ፕሮፌሰር መስፍን ያኔ ልጅ እያሉ በወቅቱ የነበሩትን የትምህርት
ሚኒስትር “ለምን አስተማራችኹን” ብለው አፋጥጠዋቸው ነበር፡: አባባላቸው ኹልጊዜም የሚያሳስበኝን የማኅበረሰባችንን ነገር ዳግም
አስታወሰኝ፡፡ “ተማር፡፡” አሉኝ፡፡ ተማርኹ፡፡ “አንብብ ፤ማንበብ ጥሩ ነው፡፡” አሉኝ፤ የዐቅሜን ያኽል አነበብኹ፡፡ መማር የተሻለ
ደሞዝ እንደሚያመጣ እንጂ ተማሪውን እንደሚቀይር አላስተዋሉትም፡፡
መማር ማለት የኾነን ዕውቀት ወይም የምስክር ወረቀትን በባለቤትነት
መያዝ ሳይኾን ለእውነት ራስን ክፍት ማድረግና እውነት ሕይወትን እንድትመራ በነጻነት መፍቀድ መኾኑን አላሰቡትም፡፡ እነርሱ የታያቸው
በምስክር ወረቀቶች ብቻ የምበልጣቸው የእነርሱ ቅጂ ኾኜ እነርሱ ማድረግ ያልቻሉትን እንዳደርግ ነበር፡፡ ምን ያድርጉ- ልጃቸው አይደለኹ እንዴ! እኔ ምክራቸውን ተከትዬ ኼድኹ፡፡ እነርሱ ባሉበት ቆመው ቀሩ፡፡
(ማለቴ ላይፍ ቢዚ አደረገቻቸው፡፡)
በመንገዱ ላይ የቀትር ሐሩርን፣ የሌሊት ቁርን፣ የመጸው ነፋስን፣ የበጋ ሙቀትን፣ የበልግ
ወበቅን፣ የክረምት ቅዝቃዜን ከነጓዛቸው አገኘኹዋቸው፡፡ አቀበቶቹ አደከሙኝ፤ ቁልቁለቶቹ አዳፉኝ፤ ዛፎቹ አስጠለሉኝ፤ እሾኾቹም ቧጠጡኝ፤
ዕንቅፋቶቹም ጣቶቼን አቆሰሏቸው፡፡ ለምለሙን መስክ እንደልቤ ቦረቅኹበት፡፡ መልኬ ጠየመ፤ ቆዳዬ ሻከረ፤ መዳፌ ጠነከረ፤ ውስጥ እግሬ
ደደረ፤ ትከሻዬ ሰፋ፤ ድምፄ ለሰለሰ፤ ዓይኖቼ ርቆ ለማየት በረቱ፡፡
ከአድማሱ ወዲያ ያለውን ዓለም አየኹ፤ አምላኬ! ቤትኽ ለካ
እንዲኽ ሰፊ ናት! በርቀት ጠቁመው ያሳዩኝ አድማስ አጠገቡ ስደርስ አድማስነቱ አከተመ፡፡ ቀድሞውንም ለካ እነርሱ ከቆሙበት
ሲታይ እንጂ አድማስ አልነበረም፡፡ ያሳደጉኝ ሲነግሩኝ፣ ሲያስተምሩኝ፣ ሲመክሩኝ “ያ አድማስ የእኛ አድማስ ነው፡፡ አድማሱ የእውነት
ዓለም ድንበር ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ያለው ስፍራም ዘንዶው የሚጫወትበት የጥፋት፣ የሐሰትና የውንብድና ዓለም ነው” ብለውኝ ነበር፡፡
ኼድኹ- አድማሱ ጋ ለመድረስ፡፡ አድማሱ አጠገብ ስደርስ ግን አድማሱ ጠፋ፡፡ ድንበሩ የለም፡፡ ለካ የማየት ዐቅማችን እንጂ ድንበሩ
እውነት አይደለም፡፡ ገርሞኝ በሕጻንነት ንጽሕና “ድንበሩ የለም፡፡ ከፈለጋችኹ ኑና እዩ፡፡” ብዬ ነገርኋቸው፡፡ አልሰሙኝም፡፡ ርቀታችን
የትየለሌ! እንዴት እንደማመጥ፡፡ ማን ነበር “ጉድጓድ ውስጥ የምትኖር ዕንቁራሪት የሰማዩ ስፋት በጉድጓዱ አፍ ልክ ብቻ ይመስላታል”
ያለው? የትውልድ ሀገሬ ለካ ድንበር የላትም፡፡ ጌታ ሆይ! ቤትኽ እንዴት ሰ...ፍ...ፍ...ፍ...ፊ ናት፡፡ አቤት የግዛታችን
ስፋቱ! ይኼ ኹሉ የኛ ነው? ዘመዶቼ ይኽን ቢያውቁ ኖሮ ዓለም እንዲያ አትጠበብብባቸውም ነበር፡፡ መንገዱ ኮ ገና አላለቀም አይገርምም?!
ታድዬ! እንኳን ልጅኽ ኾንኹኝ!