ስለኢትዮጵያ አብዮት ከተጻፈው ብዙና ካነበብኹት ጥቂት መካከል ቀጥሎ በፕሮፌሰር
ጌታቸው ኃይሌ ኦቶ ባዮግራፊ ውስጥ የሰፈረው፣ በብዙ ምክንያቶች፣ ስለከሸፉና ሀገራትን ከጭቆና ወደ ሌላ የባሰ ጭቆና ያዘቀጡ አብዮቶች
ከማስባቸው ነገሮች ጋር ስለተገጣጠመብኝ ላካፍላችኹ ወድጃለኹ፡፡ እነሆ!
...ዐመፁ ሲጀምር የአየር ኃል ሄሊኮፕተር ወረቀት ልትበትን አየር ላይ ስትታይ
የነበረኝ ደስታ ከመጠን በላይ ነበረ፤ የሚበተነው ወረቀት በኢትዮጵያ የኖረውን የፖለቲካ ጨለማ የሚገፍና ብርሃን የሚያጎናጽፍ እንጂ፣
ራሱ ተቀዳዶ የሚል መሆኑን የመገመት ዐቅም አልነበረኝም፡፡ ወታደሮቹ ያስሰሙት የነበረውን ዓይነት የጥሩምባ ሙዚቃ ዛሬ እንኳ ስሰማ
የሚቀሰቀስብኝ ስሜት ከመጀመሪያው ላይ የነበረኝ ተስፋ እንጂ፣ ወደኋላ የመጣብኝ ሐዘን አይደለም፡፡
አብዮቱ ሲጀምር የሚሆን የሚሆን የመሰለኝ መሆኑ ቀርቶ በኢትዮጵያ ላይ የደረሰ
ጹናሚ ሆነ፡፡ ጹናሚ ሲመጣ፣ ሊያድኑት የሚችሉትን ያህል ይዞ እግሬ አውጪኝ መሮጥ እንጂ፣ እኔን ያልፈኛል ማት ወይም በሰፌድ ለመመከት
መሞከር የጹናሚን ጠባይና ኃይል አለማወቅ ነው፡፡ የንጉሠ ነገሥቱ አገዛዝ ብዙ መሻሻል እንደሚያስፈልገው ማንም አይክድም፡፡ ግን
ጹናሚ መሬት ጭነቷ ከብዷት እንደሆን ጭነቷን ይቀንስላት ይሆናል እንጂ፣ የንጉሠ ነገሥቱን አገዛዝ ማሻሻያ አይሆንም፡፡ ጹናሚ የሚሻሻለውን
ከማይሻሻለው ስማይለይ፣ ሁሉንም ደፈቀው፡፡ ወታደሮቹና ተማሪዎቹ የሌለው ባለው ላይ እንዲዘምትበት አስተካክለው ሰጡት፡፡ መኪና
ያለው፣ እኔ መኪና ሳይኖረኝ አንተ ለምን መኪና? ይኖርሃል ተባለ፡፡ ቤት ያለው፣ እኔ ቤት ሳይኖረኝ አንተ ለምን ቤት ይኖሃል?
ተባለ፡፡ ርስት ያለው፣ እኔ ርስት ሳይኖኝ አንተ ለምን ይኖርሃል? ተባለ፡፡ የዩኒቨርሲቲ ዲግሪ ያለው፣ እኔ ዲግሪ ሳይኖኝ አንተ
ለምን ይኖርሃል? ተባለ፡፡ ቋንቋው የአስተዳደር ቋንቋ ያልሆነው የሆነውን ለምን እዲህ ይሆናል? አለ፡፡ ዓላማ የሌለውም እንዳለው
ይኑረው መሆን ሲገባው፣ ያለውም እንደሌለው አይኑረው ወደ ማለት ተለወጠ፡፡ ደኻው ያግኝ ማለት ቀርቶ ያልደኸየው ይደኽይ ሆነ፡፡
ሳይታሰብ ተጠራቅመው የጹናሚ ኃይል የሆኑት እነዚህ “ለምኖች” ቢዘረዝሩ ንጉሡ
በይበልጥ ባቀረቧቸው ባለሥልጣኖች ላይ የተነሡ ሌሎች ባለሥልጣኖች፣ የትምህርት ዕድል ያላገኙ ወጣቶች፣ ተምረው ሲጨርሱ ሥራ የማግኘት
ዕድል የማይታያቸው ተማሪዎች፣ ለሀገር የተሻለ ሕይወት የሚፈልጉ ሀገርና ወገን ወዳዶች፣ የሀገር ገንጣይ ቡድኖች፣ መንግሥቱን የያዙት
አማሮች ናቸው ባዮች፣ መንግሥቱን የያዙት የሸዋ አማሮች ናቸው ባዮች፣ መንግሥቱን የያዙት ክርስቲያኖች ናቸው ባዮች፣ ርስት የሌላቸው
ጪሰኞች፣ ጄኔራል ያልሆኑ ወታደሮች፣ “የኮንጎ ዘመቻ አበላችን ይሰጠን” የሚሉ ወታደሮች፣ የከተማ ቦታ ፈላጊዎች፣ የቀን ሠራተኞች፣
ዩኒቨርሲቲ መግባት ሲያቅታቸው ወታደርና ፖሊስ የሆኑ ወጣቶች፣ ወዘተ. ናቸው፡፡ የግል ቂም ያለውም አብዮቱን ተጠግቶ ቂሙን ተወጣ፡፡
አብዮቱን አራማጆች ድጋፍ ያገኙ መስሏቸው የነዚህን ሁሉ ፍላጎት አጋሉት፤ ሊያቀዘቅዙት ግን እደማይችሉ አልታያቸውም፡፡ በዚያ ጊዜ
የታያቸው ድጋፍ ማግኘታቸውን እንጂ፣ የየቡድኑ ጥያቄ እንዴት እንደሚመለስ አላሰቡበትም፡፡
… በሀገራችን የሰፈነው የፍትሕ መጓደል መታረም የሚገባው መሆኑ ባይካድም፣
አብዮቱን ያቅለበልቡት የነበሩ ዋና ኃይሎች ምቀኝነትና ቅናት መሆናቸው ለማንም ገለልተኛ አስተዋይ ድብቅ አልነበረም፤…
ምንጭ፡- ጌታቸው
ኃይሌ፡፡ አንዳፍታ ላውጋችሁ፤ በግል ሕይወቴ ከደረሰውና ካጋጠመኝ፡፡ አዲስ አበባ፣ ግራፊክስ አሳታሚዎች፣ 2006፡፡ (ገጽ
195- 197)