በየሬድዮ ጣቢያው ላይ ብሔር፣ ብሔር፣ ብሔር፣ ብሔር… እየተባለ
የሚለፈለፍበት ሰሞን ስለኾነ ጥቂት “ስለብሔር” ጉዳይ አንድ ሰው ያጫወቱኝን ገጠመኛቸውን መሠረት አድርጌ፣ ትንሽ የእውነት ቅመም
ጨምሬበት ሐሳቤን ላካፍላችኹ እወድዳለኹ፡፡
አንድ ጉዳይ ይገጥማቸውና መታወቂያ ለማውጣት ቀበሌ ይኼዳሉ፡፡ ወንበሩ
ላይ የተሠየመው ሰው ቅጽ እየሞላ ጥያቄ መጠየቅ ይጀምራል፡፡
“ስም”
“እገሌ እገሌ”
“የአያት ስም”
“እገሌ”
“የተወለዱበት ዘመን”
ሰውየው ተናገሩ፡፡
“ብሔር”
ይኼኔ ሰውየው “የለኝም፡፡” አሉ፡፡
“እንዴት የለዎትም”
“አሃ! የለኝማ! የለኝም፡፡”
“ለምንድነው የማይኖርዎት”
“ኦሮምኛ፣ አማርኛ የምታቀላጥፈው እናቴ የተወለደችው ከኦሮሞ እናትና
ከጉራጌ አባት ነው፤ ግእዝ፣ አገውኛና አማርኛ የሚናገረው አባቴ ደግሞ እናቱ አገው ሲኾኑ አባቱ ደግሞ ጎንደር ተወልደው ያደጉ
የትግራይ ሰው ናቸው፡፡ እኔ የተወለድኹት ደብረ ዘይት፣ ያደግኹት አዲስ አበባ ሲኾን ሐረሪዎች ዘንድ ብዙ ዓመታት በመኖሬ አደሪኛ
እናገራለኹ፡፡ እና የእኔ ብሔር ምን ሊባል ነው?”
“እ...እ… እንደርሱማ ሊኾን አይችልም፡፡”
“ጌታው ቢያምኑኝ ይመኑኝ፡፡ የምነግርዎት እውነቱን ነው፡፡”
“አይ… ማለቴ… የግድ መታወቂያዎ ላይ የኾነ ብሔር መስፈር አለበት፡፡”
“የግድ”
“አዎን፣ የግድ፡፡”
“የኾነ የብሔር ታርጋ ካልተለጠፈብኝ በስተቀር መታወቂያ አላገኝም
ማለት ነው?”
“ችግርዎ ይገባኛል፡፡ ግን ብሔርዎን ሳልጽፍ መታወቂያው እንዲሰጥዎት
ባደርግ “የብሔር ብሔረሰቦችን መብት ምናምን ተፃርረኻል፡፡ ምናምን ተብዬ እገመገማለኹ፡፡”
“ስለዚኽ…”
“ስለዚኽማ ያው የአንድ ብሔር አባል መኾን አለብዎት፡፡”
“እንዲኽ
ናትና! የትኛውን ቆርጬ የትኛውን ልተወው?”
“ቆይ፣ የቅድመ አያትዎ ስም ማን ነው?”
“በአባቴ በኩል ከኾነ፣ መሐሪ እንግዳ፡፡ በእናቴ በኩል ከኾነ፣ ሌንጪቺ ባሩዴ፡፡”
“እንዲያ ከኾነ ወይ አማራ ወይም ትግሬ ነዎት፡፡”
“እንዴ! በግድ? የእናቴን ወገኖችስ፣ ያሳደጉኝን ወደየት ልጣላቸው?
እኔን ለመውለድ አባቴ ብቻውን ኮ አልነበረም፡፡”
“አይ ነገርኩዎ እንግዲኽ! የትኛውን እንደሚመርጡ ይንገሩኝ፡፡
በእርስዎ የተነሣ መገምገም አልፈልግም፡፡ እንዲያውም ይተዉት፡፡ አማራ ነዎት፡፡”
“እንዴት?”
“ኦሮምኛ ይችላሉ?”
“ትንሽ ትንሽ፡፡”
“ትግሪኛ ይችላሉ?”
“ትንሽ ትንሽ?”
“ስለዚኽ እርስዎ አማራ ነዎት፡፡”
“እንዴ?!”
“በቃ፡፡”
No comments:
Post a Comment