Friday, November 26, 2010

ግጥም ስናጣጥም Enjoying Amharic poetry

ገጣሚ፡- ገብረ ክርስቶስ ደስታ           

(መንገድ ስጡኝ ሰፊ፣ ገጽ 62)

የዓለም መራራነት

ያለም መራራነት ነው የሚጣፍጠን
መቸ መጣፈጧ፤
ኮሶውን በማሯ ጠቅልላ ስትሰጠን
        ስትሰጠን እሳቱን
አመድ አስመስላ ሸፍና ረመጡን፡፡
ስትሰጥ ማየ ሕይወት ስትሰጠን መድኃኒት
መርዟ ጨምራበት፡፡
ስትሰጠን እሬቱን ስኳር አስመስላ
እንደጎመን ሠርታ ሳማዋን ስንበላ፡:
                                
                                እሷ ትዞራለች
                                ፀሐይ ትሞቃለች
እኛን በብርድ ላይ በጨለማ ጥላ፡፡
ያለም መራራነት
የሚያቆራምድ ነው፤ የሚያኮራምት፡፡
ስትወስድ ወደኋላ ስትወስድ ወደ ሌላ
ምሥጢር ያላት መስላ፡፡
ከቤተሰብ ማሕል
ሰው ስታስኮበልል፡፡
ስትወስድ ስጦታዋን
ለገጸበረከት ያቀረበችውን፡፡
ሌባ ናት ሰራቂ
ቀጣፊ ነጣቂ፡፡
አቀባባይ ቀልማዳ፤ አታላይ አስመሳይ
ዋሾ ናት ወላዋይ፡፡
ሰው ሊኖር ባለም ላይ መች ተፈጠረ!
መንገደኛ እንግዳ
መሽቶበት የመጣ
ሠራተኛ አገልጋይ ነው የተቸገረ፡፡
ብዙ ነው ልፋቱ
ሲፈጠር፤ ሲመጣ፤ ሲወጣ ከቤቱ፡፡
አይችልም መዝናናት
በደመነፍስ ባሕርይ እንደተቀረጹት፡፡
እንዳህያ እንደጅብ ወይም እንደጦጣ
ወይም እንዳንበጣ
የማይቸገሩት ለምን ያስባሉ?
ከብቶች ይግጣሉ፤ ወፎች ይዘፍናሉ
አበቦች ያድጋሉ፡፡
ውስጡን አላወቁም፤ አልተመራመሩም
ሲመጡ ወዳለም፡፡
የውሸት ሥዕል ናት
                                ለዛዋ እሚጠፋ ቀለሟ እሚጠፋ፡፡
ጠረኗ እሚያባርር፤ ጣሟ እሚከረክር
ቧልቷ የሚያስመርር፡፡
የሰው ልጅ አንድ ባንድ ልታንሸራሽረው
ሁልጊዜ እንግዳ ነው
ማናፈስ ማቅበጧ
ማቻኮል ማሮጧ፡፡
ያለም መራራነት ነው የሚጣፍጠን
                                መቸ መጣፈጧ! 





የግጥም ልክፍተኛው ወዳጄ ሲሳይ ጫን ያለው ሬድዮ ፋና ላይ “ግጥም እናጣጥም” የሚል ድንቅ ዝግጅት ይዞላችኋል፡፡


By the way,
I got the pictures from the internet.
The man on the photograph is Gebrekirstos himself. The title of the painting below the poem is Patriots. <the3rdman.com>








Monday, November 22, 2010

ግለ ቅምምስና ተሐዝቦት


ሲጥ…ሲጢጥ…ሲጢጢጢጥ…
አልጋዬንና የምተኛበትን ክፍል እየተሸከረከሩ የሚጨፍሩት አይጦች ከጣፋጭ ዕንቅልፌ ተነሥቼ እሽኮለሌያቸውን እንድመለከትላቸው ግድ አሉኝ፡፡ ሰባት ሰዐት ተኩል፡፡ ይሽከረከራሉ፡፡ በላይ፣ በታች፣ በጎን ሽው፡፡ ሽርር፣ ሽርርር፡፡ ሲጢጥ፤ ሲጢጥ፤ ሲጠጢጢጥ፡፡

ምን እንደማደርጋቸው ግራ ግብት ብሎኛል፡፡ ይኼ ‹‹እዛው በላች እዛው ቀረች!›› ምናምን እያሉ የሚዞሩትን ነገር እንዳልገዛ ሁለት ምክንያቶች ይዘውኛል፡፡ አንደኛ አይጦችን እጠላለሁ፡፡ በጣም፣ በጣም እጠላለሁ፡፡ ከቤቴ ስወጣ ስለ እነርሱ ማሰብ ጨርሶ አልፈልግም፡፡ ሁለተኛ ደግሞ መርዝ ከሰጠኋቸው የሚሞቱት ሻንጣዬ፣ ድስቴ፣ ጫማዎቼ የወጥ እህሎቼ አንድ ላይ የተጠለሉበት አልጋዬ ሥር ነው፡፡ (1[u1] ) ማን የእነሱን ሬሳ ከአልጋ ሥር ይጎትታል?! ደግሞ ድስቴ ወይም ጫማዬ ውስጥ ቢሞቱስ? ቴች! ቀፋፊ ነገሮች! ድመት እንዳላሳድግ ደግሞ ወተቱ፣ ጩኸቱ፣ ኩሱ መከራ ነው፡፡

‹‹ኡ…ኡ…ኡ…!››
ከጎረቤቴ ካለው አልቤርጎ ይሁን አልቤርጎው አጥሩን አስታኮ ከቀፈቀፋቸው የዝጅችባ ቢሮዎች ከአንደኛዋ ዘንድ ጩኸት በርክቶ መሰማት ጀመረ፡፡

ይህ ሀገር በቀሎቹም ሆኑ አውሮፓውያኑ መንግሥታት ‹‹ሕዝቡ እንደፈለገ ያድርገው!›› ብለው የረሱት ወይም ደግሞ ምናምኑ ላስጨነቀው የመተንፈሻ ስፍራ እንዲሆን አስበው የፈቀዱት የሚመስለው ሰባተኛ ነው፡፡ ቀንም ሆነ ሌት በዓልም ሆነ አዘቦት ሥራ አይፈታም፡፡ ምናልባትም ዓመት 366ቱንም ቀናት ከሥራ የማይቦዝን የሀገሪቱ ጥግ ይህ ሥፍራ ሳይሆን እንደማይቀር እገምታለሁ፡፡ መንግሥት ልማታዊ አርሷደር፣ ልማታዊ አርብቷደር፣ ምናምን እያለ ሲሸልም ለምን የዚህን ቦታ ኗሪዎች ‹‹ልማታዊ የሆነ ነገር!›› ብሎ እንዳልሸለመ አልገባኝም፡፡ ግብር ስለማይቀበልበት ነው? ከሌሎች የልማት ዘርፎች አኳያ ሲታይ በቀላል የግብአት ወጪ ሊጀመር የሚችል፣ ከፍተኛ የሰው ኃይል አሠማርቶ የሚገኝና ወደፊትም በሙሉ ዐቅም ከተንቀሳቀስን እያንዳንዷን ሴት እኅታችንን (ወንድ እኅት ያለን ይመስል) ሊያሠማራ የሚችል ዘርፍ ነው፡፡ እንኳን የሽያጭ ግብር ቀርቶ ቫት መክፈል የሚችል ዐቅም አለን፡፡ ያውም የወጪ፣ የወራጅ ምናምን እያልን ሁሉ ልናሰፋው እንችላለን፡፡

ሁለት ሜትር ተኩል ወርድና አንድሜትር ተኩል ስፋት ያላት በካርቶን ገበር የተለበጠች የቆርቆሮ ቤት፣ ሜትር ከአስር የሽቦ አልጋ፣ አንድ ባልዲ፣ አንድ ማስታጠቢያ ከነጆጉ፣ አንድ ከሠላሳ የማትዘልና ሥራ የማትወድ ሴት (የመልክ ጉዳይ ብዙም አያስጨንቅም፡፡) ይህን ዘርፍ ለማደራጀት በቂ ናቸው፡፡
‹‹ብሬን አምጪ!››
‹‹የምን ብር?››
‹‹ምንድነው? ምንድነው? ምን ሆናችሁ? ልቀቃት! ልቀቃት!››
‹‹ፖሊስ በሕግ ብያለሁ! ብሬን ወስዳለች!››
‹‹ዝም በሉት፡፡ በሰባ ብር ተስማምተን ይዞኝ መጣ፡፡ ከዚያ ሀምሳ ብሩን ሰጠኝ፡፡ ከዚያ ኮንዶም የለኝም አለኝ፡፡ ከዚያ እኔ እምቢ አልኩኝ፡፡ እምቢ ስለው ደበደበኝ፡፡ ደብድቦኝ ሲያበቃ አሁን ደግሞ ብሬን አምጪ ይለኛል፡፡››
‹‹ውሸቷን ነው፡፡ አልነካኋትም፡፡ በሰባ ብር እሺ ብላኝ መጥታ እዚህ አልጋ ከያዝኩ በኋላ ‹ኮንዶም የለኝም፡፡› አለች፡፡ እኔ ኮንዶም ልገዛ ወጥቼ ስመጣ ሸውዳኝ ልትወጣ ስትል ያዝኳት፡፡ ይኸው እኔ ሕጋዊ ሰው ነኝ፡፡ እዩት መታወቂያዬን፡፡›› 

መታወቂያው ከተፈጠረው ነገር ጋር እንዴት ሊያያዝ እንደሚችል አልገባኝም፡፡ መታወቂያ የሌለው ሰው የዚህን ሰፈር አገልግሎት ማግኘት እንዳይችል ሕግ ወጣ እንዴ? ለመሆኑ የዚህ ሀገር ሕግ ስለ ዝጅችባ[u2]  ምን ይላል? ዝጅችባ የተፈቀደ ነገር ነው? ካልተፈቀደ ለምን አይከለከልም? የተፈቀደ ንግድ ከሆነ ደግሞ ለምን ግብር አይጠየቅበትም? አንድ የመንግሥት ሠራተኛ ስምንት ሰዐት ሠርቶ ከአምስት መቶ ብር ደመወዝ ላይ ግብር የሚከፍል ከሆነ በአንድ ቀን ሰባ ብር የምታገኝ ሴት ስለምን ግብር አትከፍልም? ብትታመም አዲስ በተሠራው መንገድ ላይ ፍስስ፣ ንቅንቅ፣ ምንቅር፣ ምናምን እያለች ወደ ሆስፒታል ትሔድ የለ? ይኼ እኛ ሰፈር ሲንጎዳጎድ የሚያድረው ወንድ ሁሉስ ማኪያቶ ሲጠጣ ቫት ይከፍል የለ? ታዲያ እዚህስ ለሚንጎዳጎድበት ለምን ቫት አይከፍልም? ወይስ የኛ ሰፈር ምርት ከማኪያቶ ያንሳል? እሺ ከማኪያቶ፣ ከካፑቺኖ ይነስ፤ ከሻይ ያንሳል?! ከምር ፍትሐዊ አይደለም፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬም መኪና የመጓጓዣ መሣሪያ ሳይሆን የቅንጦት ዕቃ ተደርጎ ስለሚታሰብ ጎረቤት አገር ጂቡቲ ወይም ሶማሌላንድ በቀላል ወጪ የሚገዛው መኪና እዚህ ሀገር ሲገባ ግምት ይጣልበትና በሶስት ሺህ ዶላር የተገዛው መኪና ሶስት መቶ ሺህ የኢትዮጵያ ብር ይገመታል፡፡ ለምን? ሲባል መልሱ ለሀገር ዕድገት ገንዘቡ ያስፈልጋል ነው፡፡ ይህ ሕግ ለምን እኛ ሰፈር እንደማይሠራ አይገባኝም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ምናልባት በዓመት ሦስት ሺህ መኪና ይገባ ይሆናል፡፡ እኛ ሰፈር ግን በዓመት ከገጠር እየፈለሱ የሚመጡትን፣ እዚያው ሰፈር ተወልደው እዚያው ለመዐርገ ሽርሙጥና የሚቀቡትን፣ ከጎረቤት መንደሮች የሚፈልሱትን፣ ጎዳና የሚያድሩትን፣ ወዘተ. ከቆጠርን ቢያንስ በእጥፍ ሳይበልጥ አይቀርም፡፡ እነዚህ አዲስ ገቦች ደግሞ ብዙ ጊዜ ገበያቸው ከፍ ይላል፡፡ በመሆኑም እነዚህ የምርት ኃይሎች የቫት ተመዝጋቢዎች እንዲሆኑ ቢደረግ ለልማታችን አዋጪነቱ አያጠራጥርም፡፡ ደግሞስ ከመኪናና ከሰው ማን ይበልጣል? የገዛ እጃችንን ዘርግተን እርዳታ ከተቀበልን የገዛ እንትናችንን ቸርችረን መንገድ ብንሠራ ምናለበት? ሊበራል ዴሞክራሲም ሆነ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ይህንን የሚቃወሙ አይመስለኝም፡፡ ደግሞ ምንም እንኳ ምርቱ መቧደንን ቢጠይቅም ፈቃዱና አስፈላጊዎቹ መሣሪያዎች በሙሉ እያንዳንዱ ግለሰብ በሙሉ መብቱ የሚያዝባቸው ንብረቶቹ ናቸው፡፡ 

‹‹ወደ ጣቢያ እንሒድ፡፡››

ኮቴዎች ይሰሙኝ ጀመር፡፡ ወዲያው ግን መደዳውን ከተገጠገጡት ሰንዱቆች አንዷ ሴት ‹‹ፖሊስ! ፖሊስ! ፖሊስ! ገደለኝ!›› እያለች ወጣች፡፡
‹‹ምንድነው? ማነው? ምን ሆናችሁ?››








[u1](1) ያው እንደምታውቁት ቤቴ አሁን ባላት ስፋት ከአልጋዬ ውጪ ማቆም የምትችለው ነገር ቢኖር እኔን ወይም እንደእኔ ዐርባ ቁጥር ጫማ ያለውን ባለ ሁለት እግሮች ፍጡር ብቻ ነው፡፡ እንደ መታደል ሆኖ እግሬ ማደጉን አቁሟል እንጂ አንድ ቁጥር ቢጨምር ኖሮ አለቀልኝ! ልብስ ለመልበስ ግማሽ አካሌን ውጪ ማቆም ይጠበቅብኝ ነበር፡፡ 



 [u2]
ዝ፡- ዝሙት
ጅ፡- ጅምላና
ች፡- ችርቻሮ
ባ፡- ባለሥልጣን