Wednesday, February 26, 2014

ወፎቹ ሲሸሹ ነጻነት ፍለጋ... (When the Birds Fly Away you know that it is time for Dialogue)



ያን ጊዜ
እንደ ክፉ ምልኪ… ያስታውቃልቀኑ
የተራሮችና የኮረብቶች ፍጅት
በእልህ በቁጭት ቃል…ሲበጠስ መረኑ
ከአፋቸው ሲወጣ እንደሚነድ እሳት
ብርሃን አልባ ቀን… ሰማያት ሲጠቁሩ
ወፎቹ ሲሸሹ ነጻነት ፍለጋ
ሲመሽ ያስታውቃል… ያን ጊዜ ጠርጥሩ
ድምጻችኹ ሲታፈን ተስፋችኹ ሲላጋ
ውንጀላ ሲበዛ… መግባባት ሲጠፋ
መተንፈስ እንደ ዕዳ… እጅ ካሳበተ
ህልም ለሽልማት ለሹመት ሲጋፋ
ያ መጨረሻ ነው ምልክት ለእናንተ፡፡

የዚኽ ግጥም ወላጅ እናቱ መቅደስ ጀምበሩ ትባላለች፡፡ ሙጋ ከተሰኘው የግጥም መድበሏ ላይ ያሰፈረችውን ይኽን ግጥም ለዛሬ ቁዘማዬ መግቢያ ያደረግኹት ያለ ነገር አይደለም፣ በአካባቢዬ የማያቸው ምልክቶች የሚጠቁሙት ነገር ሳይኖር አይቀርም ብዬ እንጂ፡፡ ሰሞኑን አንድ ተመችቶት ይኖራል ብለን የምናስበው ወፍ ሸሽቶ አውሮጳ መግባቱ ሲሰማ ማኅበራዊ ገጾች ላይ ልዩ ልዩ አስተያየቶች ተነብበዋል፡፡ እኔ ግን አስተያየት ከመስጠት ይልቅ ጉዳዩን ይዤ ብቆዝም መረጥኹና በጉዳዩ ላይ ጥቂት አሰብኹበት፡፡ ከጥቂት ወዳጆቼ ጋርም ተወያየንበት፡፡ በጉዳዩ ላይ ካነጋገርኋቸው ወዳጆቼ መካከል አንዱም ፓይለቱን ሲወቅስ አላጋጠመኝም፡፡ ይልቁንም “እና ምን ያድርግ? እኛም መኼጃ አጥተን እንጂ የትም ብንኼድ ከዚኽ የተሻለ ሳንኖር አንቀርም፡፡ ወዘተ. ” እያሉ ነበር፡፡

Wednesday, February 12, 2014

ድኾችና ትምህርት በዋዲያ (The Poor (and) Education in Wadiya)


ያው እንደምታውቁት የዋዲያ የድኻ ልጆች የሚማሩባቸው ትምህርት ቤቶች“የመንግሥት” ትምህርት ቤቶች ይባላሉ፡፡ እነዚኽ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚማሩ (እንዲማሩ የተፈረደባቸው) ተማሪዎችም ሦስት ዋና ዋና ዕዳዎች አሉባቸው፡፡

አንደኛው ዕዳ
አንዲት የበሬ ግንባር የምታኽል ክፍል ውስጥ ቁናሙሉ ሙጫጭላዎች ተሞልተው “እንዲማሩ” ይደረጋሉ፡፡ እግር ጥሏችኹ ወደ እነዚኽ ትምህርት ቤቶች ስትገቡ አንድ ክፍል ውስጥ ከ140 ያላነሱ ዓይኖች ቢቁለጨለጩባችኹ እንዳትደነግጡ፡፡ የሚሌኒየሙን የልማት ግቦች በስታቲስቲክስ ሪፖርት ለማሟላት ሲባል የማይቧጠጥ ሰማይ፣ የማይፈነቀል ድንጋይ የለም፡፡ 

አንድ ክፍል ውስጥ ሰባና ሰማንያ ተማሪዎችን ከአንድ- እንደበግ እያገዳቸው ይኹን እንደተማሪ እያስተማራቸው ያልተገለጠለት የሚመስል- ከሢታ አስተማሪ ጋር ማየት የተለመደ ነው፡፡ አስተማሪው እየለፈለፈ እወንበር ሥር ገብተው ዕቃዕቃ የሚጫወቱ ልጆችም ቢያጋጥሟችኹ እንዳትስቁ፡፡ በትምህርት ቤቱ ግቢ ውስጥ የአምስት ዓመት ልጅ የሚያኽል በትር ይዞ የሚንጎራደድ አስተማሪ ቢታዩም አትሳቀቁ፣ ሰውየው ልጆቹን እንደ ጥጆች እንዲያግድ እንጂ እንደ ልጆች እንዲያስተምር አልታደለምና፡፡ ድሮስ “አንድ ለእናቱ” እንጂ “አንድ ለሰባና ሰማንያ” መቼ ተባለ?  

Thursday, February 6, 2014

የድኻ መነሻ ግሦች (The Etymology of The Poor)


“ድኻ” የሚለው ቃል የመጣው “ደኸየ” ከሚል ግሥ ሲኾን ትርጉሙንም የአለቃ ኪዳነ አበው መዝገበ ቃላት “አጣ፤ ነጣ፤ ፊቱ አመድ ነፋበት፤ ኪሱ ሸረሪት አደራበት፤ ምግቡ ሽሮ፣ ዕንቅልፉ የዶሮ ኾነ፤ ኑሮው መራራ፣ ዕዳው ተራራ ኾነ፤” ማለት እንደኾነ ያትታል፡፡ እንደሊቁ ገለጻ፣ ይኽ “ደኸየ” የተሰኘው ግሥ ደግሞ በበኩሉ ሥር መሠረቱ የግእዙ “ከየደ” ነው፡፡ “ከየደ” “ረገጠ፣ ረጋገጠ፣ ደፈጠጠ፣ ረመጠጠ” ተብሎ ይተረጎማል፤ የድኻን ተረጋጭ ተደፍጣጭነት ያመለክታል፡፡ 

በሌላ በኩል፣ ይኽ “ደኸየ” የሚለው ቃል ሌላ “ደወየ” ከሚል ቃል እንደሚነሣ የሚናገሩ ሊቃውንት አሉ፡፡ “ደወየ” ማለትም “ታመመ፤ ተሠቃየ፤ ቆዳው እንኩሮ፣ ጨጓራው ንፍሮ ኾነ፤ አጥንተ ሰባራ፣ አንገተ ቆልማማ ኾነ፤ ቀና ማለት፣ ስሙን መጥራት አቃተው፤ ምላሱ እንደ ተመታ እባብ ተጥመለመለ፣ አካላቱ እንደ ደረቀ ግንድ ተመለመለ” ማለት ነው፡፡ ሊቁ እዚኽ ላይ አያበቁም፡፡ ይልቁንም ይኽ “ደወየ” የሚለው ቃል ደግሞ መነሻ ቃሉ “ወደየ” የተሰኘው ሌላ የግእዝ ግሥ ነው ይላሉ፡፡ “ወደየ” ማለትም “ጨመረ፤ አከለ፤ ደበለ፤ ከተተ” ተብሎ ይፈታል፡፡ ይኽም ድኻ መከራው፣ ጌቶቹና ቁጥሩ ዕለት ዕለት እየጨመረ እንደሚኼድ ያሳያል፡፡ አንድም፣ ድኻ በዚያው መከራው በጨመረ መጠን ለጌቶቹ ያለው ታማኝነትና ታዛዥነት እየተጨመረ፣ እየተደበለ እንደሚመጣ ያሳያል፡፡