Thursday, February 6, 2014

የድኻ መነሻ ግሦች (The Etymology of The Poor)


“ድኻ” የሚለው ቃል የመጣው “ደኸየ” ከሚል ግሥ ሲኾን ትርጉሙንም የአለቃ ኪዳነ አበው መዝገበ ቃላት “አጣ፤ ነጣ፤ ፊቱ አመድ ነፋበት፤ ኪሱ ሸረሪት አደራበት፤ ምግቡ ሽሮ፣ ዕንቅልፉ የዶሮ ኾነ፤ ኑሮው መራራ፣ ዕዳው ተራራ ኾነ፤” ማለት እንደኾነ ያትታል፡፡ እንደሊቁ ገለጻ፣ ይኽ “ደኸየ” የተሰኘው ግሥ ደግሞ በበኩሉ ሥር መሠረቱ የግእዙ “ከየደ” ነው፡፡ “ከየደ” “ረገጠ፣ ረጋገጠ፣ ደፈጠጠ፣ ረመጠጠ” ተብሎ ይተረጎማል፤ የድኻን ተረጋጭ ተደፍጣጭነት ያመለክታል፡፡ 

በሌላ በኩል፣ ይኽ “ደኸየ” የሚለው ቃል ሌላ “ደወየ” ከሚል ቃል እንደሚነሣ የሚናገሩ ሊቃውንት አሉ፡፡ “ደወየ” ማለትም “ታመመ፤ ተሠቃየ፤ ቆዳው እንኩሮ፣ ጨጓራው ንፍሮ ኾነ፤ አጥንተ ሰባራ፣ አንገተ ቆልማማ ኾነ፤ ቀና ማለት፣ ስሙን መጥራት አቃተው፤ ምላሱ እንደ ተመታ እባብ ተጥመለመለ፣ አካላቱ እንደ ደረቀ ግንድ ተመለመለ” ማለት ነው፡፡ ሊቁ እዚኽ ላይ አያበቁም፡፡ ይልቁንም ይኽ “ደወየ” የሚለው ቃል ደግሞ መነሻ ቃሉ “ወደየ” የተሰኘው ሌላ የግእዝ ግሥ ነው ይላሉ፡፡ “ወደየ” ማለትም “ጨመረ፤ አከለ፤ ደበለ፤ ከተተ” ተብሎ ይፈታል፡፡ ይኽም ድኻ መከራው፣ ጌቶቹና ቁጥሩ ዕለት ዕለት እየጨመረ እንደሚኼድ ያሳያል፡፡ አንድም፣ ድኻ በዚያው መከራው በጨመረ መጠን ለጌቶቹ ያለው ታማኝነትና ታዛዥነት እየተጨመረ፣ እየተደበለ እንደሚመጣ ያሳያል፡፡ 


ከዚኽ በተጨማሪም፣ ድኻ ቁጥሩን እንደሰማይ ከዋክብት፣ እንደ ባሕር አሸዋ ካላበዛ በስተቀር ዕንቅልፍ እንደማይወስደው፣ እንዲያውም “ዘሬ ሊደመሰስ ነው፤ ዓይኔን ባይኔ ላላይ ነው፡፡” እያለ በሥጋት ላይ ሥጋት፣ በልጅ ላይ ልጅ፣ በጨቅላ ላይ ጨቅላ፣ በሙጫጭላ ላይ ሙጫጭላ እንደሚጨምር ያመለክታል፡፡ እንደ ሊቁ ተጨማሪ ትንታኔ፣ “ደየመ” የሚለው የአራዳ ልጆች ቃልም ከዚኹ ቃል ጋር ተዛምዶ አለው፡፡ በአራድኛ “ደየመ” ማለት “ኼደ፤ ነጎደ፤ ተሰደደ፤ ፈረጠጠ፤ በዐየር በረረ፤ በባሕር ቀዘፈ” ማለት ነው፡፡ አንድም፣ “ሞተ፤ ፍግም አለ፤ አራት እግሩን በላ፤ በቁሙ ቱኻን ጠባው፤ በሞቱ ምስጥ በላው” ተብሎ ይፈታል፡፡ ይኸው “ደየመ” የሚል የአራዳ ልጆች ቃል ምንጩ ደግሞ “ዴሚ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ነው፡፡ ፍቺውም “ኺድ፣ ጥርግ በል፣ ብትፈልግም አንጨቆረር ግባ፡፡” ማለት ነው፡፡ ይኽም፣ ድኻ የትም ቢኼድ፣ እንዴትም ቢኼድ ማንም ግድ እንደማይኖረው ሳይጠቁም አይቀርም፡፡

No comments:

Post a Comment