Wednesday, November 28, 2012

የውሎ ቅኝት ጸሎት


ባለፈው ጊዜ ቃል በገባኹት መሠረት እነሆ ቅዱስ አግናጥዮስ ካዳበራቸው የጸሎት ዓይነቶች አንዱን እንካፈል፡፡ ስያሜውን “የውሎ ቅኝት ጸሎት” ብንለው ያስማማል ብዬ አምናለኹ፡፡ ጸሎቱ አጭርና ቀላል ስለኾነ የትም ቦታ ኹነን የድርጊቶቻችንን መንፈሳዊነት ለመመርመርና በኃጢኣት ርቆ ከመጥፋት ለማምለጥ ጥሩ ራስን በእግዚአብሔር ዓይኖች የመፈተሻ (በዘመኑ ቋንቋ “የመገምገሚያ”) መሣሪያ ነው፡፡ 


“ለጸሎት ጊዜ ያጥረናል!” “ኑሮ እጅግ ቢዚ አድርጎኛል!” ለምንል ለብዙዎቻችን የገንዘብ ክፍለ ዘመን ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት የምናጎለብትበት፣ እኛ ለእርሱ "ጊዜ ባይኖረን" እንኳ ፈጽሞ ለእኛ ጊዜ የማያጣው አባታችን እግዚአብሔር በዕለት ኑሯችንና በገጠመኞቻችን ውስጥ ወደ እኛ ለሚልካቸው ጥሪዎቹ በመንፈስ ንቁ መኾንን የምናዳብርበት ቀላል የጸሎት ዓይነት ነው፡፡ ምንም እንኳ ጸሎተኛው ጸሎቱን ማድረግ እንዳለበት በተሰማው ጊዜ ኹሉ ማድረግ ቢችልም መደበኛ ጊዜው ግን የቀኑ ፍጻሜ ነው፡፡ ይህንን ጸሎት የሚያዘወትር ሰው ራሱን በጸሎት መንፈስ በየጊዜው የመቃኘቱን ነገር ይበልጥ እየለመደውና የሕይወቱ አካል እየኾነለት ይኼዳል፡፡ በዚህም የተነሣ ጸሎቱ ቀስበቀስ የጸሎተኛው አስተሳሰብ መንገድ ይኾንለታል፤ ማለትም በዚህች ቀን የሚገጥሙትንና የሚያከናውናቸውን ነገሮች ኹሉ በእግዚአብሔር ሚዛን ይመዝናቸዋል፡፡ በዚህም ከእግዚአብሔር ጋር ያለው ፍቅር እየጨመረ ይኼዳል፡፡ እግዚአብሔር የሕይወቱ ማዕከል፣ የህልውናው ምክንያት ስለሚኾንለት ፍጹም የተረጋጋ የምሥጋና ሕይወት ይመራል፡፡ ለሚተማመኑበት ልጆቹ ነገሮችን ኹሉ ለበጎ እንዲኾኑ በሚያደርጋቸው በእግዚአብሔር ላይ ፍጹም እምነት ስለሚኖረውም ነገ ምን ይዞ እንደሚመጣ ባያውቅም ነገ የሚባለው ቀን ራሱ በአባቱ በእግዚአብሔር እጅ የተያዘ እንደኾነ ስለሚያውቅ (ሮሜ 8፣ 28) አይሠጋም፡፡ አይፈራም፡፡ አይጠራጠርም፡፡ ይልቁንም እምነቱ እንደ ዕንባቆም
“ምንም እንኳ የበለስ ዛፍ ባያፈራ፣
ከወይን ተክልም ፍሬ ባይገኝ፣
የወይራም ዛፍ ፍሬ ባይሰጥ፣
ዕርሻዎችም ሰብል ባይሰጡ፣
የበጎች ጉረኖ እንኳ ባዶውን ቢቀር፣
ላሞችም በበረት ባይገኙ፣
እኔ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል፤
በአምላኬና በመድኃኒቴም ሐሤት አደርጋለኹ፡፡” (ዕን. 3፣ 17)
እያለ እንዲዘምር ይቀሰቅሰዋል፡፡ 


እግዚአብሔር ነገ የሚሠራውን በጎ ሥራ ለማየት ተስፋን ይመላዋል፡፡ ተስፋውም ደስታን ያጎናጽፈዋል፡፡ ይህም ፍቅርን እንዲያበራ ያስችለዋል- ሙሉ ልቡ በእግዚአብሔር ፍቅር ስለተያዘ ሌሎችን በጥቅመኛ ዓይን ዓይቶ ለመጥላት ጊዜ የለውምና፡፡ ሌሎችን በእግዚአብሔር ዓይን ስለሚያያቸው በፍቅር ያገለግላቸዋል፡፡ ፍቅር ባለበት ደግሞ ራሱ ፍቅር የኾነውና ዓለምን ከፍቅሩ ፈጥሮ፣ ከፍቅሩ መግቦ የሚያኖር እግዚአብሔር አለ፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ይኾናል፡፡ ይህም እምነቱን ይበልጥ ያበረታለታል፡፡ አሕዛብ ለነበርን ለእኛ ሐዋርያችን የሮሙ ሰማዕት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስስ “እምነት፣ ተስፋ፣ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፡፡ ፍቅር ግን ይበልጣል ከኹሉ፡፡” (1ኛ ቆሮ. 13፣ 13) አይደል ብሎ ያስተማረን?    

እርግጥ ነው ጸሎቱ ከ5- 15 ደቂቃዎች ሊወስድ ይችላል፡፡ ነገር ግን ዋናው ነጥብ የጊዜው ርዝማኔ ወይም እጥረት ሳይኾን የጸሎተኛው ራሱን በእግዚአብሔር መገኘት ውስጥ እንዳለ ማወቅና ለዚህ በኹሉ ቦታ ለሚገኘው (ምሉዕ በኵለሄ ለኾነው) ጌታ ራሱን በእምነት ሙሉ በሙሉ ከፍቶ በማቅረብ ለእርሱ ምሪትና ጥሪ በጎ ምላሽ መስጠቱ ዐቢይ ጉዳይ ኾኖ ይገኛል፡፡ ጸሎት ወደ እግዚአብሔር መድረስ እንጂ ለእግዚአብሔር የምሥጋና ምጽዋት ማድረስ አይደለምና፤ (ሎቱ ስብሐት! እርሱ በባሕርዩ ምሥጉን ነው! የሰው ምሥጋና ለእርሱነቱ የሚፈይድለት ነገር የለም፤ ለራሱ ለደካማው ሰው ይጠቅመዋል እንጂ፡፡)

ምንም እንኳ ጸሎተኛው ለእርሱ በተመቸው መንገድ ጸሎቱን የማደራጀትና የማከናወን መልኩ የተጠበቀ ቢኾንም ቅዱስ አግናጥዮስ ይህንን የውሎ ቅኝት ጸሎት በአምስት እርከኖች ያደራጀዋል፡፡ መሠረታዊው የጸሎቱ መርሕም “እግዚአብሔር ወደሚወስድህ ቦታ ዝም ብለህ ኺድ፡፡” የሚል ነው፡፡ ይህም የውሎ ቅኝት በራሱ ሐሳቦች የሚጠመድበት እንዳልኾነ ያሳያል፡፡ ይልቁንም ይህ የውሎ ቅኝት በተቀዳሚነት ጸሎተኛው ከእግዚአብሔር ጋር የሚኾንበት የጸሎት ጊዜ ነው፡፡

ቅዱስ አግናጥዮስ የሚጠቁማቸው አምስቱ የጸሎቱ እርከኖች የሚከተሉት ናቸው፡-

1.    በእግዚአብሔር መገኘት ውስጥ እንዳለህ አስብ፡፡ በሚወድድህ፣ በሚያበራልህና በሚመራህ እግዚአብሔር ፊት እንደኾንህ አስብ፡፡
በጸጋው በአንተ ውስጥ አድሮ የሚኖረውንና በአንተም ላይ በበጎነቱ ጥሪና ምሪት የሚሠራውን፣ ሊያቅፍህ እጆቹን ዘርግቶ በሚጠብቅህ እግዚአብሔር ዕቅፍ ውስጥ ዕረፍ፡፡ ዕረፍት ይሰማኽ፡፡
2.    ስለ ብዙ ስጦታዎቹ እግዚአብሔርን አመስግነው፡፡
በዚህ ቀን እንድታከናውናቸው ስለፈቀደልኽ ነገሮች፣ ከእርሱ ስለተቀበልኻቸው አስደሳችም ኾኑ አሳዛኝ ነገሮች፣ ስለቤተሰብህና ስለጓደኞችኽ፣ ስሕተትህን ስለተቹና ስለነቀፉኽ አራሚዎችኽ ኹሉ አመስግነው፡፡
3.    ይህን ቀን እንዴት እንዳሳለፍኸው መለስ ብለህ ተመልከት፡፡
ዛሬ ከራስህና ከሰዎች ጋር የነበሩኽ ግንኙነቶች እንዴት ነበሩ? እግዚአብሔር ባንተ ውስጥ እየሠራ የነበረው እንዴት ነበር? ምን ጠየቀህ? ለጥያቄውስ ምን ምላሽ ሰጠህ? ምላሽህ ማንን ማዕከል ያደረገ ነበር? አንተን ወይስ እርሱን? ሰዎቹ በአንተ ውስጥ እግዚአብሔርን አግኝተውት ነበር?
4.     ይቅርታ ጠይቅ፡፡ 
በችግርና በስቃይ ውስጥ ኾነው አይተሃቸው በደካማነትኽ እና በስንፍናህ ምክንያት ስላልደረስህላቸው ሰዎች፣ እግዚአብሔርን በሕይወትኽ ስላላሳየኽባቸው ቅጽበቶች ኹሉ ይቅርታ ጠይቅ፡፡ እጅግ የሚወድድኽ እግዚአብሔርን በሕይወትህ እያንዳንዷ ጥግጋት ኹሉ ስላልወደድኸው ይቅር እንዲልህ ምሕረትን ለምነው፡፡ “አባቴ ሆይ! ማረኝ!” በለው፡፡
5.    በተስፋ ኹነህም ለወደር የለሽ ፍቅሩና እጅግ ለምትመች ዕቅፉ ነገ ከዛሬው በተሻለ ለጥሪው ምላሽ ለመስጠት የሚያስችልኽን ጸጋ ታገኝ ዘንድ ጸልይ፡፡
ጌታ ሆይ! ደካማነቴን ዐውቃለሁ፤ በአንተ በጌታዬ ብርታትም እማመናለሁ፡፡ ለፍጥረት ኹሉ ብርሃን ኾኜ እንድኼድ የተጠራኹበትን የአንተን የሕይወት መንገድ ለመከተልም ዳግመኛ ቃል እገባለሁ፡፡ “ማንም በክርስቶስ ቢኖር አዲስ ፍጥረት ነው፡፡ አሮጌው አልፏል፡፡ እነሆ ኹሉ ነገር አዲስ ኾኗል፡፡” (2ኛ ቆሮ. 2፣ 17)   

አሁን ንባብዎን ጨርሰዋል፡፡ ቀጣዩ ክፍል መጸለይ ነው፡፡ ያለፉትን ጥቂት ሰዐታት መለስ ብለው ይፈትሹ፡፡ ፈላስፋው ሶቅራጥስ እንኳ “ያልተፈተሸ ሕይወት ሊኖሩት የሚገባ አይደለም፡፡” (An unexamined life is not worth living) ብሎ አልነበር? እስኪ ለአፍታ የልብ ምትዎን ወይም ትንፋሽዎን እየተከተሉ ሰ…ከ…ን… ይበሉና በዙርያዎ ያለው የእግዚአብሔር ዕቅፍ ይሰማዎት፡፡ 













ምንጮች
Jackson, Charles (S.J.). Ignatian spirituality.
Maloney, George (S.J.). In Jesus We Trust.
ያሬድ ዮሐንስ፡፡ መንፈሳዊ ብልጽግና ቁጥር 1፡ ጣዕመ ጸሎት፡፡

No comments:

Post a Comment