Thursday, June 13, 2013

የቤቲ ጉዳይ፤ ሦስቱ ዐዳዲስ የኢትዮጵያ አማልክት?


ባለፈው ሰሞን ሳልከፍተው የቆየኹትን የፌስ ቡክ ገጼን ስከፍት በርከት ያሉ ጽሑፎች “ቤቲ” የምትባል ወጣት (አንዳንዶቹ ወጣትነቷንም የሚራጠሩ ነበሩ፡፡) ስለሠራችው “ጉድ” (ብትሹ በእንግሊዘኛ ብትሹ በአማርኛ አንብቡት፡፡) የሚያትቱ፣ የሚሞግቱ ነበሩ፡፡ በርከት ያሉ ሰዎችም ድንጋጤያቸውን፣ ሐዘናቸውን ገልጸዋል፡፡ “ኢትዮጲያዊነታችን በዓለም አደባባይ ተዋረደ!” ብለው ተብከንክነዋል፡፡ ቪኦኤም፣ ዶቼ ቬሌም ጉዳዩን አነሣሥተውታል፡፡ የሬድዮ መርሐ ግብሮችም አብዝተው አራግበውታል (በተለይ ታድያስ አዲስ)፡፡ ብዙዎቹ መብከንከኖች ሲጨመቁ ዛላቸው አንድ ነው- “ቤቲ ኢትዮጵያን ወክላ በኼደችበት የቴሌቪዥን ትርኢት ውስጥ እንደ ውሾችና ድመቶች የዐደባባይ ሩካቤ ፈጽማ አዋረደችን፡፡ ድሮም ስማችን አላማረም፤ አኹን ደግሞ ይባስ ብላ ኢትዮጵያ የጋለሞቶች ሀገር አሰኘችን፡፡ ኢትዮጵያዊት መምህርት ኾና እንዴት እንዲኽ ባህላችንን ታረክሳለች?!” የሚል ቁጭት፡፡ 

ቁጭታቸውን ልረዳው ብሞክርም ድንጋጤያቸውን ግን ልረዳውም፣ ልካፈለውም አልቻልኹም፡፡ እንዲያውም አደረገች የተባለውን ነገር ስሰማ ውስጤ ፈጽሞ አልደነገጠም፡፡ ያልተጠበቀ ነገርም አልኾነብኝም፡፡ ለምን?

ተወደደም ተጠላም ልጅቱ የዚኽ ማኅበረሰብ ውጤት ናት- የሥጋችን ቁራጭ፣ የአጥንታችን ፍላጭ፡፡ ማኅበረሰብ ደግሞ ከዕለተ ልደታችን ጀምሮ በእንቅስቃሴዎቻችን ኹሉ አእምሯችንን በባህሉ እየቀረፀ የምንወድደውን እንድንወድድ፣ የምንጠላውን እንድንጠላ፣ የምናከብረውን እንድናከብር፣ የምንንቀውን እንድንንቅ አድርጎ ዳግም ይወልደናል፡፡ በመኾኑም “ቤቲ ኢትዮጵያዊት ናት፡፡” ሲባል ቤቲ ኢትዮጵያውያን ስለራሳቸው ማሰብ የሚሹትን መልካም መልካሙን ብቻ ይዛ የምታውለበልብ የባንዲራ ማማ ናት ማለት ሳይኾን የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ (ቢያንስ ያሳደጋት ከተሜው ኢትዮጵያዊ ማኅበረሰብ) አአምሮዋን በቀረፀበት መንገድ የምታስብ ፍጥረት ናት ማለት ነው፡፡

ጊርት ሆፍስቴድ የተባለ ሰው “ባህል የአእምሮ ሶፍትዌር ነው፡፡” ይላል፡፡ በሌላ አባባል የሰው ልጅ ሲወለድ ዐዲ ሐርድዌር ኾኖ ይወለድና ማኅበረሰቡ በአንድም በሌላም መንገድ የማኅበረሰቡ አባል የሚያደርገንን “ሶፍትዌር” ይጭንብንና በባህሉ ያጠምቀናል፡፡ ከልሙጥ ሰውነት ወደ ማኅበረሰቡ ልዩ አባልነት ዳግም ይወልደናል፡፡ ይኽን “ሶፍትዌሩንም” በየጊዜው “አፕዴት” ያደርገዋል፡፡

ብዙ ጊዜ “ባህል” ሲባል ነባርና የኾነ የጥንት ዘመን ላይ የነበሩ “ክቡራን አበው” የተፈጠረና “ሳይከለስ ሳይበረዝ” ኖሮ እኛ ዘንድ የደረሰ፣ እኛም ሳንበርዝና ሳንከልስ ወደ መጻኢው ትውልድ የምናስተላልፈው “ቅዱስ” ነገር ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ ይኽ ግን የባህልን ምንነት ካለማወቅ የሚሰጥ የጨዋ አስተያየት ነው፡፡ ባህል ማለት የአንድ በሕይወት ያለ ማኅበረሰብ የአኗኗር ዘይቤ እንጂ በሙዳይ የተቀመጠ ጨሌ ማለት አይደለም፡፡ የማኅበረሰቡ ሥርዓተ ዕሴት (value system) በተለዋወጠ ቁጥር ሲለዋወጥ የሚኖርና ሲለዋውጥ የሚያኖር እውነታ ነው፡፡ ለዚኽ ነው የቤቲ ድርጊት ያላስደነገጠኝ፡፡ በእኔ አመለካከት፣ ልጅቱ የኾንነውን እንጂ ያልኾንነውን አላሳየችንም፡፡ እዚኽ ላይ “እንዴት ብትደፍር ነው? ኢትዮጵያ የኩሩዎች፣ የደናግል (የእነ ፍቅር እስከመቃብሯ “ሰብለ ወንጌል”ና የአደፍርሷ “ጺወኔ”)፣ የሃይማኖተኞች ሀገር አይደለችምን!” ብሎ የሚቆጣ ሰው ይኖር ይኾናል፡፡

እርግጥ ነው ኢትዮጵያ እንደተባለው ኩሩዎች፣ ደናግል፣ ብሉይ ከሐዲስ አስተባብረው የሚያመልኩ ሃይማኖተኞች ኖረውባት ይኾናል- ድሮ፡፡ ዛሬ ግን ኢትዮጵያ (በተለይም ደግሞ እኔ የማውቃት ከተሜዋ ኢትዮጵያ) እነርሱ እንደሚሏት አይደለችም፤ ስትኾንም ዐይቻት አላውቅም፡፡ እኔ የማውቃት ኢትዮጵያ ለሦስት አማልክት የምታጥንና የምታፈነድድ እንጂ ባለ አንድ አምላክ አይደለችም ነው፡፡ እነሆ ሦስቱን አማልክት ልጠቁማችኹ፡፡