Friday, August 14, 2015

ጥቂት ስለጠባብነት






“ጠባብነት” (parochialism) ከ1960ዎቹ ጀምሮ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በተደጋጋሚ ከሚደመጡ ቃላት መካከል አንዱ ነው፡፡ ቃሉ ከቡድናቸው ጥቅም ባለፈ መመልከት የማይችሉ ኾነው የሚገኙ የፖለቲካ ቡድኖችን አቋም ያመለክታል፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በዚኽ አመለካከታቸው ብዙ ጊዜ ጣት የሚጠቆምባቸው ጎሣን መሠረት አድርገው የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ናቸው፡፡ 


የጠባብነት ሥነ ልቡና


ጠባብነት በተጠቃኹ ባይነት ላይ የሚመሠረት፣ እኔ ተበዳይ ሌላው ኹሉ በዳይ ነው የሚል፣ የእኔን ችግር መፍታት እንጂ የሌሎቹ ችግር ጉዳዬ አይደለም ብሎ የሚያምን አስተሳሰብ ነው፡፡ በሌሎች መጠቀምን እንጂ ከሌሎች ጋር አብሮ መጠቀምን ጉዳዬ አይልም፡፡ ጎሣን መሠረት አድርገው የሚነሡ ፓርቲዎች በአብዛኛው የዚኽ በሽታ ሰለባዎች ናቸው፡፡ የሚያሳዝነው ግን እነዚኽ ፖለቲካዊ ቡድኖች ሥልጣን ሲይዙ ጎሣዊ ማንነታቸውን እንደመከላከያ በመጠቀም የሥልጣን ተቀናቃኞቻቸውን ድራሻቸውን ያጠፉና “ሞትንልኽ! ቆሰልንልኽ! ምርጡ ሕዝባችን!” የሚሉትን ጎሣ በቁጥጥራቸው ሥር ያውሉታል፡፡ ነጻነቱን ይነጥቁታል፡፡ መነጠቁን እንዳያውቅ ለማድረግ አእምሮውን ይነሡታል፡፡

ሲሳካ በውድ ሳይሳካ በግድ ራሳቸውን የጎሣው እውነትና እምነት አድርገው ይተክላሉ፡፡ የጎሣውን የሻሩ ቁስሎችን ፈቅፍቆ በማድማት ላይ እንዲኹም ጎሣዊ ማንነትን የማንነት አልፋና ዖሜጋ አድርጎ በማቅረብ ላይ ያተኮረ ስብከት በማሰማት የጎሣውን ዐዲስ ትውልድ ማኅበራዊ ትውስታ (collective consciousness) ያዛባሉ፡፡ በዚኽም ሥልጣናቸውን ከፖለቲካዊነቱ ይልቅ የጎሣው ማንነት አካል አድርገው ያበጁታል፡፡ የጎሣው አባል ራሱን የሚመለከትበትም ኾነ ሌሎች ጎሣዎችን የሚያይበት አንግል በሥጋት (paranoia)፣ በተጠቂነት (victimhood) እና በበቀለኝነት መንፈስ የተበጀ እንዲኾን ያደርጉታል፡፡ ጎሣው ከእነርሱ ውጪ መድኅንና ቤዛ የሌለው አድርጎ እንዲያስብ ያደርጉታል፡፡ በዐጭሩ፣ ራሳቸውን በጎሣው ማኅበራዊ ትውስታ ውስጥ ዓምድ አድርገው ይተክላሉ፡፡ በጎሣው ዘንድ “እነርሱ ከሌሉ ምን ይውጠናል!” የሚል አስተሳሰብ ስላሠረፁ ምን ቢያጠፉ፣ ምን ቢበድሉ የእኛው ናቸው በሚል ፈሊጥ ጎሣው ሥልጣናቸውን መጠበቁን አይተውም፡፡ ይኽም ጎሣዊ የሥልጣን መሠረታቸው ሳይናወጥ ረዘም ላለ ጊዜ እንዲቆይ ያደርገዋል፡፡ ይኹን እንጂ፣ እነዚኽ ጎሣዊ ቡድኖች ከውጪ ሲታዩ ጎሣቸውን የሚጠቅሙ ይመስላሉ እንጂ ጎሣቸውን ቋሚ ተበዝባዣቸው ለማድረግ ቅንጣት ታኽል ወደኋላ አይሉም፡፡ ጎሣውን የሚፈልጉትም ቡድናዊ የጥቅም ቋታቸውን ለማስጠበቅ እንጂ ለሌላ ኾኖ አይገኝም፡፡ አስተያየቴን አንድ አአዩ የነበሩ ሰው ሲናገሩ በሰማኹት ዐረፍተ ነገር ላጠቃልል “ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ብሔር ተኮር ሥርዓት ማለት ኦሮሞው በኦሮምኛ፣ ተጋሩው በትግርኛ፣ አፋሩ በአፋርኛ፣ ሶማሌው በሶማልኛ ይገረፋል ማለት እንጂ ሌላ ትርጉም የለውም፡፡”