“የአዲስ አበባ የወንጀለኛ ምርመራ ክፍል የተመርማሪዎችን ጀርባና እግር
በመግረፍ ጥፋትን አለውድ በግድ የሚያሳምን፤ ጥፊና ስድብ የሞላበት፤ በማወናበድ ቃል የሚቀበልበት፡፡ እንደ ኦፔራሲዮን ክፍል የሰው
ሕይወት ማጉላሊያ መሣሪያዎች የሞሉበት፤ ከሰብአዊ ርኅራኄ ውጪ የሆነ ከፍተኛ ተግባር የሚፈጸምበት ክፍል ነው፡፡ ከዚህም በቀር የፈለጉትን
የሚያጠቁበት የባለሥልጣኖች መፎከሪያ ቤት ነው፡፡ ይህ መሥሪያ ቤት ለአንድ አገር ሕዝብ ከሚሰጠው አገልግሎት ይልቅ የሚፈጽመው ሕገወጥ
ተግባር የበዛበት በመሆኑ የሚወጣው የሥራ ማስኬጃ ገንዘብ የትም እንደጠፋ የሚቈጠር ነው፡፡ ለውስጥ እግርና ጀርባ መግረፊያ ጅራፍ፤
ከጩኸት የሚከላከል የማፈኛ ኳስ፤ ለእጅና ለእግር መጠፈሪያ ብረት፤ ለማንጠልጠያ መሰላል፤ ለነኝህ ለመደብደቢያ መሣሪያዎች የሚወጣው
በጀት መንግሥትን በገንዘብ በኩል ይጎዳዋል፡፡ በደል ባላደረሱትም ሰዎች ሕይወት ላይ በሚፈጸመው ድብደባ በሕግ ያስጠይቀዋል፡፡
የወንጀለኛ ምርመራ ክፍል በደል ይህ ብቻ አይደለም፡፡ የፍርድ ቤቶችን፤
ሐኪሞችን፤ ፖሊስ ጣቢያዎችንና የዐቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤቶችን በግዳጅ ሕገወጥ ድርጊት እንዲፈጽሙ የሚገፋፋ ነው፡፡ ይህንን ለመግለጥ
የተገደድኩት በእኔ ላይ የተፈጸመውን ግፍና እንደእኔም ባልፈጸሙት ወንጀል ድብደባና መጉላላት የደረሰባቸውን ሰዎች ጭምር መኖራቸውን
በማመን ነው”
ይህንን የገለጡት ያልወሰዱትን የአንድ ባለሥልጣን ገንዘብ ወስደሀል
ተብለው ያለውድ በግድ እንዲምኑ የተደረጉት የክብር ዘበኛ መምሪያ ሻምበል አዛዥ ሻለቃ አሥራት በነበሩ ናቸው፡፡ ሻለቃ በወንጀል
ምርመራው ክፍል ባለማቋረጥ በተፈጸመባቸው የድብደባ ወንጀልም ምክንያት ሞትን በመመኘት ባሉበት እስር ቤት ሆነው በተላከላቸው የምግብ
ሽፋን ታንቀው ሕይወታቸውን ለማሳለፍ ሞክረው ነበር፡፡ ነገር ግን በሰውነታቸው መዳከም ምክንያት ኃይል በማጣታቸው ከሞት መትረፋቸውን
ገልጠዋል፡፡
“የወንጀል ምርመራው ክፍል በእኔ ላይ መረጃ ባለማግኘቱ ተጨማሪ መሣሪያው
በሆነው በጠንቋይም ሊያስፈራራኝ ሞክሯል፡፡ እኔ ግን የምርመራ ዘዴውን ደካማነት ከመታዘብ በስተቀር በውሸት ቀንድ አውጥቶ ሰይጣን
መስሎ ለመጣው ሰው ፍንክች አላልኩም፡፡ እርግጥ የተዳከመውን ሰውነቴን በበለጠ ስላጉላላው ጎድቶኛል፡፡ ይህም ደግሞ ከጅራፉ ስላበለጠብኝ
ተመስገን ለማለት አስችሎኛል” ሲሉ ሻለቃ አሥራት ይናገራሉ፡፡
“በመጀመሪያው ቀን ማታ የስቃዬ የመጀመሪያ የሆነው ግርፋት ተጀመረብኝ፤
እጅና እግሬን አስረው ዘቀዘቁኝ፡፡ ዓይኔን ሸፈኑኝ፡፡ አፌ ውስጥ እንዳልጮህ ማፈኛ ኳስ ነገር አገቡብኝ፡፡ ከዚያ በኋላ ውስጥ እግሬን
ይገርፉኝ ጀመር፡፡ እንዲህ ያለው ኑሮ የሚተዳደሩትን ሰው ሲሰቃይ ደስ የሚላቸውን ኢየሱስ ክርስቶን የገረፉትን የአይሁዶችን ወንድሞች
በዓይኔ ለማየት ጓጉቼ ነበር፡፡ ነገር ግን እንዳላይ ሆንኩ፡፡ የአንደኛውን ቀን ግርፋት አዲስ በመሆኔ ተቋቋምኩት፡፡ እንደገና በማግሥቱ ከዚሁ ባላነሰ ግርፋት ተፈጸመብኝ፡፡ በዚህ ላይ በጌታ
እንዳፌዙት አይሁዶች ፌዛቸውና ስድባቸው አይጣል ነው፡፡ አሁንም የሦስተኛውን ቀን ግርፋት ለመቀበል ገባሁ፡፡ የቆሰለው እጄ ደም
የሚወርደው እግሬ ጠገግ ጠገግ ሳይል፡፡ “አውጣ፤ ተናገር” የሚለው የግርፋት ምርመራ ባለማቋረጥ ሊፈጸምብኝ ሲል መርማሪው መኰንን
“የሚገርፉ ሰዎች ችግር ስለሌለብን ዛሬ የሚገርፉህ ሌሎች ናቸው ስለዚህ እንድታውቀው” አለኝ፡፡ ግርፊያው ቀጠለ፡፡ ስታምን ምልክት
ስጥ ተብዬ ስለነበር፡፡ ገራፊዎቹ አዲሶች እኔግን ያው እኔ ስለሆንሁ ያላቋረጠው የሦስት ቀን ስቃይ ጠናብኝ፡፡ የሚፈልጉትን የውሸት
እውነት አመንኩ” ሲሉ ሻለቃ አሥራት የደረሰባቸውን መከራ ለመናዘዝ በቅተዋል፡፡
ሻለቃ ይህ ሁሉ ሊደርስባቸው የቻለው ለምንድነው? እንደሚከተለው ያብራራሉ፡፡
“ግንቦት 6 ቀን 63 ዓ/ም/ በጊዜው የነበሩት የክብር ዘበኛ ዋና አዛዥ ከጽ/ቤታቸው ሲሠሩ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ገደማ ላይ የግል
ገንዘባቸው የሆነው 21 ሺህ ብር ከካዝናቸው መጥፋቱን ጠርተው ነገሩኝ፡፡ እኔ የማውቀው ነገር የለም አልኳቸው “በምርመራ እንኳን
ይኸና ሌላም ከፍ ያለ ጉዳይ እንደሚገኝ አታውቅም?” አሉኝ፡፡ እርግጥ ይገኛል፤ ነገር ግን ያልተወሰደ ገንዘብ በታምር ይገኛል?
ብዬ ጥያቄያቸውን በጥያቄ መለስኩላቸው፡፡