በየሬድዮ ጣቢያው ላይ ብሔር፣ ብሔር፣ ብሔር፣ ብሔር… እየተባለ
የሚለፈለፍበት ሰሞን ስለኾነ ጥቂት “ስለብሔር” ጉዳይ አንድ ሰው ያጫወቱኝን ገጠመኛቸውን መሠረት አድርጌ፣ ትንሽ የእውነት ቅመም
ጨምሬበት ሐሳቤን ላካፍላችኹ እወድዳለኹ፡፡
አንድ ጉዳይ ይገጥማቸውና መታወቂያ ለማውጣት ቀበሌ ይኼዳሉ፡፡ ወንበሩ
ላይ የተሠየመው ሰው ቅጽ እየሞላ ጥያቄ መጠየቅ ይጀምራል፡፡
“ስም”
“እገሌ እገሌ”
“የአያት ስም”
“እገሌ”
“የተወለዱበት ዘመን”
ሰውየው ተናገሩ፡፡
“ብሔር”
ይኼኔ ሰውየው “የለኝም፡፡” አሉ፡፡
“እንዴት የለዎትም”
“አሃ! የለኝማ! የለኝም፡፡”
“ለምንድነው የማይኖርዎት”
“ኦሮምኛ፣ አማርኛ የምታቀላጥፈው እናቴ የተወለደችው ከኦሮሞ እናትና
ከጉራጌ አባት ነው፤ ግእዝ፣ አገውኛና አማርኛ የሚናገረው አባቴ ደግሞ እናቱ አገው ሲኾኑ አባቱ ደግሞ ጎንደር ተወልደው ያደጉ
የትግራይ ሰው ናቸው፡፡ እኔ የተወለድኹት ደብረ ዘይት፣ ያደግኹት አዲስ አበባ ሲኾን ሐረሪዎች ዘንድ ብዙ ዓመታት በመኖሬ አደሪኛ
እናገራለኹ፡፡ እና የእኔ ብሔር ምን ሊባል ነው?”