እንደ ክፉ ምልኪ… ያስታውቃልቀኑ
የተራሮችና የኮረብቶች ፍጅት
በእልህ በቁጭት ቃል…ሲበጠስ መረኑ
ከአፋቸው ሲወጣ እንደሚነድ እሳት
ብርሃን አልባ ቀን… ሰማያት ሲጠቁሩ
ወፎቹ ሲሸሹ ነጻነት ፍለጋ
ሲመሽ ያስታውቃል… ያን ጊዜ ጠርጥሩ
ድምጻችኹ ሲታፈን ተስፋችኹ ሲላጋ
ውንጀላ ሲበዛ… መግባባት ሲጠፋ
መተንፈስ እንደ ዕዳ… እጅ ካሳበተ
ህልም ለሽልማት ለሹመት ሲጋፋ
ያ መጨረሻ ነው ምልክት ለእናንተ፡፡
የዚኽ ግጥም ወላጅ እናቱ መቅደስ ጀምበሩ ትባላለች፡፡ ሙጋ ከተሰኘው የግጥም መድበሏ ላይ ያሰፈረችውን ይኽን ግጥም ለዛሬ
ቁዘማዬ መግቢያ ያደረግኹት ያለ ነገር አይደለም፣ በአካባቢዬ የማያቸው ምልክቶች የሚጠቁሙት ነገር ሳይኖር አይቀርም ብዬ እንጂ፡፡
ሰሞኑን አንድ ተመችቶት ይኖራል ብለን የምናስበው ወፍ ሸሽቶ አውሮጳ መግባቱ ሲሰማ ማኅበራዊ ገጾች ላይ ልዩ ልዩ አስተያየቶች ተነብበዋል፡፡
እኔ ግን አስተያየት ከመስጠት ይልቅ ጉዳዩን ይዤ ብቆዝም መረጥኹና በጉዳዩ ላይ ጥቂት አሰብኹበት፡፡ ከጥቂት ወዳጆቼ ጋርም ተወያየንበት፡፡
በጉዳዩ ላይ ካነጋገርኋቸው ወዳጆቼ መካከል አንዱም ፓይለቱን ሲወቅስ አላጋጠመኝም፡፡ ይልቁንም “እና ምን ያድርግ? እኛም መኼጃ
አጥተን እንጂ የትም ብንኼድ ከዚኽ የተሻለ ሳንኖር አንቀርም፡፡ ወዘተ. ” እያሉ ነበር፡፡
በአካባቢዬ ያለው ተስፋ መቁረጥ ያስደነግጣል፡፡ እትብቴ የተቀበረበት ሀገር ውስጥ ከመኖር
የማላውቀው ሀገር
ውስጥ ሃያ ዓመት መታሰር የሚያስመርጥ ተስፋ መቁረጥ ያስፈራል!ተስፋ የቆረጠና መሸሽ የሰለቸው ሰው ምንም ሊያደርግ ይችላል፡፡ እናም
ይኽ የታፈነ ምሬት የፈነዳ ቀን ለመቆጣጠር ያስቸግራል፡፡ ቁልቁል እየተገማሸረ የሚንደረደረው ደራሽ ወንዝአንድ ቀን መምጣቱ አይቀርም፡፡
አኹን ደራሹን ጎርፍ ከመምጣት ለማቆም የሚቻል አይመስለኝም፡፡ በጣም ሳይረፍድብን አልቀረም፡፡ ነገር ግን ጎርፉ የሚመጣበትን ፍጥነትና
የአመጣጡን አቅጣጫ አጢነን ቶሎ አቅጣጫችንን ማስተካከል፣ የጎርፉንም ፍጥነቱን በአእምሮ፣ በማስተዋልና በመደማመጥ ቀንሰን አጥፊነቱን
ወደ አልሚነት ልንቀይረው ግን እንችላለን፡፡ አልያ፣ ጎርፉ ከፊቱ
ያገኘውን ኹሉ ጠራርጎ የሚነጉድ፣ ንዝኅላሎቹንና ራስ ወዳዶቹን እረኛ ተብዬ ምንደኞችም ጠርጎ የሚኼድ ነው፡፡ ምንደኞቹ እረኞች ጎርፉ ሲጠርጋቸው ነፍሳቸውን ለማትረፍ ብዙ ዋጋ ከፍለን ወንዙ ዳር ዳር የተከልናቸውን ለጋ
ችግኞች ሙጥኝ ብለው መጨበጣቸው ስለማይቀርበስንት ስስትና ዋጋ ያሳደግናቸውን ችግኞቻችንንም ነቃቅለው ያጠፏቸዋል፡፡ ከውድመቱ በኋላም
“ፀጥታ ለማስፈን፤ ሰላምና መረጋጋትን ለማስከበር” በሚል ስም ጨካኝ ቀበሮዎችና ተኩላዎች የምንደኞቹን ቦታ ይይዛሉ፡፡ ከጎርፉ የተረፈውን
ኹሉንም በርጉም መዳፋቸው፣ በብረት ክንዳቸው ደቅድቀው ይገዛሉ፡፡ ግብጽንና ሶርያን ያየ፣ ከ1960ዎቹ ጀምሮ እላያችን ላይ እየዘነበ
ያለውን የመከራ ዶፍ ያጤነ በአብዮት አይጫወትም፡፡ እዚኽች ሀገር ላይ ዳግመኛ ወንድም ወንድሙን ሲገድል ማየት የለብንም፡፡ የማሪቱ
ለገሠ
ያም ልጅሽ፣ ያም ልጅሽ ያም ዘመድ ያም ዘመድ፣
በማን ታደያለሽ በማንስ ይፈረድ?
የሚል ሙሾ ዳግ ኢትዮጵያ ላይ መዜም የለበትም፡፡ (በመቀነት ፈንታ ገመድ መታጠቅ የጽኑ ሐዘን፣ የመራር ልቅሶ ምልክት መኾኑን ልብ
ይሏል፡፡)
ይኹን እንጂ፣ አብዮት አያስፈልገንም እያልኹ አለመኾኑን ልብ በሉልኝ፡፡ አብዮት የሚለው ቃል መነሻው የግእዙ “አበየ”
ሲኾን ፍቺውም “እምቢ አለ” ነውና በእውነት፣ እምቢ የምንለው ነገር አለን፡፡ ይኸውም “አትሞግቱን! አትጠይቁን! የምንላችኹን እንዲያው
ዝም ብላችኹ ዋጡ!” የሚልን ከሰው ልጅ ተፈጥሮ ውጪ የኾነ ትእዛዝ ነው፡፡ እምቢ የምንልበት ምክንያቱ ደግሞ መደማመጥ የሞላበት
ውይይት፣ መከባበር የሰፈነበት ንግግር፣ በጥበብ የሚከወን ሙግት፣ በቅንነት መንፈስ እየተደረገ አእምሮዎችን የሚያሰላ ክርክር በቤታችን
ውስጥ ስፍራ አግኝተውየችጋር፣ የፍርኀት፣ የሐሰትና የጭንቀት ቆፈን የቀፈደደውን ቤታችንን እንዲያሟሙቁልን ነው፡፡ እምቢታችን ኅሊናችንን
የማደንዘዝ ዐቅም ላላቸውለዝምታው፣ ለድብታው፣ ለብርዱና ለቆፈኑ ነው፡፡
ውይይት ሲባል ግን አንዳችን አጀንዳ ሰጪ ሌላችን አጀንዳ ተቀባይ፣ አንዳችን ተማሪ ሌላኛችን አስተማሪ፣ አንዳችን
ተንታኝ አንዳችን ተተንታኝ፣ አንዳችን መሪ ሌሎቻችን ተከታይ የምንኾንበት ግን አይደለም፡፡ ይኽማ ልዩነቶችን መታገሥ የማይችለው
አብዮታዊ ዴሞክራሲ እንጂ የሚጠቅመን የነጻነት መንገድ አይደለም፡፡
የካቲት ስምንት፣ 2006 ዓ.ም.በወጣው ሎሚ መጽሔት ላይ አንድ የተቀናቃኝ ፖለቲካ ፓርቲ መሪ “የፖለቲካ ድርጅት
ማለት (እኔ እንደማስበው) የአእምሮ ሥራ ነው፡፡ ሕዝብ ደጋፊ ነው፡፡”
ብለው መናገራቸውን አንብቤያለኹ፡፡ ለእኔ፣ ነጻነትን የማያውቅ ነጻ አውጪ ይሏል ይኽ ነው፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲስ ከዚኽ ውጪ ምን
አለ? ኅብረተሰባዊ ነኝ ባዩ ጨቋኝ ሥርዓትስ ከዚኽ ውጪ ምን አደረገ? ዘውዳዊው ሥርዓትስ ከዚኽ የተለየ ምን አደረገ? “እኛ እናውቃለን፤
እናንተ ስሙን፡፡ እኛ እናስባለን፤ እናንተ አድርጉ፡፡ እኛ እንመራለን፤ እናንተ ተከተሉ፡፡” የሚል አስተሳሰብ ከባርነት ወደ ባርነት፣
ከአገዛዝ ወደ አገዛዝ፣ ከፍርኀት ወደ ፍርኀት እንጂ ወደየትም እንደማያደርሰን የዓለምም፣ የራሳችንም ተሞክሮ በበቂ ኹኔታ ያስተማረን
ይመስለኛል፡፡
እንዲኽ ዓይነቷ “ሕዝብ ደጋፊ ነው፡፡” የምትል ዐረፍተ ነገር ከበስተጀርባዋ ሕዝብ ደደብ፣ ማሰብ የማይችልና ለድጋፍ
ብቻ የሚፈለግ ድንጋይና ሲሚንቶ አድርጎ የማሰብ ሥውር አለኝታ (presupposition) ተሸክማለች፡፡ ይኽ አስተሳሰብምኹልጊዜ
መሪዎችንና ሕዝብን በመደጋገፍ ሳይኾን በተቃርኖ እንዲቆሙ ያደርጋቸዋል፡፡ የነጻነት ታጋዮች የነበሩ ሰዎች ሳያስቡት በአምባገነንነት
የሚጠመዱት በዚኽ ተቃርኖ የተነሣ ነው፡፡
መሪዎች ሕዝብን ይመራሉ ማለት በምንም ተአምር በሕዝቡ ፈንታ ያስባሉ ማለት አይደለም፡፡ ይልቁንም መሪዎች ሕዝቡን
ያሳስባሉ፤ ከሕዝቡ ጋር ያስባሉ ማለት ነው፡፡መሪዎች ሕዝቡ የችግሮቹን መንሥኤ ሳይፈራ ሳያፍር እንዲመረምር ይተነኩሱታል፤ ይገዳደሩታል፤
ይጠይቁታል፤ ከተኛበት ይቆሰቁሱታል፡፡ ሕዝቡም መሪዎቹ ኑሮን ከእርሱ የእይታ አቅጣጫ እንዲያዩለት ያደርጋቸዋል፡፡ ኹለቱም በጋራ
ችግራቸውን ያጠናሉ፤ ይመረምራሉ፤ መፍትሔም ያበጃሉ፡፡
“እኛ-እንናገር-እናንተ-ስሙን” ያልኾነ፣ በጥቅማጥቅም ያልታሠረ፣ እውነተኛ ውይይት ልዩ ልዩ የማኅበረሰብ አካላት
እርስበርስ እንዲተዋወቁ፣ እውነተኛውን የችግራቸውን መንሥኤ እንዲያጠኑና መፍትሔያቸውንም በጋራ እንዲቀርጹ ያስችላል፡፡ ለምሳሌ፣
ሕዝቡ የሚያስጨንቀው ነገር የኑሮ ውድነት ይኾናል፡፡ መሪዎች ግን የኑሮ ውድነቱ ከየት እንደመጣ ምንጩን ጭምር እንዲመረምር እነርሱ
በቅድሚያ ችግሩን መርምረው በልዩ ልዩ ምክንያቶች የችግሩን ምንጭ ችላ ያለውን ሕዝብ ይሞግቱታል፡፡ ሕዝቡ ደግሞ እንደ ሕዝብ መኖር
ማለት ምን ማለት እንደኾነ በመልሶቹ መሪዎቹን ያስተምራቸዋል፡፡ የጋራ ግብም ያበጃሉ፡፡
የነጻነት ትግል ጭቁኖችን ከጭቁንነት ብቻ ሳይኾን ጨቋኞችንም ከጨቋኝነት ነጻ የማውጣት ዓላማ ይዞ ነው የሚጓዘው፡፡
ኹለቱም ወገኖች ከደረሱበት የሰብአዊነት መንጠፍ (dehumanization) ነጻ የሚያወጣቸው እንቅስቃሴ ነው፣ የነጻነት ትግል፡፡
የነጻነት ትግል ዓላማ ሰዎችን ሰው ኾነው የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው በነጻነት የሚወስኑ፣ በዕድላቸው ላይ ሥልጣን ያላቸው ፍጥረታት
እንዲኖሩ ማቻል ነው እንጂ ጨቋኞችን አባርሮ መግደል አይደለም፡፡ ጨቋኞች ከሚኖሩበት በፍርኀት የታሠረ ሕይወት ወጥተው ጨቋኝ ሳይኾኑ
መኖር እንደሚቻል ማሳየት ነው፡፡ ጭቆና ተጨቋኙን “ቢጭኑት አኽያ ቢለጉሙት ፈረስ” ዓይነት ግዑዝ ዕቃ የሚያደርገውን ያኽል ጨቋኙንም
የተጠጋውን ኹሉ የሚናደፍ የቆሰለ አውሬ ያደርገዋል፡፡
ለብዙ ዓመታት የኖርንበት ፍጹም አምባገነናዊ ሥርዓት ጨቋኝ ስለኾነ እያንዳንዱ ሰው ራሱን እንደሰው ቆጥሮ “በሕይወቴ ላይ ወሳኙ ሰው እኔ ነኝ” ከማለት ይልቅ አለቃ፣ ጌታ፣
መሪ፣ አስከታይ መፈለግን አስለምዶናል፡፡ መሪዎቻችን ብለን የምንመርጣቸውና ከጉሮሯችን ነጥቀን እያጎረስን ያጠነከርናቸው፣ ደማችንን
እየገበርን ሥልጣን ላይ ያወጣናቸው ሰዎችም ጥቂት ቆይተው ራሳቸውን ለሰፊው ሕዝብ እውነትና ነጻነት እንደተሰዋ ምትክ የለሽ ሰማዕት
እየቆጠሩ ያሰቃዩናል፡፡ ከፊተኞቹ የማይሻሉ ብቻ ሳይኾን በብዙ ፈርጅ የባሱ ኾነው ይገኛሉ፡፡ የዚኽ ምክንያቱ የአእምሮነቱን ቦታ
በፍጹም ጌትነት እንዲቆጣጠሩ ስለምንፈቅድላቸው ነው፡፡
አንሞግታቸውም፤ እነርሱም እኛን እናስተምራችኹ፣ እናሠልጥናችኹ ይሉናል እንጂ
አይሞግቱንም፡፡ እኛም ከመሞገት ይልቅ ትናንት ከመካከላችን የወጡ ሰዎች መኾናቸውን ዘንግተን መለኮታዊ ስፍራ ልንሰጣቸው ይቃጣናል፡፡
ስለ ፍጹምነታቸው፣ ስለ አእምሮ ብቃታቸው፣ ስለ ስሜት ብስለታቸው እንጂ ስለ ስሕተታቸው፣ ስለ ውድቀታቸው እንዲነገረን አንፈልግም፡፡
የኖርንበት የጭቆና ሥርዓት ነገሮች ፍጹም ጥሩ ወይም ፍጹም መጥፎ፣ ፍጹም ነጭ ወይም ፍጹም ጥቁር፣ ፍጹም አስቀያሚ ወይም ፍጹም
ቆንጆ ወዘተ. ብቻ የሚኖሩበት ሚቶሎጂያዊ ዓለም አድርጎ ይቀርጽብናል፡፡
ጨቋኞችም ህልውናቸውን ለማስጠበቅ ይኽንን ሚቶሎጂ በልዩልዩ መንገዶች ሕዝቡ እንዲጋት ያደርጋሉ፡፡በቁጥጥራቸው ሥር የሚገኙ የሚዲያ
ተቋማት ሥራቸውም ይኽንኑ ሚቶሎጂ መፍጠር፣ መመገብና ማጽናት ነው፡፡ በዚኽ ሚቶሎጂ መሠረት ጨቋኞች ሕዝብ ከእነርሱ ውጪ ህልውና
የሚኖረው እንዳይመስለው የማድረግ ብቃት አላቸው፡፡ ራሳቸውን የበጎ ነገር ሥጋዌ አድርገው ያቀርባሉ፡፡ በጎ ነገር በተነሣ ቁጥር
ስማቸው አብሮ እንዲነሣ የሚያደርጉትም ለዚኽ ነው፡፡ አንድነት፣ ልማት፣ ብልጽግና፣ ሰላም፣ ድል፣ ስኬት የሚባሉ ቃላት ባሉበት ቦታ
ኹሉ ጨቋኞቹ ስማቸው አብሮ እንዲነሣ ያደርጋሉ፡፡ቀስ እያለም በፕሮፓጋንዳው ብዛትልማት፣ ብልጽግና፣ ሰላም፣ አንድነት ማለት እኛ
ነን ይሉናል፡፡ እነርሱ ባይሉንም እኛ እንደኾኑ አድርገን ማሰባችን አይቀርም፡፡ በዚኽም የተነሣ ሰላማችን፣ ብልጽግናችን፣ ልማታችን፣
አንድነታችን ኹሉ እነርሱ ከሌሉ የማይኖሩ አድርገን ማሰብ እንጀምራለን፡፡ ህልውናችንን ከህልውናቸው ጋር በወንድማማችነትና በእኩልነት
የተሣሠረ አድርገን ከማየት ይልቅ፣ ህላዌያችንን በህልውናቸው ላይ የተመሠረተ አድርገን እንቆጥራለን፡፡ በቃ! እነርሱም ዕቃ አድርገውን፣
እኛም ተናካሽ አውሬ አድርገናቸው በጨቋኝ ተጨቋኝ አዙሪት ውስጥ እንሰጥማለን፡፡
ለዚኽ መፍትሔው ውይይት ነው፡፡ አብሮ ማሰብ ነው፡፡ መሟገት ነው፡፡ የሰው ልጆች በመኾናችን የተነሣ ብቻ ዕድል ፈንታችን፣ ጽዋ ተርታችን አንድ ላይ እንደተገመደ አለመዘንጋት ነው፡፡ ይኽ የውይይት፣ የክርክር፣ የመደማመጥ ሰው የመኾን መንገድ ብቻ ነው መሪና ተመሪ፣ አስተማሪና ተማሪ፣ ሊቅና ደንቆሮ፣ “አሳቢ”ና “ደጋፊ” ከመኾን የሚቤዠን፡፡ በነጻነት ትግል ውስጥ ተባባሪና አስተባባሪ በመኾን ሰው ወደ መኾን ከፍታ አብረን እንጓዛለን፡፡
"የሰው ልጆች በመኾናችን የተነሣ ብቻ ዕድል ፈንታችን፣ ጽዋ ተርታችን አንድ ላይ እንደተገመደ አለመዘንጋት ነው፡፡"
ReplyDeleteወደ መጨረሻ ስለ መሪዎቻችንን (ስለራሳችንም ጭምር) ባለ አንድ ጫፍ ታሪክ ብቻ የማመን አባዜ ባልልከው ላይ እኔም ያልኩትን ልጨምር::
ReplyDelete"ወደ ፖለቲካው እንሂድ::ስለ ቴዎድሮስ 'ስለ ምኒሊክ' ስለ ኃ/ስላሴ'ስለ ደርግ' ስለ ኢህአዴግና ሰለ ተቃሚዎቹ አንድ ታሪክ ነጥለን እንይዛለን:: ያችን እየደጋገምን እሸሸው ገዳሜ እንዘፍናለን:: ቴዎድሮስ ጀግና ነው' ምኒሊክ እምዬ ናቸው' ኃ/ስላሴ ፊወዳል ናቸው' ደርግ ነቭሰ በላ ነው' ኢህአዴግ ሌባ ነው' የኢህአዴግ ተቃዋሚዎች ወሽካታ ናቸው.........ብቻ የምንመርጠውን ጥሩ ወይም መጥፎ አንድ ታሪክ መርጥን በማቀንቀን ሌላወን ሁሉ ዜማ ውበትና እውነት አልባ እናደርግዋለን:: ሁለተኛ ሶስተኛ የሚባሉ ታሪኮች አናወሳም::መካካል የሚባል ቦታ የለንም:: " (from "The Danger of a single story - I wrote the piece inspired by Nigozie Chimamanda Adichie's speech of the same title)