የዛሬው ነገሬን የምወስደው ከ ዳኛቸው ወርቁ “አደፍርስ” ነው፡፡ ምናልባት መጽሐፉን የማታውቁ ሰዎች ካላችሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ከተጻፉት ምርጥ ልቦለዶች አንዱ ነው፡፡ የተጻፈበት ዘመን ትንሽ ራቅ ስለሚል (1962 ዓ.ም.) ለማግኘት በጣም አስቸጋሪ እንደሆነ ከወዲሁ ልጠቁማችሁ እወዳለሁ፡፡ ይሁንና እንደው በአንዳች ተአምር መጽሐፉ እጃችሁ ከገባ አደራ የከፈላችሁትን ከፍላችሁ ከመግዛት ወደኋላ እንዳትሉ፡፡ መጀመሪያ አይታችሁት የሚገፋተር ከመሰላችሁ እንዳትሸሹ አደራ፡፡
በነገራችን ላይ የቴዎድሮስ ገብሬን “በይነ- ዲሲፕሊናዊ የሥነ ጽሑፍ ንባብ” የሚለውን መጽሐፍ ብታነቡት አደፍርስን “በአንድምታ” ትረዱታላችሁ፡፡ በኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ጀርናል ላይ የታተመለትን “አደፍርስ ዘመናዊው ልቦለድ” የተሰኘውን መጣጥፉን ብታነቡም የበለጠ ታጣጥሙታላችሁ፡፡
ለዛሬ ወ/ሮ አሰጋሽ የሚባሉ ገጸ ባሕርይ ከሚናገሩት ንግግር እግዜርን እንዴት እንደሚበይኑት እንመልከት፡፡ እንደኔ እንደኔ ብዙ ሰው እግዚአብሔርን እንደ ወ/ሮ አሰጋሽ የሚመለከተው ይመስለኛል፡፡
“እግዜር ሩቁን የማያይ ይመስልሃል? ተሳስተሃል ወንድሜ፤ እግዚአብሔርን ርቀትና ቅርበት አይወስነውም፡፡ እግዚአብሔር እዚህ እዚያ እሁሉ ቦታ ነው- አሁን ከኛ ጋር ነው ስንነጋገር- ሁሉን ይሰማል- ሁሉን ያያል- ሁሉን ያውቃል፡፡ አዎ፣ አንዳንዴ የማያይ፣ የማይሰማ፣ የማያውቅ መስሎ መታየትን ይመርጣል፡፡ የበደሉትን ሰዎች እግር ተንበርክኮ ያጥባል- እንደፈለጋችሁ- እንደምላዳችሁ- እንደስሜታችሁ ኑሩ የሚል ይመስላል፣ ለብልኀቱ፡፡ አንድ ቀን የሱን ትልቅነት፣ የሱን ወሰን የለሽነት፣ የሱን አይመረመሬነት ዘንጋ ያልን ጊዜ ድራሻችንን ሊያጠፋ፡፡ ሊያመጣው ውርጅብኙን፡፡- ሥልጣናችሁን በሚገባ አልተጠቀማችሁበትም- ለክብሬ የሚገባኝን አላቀረባችሁልኝም- ከየምታገኙት ገንዘብ ጥቂት ጥቂት እያነሣችሁ- ጧፍ ዕጣን፣ ጋድና ሻማ፣ መገበሪያና ጃንጥላ በማቅረብ ፈንታ በሙሉ ተጫወታችሁበት- ጠጅ መሰርገቢያና በገሰቢያ አደረጋችሁት- ስለዚህ እኔም የምሠራውን አውቃለሁ ሊለን- መጠጡ ራሳችሁን እያብረጀረጀ ከሳንቃ ጉበን እንዲደስማችሁ፣ አንበጣ፣ አመዳይና ቸነፈር የምትበሉትን አሳጥተው ችጋር እንዲነዙባችሁ- ተጓባቢውን ጎረምሳ፣ ጥጋብ የነፋውን፣ በዱላ የሚጎላመደውን ዱለኛ፣ ለባለ ርስቱ ለባላባቱ የማይታዘዘውን ገበሬ፣ አንገቱን ሰብረው ጭራውን እንደውሻ እንዲሸጉብ እስኪያደርጉት ድረስ- ሊለን! ሊያመጣው የጭቃ ጅራፉን…” ይላሉ ወይዘሮ አሰጋሽ ለአንዱ ጭሰኛቸው-