Wednesday, June 25, 2014

እኔና ወ/ሮ አስቴር ማሞ


የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትር ወ/ሮ አስቴር ማሞ፡- “Happy 8th Ethiopian Civil Service Anniversary”

እኔ፡- በሳቅ! እጅግ የተከበሩ ወይዘሮ አስቴር ማሞ ሆይ! የኛ (ይቅርታ፣ የእርስዎ መንግሥት) ሲቪል ሰርቪስ ሰዎችን በሥራ ብቃታቸው ሳይኾን በፖለቲካ ታማኝነታቸው እንደሚሾም ከራስዎ (እደግመዋለኹ፤ ከራስዎ) ተሞክሮ ያውቃሉ፡፡ እነዚኽ የፖለቲካ ታማኞች ተብለው የሚሾሙት ሰዎች ደግሞ ብዙውን ጊዜ ከዕውቀት የጾሙ፣ ጥቅማ ጥቅም በማሳደድ የተካኑ፣ በሙስና የተነከሩ እንደኾኑም አይዘነጉትም፡፡ የእርስዎ ድርጅት የሚሾማቸውም ይኽንኑ ሳያውቅ አይመስለኝም፡፡ ያኚ የሞቱት ሰውዬም ፓርቲው የሚለውን (በውስጠዘ ስንፈታው እርሳቸው የሚሉትን) የሚያደርግ እስከኾነ ድረስ የአራተኛ ክፍል ተማሪም ቢኾን ትምህርት ሚኒስትር አድርገው እንደሚሾሙ የዛሬ ምናምን በፊት በአደባባይ አርድተውናል፡፡ ያቺ የምናውቃት ማንትስዮ የምትባለው ዩኒቨርሲቲ የተከፈተችውም ለእንዲኽ ዓይነቶቹ አቆላማጮች (በእናቴ አማርኛ አንቋላጮች) ዲግሪ ለማደል መኾኑን አይዘነጉትም፡፡ ምነው ባያሾፉብን!

ወ/ሮ አስቴር፡- “Serving to beat poverty is a double honour”

እኔ፡- ዖኾሆኾሆኾሆኾሆኾሆኾ! (እንደሀብታም ልሳቅ እንጂ) እጅግ የተከበሩ ሚኒስትር ወይዘሮ አስቴር ማሞ ምነው ሀገራችን ኢትዮጵያ ከዓለም ኹለተኛዋ ፈርጀብዙ ድኽነት (multidimensional poverty) የተንሰራፋባት ሀገር እንደኾነች ከአንድ ሳምንት በፊት ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ያወጣውን መረጃ ዘነጉት እንዴ? ወይ ወ/ሮ አስቴር ማሞ! “to beat poverty” ይሉኛል? Let me remind you, የእርስዎ መንግሥት “ለሕዝቡ ጥቅም ሲል” ምናምን ብሎ ሥልጣን ላይ ከወጣ እነሆ 23 ዓመታት አለፉ፡፡ ነጻ ልናወጣችኹ መጣን ምናምን ምናምን ያሉን ሰዎች ራሳቸውን ከድኽነት ነጻ አወጡና እኛን ignore ገጩን፡፡ ለመኾኑ የእርስዎ መንግሥት ስለ ድኾች ግድ ይለዋል እንዴ? እውነት የእርስዎ መንግሥት ድኽነት እንዲጠፋ ይፈልጋል? የዕውቀት ጾመኞችን በየቦታው የሚሾምና እነዚኹኑ ሐሳበ ድንክ ሰዎች ፖሊሲ የሚያስረቅቅ መንግሥት ድኽነት እንዲጠፋ ይፈልጋል ብሎ ለማሰብ ቂል መኾን ይጠይቃል፡፡


ምን መሠለዎት፣ ድንኮቹ የሚያወጧቸው ፖሊሲዎች በቁመታቸው የተሰፉ ናቸው፡፡ ድንኮች ጥቅማቸውን አስጠብቀው ሥልጣናቸው ላይ የሚቆዩበትን መንገድ ለመፍጠር ከመታገል የሚዘል ሐሳብ የላቸውም! ለምሳሌ፣ ከድንኮቹ አንዱ በአንድ ወቅት በአንድ ዩኒቨርሲቲ “ተቀባይነት የለውም” (differ) ተብሎ የተጣለበትን የፒኤችዲ ጥናቱን የሀገሪቱ የምጣኔ ሀብት ፖሊሲ አድርጎ እንደቀረጸው ያስታውሳሉ፡፡ ያው የድንክ ነገር እንዲኹ ነው፡፡ ጉድጓድ ውስጥ ያለች ዕንቁራሪት የሰማዩ ስፋት ከጉድጓዱ አፍ የሚበልጥ አይመስላትም፡፡

እና እንዲኽ ሐሳበ ድንኮችን በሚያበረታታ ሥርዓት እንደሰት? አያሹፉብን፡፡ ይልቅ እርስዎና አጋሮችዎ ያው በእኛ ገንዘብ ድግስ ደግሱና በፈገግታ ተሞልታችኹ ቁርጥ ምናምን ስትበሉ፣ እስክስታ ስትወርዱ፣ ወዘተ. ፎቶ ተነሡና ፌስቡክ ላይ ለጥፉልን፡፡

በነገራችን ላይ፣ የመሥሪያ ቤትዎ ስም በእንግሊዘኛ በምሕጻረ ቃላት ሲጻፍ MOCS ነው፡፡ ሲነበብም “ሞክስ” ይኾናል፡፡ በእንግሊዘኛ ደግሞ ሞክ “Mock” ሹፈት ማለት ነው፡፡ ስለዚኽ መሥሪያ ቤትዎን አሹዋፊው መሥሪያ ቤት እንዳያሰኙ ኹለተኛ እንዲኽ ዓይነት መልእክት አይላኩልኝ? በይስማዕከ ግጥም ልሰናበትዎ፡-
ተላለፉ ሲለን
ከመረዋው ውግረት ከቃጭሉ ወይታ እኩል ብንሰማም
በአንድ የደወል ድምፅ ግለ ኅሊናችን አንድ ላይ ቢደቃም

                    ተላለፉ ሲለን ፊትና ኋላ እንጂ እኩል አንነቃም፡፡ (የወንድ ምጥ፣ 30)

Tuesday, June 10, 2014

ፈረንሳይኛ ዋጋው ስንት ነው?

የዚኽ ጽሑፍ መነሻው በአዲስ አበባ መስተዳድር ባሉ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የፈረንሳይኛ ትምህርት እንዲሰጥ መወሰኑን ከኹለት የዜና ምንጮች መስማቴ ነው፡፡ ከአንዳንድ ምንጮች እንደሰማኹት ደግሞ ፈረንሳይኛን በሀገሪቱ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ኹሉ እንዲሰራጭ የማድረግ ዕቅድ በመንግሥትና በኤምባሲው ተይዟል፡፡ እውነቱን ልንገራችኹና ዜናውን ስሰማ ልስቅ ቃጥቶኝ ነበር፡፡ ይኽን ውሳኔ የሰጡትን ሰዎችም የሚሠሩትን የማያውቁ የዋኀን፣ ወይም ለአንዳች ቡድናዊ ወይም ግላዊ ጥቅም ሲሉ የሀገር ሀብት ማባከን የማይገዳቸው ጨካኞች እንደኾኑ አድርጌ እንድመለከታቸውም አሳስቦኛል፡፡ ቀጥሎ የዚኽን ውሳኔ ስሕተትነት በዝርዝር ለመሞገት እሞክራለኹ፡፡  

የቋንቋ ትምህርትና ሀገራዊ ምጣኔ ሀብት
እንደኢትዮጵያ ባሉ ድኻ ሀገራት አንድን ቋንቋ በትምህርት ቤቶች ውስጥ ለማስተማር ቢያንስ ኹለት ዐበይት ምክንያቶች ያስፈልጋሉ፡፡ አንደኛ የቋንቋው ምጣኔ ሀብታዊ (ኢኮኖሚያዊ) ጠቀሜታ ነው፡፡ ማለትም፣ ቋንቋው በማኅበረሰቡ ውስጥና በማኅበረሰቡ አካባቢ ካሉ ሌሎች ጎረቤት ማኅበራተ ሰብ ጋር ለሚኖረው ምጣኔ ሀብታዊ መስተጋብር የሚጫወተው ሚና መታሰብ አለበት፡፡ በዚኽ ረገድ ፈረንሳይኛን ስንመዝነው በአፍሪቃ ቀንድ አካባቢ በሚደረግ የገበያ ልውውጥ እዚኽ ግባ የሚባል ስፍራ የለውም፡፡

በአንጻሩ፣ በቅርቡ የጋራ የንግድ ቀጠና ከመመሥረት አልፈው በአሥር ዓመታት ውስጥ በአንድ ገንዘብ ለመገበያየት ደፋ ቀና እያሉ የሚገኙት ኬንያ፣ ታንዛንያ፣ ኡጋንዳ፣ ሩዋንዳና ቡሩንዲ ኪስዋሒሊን በዐቢይ ልሳነ ምሥያጥነት (lingua franca) ይጠቀማሉ፡፡ የሀገራቱን የጋራ ግብይት በማሣለጥ ረገድ ቋንቋው ከፍ ያለ ሚና እንደሚጫወት ለማወቅ የማኅበራዊ ሥነ ልሳን ባለሙያ መኾንን አይጠይቅም፡፡ ስለዚኽም የምሥራቅ አፍሪካ አካል የኾነችው ኢትዮጵያ የዚኽ ገበያ ተጠቃሚ እንድትኾን ልጆቻችን ፈረንሳይኛ ሳይኾን ኪስዋሒሊን ቢማሩ ይሻላቸዋል፡፡ ለፈረንሳይኛ የምናወጣውን ገንዘብ ለኪስዋሒሊ ብናወጣው ቢያንስ ነገ እዚኽ ደጃፋችን ላይ እየተመሠረተ ካለው ገበያ እንደልብ መገበያየት የሚችል ሕዝብ እንዲኖረን ያደርጋል፡፡  

የአፍሪካውያንን ቋንቋ አንፈልግም አንፈልግም ከተባለም፣ ላለፉት 23 ዓመታት ሲቀነቀን በኖረው የዘውግ ፖለቲካ የተፈጠሩትን በልሳነ ዋሕድነታቸው (monolingual) የተነሣ ከክልላቸው ተሻግረው መሥራትም ኾነ መኖር እየተሳናቸው የመጡትን ወጣቶቻችንን በሀገሪቱ የትኛውም ስፍራ ተዘዋውረው እንዲሠሩ ለማስቻል ገናን የሀገሪቱን ቋንቋዎች እንዲማሩ ማድረግ ይገባል፡፡ ለፈረንሳይኛ የምናወጣውን ገንዘብ የሀገራችን ወጣቶች አፋቸውን ከፈቱበት ቋንቋ በተጨማሪ ሌላ ቋንቋ እንዲማሩ ብናደርግ  (ለምሳሌ፣ በአማርኛ አፉን የፈታውን ወጣት ኦሮምኛንና ትግርኛን፣ በሶማልኛ አፉን የፈታውን ወጣት ኦሮምኛን ወይም አማርኛን፣ ለአፋሯ ወጣት ኦሮምኛንና ትግርኛን፣ በኦሮምኛ አፉን የፈታውን ወጣት አማርኛና ወላይትኛ፣ በትግርኛ አፉን የፈታው አማርኛና አፋርኛ፣ ወዘተ.) ሀገሪቱ ወጣቶቿን በፈለገቻቸው ቦታ ኹሉ ለማሠማራት ትችላለች፡፡ ልጆቻችንም አባቶቻችን ሲያደርጉት እንደኖሩት እንደልባቸው በሀገሪቱ እየተዟዟሩ መገበያየት ይችላሉ፡፡ ባቢሎን ኾነንም አንቀርም፡፡ የሀገር ውስጥ ግብይቱን ለማፋጠንና ክልሎቻችንን ይበልጥ ሚዛናዊ በኾነ ምጣኔ ሀብት ለዘለቄታው ለማስተሣሠር ይኽ እጅግ በጣም አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡
  
የቋንቋ ትምህርት እና ሀገራዊ ጂኦፖለቲካ
ቋንቋዎችን በትምህርት ቤት ውስጥ በትምህርት ዓይነትነት ለማስተዋወቅ ከምጣኔ ሀብቱ ጉዳይ በተጨማሪ መታየት የሚገባው ዐቢይ ነጥብ የቋንቋው ፖለቲካዊ ፋይዳ ነው፡፡ ለምሳሌ፣ በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን ትምህርት ሀገራችን ውስጥ ድክድክ ማለት ሲጀምር የምዕራብ አውሮፓን ቋንቋዎች (ፈረንሳይኛ፣ ጣልያንኛ፣ እንግሊዘኛ) መማር ከፍ ያለ ስፍራ ነበራቸው፡፡ የዚኽም ምክንያቱ ዙሪያዋን እንደጥንብ አንሣ ከብበዋት ከነበሩት ቅኝ ገዢዎች ጋር መደራደር የሚችሉ፣ የቅኝ ገዢዎቹን ቋንቋዎች የሚያውቁ ዲፕሎማቶችን ለሀገሪቱ ማፍራት ማስፈለጉ ነበር፡፡

Monday, June 2, 2014

እስከዛሬ የጭቁኖች ድምፅ ነኝ ብዬ አስብ ነበር፡፡ ለካ የጭቁኖች ጦስ ነኝ፡፡

ወገን! ቀጥሎ የለጠፍኹትን ጽሑፍ እኔ እያነባኹ እንደሳቅኹበት እናንተም አንብባችኹና አንብታችኹ እንድትስቁልኝ ጀባ ብያችኃለኹ፡፡ ሙሉ ጽሑፉን አዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ ታገኙታላችኹ፡፡ ሀብቴና አዲስ ጉዳዮች ተባረኩ! (በቢላ አይደለም!) ዕድሜ ይስጣችኹ! (የሸቢ ሳይኾን የሥራ)




...

አጎቴ መቀጠል አልቻለም፡፡ ልማታዊ ንዴቱ ገታው፡፡ ሚስቴ ተራዋ ደረሰ፡፡
“ተው! ተው! የኔ ፍቅር፡፡”
“አንቺን ደግሞ ምን አደረግኹሽ?”
“ቤታችን በተንኳኳ ቁጥር ሊወስዱኽ መጡ እያልኹ በሥጋት ልሞት ነው፡፡ እንደምታየኝ ነፍሰጡር ነኝ፡፡ ዶክተሩ ከወራት በፊት መንታ ማርገዜን ነበር የነገረኝ፡፡ ትናንትና ስመረመር ግን “አንድ ብቻ ነው” አለኝ፡፡ እንዴት ብዬ ስጠይቀው “አንደኛው ወጥቼም ፍዳ ነው ብሎ ጠፍቷል” አለኝ፡፡ የኔ ቆንጆ፣ መንገድ ላይ ድሮ አስቁሜ እስማቸው የነበሩ ሕጻናት ሳይቀሩ ዛሬ ሲያዩኝ ከሩቁ ይሸሻሉ፡፡ አንዱን ባለፈው ጊዜ ይዤ ለምን ትሸሻለኽ ብለው “እና ከሰባ ዓመቴ ጀምሮ ቃሊቲ ልግባልሽ!” አለኝ፡፡ ተው፡፡ ተው፡፡ ሌላው ቢቀር ብዙ ምክሮችን ሰጥቼኽ አንዱን ምክር እንኳ ለመተግበር ፈቃደኛ አልኾንኽም፡፡”
“መጥተው የሚወስዱኽ ቀን አይታወቅምና ወፈር ያለ ቱታ ግዛ ብዬኽ ነበር እንቢ አልኸኝ፡፡ መቼም ካሰሯችኹ በኋላ ዱላ ስለማይቀርላችኹ እስከዚያው ሥጋ ለመደረብ ምግብ አብዝተኽ ብላ አልኹኽ፡፡ አልሰማኸኝም፡፡ አንጀት በልተኽ ታልፋቸው እንደኾነ አላውቅም፡፡ ይኼ አካልኽ እንኳን ዱላ ማሳጅ የሚችል አይመስለኝም፡፡ እሺ አልጋ ላይ መተኛቱን ትተኽ ወለል ላይ መተኛት ልመድ አላልኹም? አንተ ግን ቃሊቲ ሳይኾን ላንጋኖ እንደሚኼድ ሰው መዝናናት አብዝተኻል፡፡ ተው! ተው!...”
ለቅሶው ተጀመረ፡፡

እኔ ግን “ምክራችኹን ተቀብያለኹ የሚል ነገር ፊቴ ላይ አልተነበበም፡፡ እስከዛሬ የጭቁኖች ድምፅ ነኝ ብዬ አስብ ነበር፡፡ ለካ የጭቁኖች ጦስ ነኝ፡፡


ከረጅም ጸጥታ በኋላ እናቴ ለንግግር ቆረጠች፡፡
“የእኛ ቤት ሰው ሠላሳን አልፎ አያውቅም፡፡ ነፍሱን ይማረውና አባትኽ ደፋር ሰው ነበር፡፡ ክደቱ 45 በነበረበት ሰዓት ነው ለአየር ወለድነት የተመዘገበው፡፡ በአንድ የሥልጠና’ለት ከእሱ ክብደት በእጥፍ የሚልቅ ፓራሹት አዝሎ ከአውሮፕላን ዘለለ፡፡ ወደ ምድር አልተመለሰም፡፡ ከመዝለሉ በፊት አንዱ ጀነራል ላይ ምላሱን አውጥቶ ነበር አሉ፡፡ ዕድሜው ሠላሳ ነበር፡፡ ታላቅ ወንድምህም ደፋር ነው፡፡ ለመጨረሻ ጊዜ የታየው 97 ላይ የአንድ ተቃዋሚ ፓርቲ ቲሸርት ለብሶ ፓርላማ ምግብ ቤት ውስጥ ቦንቦሊኖ ሲበላ ነው፡፡ እሱም ሠላሳ ዓመቱ ነበረ፡፡ ይኸው አንተ ደግሞ መጣኽ፡፡ በጅብ ቅኝ ግዛጽ በተያዘች ሀገር ውስጥ አንበሳ ለመኾን ጣርኽ፡፡ የዛሬ ሳምንት ሠላሳ ዓመት ይሞላኻል፡፡ የፈራኹት ከመድረሱ በፊት ግን አባትኽና ወንድምኽ ያጡትን ነገር አንተ እንዳታጣ የነፍስ አባታችንን ጠርቻቸዋለኹ፡፡ ኹለቱም ከመጥፋታቸው በፊት ጸሎተ ፍትሐት አልተደረገላቸውም ነበር፡፡ እንግዲኽ አንተም የእርሱ ዕጣ እንዳይደርስብኽ አባ ቄሱ እባክዎ ኹላችንም ባለንበት የቁም ፍትሐት እንዲያደርሱልን ልለምነዎ!”
አጎቴም፣ ባለቤቴም፣ እናቴም የቁም ፍትሐቱን ሊቀበሉ ከተቀመጡበት ተነሡ፡፡ የነፍስ አባቴና እኔ ብቻ ተፋጥጠን ቆየን፡፡ የነፍስ አባቴ ከተቀመጡበት ተነሡ፡፡ ወደ በሩ አዘገሙ እያልጎመጎሙ፡፡

“ፍትሐቱንማ የጨረስኹት ጋዜጠኛ በጠፍ ጨረቃ በሚለቀምበት ዘመን ልጄ ጋዜጠኛ ነው ስትዪኝ ነው ወለተ ማርያም፡፡”  





ምንጭ፡- ሀብታሙ ሥዩም፡፡ "እሪ ብሎ መሳቅ፡፡" አዲስ ጉዳይ መጽሔት፡፡ ግንቦት 23፣ 2006 ፡፡