Tuesday, March 5, 2013

እመርጣለኹ!


እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ከሰጠን ስጦታዎች አንዱ መምረጥ መቻላችን መኾኑን አምናለኹ፡፡ ምርጫችን ላይም ገደብ የለብንም፡፡ እንኳን የምናደርገውን የምናመልከውን ሳይቀር መምረጥ እንድንችል ነጻ ተለቅቀናል፡፡ ለምን ነጻ ተለቀቅን ለሚል ጥያቄ እኔ መልስ መስጠት እንደማልችል ከወዲሁ ልገልጽላችኹ እወድዳለኹ፡፡[i] ምክንያቱም ውብ አድርጎ ፈጥሮ ያቀረበልንን ዓለምን እንኳ ራስን ብቻ ማዕከል አድርጎ የመጓዝ አቅጣጫን በመምረጣችን ምክንያት እነሆ በሥቃይ እንቀቅላታለን፡፡ በሰው ልጅ የተነሣ እነሆ ፍጥረት ይሠቃያል፡፡ የፍጥረት አካል የኾነው የሰው ልጅም በዚህ በምርጫው ካመጣው ሥቃይ ተካፋይ ከመኾን አላመለጠም፡፡ የአብዛኛው ሥቃዮቻችን መነሻም ራሳችንን መውደዳችን ነው፡፡[ii]

“እኔ” የሚባል መሥዋዕት የማይጠግብ አምላክ ባሮች ነን፡፡ በርትራንድ ረሰል የሚባል ፈላስፋ “የሰውልጆች ኹሉ አምላክ መኾን እንሻለን፡፡ እርስበርስ እንዳንግባባ ያደረገንም ይኸው አምላክ የመኾን ጥማታችን ነው፡፡ ከሌሎች ሰዎች ጋር በምንነጋገርበት ጊዜ ኹሉ እኛ አምላክ ሌሎቹ ደግሞ አምላኪዎቻችን እንዲኾኑ እንሻለን፡፡”[iii] ይላል፡፡


በየመንደሩና በየመንገዱ ለቁጥር የሚያታክቱ የአእምሮ ሕሙማንን የምንመለከተው፣ ፍርድ ቤቶች በፍቺ ፋይሎች ሲጣበቡ የምናስተውለው፣ ሴተኛ አዳሪነትና የሩካቤ ቱሪዝም (sex tourism) እጅግ በሚያስደነግጥ ኹኔታ እየተስፋፋ የሚታየው፣ በየቢሮዎች ስንኼድ ዓይን ያወጣ ልዩ ልዩ መልክ ያለው “የጉቦ አምጡ!” “ጥያቄ” (ትእዛዝ ቢባል ይሻል ይኾን?) የሚቀርብልን፣ እርስበርስ ብቻ ሳይኾን ከሌላው ፍጥረት ጋርም ፈጽሞ ስምምነት አጥተን፣ ሥነ ምኅዳሩን እየበጠበጥነው ለመኖር የዳረገን ይኸው ዓለምን በ”እኔ” ዛቢያ ብቻ እንድትሽከረከር የመፈለግ አባዜ ይመስለኛል፡፡

“እግዚአብሔር ፍቅር ነው፡፡” ብለን ካመንን በፍቅር ተፈጥረናልና ለፍቅር ከመኖር ውጪ ሕይወታችን በጭራሽ ትርጉም ሊኖራት አይችልም፡፡ እንኑር ብንልም ከፍጥረታችን ውጪ ለመኖር በመታገል ጊዜና ጉልበት ከማባከን ውጪ የምናገኘው አንዳችም ነገር የለም፡፡ ፍቅር ደግሞ ኹሌም ወደ ውጪ ይፈስሳል፡፡ ስለዚህም በእያንዳንዷ ሰከንድ በምናደርገው እንቅስቃሴ የምንወስነው ውሳኔ የሕይወታችንን መሠረታዊ ምንትነት (essence)-የፍቅር ፍጥረት መኾናችንን- የተመረኮዘ ማድረግ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው፡፡ በቅርቡ መንበራቸውን በትሕትና ያስረከቡት አቡነ ቤኔዲክቶስ የመጨረሻ መልእክታቸው “ክርስቶስን የሕይወታችኹ ማዕከል አድርጉት፡፡” የሚል ነበር፡፡ በሌላ አባባል ስናየው ክርስቶስን በየትኛውም ጊዜና ቦታ ውስጥ ምረጡት የሚል ይመስለኛል፡፡

ቀጥሎ የቀረበው ጸሎት አባ ዮሴፍ የሚባሉ “የመንፈሳዊነት ነገረ መለኮት” (Spiritual Theology)  ሊቅ ያዘጋጁት/ የጸለዩት ነው፡፡ የልሳነ እንግጣሩ (የእንግሊዘኛው) ጽሑፍ ርእስ  “I choose” ስለሚል “እመርጣለኹ!” የሚል ርእስ ቢሰጠው ተስማሚ መስሎኛል፡፡ እግረመንገዳችኹን ክርስቶስን መምረጥ ማለት ምን ማለት እንደኾነ አስተንትኑልኝማ፡፡              

እመርጣለኹ!
ሕይወትን ኹሉ የሚቀድሰውን የክርስቶስን እስትንፋስ መተንፈስን እመርጣለኹ፡፡
በኃጢኣት መበስበስና መበላሸት የሌለበትን የክርስቶስን ሥጋ መልበስን እመርጣለኹ፡፡
በሐሴት የሚያረሰርሰኝን የክርስቶስን ደም በደም ሥሮቼና በልቤ እንዲመላ እመርጣለኹ፡፡
ራሴንና ዓለምን በሙሉ ከኃጢኣት የሚያነጻውን ከጎኑ የሚፈልቀውን የሕይወት ፏፏቴ እመርጣለኹ፡፡

ትርጉም አልባ ሐዘኖቼ ትርጉም ያገኙ ዘንድ
ሥቃዬም ኃይልን እንዲወልድልኝ
አሰቃቂውን የክርስቶስን ሥቃይ እመርጣለኹ፡፡
መልካሙ ኢየሱስ ሆይ! እንደምመርጥኽ ታውቃለኽ፡፡   

መልካሙ ጌታዬ ሆይ! አዎን አንተን እመርጣለኹ፡፡
በመራራው ብዙ ሥቃይኽ ድል ከነሣኸው ምርኮ ጋር ልቆጠር፡፡
አንተን ከማያውቁ ጋር በፍጹም አትደምረኝ፡፡
ሊያጠፋኝ ከሚሻው ኹሉ ጠብቀኝ፡፡
ወደ አንተ እንድመጣ ጥራኝ፡፡
ስላደረግኸው ኹሉ “አሜን!” እያሉ ከሚዘምሩልኽና ዘለዓለም በምትሠራው ኹሉ ከፍ ከፍ ከሚያደርጉኽ መላእክትና ቅዱሳን ጋር አቁመኝ፡፡
የኹሉ አባት ሆይ! እኔን “ከእኔ” አድነኝ፤
በዓለም ክርስቶስን እንድመርጥም እድርገኝ፡፡
                                                                            አሜን፡፡



[i]ታላቁ ሊቅ ቤኔዲክቶስ 16ኛ እንኳ በአንድ ወቅት እግዚአብሔርን ጥያቄ እንዲጠይቁ ቢፈቀድልዎት ምን ይጠይቃሉ ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ “ዓለምን የምታስተዳድረው ለምን ከመስቀል ላይ ኾነኽ ኾነ ብዬ እጠይቀው ነበር፡፡” ብለዋል፡፡
[ii] በክርስቲያናዊ ዕይታ The Virtue of Selfishness” የሚባል ነገር የለም፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር ፍቅር ነው፡፡ በፍቅር የተፈጠረ ሰው የህልውናው ዓላማም ኾነ ትርጉም ለፍቅር መልስ መስጠት ብቻ ነውና፡፡ ፍቅር ደግሞ ኹሌም ሞልቶ ሲፈስስ ይገኛል እንጂ ጫፍ እንደሌለው ጉድጓድ ኹሉን ወደራሱ ሲያግበሰብስና ሲከት አይገኝም፡፡ 
[iii] Russel, Bertrand. 1938. Power: A New Social Analysis. London, Rutledge.
iv.BenedictXVI@ pontifex february28 twitter

No comments:

Post a Comment