Monday, December 12, 2011

St. Francis de Sales



ሰሞኑን አንድ በአስራ ሰባተኛው  ክፍለ ዘመን የተጻፈ መጽሐፍ እያነበብሁ ነበር፡፡ ጸሐፊው ቅዱስ ፍራንሷ ደ ሳል[i] ይባላል፡፡ የጄኔቫ ጳጳስ እንደነበረ የሕይወት ታሪኩ ያስረዳል፡፡ የመጽሐፉ ርእስ “Introduction to the Devout Life”[ii] ነው፡፡ ክርስቲያን የሆነ ሰው ሁሉ ሊያነበው እንደሚገባም አምናለሁ፡፡ ምንም እንኳ ራሱ ቅዱስ ፍራንሷ በትሕትና መጽሐፉን የጻፍሁት በዓለም ላሉ ሰዎች ነው[iii] ቢልም መጽሐፉ የያዘው በመንፈሳዊነት፣ በንባብና በልምድ ከታሸ ዕውቀት የሚፈልቅ ምክር ስለሆነ በእግዚአብሔር ምሕረት ያገኘውን የክርስቲያንነት ጸጋ ለሚያከብር ሰው ሁሉ እጅግ ጠቃሚ እንደሆነ አምናለሁ፡፡[iv]

መጽሐፉ ከኃጢአት እስከ ንስሐ፣ ከንስሐም እስከ ቅድስናን ጠብቆ መኖር ያለውን የክርስትና ጉዞ ያስተዋውቃል፡፡ ፈተናዎቹን በዝርዝር ያሳያል፡፡ ለምሳሌ አንዳንዶቻችን ከእግዚአብሔር ጋር ለመኖርና ኃጢአትን እርግፍ አድርገን ለመተው መቁረጥ ብዙም አያስቸግረንም፡፡ እንዲያውም ውሳኔያችን እንደሚያመጣልን የምናስበውን ቅድስና ለማግኘት እጅግ እንጣደፋለን፡፡ ልባችን ስቅል ይላል፡፡ እንጓጓለን፡፡

ነገር ግን እንደምታውቁት የቅድስናን ጉዞ አልጋ በአልጋ ሆኖ አያውቅምና ጥቂት ስንቆይ የኃጢአቶቻችን አጥፊ ጣዕም ይናፍቀን ይጀምራል፡፡ ጉዟችንን ስንጀምረው የነበረን መንፈሳዊነት ግለትም ይቀዘቅዝብናል፡፡ ይሄኔ የተውናት ዓለም በዓይነ ኅሊናችን ፊት ውል ማለት ትጀምራለች፤ ጠረኗ ይሸተን ይጀምራል፡፡ የጠላነው ሥጋዊ ምኞት ሊያባብለን ይሞክራል፡፡ ለመራቅ እንሞክራለን ግን የትናንቱ ዓለማችን ትዝታ በጆሯችን፣ በዓይናችን በትዝታችን ውስጥ እያደባ እንደጥላ ይከተለናል፡፡ ጸሎታችን ሰሚ ያለው አልመስል ይለናል፡፡ የጓጓንለት ቅድስና እንደሰማይ የራቀ ሆኖ ይሰማናል፡፡ መድረስ የሚቻልም አይመስለንም፡፡ ራሳችንን መጠየፍ እንጀምራለን፡፡ እንበሳጫለን[v]፡፡ ከፈተናዎቹ ጥንካሬ የተነሣም ይሁን በደካማነታችን ምክንያት አንዳንዶቻችን ከእግዚአብሔር ጋር ለመኖር የወሰንነውን ውሳኔ ትክክለኝነትም እንጠራጠራለን፡፡ ሲብስም “በቃ! ለእኔ አልተሰጠኝም ማለት ነው፡፡” ብለን በቶሎ ከጀመርነው የቅድስና ጉዞ እናፈገፍጋለን፡፡ መፍትሔው ምን ይሆን?

ቅዱስ ፍራንሷ “የችግሩን ምንጭ ማግኘት የመፍትሔውን ግማሽ ማወቅ ነው፡፡” በማለት በቅድሚያ የችግሩን ምንጭ ያሳየናል፡፡ እንደርሱ አባባል የችግሩ መነሻ ያለው አነሣሣችን ላይ ነው፡፡ “እንዴ! ደግሞ በቅድስና ለመኖር በጉጉት መነሣት ምን ችግር አለው?” ብለን ልንጠይቅ እንችላለን፡፡ ነገር ግን መነሣቱ አይደለም ችግሩ ይልቁንም መጓጓታችን ነው፡፡ በጉዟችን መጀመሪያ ላይ ለመጓዝ መነሣት እንጂ ለፍጻሜው መጓጓት አልነበረብንም፡፡ ሁሉም በጊዜው ይደርሳልና እግዚአብሔር ያልሰጣችሁን ጸጋ ከመመኘት ራቁ ይላል፡፡ ይልቁንም በተሰጠን ጸጋ እንደአቅማችን በልክ ለመኖር እንድንጥር ይነግረናል፡፡

ጸሎት ሰልችቷችሁ ያውቃል? ያን ጊዜ ምን ታደርጋላችሁ?
አንዳንዶቻችን “ልቤ የማይነካበትና ከልቤ የሚፈልቅ የማይመስለኝን ጸሎት ለአምላኬ እንዴት ብዬ አቀርባለሁ?” ብለን መጸለዩን እርግፍ አድርገን እንተወዋለን፡፡ ሌሎቻችንም ሙሉ በሙሉ ባንተወውም እንኳ ልባችን ይሰንፍብናል፡፡ ምን ይሻላል? ቅዱስ ፍራንሷ መልስ አለው፡፡

ጸሎታችን ለእኛ ደረቅ ቢሆንብንም ሰው እውነተኛ ወዳጁ ቤቱ ሲመጣበት ያለውን እንደሚያቀርብ፣ እንግዳውም የቀረበውን ነገር ትንሽነት ሳይሆን ያቀረበውን ታዛዥና አፍቃሪ ልብ እንደሚመለከት፣ ስለፍቅርም ብሎ የቀረበለትን በደስታ እንደሚቀበል ሁሉ ደካማነታችንን የሚያውቅ እግዚአብሔርም ጸሎታችንን እንደማይተውብን ያሳስበናል፡፡ በትዕግስት ከጠበቅንም የመንፈሳዊነት ድርቅ ያጠቃውን እኛነታችንን በጸጋው ዝናብ ዳግም ያረሰርሰዋል ይለናል፡፡[vi]
በትዕግስት ጠብቀው በዝምታ
ዘንበል ይላል ጌታ፡፡” (አንድ ኢትዮጵያዊ ዘማሪ)


በሌላም በኩል ይህ የመንፈሳዊነት በረኃ እግዚአብሔር ለእኛ ለልጆቹ ዕድገት የሚያዘጋጀው የጉዞው አካል ነው- እንደ ቅዱስ ፍራንሷ አባባል፡፡ እናት ለሕጻን ልጇ ጣፋጭ ነገር ስትሰጠው ያቅፋታል ይስማታል፡፡ ነገር ግን መሳሙ በጣፋጩ የተነሣ የመጣ ይሁን በእናትነቷ እዚህ ላይ ማወቅ አንችልም፡፡ ነገ መራራ ነገር ብትሰጠው እንደሚስማት እርግጠኛ መሆንም ከባድ ነው፡፡ ይህንን ለማረጋገጥም ሆነ ልጁን በእናትነት ፍቅሯ ለማበልጸግ ልጁ ያለ ጣፋጭ እናቱን እንዲያገኝ ማድረግ ይገባል፡፡ በዚህም እናቱን ለእናትነቷ ሲል ማፍቀርንም ይማራል[vii]፡፡ እግዚአብሔርም ጸጋው በእኛ ላይ እንዳለች እንድናውቅና ተጠንቅቀንም እንድንይዛት አንዳንዴ ጸጋውን ከእኛ ይሰውራል፡፡ ቅዱስ ዳዊት “ደለወኒ ዘአሕመምከኒ” (ያስጨነቅኸኝ ለመልካም ሆነልኝ፡፡) (መዝ 118፡ 71) እንዳለው፡፡ 

ስለ ፈተና ዓይነቶች፣ ስለ ፈተናና ኃጢአት ተዛምዶ፣ ፈተናን እንዴት ማራቅ እንደሚገባ፣ በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ ፈተናን እንዴት ማለፍ እንደሚቻል ይተነትናል፡፡ ለምሳሌ ቀጥሎ ያለውን የሲየናዋን ቅድስት ካተሪን ተጋድሎ እንዲህ አቅርቦታል (አራተኛ ክፍል ምዕራፍ አራት)፡-

ሰይጣን የዚህችን ድንግል ንጽሕና ይፈታተን ዘንድ እግዚአብሔር ፈቀደለት፤ ነገር ግን አካሏን በምንም ዓይነት መልኩ እንዳይነካት ከለከለው፡፡ በዚህም የተነሣ ዲያብሎስ ርኩሳን የሆኑ ምክሮችን ለልቧ ያቀርብ ጀመር፡፡ ከአጋሮቹ ጋር በመሆንም በወንድና በሴት አምሳል እየቀረበ እጅግ አጸያፊ የሆኑ ድርጊቶችን አሳያት፡፡ እጅግ የረከሱ ንግግሮችንም አሰማት፡፡ እነዚህ ሁሉ ነገሮችም ምንም እንኳ የሚከናወኑት ከእርሷ ውጪ ቢሆንም በስሜት ሕዋሳቶቿ በኩል ወደ ልቧ ጠልቀው ገቡ፡፡ ራሷ በኑዛዜዋ እንደ ገለጠችውም ልቧ በእነርሱ ተመላ፡፡ ነገር ግን የነፍሷን ፈቃድ ለዚህ ርኵሰትና ሥጋዊ እርካታ አሳልፋ አልሰጠችም፡፡ ይህ ፈተና ጌታችን ወደ እርሷ እስከመጣበት ቀን ድረስ ለረጅም ጊዜ አብሯት ቆየ፡፡ ጌታችን በታያት ጊዜም
“ውዱ ጌታዬ ሆይ! ልቤ በጨለማና በርኵሰት ሲሞላ የት ነበርህ?” በማለት ጠየቀችው፡፡
እርሱም “ልብሽ ውስጥ ነበርሁ ልጄ፡፡” ሲል መለሰላት፡፡
እርሷም መልሳ “በርኵሰት በተመላው ልቤ ውስጥ እንዴት ልታድር ቻልህ? እንደዚህ ንጹሕ ባልሆኑ ስፍራዎች ውስጥ ትገኛለህ ማለት ነውን?” አለች፡፡
ጌታም “እስኪ ንገሪኝ፤ የልብሽ ክፉ ሐሳቦች እርካታን ሰጡሽ ወይስ ሐዘንን አመጡብሽ? መራርነትን አፈለቁብሽ ወይስ ደስታን አቀበሉሽ?” ሲል ጠየቃት፡፡
“እጅግ ከባድ መራርነትና ሐዘን” ብላ መለሰች፡፡      
እርሱም፡- “ይህንን ሐዘንና መራርነት ማን የፈጠረው ይመስልሻል? በመንፈስሽ ጥልቅ ውስጥ ተሰውሬ የነበርሁት እኔ ነኝ፡፡ እመኚኝ ልጄ፤ እኔ ባልኖር ኖሮ እነዚህ ፈቃድሽን የከበቡ ነገር ግን ሊረቱት ያልቻሉ ሐሳቦች ባሸነፉሽና ወደ ውስጥ በዘለቁ፣ ፈቃድሽም በተቀበላቸውና ለነፍስሽም ሞትን ባስከተሉባት ነበር፡፡ ነገር ግን እኔ ውስጥ ስለነበርሁ ጥላቻውንና መቋቋሙን ፈጠርሁልሽ፡፡ በዚህም ልብሽ ፈተናውን በሙሉ ዐቅሙ እንዲከላከል አስቻልሁት፡፡ ነገር ግን መከላከል የሚፈልገውን ያህል አልተከላከለምና አሁንም ፈተናውንና ራሱን በእጅጉ ይጠላል፡፡ ስለሆነም ትግሎችሽ መልካምነትሽንና ጥንካሬሽን ይጨምሩልሻልና የታላቅ በጎነትና የጥልቅ ጥቅምሽ ምንጮች ናቸው፡፡” ብሎ መለሰላት፡፡

መጽሐፉ ክርስቲያኖችን ከሚገጥሙ ፈተናዎች መካከል ያላነሣው ዐቢይ ነጥብ ያለ አይመስለኝም፡፡ ነጥቦቹን የሚያነሣበት መንገድና መፍትሔዎቻቸውን የሚያመጣበት አቀራረብ ቀላልነትና ቀጥተኛነት መጽሐፉ ከዐራት መቶ ዓመታት በፊት የተጻፈ መጽሐፍ መሆኑን እንድትረሱ ያደርጋል፡፡ ስለ ሐሜት ያነሣውን ጥቂት ላቃምሳችሁ፡-

የሰው ልጅ ሦስት ሕይወት አለው፡-
ሀ. በእግዚአብሔር ጸጋ የሆነው መንፈሳዊ ሕይወት
ለ. ከነፍስ የተነሣ የሆነው ሥጋዊ ሕይወት
ሐ. በመልካም ስም ላይ የሚመሠረተው ማኅበራዊ ሕይወት
የመጀመሪያውን (በእግዚአብሔር ጸጋ የምናገኘውን መንፈሳዊ ሕይወት) ኃጢአት ከእኛ ትወስድብናለች፤ ሁለተኛውን (ነፍሳችንን) ሞት ይነጥቀናል፤ ሦስተኛውን (በመልካም ስም ላይ የሚመሠረተውን ማኅበራዊ ሕይወት) ሐሜት ይገፍፈናል፡፡ ሐሜት ግድያ የሚሆነውም በዚህም የተነሣ ነው፡፡
ሐሜተኛ በአንዲት የምላስ ስንዘራ ሦስት ግድያዎችን ይፈጽማል፡፡ በቅድሚያ የራሱንና የሰሚውን ነፍሶች በመንፈሳዊ ግድያ ከጸጋ እግዚአብሔር ያርቃል፡፡ ቀጥሎም የሚታማውን ሰው ማኅበራዊ ሕይወት ይገድላል፡፡ ቅዱስ በርናርዶስ “ሐሜተኛ በምላሱ ላይ፣ ሐሜት አድማጩ ደግሞ ጆሮው ውስጥ ሰይጣን አለባቸው፡፡” ይላል፡፡ ዳዊትም ሐሜተኛን አስመልክቶ “ምላሳቸውን እንደ እባብ አሰሉ፡፡” (መዝ 141፡ 3) ይላል፡፡ አሪስጣጣሊስ ደግሞ “የሐሜተኛ ምላስ እንደእባብ ምላስ ጫፉ መንታ ነው በአንዱ የሰሚውን ጆሮዎች በሌላኛውም ጫፍ የሚታማውን ሰው ስም ይመርዛልና፡፡” ማለቱ ይጠቀስለታል፡፡
ስለሆነም የእግዚአብሔር ወዳጅ ሆይ አንቺ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ስለሰዎች ክፉ እንዳትናገሪ፡፡ ጎረቤትሽ ያላደረገውን ኃጢኣትም እንዳትጭኚበት፣ ምሥጢር የሆኑትን ስሕተቶቹንም የግድና አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር እንዳታወጪበት፣ የሚታወቁትንም እንዳታጋንኚበት ተጠንቀቂ፡፡ መልካም ሥራውን በክፉ እንዳትተረጉሚ፤ የምታውቂውን በጎ ጎኑንም እንዳትክጂ፡፡ በክፋት ወይም በቃላት እንዳታንኳስሺው፡፡ ምክንያቱም በእነዚህ ሁሉ መንገዶች በተለይም ደግሞ በሐሰት በመክሰስና እውነትን ሸፍጠሽ ጎረቤትሽን በማንኳሰስ እግዚአብሔርን በእጅጉ ታስቀይሚዋለሽና፡፡    

አንዳንድ ከሁሉም የባሱ ረቂቅና መርዘኛ ተቺዎች ደግሞ ሐሜታቸውን በአክብሮት ወይም በሙገሳ ይጀምራሉ፤ ወይም ቀልዶችን ጣል ጣል ያደርጉበታል፡፡ “እርግጥ ነው  እወደዋለሁ” ወይም “እርግጥ ነው ጎበዝ ሰው ነው፡፡ ነገር ግን እውነቱ መነገር አለበት፡፡ እንዲህ ዓይነት ስሕተት ተሳስቷል፡፡” “በጣም መልካም ሴት ነበረች፤ እንደው በትንሽ ነገር ተሳሳተች፡፡” ይላሉ፡፡ ዘዴያቸውን ትመለከታለህ? ቀስትን አርቆ ለመወርወር የሚሻ ሰው ፍላጻውን በተቻለው መጠን ወደራሱ ይስበዋል፡፡ ዓላማው ግን ቀስቱን ላቅ ባለ ኃይል ርቆ እንዲጓዝ ማስቻል ነው፡፡ እነኚህ ተቺዎችም ሐሜታቸውን ወደራሳቸው የሚያቀርቡት ይመስላሉ ዓላማቸው ግን የአድማጮቻቸውን ልብ በኃይል በስቶ እንዲገባ ማድረግ ነው፡፡     

በቀልዶች መልክ የሚነገሩ ማንኳሰሶች ደግሞ ከሁሉም የበለጠ ጭካኔን የተመሉ ናቸው፡፡ ሄምሎክ ብቻውን ከባድ መርዝ አይደለም፤ በቀላሉ ሊረክስም ይችላል፡፡ ከወይን ጠጅ ጋር በመቀላቀል የተወሰደ እንደሆነ ግን ፈጽሞ ለማዳን አይቻልም፡፡ ልክ እንደዚሁ ሐሜት በአድማጩ በአንዱ ጆሮ ገብቶ በሌላኛው ሊፈስ የሚችል ቢሆንም ቅሉ በቀልድ ተዋዝቶ በሚመጣበት ጊዜ በአድማጮች አእምሮ ለረጅም ጊዜ ይቀመጣል፡፡[viii] ቅዱስ ዳዊት “የእባብ መርዝ በምላሳቸው ሥር አለ፡፡” ይላል፡፡ (መዝ 12፡3 እና መዝ 140፡ 3)፡፡

ይህ መጽሐፍ የማይዳስሰው የሕይወት ጥጋጥግ ብዙ አይመስለኝም፡፡ ከምግብ ጠረጴዛ እስከ አልጋ፣ ከሥራ ቦታ እስከ መዝናኛ ያሉት መገኛዎቻችን ተዳስሰዋል፡፡ ለወጣቶችም ሆነ ለአረጋውያን፣ ላገቡትም ሆነ ለማያገቡት፣ ለደናግልም ሆነ ለመዓስባን፣ ለወጣንያንም ሆነ ለፍጹማን፣ ለመካሪዎችም ሆነ ለተመካሪዎች የሚለው ነገር አለው፡፡ ምናልባት ዐቅሙና ጊዜው ያላቸው ሰዎች በግል ወይም በቡድን ይህን መጽሐፍ ወደ ኢትዮጵያውያን ቋንቋዎች ቢተረጉሙት እጅግ መልካም ፍሬ የሚሆን ይመስለኛል፡፡


[i] St. Francis de Sales
[ii] ምናልባት በአማርኛ “የመሰጠት ሕይወት መግቢያ” ልንለው የምንችል ይመስለኛል፡፡
[iii] My purpose is to instruct people living in towns, the married, and those at princely courts (preface)
[iv] በነገራችን ላይ ከሰዎች መካከል መርጦ ክርስቲያን ስላደረገን አመስግነን የምናውቅ ምን ያህል ነን?
[v] መጽሐፉ ስለ ብስጭትም ራሱን በቻለ ምዕራፍ ይናገራል፡፡
[vi] እዚህ ላይ የእማሆይ ሜላኒ ስቦቮዳ “Meeting God in Small Things” (እግዚአብሔርን በትንንሽ ነገሮች ውስጥ ማግኘት) የተባለው መጽሐፍ ውስጥ ያየሁት አንድ የቻይኖች ጥቅስ እንዲህ ይላል፡- “መቆምን እንጂ ቀስ ብሎ ማደግን አትፍራ፡፡” አንድ ሌላ ጸሐፊም ስለ አሲሲው ቅዱስ ፍራንቸስኮስ ሲናገሩ “ለእርሱ ወደፊት አለመሔድ ማለት ወደኋላ መመለስ ነው፡፡” ማለታቸውን አስታውሳለሁ፡፡ 
[vii] ይህ የቅዱስ ፍራንሷ አባባል የአንዲት ራቢያ የተባለች በእስልምና ሃይማኖት የሱፊ ዘውግ ተከታይ የነበረችን ተማሐላዪ (Mystic) የአስራ ሁለተኛው ክፍለ ዘመን ሴት ያስታውሰኛል፡፡ ብላለችና፡-
Oh my God, if I worship you for the fear of hell, burn me in hell.
If I worship you to enter to paradise, exclude me from paradise.
But, if I worship you for your own being, withhold not your beauty from me.
አምላኬ ሆይ!
የማመልክህ ሲዖልን ስለምፈራ ከሆነ በሲዖል አቃጥለኝ፡፡
ገነትን ለማግኘት ሽቼ ከሆነም ከገነት አስቀረኝ፡፡
ግና አንተን ለአንተነትህ የማመልክህ ከሆነ ውበትህን አትሰውርብኝ፡፡

[viii] በነገራችን ላይ በምዕራፍ 27 ላይ “ሰውነትን የሚመርዝ ነገር የሚገባው በአፍ እንደሆነ ሁሉ ልብን የሚመርዘው ነገር ደግሞ በጆሮ ይገባል፡፡” በሌላም ቦታ እንዲሁ “የልብ መተንፈሻዎቿ ጆሮና አንደበት ናቸው፡፡ በጆሮ ወደውስጥ በአንደበት ደግሞ ወደ ውጭ ትተነፍሳለች፡፡” ይላል፡፡