የገዛ ልጇ እከክ ኾኖ ጎን ጎኗን ሲያቃጥላት፣
መጥባቱን ሳትከለክለው እየነከሰ ሲያቆስላት፣
ወልዳ ያዘለችውን ተስገብግቦ ሲቦጭቃት::
እዩ...
"እሳት ወለደች!" በሉላት፤
በእንባ ሟሙ፤ አልቅሱላት፡፡
"ያድግልኛል፡፡" ብላ ቻለች፤
የልጅ ክፉ አደገባት፡፡
ደግሞ መጥምጦ መጥምጦ…
ወፍሮ፣ ቦካክቶ ቢያድግም፤
አልጠረቃም፡፡
ሆዱ ግን ገዝፎ ተሾልሹሎ፣
ውስጥ ኅሊናው ሰውነቱ በከርሥ ሰደድ ተቃጥሎ፣
በቃኝን ላያውቅ በቦርጩ ምሎ፡፡
እርሷ አቂማ፣ ውስጧ ቆስሎ፣ "እርሜ ነህ አንተ!" ብላ፣
የነፍሷን ጠላት ግና በኵሯን በአዲስ ልትተካው ፍሬ አዝላ-
በሆዷ፡፡
ወሯን ስትጠብቅ በተስፋ እየጠዘጠዛት ቁስሉ፣
የሚያጽናናት ማንም ሳይኖር የእርሷኑ እርም ሥጋ ከበኩሯ ጋራ እየበሉ...
የሚያጽናናት ማንም ሳይኖር የእርሷኑ እርም ሥጋ ከበኩሯ ጋራ እየበሉ...
ቀኗ ደርሶ ምጥ ስትጀምር ልትገላገል ከመከራ፣
ያው ጠላቷ፣ ደግሞም በኵሯ፣ የምጥ ሐሤቷን ሰምቶ እጅግ ፎከረ አቅራራ፡፡
“እኛ ያደግንበትን ሌላ ሊጠባው ከቶ?!
አሮጊቷም ልታገግም በሚያድግ ልጅ ገና ፋፍቶ!?
ሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃ...!"
ቁጣው ተቀጣጠለ፤
ተወራጨ፤
ተበሳጨ፤
ሰማይ ቧጥጦ መሬት ነጨ፡፡
አላበቃም…
የጨቅላውን አናት ለመፈጥፈጥ የእናቱን ሆድ ረገጠ፤
የእምዬን ልጅ ወንድሙን ከሽርት ውኃው አፈረጠ፤
እናትየውም ደም መታት ጨቅላውም ልጅ ጨነገፈ፡፡
ሸሽታ ስትሰደድ...
በየጎዳናው፣
በየጥጉ፣
በየውቅያኖስ፣
በየደኑ፣
በየሻርኩ ሆድ፣
በየሻርኩ ሆድ፣
በየአሞራው ከርሥ፣
የበረኀው፣
በየጓዳው፣
በየገንዳው...
የተረጨ፣
የፈሰሰ፣
የተቀዳ፣
የተጠጣ፣
የተደፋ
ደሟን ዐይተው ጎረቤቶቿ ተሳቀቁ፤
አንዳንዶቹም ተሳለቁ፡፡
እንዲህም ብለው በጋራ ሕመምተኛይቱን አሟት፡-
“ሴሎቿ እርስ በርሳቸው የሚባሉባት ይህቺ ሴት፣
ምንም ጥርጥር የለውም የልጅ ሾተላይ
አለባት፡፡”
(መቼ ትድን ይኾን? )
(መቼ ትድን ይኾን? )