥራት አመሰግነዎ አለኍ፡፡ 

የእግሊዞች ተንኮል አውለቃኍ፡፡ ቈንስላቸውን ቴዎድሮስ በሉኝ ወደሚል ቋረኛ ካሳ መስደዳቸውን አውቃለኁ፡፡ ክፋታቸው ሳይበዛ በጭንቅ ጊዜ ልቤን ወደርስዎ የፈረንሲስ ንጉሠ ነገሥት አድርጌ አለኍ፡፡ አድርጌም ከእርስዎ የኢጣልያን ዓርነት ጠባቂ በታላቅ ኃይልዎ ያገሬን ዓርነት እንዲጠብቁልኝ የሥራት ብርሃንም ወዳገሬ እንዲያደርሱልኝ ከዘራፊ ከቴዎድሮስ እጅ እንዲጠብቁልኝ እለምነዎ አለኍ፡፡ ይህነንም እንዲፈጸም ሁለት ነገር ያስፈልጋል፡፡ አንዱ በፊት እንደላክሁበዎ ሥራትን ሁሉ የሚያይ የርስዎ ምስለኔ ቢሰዱልኝ ባገሬ እንደራሴ እጠብቃለኍ፡፡ የፈረንሳዊ ባንዴራንም አስተክላለኍ፡፡ ሁለተኛው እኔ የምመኘው እርሱ ነውና ሁለት ባተርያ የመድፍ ከነተኳሽ ጋራ ነው፡፡ ስለሚያደርጉልኝ ነገር ደስ አሰኘዎ አለኊ ብዬ ተስፋ አለኝ፡፡ ስላደረጉልኝና የስዊስን መንገድ ባሕርም በመግጠም ላገሬ ስለሚያደርጉልኝን ራስ ዱማራ የሚባል ዙላን አበረክትዎ አለኍ፡፡
ንጉሠ ነገሥት ሆይ! የነገርሁዎ የልቤን ሐሳብ ቶሎ እንዲፈጽሙልኝ ተስፋ አለኝ፡፡ 


ተወከፍ አምኃተ ትሑታተ እምእኁከ ትሑት ንጉሤ፡፡(ከዝቅተኛ ወንድምኽ ዝቅተኛ ሥጦታዎችን ተቀበል፡፡)


ምንጭ፡- ተስፋዬ አካሉ፡፡ አጤ ቴዎድሮስ በሦስቱ ቀደምት ጸሓፍት፡፡

Monday, September 22, 2014

ፕሮፓጋንዳ የፈጠራት ወያኔ


ኢሕአዴግ ባሕር ዳር የገባ ሰሞን ነው አሉ፡፡ የኢሕአዴግ ሠራዊት ለዕቃ ማጓጓዣነት የሚጠቀምባቸውን ግመሎቹንና አጋሰሶቹን ኹሉ ይዞ ከተማዋን በቁጥጥሩ ሥር እንዳዋላት ግመል አይተው የማያውቁትትንንሽ ልጆች “ወያኔ ያቻት! ወያኔ! ወያኔ ያቻት!” እያሉ ወደ ግመሎቹ ፡፡ ይኼኔ ከሠራዊቱ አባላት አንዱ “ልጆች፣ ይቺ ወያኔ አይደለችም፡፡ ወያኔ እነርሱ ናቸው፡፡” በማለት ጓዶቹን ያሳያቸዋል፡፡ እነርሱም “ወይድ! ልታሞኘን ነው?! እነርሱማ እንደኛ ሰዎች ናቸው፡፡” ብለውት ዕርፍ፡፡ ለካ ወያኔ ማለት ለእነርሱ የኾኑ ታይተው የማያውቁ ፍጥረታት ጭራቆች ነበሩ፡፡ 

አኹን ርእዮት ዓለሙን፣ በቀለ ገርባን ወይም ዞን ዘጠኞችን አይቶ የማያውቅ የኢቲቪ ደንበኛ እኮ “አሸባሪ!” ምናምን ሲባሉ ሲሰማ የኾኑ ፈንጂ ታጥቀው የሚዞሩ ጨካኝ መላእክተ ሳጥናኤል ይመስሉት ይኾናል፡፡ ባለ ራእዩ መሪ ሲባል ደግሞ ብርሃናማ ክንፎች ያሉት፣ ጭንቅላቱ ዙሪያ አክሊለ ብርሃን የተጎናጸፈ፣ ፈገግታው ከሩቅ የሚጣራ ቅዱስ መልአክ ይታየው ይኾናል፡፡ የፕሮፓጋንዳ ጉልበት!የፕሮፓጋንዳ ጉልበት!
 

Friday, September 19, 2014

ግንቦትና ቦረንትቻዎቹ

ሴት አያቴ ጫሊ ወዬቻ ትባላለች፡፡ እውነቴን ነው፡፡ ሐምሌ 24፣ 2002 ዓ.ም. ዐርፋ ቢሾፍቱ መድኃኔዓለም ነው የተቀበረችው፡፡ ነፍሷን ይማርልኝና እጅግ ትወደኝ ነበር፡፡ አንድ ቀን እንዲኽ ጠየቅኋት፡፡ እኔ፡- እማማአያቴ፡- ኦእኔ፡- ቆይ፡ በግንቦት ወር ለምንድነው ሠርግ የማይደረገው? ምን ችግር አለው?አያቴ፡- እንዴት ያለ ጥያቄ ነው ልጄ? በግንቦት ለቦረንትቻ የሚታረድ ከብት እንጂ የልጃጋረድ ደም አይፈስም፡፡ ነዉር ነው!እኔ፡- አሃ! ደግሞ ቦረንትቻ ምንድነው?አያቴ፡- ቦረንትቻ ማለት የደም ግብር የሚገበርለት መንፈስ ነው፡፡ የደም ግብር ካላገቡለት ከብቱን ያጠፋል፤ እኽሉን ያጠፋል፤ ሀብቱን ያጠፋል፡፡
ዛሬ ላይ ቆሜ ይኽን የአያቴን ንግግር ሳስበውና አንዳንድ ሰዎች “ኢትዮጵያ ውስጥ ደም ሳይፈስ ፖለቲካዊ መሻሻል ሊመጣ አይችልም፡፡” ብለው የሚናገሩ ሰዎችን ስሰማ እነዚኽ “ደም ካላፈሰሳችኹልን ወይም ደማችኹን ካላፈሰስን ከሥልጣን አንወርድም፤ ወይም ወደ ሥልጣን አንመጣም፤” የሚሉ ሰዎች ቦረንትቻዎች ናቸው ማለት ነው?” ብዬ አስባለኹ፡፡ “መጠርጠር ደግ ነው!” ይባል የለ? ደግሞ ወሩ ግንቦት መኾኑ! ሆሆ ብዬ ላሽሟጥጥ እንጂ!