ልክ የዛሬ 18 ዓመት በዚኽ ሰሞን ሚያዚያ 30፣ 1989 ዓ.ም. የ37 ዓመት ጎልማሳ የነበረው የኹለት ልጆች አባት አቶ አሰፋ ማሩ በፖሊሶች ከቤቱ ወደ ሥራው በመጓዝ ላይ እንዳለ ከጠዋቱ 2፡20 ጉድ ሼፐርድ አካባቢ ተገደለ፡፡
አሰፋ
እንዴት እንደተገደለ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (EXTRA-JUDICIAL KILLING. Special
Report No. 14 May 13, 1997) የዓይን እማኞችን ጠቅሶ እንዲኽ ይተርከዋል፡-
ጉድ
ሼፐርድ አካባቢ አቶ አሰፋ ዳገቱን ወጥቶ ሊጨርስ አካባቢ አንዲት ፒክአፕ መኪና መጥታ ከፊቱ መንገዱን ዘግታበት ቆመች፡፡ የመገናኛ
ሬድዮን የያዘውን ሰውዬ እና ሹፌሩን ሳይጨምር መኪናዋ ክላሽንኮቭ ጠብመንጃዎችንና የእጅ ቦምቦችን ወገባቸው ላይ የታጠቁ ስድስት
ፖሊሶችን ይዛ ነበር፡፡ አቶ አሰፋ ወደ ግንቡ ተጠግቶ መኪናዋን ለማለፍ ሞከረ፡፡ በዚኽ ጊዜ አቶ አሰፋን ከቅርብ ርቀት ስትከተለው
የነበረች ሌላ ኦፔል የፖሊስ መኪና የአደጋ ጥሪ እያሰማች ወደ እርሱ ቀረበች፡፡ ከኋላ ወንበር ላይ ተቀምጦ የነበረ ፖሊስም አውቶማቲክ
መሣሪያ አውጥቶ አሰፋ ላይ አከታትሎ ተኮሰበት፡፡ አቶ አሰፋም ወዲያው ነፍሱ ከሥጋው ተለየች፡፡
በፒክአፕ
መኪና ላይ ከነበሩትም ኾነ በኦፔሏ ውስጥ የነበሩት ፖሊሶች አቶ አሰፋን እንዲቆም አላዘዙትም፡፡ የማጠንቀቂያ ተኩስ ወደ ሰማይም
አልተኮሱም፡፡ ወይም ከመያዝ ለማምለጥ የሚሞክርን ሰው ከሩጫው ለመግታት እንደሚደረገው ወደ እግሮቹ አልተኮሱም፡፡ ይልቁንም የተተኮሱት
ጥይቶች በሙሉ የታለሙት ወደ ጭንቅላቱና ወደ ደረቱ ነበረ፡፡ አቶ አሰፋ ሲወድቅ ኦፔሏ መኪና መንገዷን ሳታቋርጥ ወደፊት ቀጠለች፡፡
በፒክ አፕ መኪናዋ ላይ የነበሩት ስድስት ፖሊሶች ግን ከፒክአፓቸው ላይ ወርደው መንገዱን ከላይም ከታችም ዘጉት፡፡ ከእነርሱ መካከል
የተወሰኑት የአቶ አሰፋን አስከሬን ኪሶች በረበሩ፤ የእጅ ቦርሳውንም ወሰዱ፡፡ ከዚኽ በኋላ ተጨማሪ አራት ፖሊሶች በላንድሮቨር የፖሊስ
መኪና ተጭነው መጡ፡፡ መኪናውም እነርሱን አራግፎ ተመለሰ፡፡
ጥቂት
ቆይቶም አስከሬን ለመጫን የሚያገለግል የፖሊስ መኪና መጥቶ የሟቹን አስከሬን አነሣ፤ በእንጦጦ አጠቃላይ ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት
ቤት (እንጦጦ ቴክኒክና ሙያ ማሠልጠኛ ኮሌጅ) በስተጀርባ አድርጎ ወደ ስድስት ኪሎ በረረ፡፡ አስሩ ፖሊሶችም በቶዮታ ፒክ አፕ መኪናዋ
ላይ ተጭነው የአስከሬን መኪናውን ተከተሉት፡፡ አቶ አሰፋ ከተገደለ ከ25 ደቂቃዎች በኋላ (8፡45) የመገናኛ ሬድዮዎችን የያዙ፣
አውቶማቲክ መሣሪያዎችንና የእጅ ቦምቦችን የታጠቁ ፖሊሶች አቶ አሰፋ ቤት በመኼድ የፍርድ ቤት የብርበራ ማዘዣ በማቅረብ የሟቹን
ቤት በረበሩ፡፡ በቤቱ ውስጥ ግን ከካሴቶች፣ ከኢሰመጉና ከኢመማ ሰነዶች ውጪ አንድም ያገኙት ጦር መሣሪያ አልነበረም፡፡ ወረቀቶቹንና
ካሴቶቹንም ወሰዷቸው፡፡ በተመሳሳይ ሰዓት በኢመማ ጽሕፈት ቤት 12 ፖሊሶች ደርሰው ነበር፡፡ እነዚኽ ፖሊሶች ግን የፍርድ ቤት የብርበራ
ማዘዣ አልነበራቸውም፡፡ ይኽ ግን የማኅበሩን ሠራተኞች ጨምሮ 34 ሰዎችን ከማሰር የሊቀመንበሩን የዶ/ር ታዬ ወልደ ሰማያትን ቢሮ
ከመበርበር አልከለከላቸውም፡፡
ከረፋዱ
4፡00 ሰዓት ገደማ የማይታወቅ ሰው ወደ ኢሰመጉ ቢሮ ስልክ በመደወል “አሰፋ ማሩ የሚባል ሰው ታውቁታላችኹ? የእናንተ አባል ነው?”
በማለት ጠየቀ፡፡ አዎንታዊ ምላሽ ሲያገኝም “አቶ አሰፋ በመኪና አደጋ ስላረፈ አስከሬኑን ከምኒልክ ሆስፒታል መጥታችኹ ውሰዱ፡፡”
የትና መቼ እንደሞተ እንዲናገር ሲጠየቅ ለመናገር ፈቃደኛ አልነበረም፤ ይልቁንም “ትፈልጉ እንደኾነ፣ አስከሬኑን ውሰዱና ቅበሩት፡፡”
በሚል ዐረፍተነገር ንግግሩን ቋጨው፡፡ የኢሰመጉ አባላት ወዲያው ወደ ምኒልክ ሆስፒታል በፍጥነት ኼዱ፡፡ ያገኙት ግን በመኪና የተገጨ
ሰው ሳይኾን ጭንቅላቱና ደረቱ በጥይት የተበሳሱ ፊቱ በደም አበላ የተሸፈነ፣ የሸሚዙ ደረት በደም የተነከረ የአሰፋ ማሩን አስከሬን
ነበር፡፡
እኩለ
ቀን ላይ የፌደራል ፖሊስ በሀገሪቱ የብዙኃን መገናኛ ተቋማት አሰፋ ማሩ የአርበኞች አንድነት ግንባር የሚባል “ፀረ-ሰላም ታጣቂ
ቡድን” አባል እንደነበርና “አልያዝም ብሎ በማስቸገሩ” እርምጃ እንደተወሰደበት ታወጀ፡፡ አሰፋ ግን የተባለው ቡድን አባል መኾኑን
የሚያረጋግጥ አንድም መረጃ አልቀረበም፡፡
አሰፋ ለምን ተገደለ?
አሰፋ
ከጅምሩ በኢሕአዴግ ጥርስ የተነከሰበት የአንጋፋው የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ሥራ ምክትል ሊቀ መንበር ነበር (ዋና ሊቀ መንበሩ
ዶ/ር ታዬ ወልደ ሰማያት ነበር)፡፡ ይኽ ማኅበር ደግሞ የተማሩና የሀገራቸው ዕጣ ፈንታ የሚያሳስባቸው ሰዎች የተሰባሰቡበት ተቋም
ስለነበር ኢሕአዴግ እንደልቡ ሊያዘው፣ ሊጠመዝዘው የሚችል ማኅበር አልነበረም፡፡ በተጨማሪም ኢሕአዴግ ገና አዲስ አበባ ከመግባቱ
ከአአዩ 42 መምህራንን ማባረሩን አስታውሱልኝ፡፡ ከእነዚኽ ተባራሪ መምህራን አንዱ የኢመማ ሊቀመንበር የነበረው ዶ/ር ታዬ ወልደ
ሰማያት ነበር፡፡
ከዚኽም
በተጨማሪ፣ አሰፋ ማሩ በየጊዜው በመንግሥት ኃይሎች የሚፈጸሙትን አስከፊ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የሚያጋልጠው የኢትዮጵያ ሰብአዊ
መብቶች ጉባኤ ሥራ አስፈጻሚ አባል ነበር፡፡ የጉባኤው ሥራ አስፈጻሚ ለመኾን አንዱ መስፈርት ደግሞ የምንም ዓይነት የፖለቲካ ድርጅት
አባል አለመኾን ነበር፡፡ እንኳን ብረት ያነሣ ቡድን አባል ይቅርና ሰላማዊ ትግልን የመረጠ የፖለቲካ ፓርቲ አባል የኾነ ሰው እንኳ
ለሥራ አስፈጻሚነት መመረጥ አይችልም፡፡ አሰፋም በጉባኤው ለሥራ አስፈጻሚነት ሲመረጥ የምንም ዓይነት የፖለቲካ ድርጅት አባል አለመኾኑን
አስረድቷል፤ ጉባኤውም ተቀብሎታል፡፡
አሰፋ
ንቁና የሀገሬ ጉዳይ ያገባኛል ባይ ነበረ፡፡ አገዛዙ ደግሞ ይኽቺ አልተመቸችውም፡፡ በግፍ የፈሰሰ የአቤል ደም!