Thursday, March 21, 2013

"ወንጌል ስማ፡፡" ለምትሉኝ


“ወንጌል” ምንድነው? አንድ ከኾነ የነገረ መለኮት ትምህርት ቤት የተመረቀ፣ ወይም የኾነ ማኅበር አባል የኾነ፣ ወይም ደግሞ የኾነ ነገር ሸምድዶ ዲያቆን ወይም ቄስ ወይም ፓስተር የተባለ ሰውዬ ቀሚስ ለብሶ ወይም ከረባት አድርጎ ወይም ዐውደ ምሕረት ላይ አልያም በቲቪ ቆሞ የሚያወራው ነገር ኹሉ ወንጌል ነው? ሰውየው “ወንጌል እሰብካለኹ!” ስላለ ብቻ ጌታ ኢየሱስ ከአብ ዘንድ ይዞልን የመጣውን የምሥራች እንደሚሰብክ በምን እርግጠኞች እንኾናለን? “ወንጌላዊ ነኝ!” “ሰባኬ ወንጌል ነኝ!” ስለተባለ ብቻስ ወንጌላዊ መኾን ይቻላልን? “ክርስቲያን ነኝ!” “ቤተክርስቲያን ነኝ!” ስለተባለ ብቻስ ቤተክርስቲያን መኾን ይቻላልን? የምንገነባው ካቴድራል ወይም የምንለብሰው ቀሚስ አልያም የምንጠቅሰው መጽሐፍ ቅዱስ አልያም የምንኮፈስበት ወንጌል-ጠቀስ ባህል ስላለንና በዓል "በድምቀት ስላከበርን" ክርስቲያን መኾን ይቻላል?  

ወንጌል ስንል የምሥራች ማለታችን ከኾነ ምን ስለኾንን ነው የምሥራች የሚያስፈልገን (ያስፈለገን)? ክርስትና “እንዲኽ ስላደረግኹ እንዲኽ ይሆንልኛል” ከሚል ተራ አስማትና ከሱፐርስቲሽን በምን ይለያል?

እዚህ ላይ በተለይ በየታክሲውና በየፖሉ ላይ ተለጥፎ የማየው “ታላቅ የፈውስና የምናምን ኮንፈረንስ” ወይም “ከእንዲኽ እንዲኽ ዓይነት በሽታ ፈውስ ወደሚገኝበት ታላቁ የምናምን ገዳም የሚደረግ ታላቅ ምናምናዊ ጉዞ!” እየተባለ የሚለጠፈው ማስታወቂያ፣ የቅቤ እምነት፣ የሎሚ እምነት እየተባለ የሚነገረው ነገር፣ እንትን ለሚባል በሽታ ይኽን ያኽል ሊትር ጠበል ጠጡ የሚባለው “የጠበላውያን ምክር”፣ “ታቦቱ አልንቀሳቀስ አለ!” እየተባለ የሚወራው ትርክት፣ እገሌ የተባለ ቦታ አዲስ ጠበል ፈለቀ፣ ተአምር ተደረገ እየተባለ የምንነጉደው ነገር፣ “የቁልቢው ተከተለኝ!” እየተባለ በየመኪናው ላይ የሚለጠፈው ማስታወቂያ (“እኔ የፈለግኹበት ስኼድ አንተ እየተከተልኽ ከዐቅሜ በላይ የኾኑ ችግሮችን እየፈታኽ፣ መና እያወረድኽ፣ ከአደጋ እየተከላከልኽ የዘበኝነት አገልግሎት ስጠኝ፡፡” ለማለት ይመሥላል፡፡) ወዘተ. በአስተዋይ ኅሊና ሊመረመሩ እንደሚገባቸው አምናለኹ፡፡ 

እዚኽ ላይ ፈውስ ለምን ተገኘ እያልኹ ወይም የቅዱሳንን ረድኤት እየተቃወምኹ አለመኾኔን ተረዱልኝ፡፡ እግዚአብሔር በወደደው መንገድ ይፈውሳል፡፡ እዚያ ላይ ተቃውሞ የለኝም፡፡ የእኔ ጉዳይ እግዚአብሔርን ተገማች (predictable) ያደረግንበት መንገድ እንዲመረመር መጋበዝ ነው፡፡ 

በእኔ እምነትና ዕውቀት Predictable የኾነ እግዚአብሔር ሰዎች በአምሣላቸው የፈጠሩት ዕግዜር እንጂ አማናዊው እግዚአብሔር አይደለም፡፡ ሊኾንም አይችልም፡፡ ቤተክርስቲያን የምኼደውና የምጸልየው እኔ የምፈልጋቸው ነገሮች በሙሉ ማለትም ጎጆዬ ወይም ግራ ጎኔ ወይም ትምህርቴ ወይም ምናምኔ እንዲሞሉ ብቻ ከኾነ እየፈለግኹ ያለኹት የአላዲን ፋኖስ ውስጥ ያለውን ጂኒ እንጂ እንዴት ድኾችንም ሀብታሞችንም የሚወድደውን እግዚአብሔርን ሊኾን ይችላል? 

ይቺ እግዚአብሔርን በእኛ ፎርሙላና ሐሳብ ለመለካት የመመኘት መንገድ ድሮ ድሮ በእነ ልፋፈ ጽድቅና በነዐውደ ነገሥት፣ በነፍካሬ ኢየሱስና በሞራ ገለጣ ትገለጥ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ዘመኑን ተከትላ ነቢዩ ኤልያስን  ከምድረ ፍልስጥኤም የነጠቀው ሠረገላ ከሦስት ሺህ ዓመት በኋላ ኢትዮጵያ አምጥቶ ጣለው በሚሉን ሰባክያነ ኤልያስ በጋዜጣና በገጸ ድር መጣች፡፡ 

ዛሬ ኤልያስ መጥቷል ተብለናል፤ ነገ ቴዎድሮስ መጥቷል እንባላለን፡፡ ስላላመንን ነገን እንፈራለን፤ ስለምንፈራም ከፍርኀታችን ለመላቀቅ ስንል ነገን ለመቆጣጠር እንፈልጋለን፡፡ ነገን ለመቆጣጠር ያለው አማራጭ ደግሞ ነገን ራሱን የሚያመጣውን ኃይል መቆጣጠር ይኾናል፡፡ በቁጥጥር ሥር ያዋሉት ነገር አይከብድማ፡፡ "ተማክረው የፈሱት ፈስ አይገማም፡፡" አይደል ተረታችንስ፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሔርን የነገ ዕቅድ ለማወቅ ተአምርና ትንቢት ስናሳድድ እንገኛለን፡፡ 

እግዚአብሔር ዓለሙን በሰው ልጆች በጥላቻ በየቀኑ እየተቸነከረ በፍቅሩ ከሚያስተዳድርበት መስቀሉ እንዲወርድ እንፈልጋለን፡፡ “እስኪ! እውነት አንተ እግዚአብሔር ከኾንኽ ከመስቀል ውረድ!” እንላለን፡፡ ከመስቀል ቢወርድ ምትሐት ነው ልንል፡፡ ሰማይ ከነ ግሡ ምድር ከነግሣንግሡ የእርሱ ተአምር ኾኖ እያየነው ማመን አቅቶን ሌላ ተአምር እንሻለን፡፡ ይህ ነው የእኛ ፎርሙላ፡፡ ይኽ ነው መፈለጊያችን፡፡ ጌታ ኢየሱስ ግን “ክፉና አመንዝራ ትውልድ ተአምር ይሻል፡፡” አለ፡፡   

Monday, March 18, 2013

ኹለቱ የኑሮ መርሖች


በዓለም ላይ ስኖር የቀረቡልኝ ኹለት አማራጭ የመኖሪያ መንገዶች አሉ፡፡ አንደኛው መሥመር መነሻው « እኔ » ነኝ፡፡ እኔን ተጠቃሚ ለማድረግ፣ የእኔን ፍላጎቶች ለማሟላትና አንድም ሳይሟላ የሚቀር ፍላጎት እንዳይኖረኝ ምኞቶቼን ኹሉ እውን ለማድረግ በሚደረግ ሩጫ ይጀመራል፡፡ የመነሻ መሥመሩ ሌላው መጠሪያ «የለኝም/ ይጎድለኛል» ይሰኛል፡፡

ሩጫው በዚኽ መሥመር ይጀመርና ፍላጎቶቼን ለማሟላት የሚያስችሉ የሚመስሉኝን ነገሮች ኹሉ ለመሰብሰብ እሮጣለኹ፡፡ አባርሬ እይዛለኹ፡፡ አሳድጄ እጨብጣለኹ፡፡ እሰበስባለኹ፤ እሰበስባለኹ፤ እሰበስባለኹ፡፡ በሰበሰብኋቸው ነገሮች ደስ ይለኛል፡፡ ግን ጥቂት እንደቆየኹ የሰበሰብኹት ነገር ኹሉ ይሰለቸኛል፡፡ ስለዚኽም ሌላ አዲስ ነገር ለመሰብሰብ ሩጫዬን እቀጥላለኹ፡፡ ደስታዬን ዘላቂ ለማድረግ ሰውንም፣ ፍጥረትንም በቁጥጥሬ ሥር ለማዋል እጥራለኹ፡፡ ምንም ነገር ከእኔ ቁጥጥር ውጪ እንዲኾን አልፈቅድም፡፡ ከቁጥጥሬ ውጪ ሊኾኑ የሚሞክሩ ነገሮች ቢኖሩ እንኳ ሲደክመኝ ወንበር እያቀረበ፣ ሲርበኝ መና እያወረደ፣ ሲጠማኝ ውኃ እያፈለቀ፣ ቀን ሐሩር እንዳይመታኝ በደመና፣ ሌሊት ጨለማ እንዳያስፈራኝ በእሳት ዓምድ እንዲመራኝ የምጠብቀው አምላክ አበጃለኹ፡፡

ይህ አምላኬም ጾሙን በቀበላና በፋሲካ እያጀብኹ እስከ ጾምኹለት፣ ለቤተ መቅደሱ አሥራት በኵራቱን እስከ ሰጠኹለት፣ ጠዋት ጠዋት እየተነሣኹ የውዳሴ ቀለቡን እስከሰፈርኹለት፣ በዓላቱን ሞቅ ደመቅ አድርጌ እስካከበርኹለት፣ ድረስ ከእኔ ጋር እንደሚኾን እርግጠኛ ነኝ፡፡ የምፈልገውን ኹሉ እንደሚያሟላልኝም እተማመናለኹ፡፡ እንዴ! የኔ አምላክ ነዋ! «አባቶቼ ያመለኩት!» እኔ እርሱ የሚፈልገውን አደርጋለኹ፤ እርሱ ደግሞ እኔ የምፈልገውን ኹሉ ያደርጋል፤ ወይም ይፈቅድልኛል፡፡ ታዲያስ! ሕይወት ሰጥቶ የመቀበል ገበያ አይደለች እንዴ!

Tuesday, March 5, 2013

እመርጣለኹ!


እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ከሰጠን ስጦታዎች አንዱ መምረጥ መቻላችን መኾኑን አምናለኹ፡፡ ምርጫችን ላይም ገደብ የለብንም፡፡ እንኳን የምናደርገውን የምናመልከውን ሳይቀር መምረጥ እንድንችል ነጻ ተለቅቀናል፡፡ ለምን ነጻ ተለቀቅን ለሚል ጥያቄ እኔ መልስ መስጠት እንደማልችል ከወዲሁ ልገልጽላችኹ እወድዳለኹ፡፡[i] ምክንያቱም ውብ አድርጎ ፈጥሮ ያቀረበልንን ዓለምን እንኳ ራስን ብቻ ማዕከል አድርጎ የመጓዝ አቅጣጫን በመምረጣችን ምክንያት እነሆ በሥቃይ እንቀቅላታለን፡፡ በሰው ልጅ የተነሣ እነሆ ፍጥረት ይሠቃያል፡፡ የፍጥረት አካል የኾነው የሰው ልጅም በዚህ በምርጫው ካመጣው ሥቃይ ተካፋይ ከመኾን አላመለጠም፡፡ የአብዛኛው ሥቃዮቻችን መነሻም ራሳችንን መውደዳችን ነው፡፡[ii]

“እኔ” የሚባል መሥዋዕት የማይጠግብ አምላክ ባሮች ነን፡፡ በርትራንድ ረሰል የሚባል ፈላስፋ “የሰውልጆች ኹሉ አምላክ መኾን እንሻለን፡፡ እርስበርስ እንዳንግባባ ያደረገንም ይኸው አምላክ የመኾን ጥማታችን ነው፡፡ ከሌሎች ሰዎች ጋር በምንነጋገርበት ጊዜ ኹሉ እኛ አምላክ ሌሎቹ ደግሞ አምላኪዎቻችን እንዲኾኑ እንሻለን፡፡”[iii] ይላል፡፡