ያው እንደምታውቁት የዋዲያ የድኻ ልጆች የሚማሩባቸው ትምህርት ቤቶች“የመንግሥት” ትምህርት ቤቶች ይባላሉ፡፡ እነዚኽ
ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚማሩ (እንዲማሩ የተፈረደባቸው) ተማሪዎችም ሦስት ዋና ዋና ዕዳዎች አሉባቸው፡፡
አንደኛው ዕዳ
አንዲት የበሬ ግንባር የምታኽል ክፍል ውስጥ ቁናሙሉ ሙጫጭላዎች ተሞልተው “እንዲማሩ” ይደረጋሉ፡፡ እግር ጥሏችኹ
ወደ እነዚኽ ትምህርት ቤቶች ስትገቡ አንድ ክፍል ውስጥ ከ140 ያላነሱ ዓይኖች ቢቁለጨለጩባችኹ እንዳትደነግጡ፡፡ የሚሌኒየሙን የልማት
ግቦች በስታቲስቲክስ ሪፖርት ለማሟላት ሲባል የማይቧጠጥ ሰማይ፣ የማይፈነቀል ድንጋይ የለም፡፡
አንድ ክፍል ውስጥ ሰባና ሰማንያ
ተማሪዎችን ከአንድ- እንደበግ እያገዳቸው ይኹን እንደተማሪ እያስተማራቸው ያልተገለጠለት የሚመስል- ከሢታ አስተማሪ ጋር ማየት የተለመደ
ነው፡፡ አስተማሪው እየለፈለፈ እወንበር ሥር ገብተው ዕቃዕቃ የሚጫወቱ ልጆችም ቢያጋጥሟችኹ እንዳትስቁ፡፡ በትምህርት ቤቱ ግቢ ውስጥ
የአምስት ዓመት ልጅ የሚያኽል በትር ይዞ የሚንጎራደድ አስተማሪ ቢታዩም አትሳቀቁ፣ ሰውየው ልጆቹን እንደ ጥጆች እንዲያግድ እንጂ
እንደ ልጆች እንዲያስተምር አልታደለምና፡፡ ድሮስ “አንድ ለእናቱ” እንጂ “አንድ ለሰባና ሰማንያ” መቼ ተባለ?
ኹለተኛው ዕዳ
እነዚኽ ተማሪዎች ከአንደኛ ክፍል እስከ አራተኛ ክፍል ድረስ ኹሉንም
የትምህርት ዓይነቶች በአንድ አስተማሪ እንዲማሩ ይገደዳሉ፡፡ ቀሽምም ኾነ ጎበዝ፣ አንደኛ ክፍል ላይ ያገኙት ወይም ያገኛቸው አንድ
አስተማሪ አራት ዓመት ሙሙሙሙሉ እንዲያስተምራቸው ይኾናል፡፡ ይኸው አንድ አስተማሪ (እኔስ “አስማት-ሠሪ” ልለው ይቃጣኛል) የጨቅሎቹ
የአማርኛም፣ የእንግሊዘኛም፣ የሒሳብም፣ የአካባቢ ሳይንስም፣ ወዘተ. አስተማሪ ለመኾን ይገደዳል፡፡ የጨቅሎቹን አእምሮ “የመቅረጽ”
ኃላፊነት ይሸከማል፤ ወይም እትከሻው ላይ ይጣልበታል (ችጋር ጠመኔ ያስመሰለው አስተማሪ ኹላ ደግሞ ምን ትከሻ አለውና ነው ትከሻው
ላይ የሚጣልበት?! ብሎ ማሽሟጠጥ ይቻላል)፡፡ አስተማሪው አንሻፍፎ የሚያውቀውን ነገር ኹሉ አንሻፍፎ እያስተማረው፣ የተማሪዎቹ ጭንቅላትም
እየተንሻፈፈ አራት ዓመታት ያልፋሉ፡፡
በእነዚኽ ትምህርት ቤቶች ያሉ መምህራንን (በተለይ በገጠሪቱ የዋዲያ
ክፍል) ብቃት ደግሞ አንድዬ ያመልክታችኹ፡፡ እነዚኽ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ያለ አስተማሪ፣ ከየ-ዮ ድረስ በቅጡ መጻፍ የማይችልና
በፖስታና በፓስታ መካከል ያለውን ልዩነት አጥርቶ የማይለይ ቢኾንም የአማርኛ አስተማሪይኾናል፤ የሒሳብ ዕውቀቱ ከመቅጠኑ የተነሣ
ያለበትን ዱቤ እንኳን ባለሱቁ እየደመረለት የሚኖር የቁጥር አለርጂ ያለበት ሰው ቢኾንም የሒሳብ አስተማሪ ይኾናል፡፡ በእንግሊዘኛ
ራስሽን አስተዋውቂ ስትባል እታለም የተሰኘውን ስሟን ጭምር “me name sister is world.” ብላ “ተርጉማ”ለማቅረብ የሚቃጣት
የእንግሊዘኛ መቃብር ጠባቂ እንግሊዘኛ አስተማሪት መኾን አይቀርላትም፡፡ የጨቅሎቹም አንጎል እነዚኽ ሥርዓቱ ያለዐቅማቸውና ያለፍላጎታቸው
በሾማቸው ሸራፋዎች “ይቀረጻል” አሉ፤ ድንቄም ቀረጻi ጃርት እንደበላው ዱባ ይቸረቸፋል ቢባል ይቀላል፡፡
ሦስተኛው ዕዳ
በእነዚኽ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚገኙ ተማሪዎች ከአንደኛ እስከ አራተኛ
ክፍል ድረስ መውደቅ፣ ወይም ክፍል መድገም አይፈቀድላቸውም፡፡ ጨቅሎቹ ትምህርቱን ባይረዱትም፣ በፈተናዎች ኹሉ ቢወድቁም፣ ማንበብና
መጻፍ በቅጡ ባይችሉም ከክፍል ክፍል መዛወር አይቀርላቸውም፡፡ ክፍል መድገም የሚባል ነገር፣ መውደቅ የሚሉት ጣጣ አይታወቅም፡፡
እንደው ማለፍ ነው፡፡ ማለፍ፡፡ ማለፍ፡፡ ማለፍ፡፡ ተማሪው ያላለፈ እንደኾን የክፍሉ መምህር ይገመገማታል፡፡ “ተማሪዎቹን ባለማብቃት”
በሚል ይገመገምና የደመወዝ ዕድገቱ፣ የትምህርት ዕድሉ ይቀነስበታል አሉ፡፡ ስለዚኽ፣ ማን ሞኝ አለ?! ተማሪው ፊደል መጻፍ ባይችልም፣
ሒሳብ ማስላት ባይኾንለትም፣ እንግሊዘኛም ኾነ አማርኛ ማንበብ በቅጡ ባያውቅም ማርክ እየጨመረለት ያሳልፈዋል፡፡ አለቆቹም ኾነ የአለቆቹ
አለቆች የሚፈልጉት የቁጥር ሪፖርት እንጂ የልጆቹን እውነተኛ ትምህርት አይደለ፤ ምን አስጨነቀው?!
ይኽ ብቻ አይደለም፤ ተማሪው ከክፍል ሲቀርም ዕዳው ለአስተማሪው ነው፡፡
ተማሪውን እቤቱ ድረስ ኼዶ በቀበሌ አስገድዶ ወደ ክፍል እንዲያመጣው ይጠበቅታል አሉ፡፡ ይኽ እንኳን በመሠረቱ የተማሪውን ሕገ መንግሥታዊ
የመማር መብት በማስከበር ረገድ መልካም ነበር፡፡ ይኹን እንጂ፣ ተማሪው በቀረ ቁጥር አስተማሪውን መገምገምና ልዩ ልዩ ጥቅማጥቅሞችን
መከልከል ቀጥሎ የምነግራችኹ ከሰሜናዊ የሀገራችን ክፍል የመጡ ወዳጆቼ የነገሩኝን ዓይነት አሳፋሪ ክሥተት ያመጣል፡፡
መቼም ድኻ አደብ ገዝቶ መቀመጥ አይኾንለትም አይደል? ኹለት ድኾች ይወልዱና ለዕድሜው ለትምህርት ሲደርስ ልጃቸውን
ወደ መንግሥት ትምህርት ቤት ይልካሉ- አንደኛ ክፍል፡፡ ኾኖም፣ ይኽ ልጅ ይታመምና (ሕመሙ ጠኔ ይኹን፣ አተት አላጣራኹም) እዚያው
አንደኛ ክፍል ላይ ሳለ ይሞታል፡፡ አስተማሪው ግን በክፍሉ ውስጥ ያሉትን ቁና ሙሉ ሙጫጭላዎች በማስተማር ተጠምዶ የዚኽን ልጅ ከክፍል
መቅረት ሳያጤነው ዓመቱ ያልቃል፡፡ ዓመቱ ሲያልቅ ግን ይኽ አስተማሪ አንድ ተማሪ ቀርቶብኻል፤ አንድ ተማሪ ወድቆብኻል ተብሎ መገምገም
አልፈለገም፡፡ ስለዚኽም ማርክ ሞላ ሞላ አድርጎ ይኽን ልጅ ያሳልፈዋል፡፡ ይኽ ቤተሰቦቹ ሞቶ ቀብረነዋል ያሉት ልጅ ወደ ኹለተኛ
ክፍል ተሸጋገረ፡፡ ኹለተኛ ክፍል ላይም እንዲኹ አለፈ፡፡ ጓደኞቹ ሦስተኛ ክፍል ሲገቡ የልጁ ስም አኹንም አብሯቸው ነበር፡፡ አራተኛ
ክፍልም እንዲኹ ታለፈና አምስተኛ ክፍል ተደረሰ፡፡ አኹን አራት ዓመት ሙሉ በአንድ አስተማሪ “ሲበቁና ሲነቁ” የነበሩት ልጆች ሌላ
አስተማሪዎችን ለማየት ዕድል አገኙ፡፡ ዐዲስ የክፍለ ኃላፊት መምህርትም ተመደበችላቸው፡፡
ወራት ተቆጠሩ፡፡ ዐዲሷ አስተማሪት ትምህርት
ከተጀመረ ጀምሮ ስም በምትጠራበት ጊዜ የማይገኝ አንድ ተማሪ ያሳስባት ጀመር፡፡ የዚኽን ልጅ ጉዳይ በቶሎ ካልቋጨችው አለቆቿ በግምገማ
አፈር እንደሚያስግጧት እየታሰባት ተጨነቀች፡፡ልጁ ደግሞ ስሙን በየዕለቱ ብትጠራም አቤት ሲል ልትሰማው አልቻለችም፡፡ ቢቸግራት፣
ከመዝገብ ቤት ፋይሉን አስወጥታ አድራሻውን አገኘችና የልጁን ወላጆች ለምን ልጃቸውን ትምህርት ቤት እንደማይልኩት ለመጠየቅ ወደ
ወላጆቹ ቤት ገሠገሠች፡፡ መድረስ አይቀርም፣ በቀበሌው ባለሥልጣናት ታጅባ ደረሰችና ወላጆቹን “እገሌ የተባለው ልጃችኹን ለምንድነው
ወደ ትምህርት ቤት የማትልኩት?” ብላ ታፋጥጣቸው ጀመር፡፡ ይኼኔ የልጁ አባት ግራ ገባው፡፡ የልጁ እናት ደግሞ የሞተውን ልጇን
አስታውሳ እዬዬ! የሞተው ልጇ አምስተኛ ክፍል ደርሶልሻል ስትባል ምን ታድርግ?!
የዋዲያና የትምህርቷ ነገር እንዲኽ በቀላሉ አያበቃም፡፡ የቁልቁለት ጉዞው ይቀጥላል፡፡
No comments:
Post a Comment