ቀጥሎ ያቀረብኹላችኹ
ትናንትና ሌሊት የአማርኛ አስተማሪዬ በሕልሜ መጥተው ያስተማሩኝን ነው፡፡ ከተመቻችኹ ሕልሜን ፍቱልኝ፡፡ “ካልተመቻችኹ በሊማሊሞ
አቋርጡ” ያለው ማን ነበር? ሕልሙ እንዲኽ ነበር፡-
እንደምን አደራችኹ
ተማሪዎች፡፡
ደኅና እግዚአብሔር
ይመስገን መምህህህህህር፡፡
ቁጭ በሉ፡፡
እናመሰግናለን፡፡
አጥንቱን ልልቀመው መቃብር ቆፍሬ
ጐበናን ተሸዋ አሉላን ተትግሬ፣
ስመኝ አድሬያለኹ ትናንትና ዛሬ፣
ጐበናን ለጥይት አሉላን ለጭሬ፡፡
…
ተሰበሰቡና ተማማሉ ማላ፣
አሉላ ተትግሬ ጐበና (ከሸዋ)፣
አሉላ ሴት ልጁን ጥይት ሊያስተኩስ፣
አገሬ ተባብራ ታልረገጠች እርካብ፣
ነገራችን ኹሉ የእንቧይ ካብ፣ የእንቧይ ካብ፡፡
ልጆች፣ እነዚኽን ስንኞች ከዚኽ በፊት የኾነ ቦታ ሲነገሩ ሰምታችኹ ይኾናል፡፡ አፍላቂያቸውን ስንቶቻችኹ እንደምታስታውሱ ግን
እርግጠኛ አይደለኹም፡፡ አብሽር! ረኪና ሂንጅሩ! (ችግርየለም!) እኔ እነግራችኋለኹ፡፡ የእነዚኽ ውብ ስንኞች መፍለቂያቸው ዮፍታሔ
ንጉሤ ይባላል፤ በሀገራችን የቴአትር ጥበባት ነገር ሲነሣ ስማቸው በግንባር ቀደም ከሚጠራላቸው ሰዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ ይኽ
ሰው ጎጃም ደብረ ኤልያስ ከቄሰ ገበዝ ንጉሤ ተወልዶ፣ ንባብ ቆጥሮ፣ ዜማ ቀጽሎ፣ ቅኔ ተቀኝቷል፡፡ ገና በ19 ዓመቱ ገደማም “ቀኝ
ጌታ” ተብሏል፡፡ ከአባቱ ሞት በኋላ በገጠመው ማኅበራዊ ምስቅልቅል ወደ አዲስ አበባ ተሰድዶ መጣና እዚኽ ቀበና አቦ በድብትርና
አገልግሏል፡፡ ቀጥሎም በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት በአማርኛ መምህርነት ተቀጥሮ ይሠራ ነበር፡፡ ኋላም የቅዱስ ጊዮርጊስ ትምህርት
ቤት ዲሬክተር ኾኖ ሠርቷል፡፡ የምናብ እግሮቹ ወደ ቴአትሩ ዓለም ያመሩትም በዚኽ የመምህርነት ጊዜው ነው፡፡ ዮፍታሔ በ1920 ዓ.ም.
ገደማ የጀመረው የድርሰት ሥራ የአምስት ዓመቱ የፋሽት ወረራ እስኪመጣ ድረስ ይበልጥ እያበበና እየፈካ ኼዶ እንደነበር የሕይወት
ታሪኩን ያሰናዳው ዮሐንስ አድማሱ ይገልጣል፡፡ ዮፍታሔ የሀገር ፍቅር በእጅጉ ይሰማው የነበረ ሰው እንደኾነ ቴአትሮቹ ውስጥ ይስተዋል
ነበር፡፡ ከላይ በመግቢያነት የሰፈረችው ቅንጭብም ይኽንኑ የሀገር ፍቅሩን ሳትጠቁም አትቀርም የሚል ተስፋ አለኝ፡፡ ይኽንኑ ለማጽናት
አንድ ሌላ ቅንጭብ ብጨምርላችኹ አይከፋኝም፡፡ ፋሽስት ቀስ እያለ ኢትዮጵያን ቅኝ የመግዛት ዓላማውን ሊያሳካ ምሥራቅ ኢትዮጵያ ላይ
ሲያደባ አካኼዱን የታሰበው ዮፍታሔ (1928) እንዲኽ ብሎ ነበር፡-
ከአገር ዕድሜ ተርፎ የሚቀረው ዕድሜ፣
ሞተ-ነፍስ ይባላል ልናገር ደግሜ፡፡
የፈሰሰ ስንዴ ተርፎ ከስልቻ፣
ለጌታው አይደለም ለዐይጥ መጫወቻ፡፡
ወታደር ገበሬ መጠንቀቅኽ የታል፣
ፍልፈልም ይገፋል፤ ዐፈር ይጎልታል፡፡