በዚህ በሰሙነ ፋሲካ አንድ ጧት የሰውየው በር ተንኳኳኳ፡፡ ሰውየው በሩን ሲከፍት
ያየውን ማመን አቃተው፡፡ ኢየሱስ! አዎን ኢየሱስ ከበሩ ላይ ቆሟል፡፡ በድንጋጤ ፈዝዞ ቀረ፡፡ ኢየሱስ ግን “አይዞህ፡፡
አትፍራ፡፡ እኔ ነኝ፡፡” ሲል አረጋጋውና ወደ ውስጥ መዝለቅ ይችል እንደሆነ ጠየቀው ሰውየውም “በደስታ ጌታዬ!” ሲል
መለሰለት፡፡ ኢየሱስ ወደ ቤቱ ውስጥ ገባ፡፡ ገና ወንበር ላይ እንኳ አረፍ ሳይል ሰውየው ችግሩን ይዘረዝርለት ገባ-
ያደረገውን፣ ማድረግ ያልቻላቸውን፣ ሰዎች ያደረጉበትን፣ በሰዎች የተነሣ በኑሮው ላይ እንዴት ችግር እንደተፈጠረበት፣
ወዘተ.፡፡ ኢየሱስም በፀጥታ ይመለከተው ነበር፡፡ አንዳችም
አስተያየት አልሰጠም፡፡ ዝም፡፡
“ጌታዬ እኔ ካንተ ጋር መኖር እፈልጋለሁ፡፡ እባክህን ሁል ጊዜ ናልኝ፡፡ ከእኔ
አትለይ፡፡ እኔ ኮ ብቸኛ ነኝ…”
ችግሩን ዘርዝሮ፣ ዘርዝሮ፣ አልቅሶ፣ አልቅሶ ሲጨርስ ኢየሱስ ከመንገድ እንደመጣ ትዝ
አለው፡፡
“ጌታዬ ወንበር ላይ አረፍ በል እንጂ፡፡” ብሎ ወደ ወንበሩ አመለከተውና “ቆይ ሻይ
ላፍላ፡፡” ብሎ ወደ ማድቤት ሮጠ፡፡ ሻዩን ይዞ ሲመለስ በር ተንኳኳ፡፡
ኢየሱስም “ኦ! ዘመዶቼ መጡ፡፡ ታስገባቸዋለህ?” ሲል ጠየቀው፡፡
“ጌታዬ ያንተ ዘመዶች መጥተውልኝ? እንዴታ!” የሰውየው መልስ ነበር፡፡ በሩ ላይ
ደርሶ እስኪከፍት ድረስ በልቡ ሐዋርያት፣ ሰማዕታት፣ እመቤታችን፣ ቅዱሳን፣ እጣን፣ ደመና፣ መላእክት ወዘተ. እያለ ኼደ፡፡
በሩን ሲከፍት ያያቸው ሰዎች ግን ቡጭቅጭቅ ያለ ልብስ የለበሱ
ወጣቶች፣ ጉስቁል ሕጻናት የታቀፉ የቆሸሹ እናቶች፣ የወገቦቻቸው አለልክ መጉበጥ ደጋፊ ማጣታቸውን የሚመሰክርላቸው ሽማግሌ፣
ወዘተ. ሆኑበት፡፡ አገጩ በድንጋጤ ቁልቁል ወደቀ፡፡ አስገባቸው፡፡ እንዴት እንደሆነ ሊገባው ባይችልም የተፈላው ሻይ ለሁሉም
በቃቸው፡፡ ከሻዩ ጋር አብሮ የቀረበው አንድ ሳህን ቆሎም አላለቀም፡፡
በምሳ ሰዐትም፣ በራት ሰዐትም እንደነዚሁ ዓይነት ሰዎች ያለምንም ቅድመ ማስጠንቀቂያ
የቤቱ እንግዶች ሆኑበት፡፡ ምንም እንኳ ከተለመደው ወጪው የዘለለ ወጪ ባያወጣም የቤት አከራዩ የወይዘሮ ይርገዱልሽ አስተያየት
ምን ሊሆን እንደሚችል አላጣውም፡፡ እኒያን ኳስ ኳስ የሚካክሉ ዓይኖቻቸውን ጎልጉለው በግልምጫ ቆዳውን ከላጡት በኋላ “ምነው
እኔ ይርገዱ! ቤቴን የማንም በረንዳ አዳሪና ለማኝ መሰብሰቢያና መቀለቢያ ታደርገው?! ነገውኑ ቤቴን ለቀህ እንድትወጣልኝ!”
ብለው ቀይ ካርድ ሲመዝዙበት እየታየው እንዲሁ ሲባትት ሌሊቱ ተጋመሰ፡፡ ለኢየሱስ እንዳይነግረው “እንዴት ዘመዶቼን
አላስተናግድልህም ትለኛለህ?” ብሎ ቢቀየመኝስ ብሎ ፈራ፡፡ ጠዋት ሲመጣ የነገርሁትን ችግሬን ሁሉስ መቼ ፈታልኝ፡፡ ዝም ነው
ያለኝ፡፡ ስለዚህ አለመናገር ይሻላል፤ ይልቅ ሌላ ዘዴ ልፈልግ፡፡
ሲያውጠንጥን ቆየና በስተመጨረሻ አንድ ዘዴ ብልጭ አለለት፡፡ እርሷን እያሰላሰለም ዕንቅልፍ ወሰደው፡፡
ልክ በትናንቱ ሰዐት ኢየሱስ በሩን አንኳኳ፡፡ ሰውየውም “ጌታዬ መጣህልኝ? ወደ
ቤተክርስቲያን ልኼድ ነበረ፡፡ አብረን እንኺድ?” ሲል ጠየቀው፡፡ ኢየሱስም በፈቃደኝነት ሰውየውን ይከተለው ጀመር፡፡ መንገድ
ላይ እያሉ ኢየሱስ ጎዳናው ጠርዝ ላይ ማዳበሪያ ለብሶ ወደተኛ ወደ ሰው እያመለከተው “አየኸው አያሳዝንም? እየበረደው `ኮ ነው?”
አለው፡፡ ሰውየውም “አዎን ጌታዬ እጅግ ያሳዝናል፡፡ ምን ታደርገዋለህ? ሰዉ ተጨካክኗል፡፡ ካሉን በርካታ ሚሊዬኔሮች መካከል
አንዱ እንኳ እነዚህን ሰዎች የሚያስጠልል ቤት አለመሥራቱ ያሳፍራል፡፡ የኢየሱስ አገልጋዮች ነን፡፡ የሚሉትም ጥይት የማይበሳው መኪና
ለመግዛትና የራሳቸውን ፎቅ ቤቶች ለማቆም እንጂ እነዚህን ሰዎች የሚጠቅም አንዳችም ነገር አይከውኑም፡፡ ያሳዝናል ጌታዬ፡፡
በእውነት ያሳዝናል፡፡” አለ ከወፍራሙ ጃኬቱ ላይ የደረበውን ጋቢውን እያስተካከለ፡፡ እርሱ ይህን ሁሉ ሲናገር የኢየሱስ ዓይን
ግን ጋቢው ላይ እንደነበር አስተውሏል፡፡
እንዴ ጋቢዬን እዚህ ሰጥቼ ቤተክርስቲያን በምን ልኼድ ነው? ቅዳሴውንስ እንዴት
አስቀድሳለሁ? የንስሐ አባቴ አባ ዐጻዌ ያለ ነጠላ ራቁቴን በጃኬት ቢያዩኝ ምን ይሉኛል? ደግሞ ባለፈው ጊዜ እንዳሰፋላቸው የጠየቁኝን የግል ልብሰ ተክህኖ
ስላላሰፋሁላቸው ቅር እንዳላቸው ዐውቃለሁ፡፡ የቀዳም ሥዑር ዕለት “ገብረ ሰላመ በመስቀሉ” ብለው ቀጤማ ሊሰጡኝ እቤት በመጡ
ጊዜ የሰጠኋቸውን ዐስር ብር እንዴት በንቀት እያገላበጡ እንደተመለከቷት አስታውሳለሁ፡፡ እውነት ለመናገር የሰጡኝን የሚያምር
ቀጤማ መልሰው የሚወስዱብኝ መስሎኝ ነበር፡፡ ታዲያ አሁን ደግሞ ያለ ነጠላ ቆሜ ቢያዩኝ ምን ሊሉኝ ነው? አረ ጎመን በጤና…
ሰውየው ጋቢውን በደመ ነፍስ ሙጭጭ አድርጎ ይዞ ይህን እያሰበ፣ ኢየሱስ ደግሞ
መንገዱን የሞሉትን ነዳያን እየተመለካከተ ዝም እንዳለ ቤተክርስቲያን ደረሱ፡፡ ቅዳሴ ተጀመረ፡፡ ወንጌል ከተነበበ በኋላ እስካሁን
ከሰውየው አጠገብ ቆሞ የነበረው ኢየሱስ ሊያስተምር ወደ አትሮንሱ አመራ፡፡
“ሰላም ለእናንተ ይሁን!”
“ከውጭ የቆማችሁ ወደ ውስጥ ግቡ፡፡ ዘበኞች የግቢውን ደጃፎች ክፈቱላቸው፡፡ ወደ እኔ
ይምጡ ተዉ አትከልክሏቸው፡፡” ቤተክርስቲያኑ በአንድ ጊዜ በሰዎች ተሞላ፡፡
“ግቡ አረፍ በሉ፡፡ ይህ የአባታችሁ ቤት ነው፡፡ ስለዚህም ወደዚህ ስትመጡ ማንም
የሚከለክላችሁ ቢኖር እርሱን አትስሙት፡፡ እናንተ የአባታችሁ ልጆች ናችሁና ከየትም ቦታ ይልቅ በዚህ አባታችሁ ለስሙ መቀደሻነት
በሰጣችሁ ቦታ ልትገኙ ይገባችኋል፡፡ ይህ ቤት የካህናቱ ንብረት አይደለም፤ ካህናቱ እናንተን እንዲያገለግሉበት አባታችሁ
ለእናንተ በልጁ ደም የሠራላችሁ ቤት ነው እንጂ፡፡ ስለዚህም አትፍሩ፡፡ ኑ ግቡ፡፡ ሌሎችንም ጥሩ፡፡ ቀንበራቸው የከበዳቸውን፣
ሕመማቸው ያስጨነቃቸውን፣ ድካም የበረታባቸውን “ኑ! በዚህ ቤት አብ ለዓለም ያለ አንዳች ዋጋ የሰጠው መድኃኒት አለ፡፡”
በሏቸው፡፡
የዚህ ቤት አገልጋዮች የሆናችሁም አባቴ ይህን ቤት እንድታገለግሉ የጠራችሁ እኔን
መስላችሁ እንድትኖሩ ነውና ወደ አባቴ ቤት የሚመጡትን ወንድሞቼን ቀንበር እያከበዳችሁ አታስጨንቋቸው፡፡ እናንተ በስንፍናና
በትዕቢት መግነዝ ተጠቅልላችሁ እነርሱን በድንቁርና እንዲጠፉም አታድርጉ፡፡ እናንተ እርስ በርሳችሁ እየተባላችሁ የእነርሱን
ሰላምም አትንሡ፡፡ እናንተ እየተለያያችሁ የእነርሱን አንድነት አታውኩ- እኔና አብ አንድ እንደሆንን አንድ እንዲሆኑ ድከሙላቸው
እንጂ፡፡
እነሆ ከእናንተ ውስጥ ብዙዎቻችሁን የዚህ ዓለም ገዢ ዲያብሎስ በገንዘብ ፍቅር
አሳውሯችኋል፡፡ እያንዳንዳችሁም በሌላኛችሁ ዓይን ውስጥ ያለውን ጉድፍ ለማውጣት ትጣጣራላችሁ፡፡ ሕዝቤን ትንኝን እንዲያጠራ ታስተምራላችሁ፤
እናንተ ግን ግመልን ትውጣላችሁ፡፡ በመዋጣችሁም ሰውን አታፍሩም፤ እግዚአብሔርንም አትፈሩም፡፡ ሕዝቡን “ከእኔ ሌላ አማልክት
አይሁኑልህ፡፡” መባሉን ታስተምራላችሁ እናንተ ግን እነሆ የየራሳችሁን ከንቱ ክብር አቁማችሁ ትሰግዳላችሁ፡፡ ታግዳላችሁም፡፡
ስለዚህ ዓለም ክብራችሁ ትጋደላላችሁ፤ ትገድላላችሁም፡፡ ቤቴንም ታውካላችሁ፡፡ ቤቴን የዚህን ዓለም ክብር ለማግኘት መንጠላጠያ
መሰላል አደረጋችኋት፡፡
መቅደሶቼን ትቆልፉብኛላችሁ፡፡ ጠዋት ከቤቴ ትገኛላችሁ ማታም በመሸተኞች ተርታ
ተሰልፋችሁ ሰካራሞች ንስሐ እንዳይገቡ የመንግሥተ ሰማያትን በር ትዘጉባቸዋላችሁ፡፡ ቤቴ ጸሎት ቤት መባሏ ቀርቶ ደመወዝ የምትቀበሉባት
መሥሪያ ቤት አድርጋችኋታል፡፡ መስቀሌን ዓይታችሁ መስቀላችሁን ከመሸከም ይልቅ መስቀሌን በወርቅ ቀርጻችሁ አጌጣችሁበት፡፡ ተራ
የመዋቢያ ቁስም አደረጋችሁት፡፡ ከአብ ዘንድ ያጣችሁትን ሞገስ በቀሚሳችሁ ርዝማኔና በምታነበንቧቸው ቃላት ከሰዎች ዘንድ
ልታገኙት ፈለጋችሁ፡፡ ስለ ልባችሁ ሳይሆን ስለ ልብሳችሁ ትዋትታላችሁ፡፡ እናንተ የተለሰኑ መቃብሮች የምትመስሉ፤ ሕዝቤን እንደ
እንጀራ የምትበሉ፤ ከመንጋው ስለምታገኙት ስብና ፀጉር እንጂ መንጋውን ስለሚያሳድዱትና ስለሚያስጨንቁት ተኩላዎች ግድ የሌላችሁ
ምንደኞች! እነሆ ንስሐ ትገቡ ዘንድ የእግዚአብሔር ቃል ይጠራችኋል፡፡ የወጪቱን ውጪውን ያይደለ ውስጡን አጥሩ! በሜጋ ፎን ሳይሆን
በልባችሁ አዚሙ፡፡ ሰዎች እንዲያደንቋችሁ ሳይሆን አባቴ እንዲሰማችሁ ዘምሩ፡፡ ለበዓል ድምቀት ሳይሆን ለአምላካዊው ምሕረት
ዘምሩ፡፡ “እግዚአብሔር ይፈትን ልበ ወኵልያተ” (እግዚአብሔር ልብንና ኵላሊትን ይመረምራል፡፡) የተባለው ምን ማለት እንደሆነም
አስተውሉ፡፡ “እግዚአብሔር ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ፡፡” የተባለውም ምን ማለት እንደሆነ ይግባችሁ፡፡ እነሆ
እስካሁንም ድረስ ታገሥኋችሁ፡፡
ሕዝቤ ሆይ! ለድኾች ምሕረት፣ ለተጨነቁት ነጻነት፣ ለተቸገሩት ድጋፍ አልሆናችሁም፡፡
እርስበርሳችሁ ከመተቃቀፍ ይልቅ ትነካከሣላችሁ፡፡ አንዳችሁ ሌላኛችሁን ታንገላታላችሁ፡፡ በሞቀ ብርድ ልብስ ውስጥ የምትተኙት
ብርድ እየጠባቸው ለሚያድሩት አታስቡም፡፡ ድኾችም ድኽነታችሁን ለርኅራኄ ቢስነትና ለአታላይነት መሸፈኛ ታደርጉታላችሁ፡፡ ረዥም
ሰዐት ከምግብ በመከልከል፣ በብዙ ገንዘብ መባዕ በማቅረብ፣ ታላቅ ቤተ መቅደስ በመሥራት አባቴን ደስ ማሰኘት የሚቻል
አይምሰላችሁ፡፡ እነሆ በነቢዩ ኢሳይያስ “ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፤ ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነው፡፡” ተብሎ የአባታችሁ
ሐዘን ተነገረ፡፡
ባሎች የልጅነት ሚስቶቻችሁን እያሳዘናችሁ፤ ሚስቶች የባሎቻችሁን ልቡና እየሰበራችሁ፤
ወንድማማቾች ፍርድ ቤቶችን በክሶች እያጨናነቃችሁ፤ ጎልማሶች እርስ በርሳችሁ እየተናናቃችሁ፤ ዓይኖቻችሁ በዝሙትና በፍቅረ ንዋይ
ታውረው ፍርድ እያጓደላችሁ፣ ድኻ እየበደላችሁ፤ በሚዛን እያጭበረበራችሁ፤ ለወንድሞቻችሁም አንዳችም ርኅራኄ ሳታሳዩ ቤተ መቅደስ
በመመላለስ ብቻ፣ ወይም ትልቅ መስቀል አንገታችሁ ላይ በማሰር ብቻ፣ ወይም በዓል ለማክበር ግርግር በማለት ብቻ እግዚአብሔርን የምትሸነግሉት
አይምሰላችሁ፡፡ እግዚአብሔርን በራሳችሁ አምሳል አትሳሉት፡፡
እግዚአብሔር በልባችሁ መሰበር እንጂ በሆዳችሁ መራብ የሚደሰት አምላክ አይደለም፡፡
ጮኻችሁ የዘመራችሁትን ሳይሆን ከልብ የዘመራችሁትን ይቀበላል፡፡ በጠብ የከመራችሁለትን ሳይሆን በፍቅር የቃረማችሁትን
ይወድዳል፡፡ በየጥጋ ጥጉ የለጠፋችሁትን ጥቅስና ሥዕል ሳይሆን በየደቂቃው የምትኖሩትን ልጁን የሚመስልን ኑሮ ይፈልጋል፡፡ እነሆ!
ቃሉን እንድታጠኑለት፣ ትእዛዛቱን እንድትማሩለት ይጣራል፡፡ ጽድቃችሁን ሳይሆን ምሕረቱን እንድትታመኑበት፣ ክብራችሁን ሳይሆን
አምላክነቱን እንድትመኩበት ይጠይቃችኋል፡፡ ልጆች ሆይ! ይህን ዓለም ኑሩበት እንጂ በፍቅሩ አትታሠሩ፡፡ እናንተ ይህንን ዓለም
የሠራው ልዑል አምላክ ልጆች ናችሁና በሥራው ሠሪውን ተመልከቱት፤ አድንቁት፤ አመሥግኑት፡፡ በሥዕሉ ውስጥ ሠዐሊውን እዩት፤
ውደዱትም፡፡ እርሱ እናንተ የማታዩዋቸውን ሌሎች ስንት ድንቅ ሥዕሎች ሊሠራ እንደሚችል አስተንትኑ እንጂ ጣዕሙ ከምላስ እስከ
ጉሮሮ ብቻ በሆነው በዚህ ዓለም ፍቅር አትታወሩ፡፡
ዳግመኛም አገልጋዬ አውጉስጢኖስ “ጌታ ሆይ! የሚወዱኝን ባንተ የሚጠሉኝንም ስላንተ
እንድወድ አድርገኝ፡፡” ብሎ እንደ ጸለየው እናንተም እንዲሁ ስለሰማዩ አባታችሁ ብላችሁ ሁሉን ውደዱ፡፡ ደቀ መዛሙርቴ
እንደሆናችሁ ለሰዎች የምትመሰክሩትም በመጀመሪያ እርስ በርሳችሁ በመዋደድ ይሁን፡፡ በፍቅሬ ኑሩ፡፡ እነሆ! የእግዚአብሔር
መንግሥት በመካከላችሁ ናት፡፡
ቤት ክርስቲያኑ ፀጥ ረጭ ብሏል፡፡ አንድም ሰው “ማነህ?” ሊለው የወደደ አልነበረም፡፡
ሰውየው ልቡ ጭንቅ አለው፡፡
ወይ ጣጣ! አሁን እስኪ ዝም ቢል ኖሮ ምን አለበት? ሰዉ ሁሉ በእኔ ላይ በጠላትነት
እንዲነሣ ሊያደርግብኝ ነው እንዴ? አሁን እንዲህ ያለ ወቀሳ ምን ይባላል?
ቅዳሴ ተፈጸመ፡፡
ሰውየው ከቤተክርስቲያኑ ሊወጣ ሲል አባ ዐጻዌ ከሰውየው ፊት ለፊት ቆመው አያቸው፤
እርሱን እየጠበቁት መሆኑ ገብቶታል፡፡ “ምነው ምነው ምነው? እንዴት እንዲህ ተወልደን ባደግንበት፣ ተክነን በከበርንበት ሀገር
እንዲህ ጉዳችንን ሁሉ ዘክዝኮ የሚያሳጣን ሰባኪ ይዘህብን መጣህ? ልትሰድበን ከፈለግህ አንተው አትሰድበንም ኖሯል? እኔ ባለፈው
የጠየቅሁህን ጥያቄ የጠየቅሁህ ኮ ለበረከት እንዲሆንህ ብዬ ነበረ፡፡ ያሳዝናል፡፡ በጣም በጣም ያሳዝናል፡፡ ሰካራሞች አልኸን?
ገንዘብ አምላኪዎች አልከን?” ጭንቅላታቸውን እየነቀነቁ ሄዱ፡፡
ሰውየው የምር ሐሳብ ገባው፡፡ አንገቱን ደፍቶ ጥቂት እርምጃ እንደተራመደ ትከሻውን
ከብዶት ወደ ግራ ዞረ የቢሮ አለቃውና ቤተክርስቲያኑን በማሠራት ስሙ ከፍ ብሎ የሚጠራለት አቶ ዳርም የለህ ነው፡፡ ከዚህ ሰውዬ
ጋር ወትሮውንም ሰላም አይደሉም፡፡ “ስማ አንተ?” አለው ጋቢውን አፈፍ አድርጎ፡፡ ለካ እዚህ ድረስ ተናንቀናል፡፡ አላወቅሁም
ነበር፡፡ ብለህ ብለህ ድራሹ የማይታወቅ ባሕታዊ በአሉባልታ ሞልተህ አምጥተህ ታሰድበን፡፡ ቤተክርስቲያን ውስጥ ነኝ ብዬ እንጂ
ዛሬ አከርካሪህን ሰብሬ አስቀምጥህ ነበር! ጭራሽ በእጄ ባሠራሁት ቤተክርስቲያን ሰባኪ አምጥተህ ሸንጋይ፣ አታላይ ታሰኘኝ?”
ሰውየው መልስ አልሰጠም፡፡ ጋቢውን ሲለቅለት አሁንም አንገቱን ደፍቶ መንገዱን
ቀጠለ፡፡ የንስሐ አባቱ ቅሬታ ከአለቃው ቁጣ ጋር ተደማምሮ ድንጋጤውን ከፍ አድርጎታል፡፡ በቃ ይኼ ሰውዬ ከበላይ አለቆች ጋር
ተስማምቶ የሥራ ዕድገቴን ሊያስከለክለኝ ነው፡፡ ወይ ጉድ! ወይ ኪሣራ!
“ስማ እንጂ! ትናንትና እርሷ የለችም ብለህ የማንንም ለማኝና በረንዳ አዳሪ በቤቴ
ላይ ስታተራምስብኝ እንደዋልህ ተነግሮኛል፡፡ አረ ለመሆኑ የኔ ቤት ክብሩ አልታይህ ያለው ከመቼ ወዲህ ነው በል? ገዳም ልሳለም
ብኼድ የሞትሁ መሰለህ?”
“አረ… እኔ… እማማ… እኔ ኮ…” የሚናገረው ጠፋው፡፡
“በል በል በል አትቀላምድ! ደግሞ ይባስ ብለህ በገንዘባችን ባሠራነው ቤተስኪያን
ሰባኪ አምጥተህ አታላዮች! እግዜርን በጉቦ ልታታልሉ የምትፈልጉ ሌቦች! ብለህ አሰደብኸን አሉ፡፡ ምነው ይህን ያህል ራስህን
አጠደቅኸውሳ?” ሴትየዋ ጮኸው ይናገሩ ስለነበር ጎረቤቶች ሁሉ ከየበራቸው ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል፡፡
ሰውየው ቀይ ፊቱ በኀፍረት ቲማቲም መሰለ፡፡ ዝም ብሎ ወደ ቤቱ አቅጣጫ መራመድ ጀመረ፡፡
ወ/ሮ ይርገዱልሽም አንድ ሁለት እርምጃ እየተከተሉ በነገር ከለበለቡት በኋላ ተመለሱ፡፡
ቤቱ ገባ፡፡ እንዴ ይኼ ጌታ ኢየሱስ ግን ምን ማለቱ ነው? እኔ ሰላሜ ሁንልኝ ብለው
አካባቢዬን በሙሉ የጦር ቀጠና አድርጎት እርፍ ይበል? አሁን አከራዬ ከቤታቸው ቢያስወጡኝስ? አባ ዐጻዌ ከቤተክርስቲያን ውስጥ
ያለኝን ሕይወት ምስቅልቅሉን ቢያወጡትስ? ያልሆነ ስም ሰጥተው በሌሎች ሰዎች እንድጠላ ቢያደርጉስ? የዕድገቴ ነገርማ በቃ
አከተመለት፡፡ እንዲሁ ከቀጠለ ምን ዓይነት ኑሮ ይኖረኛል? አሁን ኢየሱስ ነገ ሲመጣ ምን ላደርገው ነው? መሥሪያ ቤት ይዤው ብኼድስ?
እንዴ ይኼማ አይሆንም፡፡ ደግሞ ጭራሽ ነገር ዓለሙን አደበላልቆት ይረፍ? ምን ይሻላል? ያለ ኢየሱስ መኖር አልችልም፡፡ እርሱ አምላኬ
ነው፡፡ እወድደዋለሁ፡፡ ግን ከእርሱ ጋር ስሆን ደግሞ ዓለሙ ሁሉ የጦር ቀጠና ሆነብኝ፡፡ ለረዥም ሰዐት ሲያስብ ቆየና አንድ
መላ ብልጭ ስላለለት ተነሥቶ ወጣ፡፡
ሦስተኛ ቀን
እንደተለመደው ጧት ላይ በሩ ተንኳኳ፡፡ ጌታ ኢየሱስ ነው፡፡ ጌታዬ መጣኽልኝ? ግባ፡፡
ሰውየው ደስ ብሎታል፡፡ የትናንቱ ጭንቀቱ ሁሉ የት እንደገባ እንጃ፡፡ ኢየሱስ ሲገባ በመጀመሪያው ቀን ያረፈበትን ወንበር አላገኘም፡፡
ይልቁንም ወንበሩ በነበረበት ቦታ ላይ አንድ የሚያምር ሳጥን ተቀምጧል፡፡ ሰውየው ኢየሱስን ሳጥኑ ውስጥ እንዲቀመጥ ጋበዘው፡፡
ከዚያም በቆንጆ ማስቀመጫ ላይ የተደረደሩ የሚበሩ ሻማዎች ከሳጥኑ ፊት አቀረበ፡፡ በግራና በቀኝ በሚበሩት ሻማዎች መካከልም
መጽሐፍ ቅዱስ አኖረ፡፡ ቀጥሎም ከሳጥኑ ፊት ወድቆ ሰገደና እንዲህ አለ፡፡ “ጌታዬ ሆይ! ከዚህ ሳጥን አትውጣ፡፡ በዚህ በኩል
ባለፍሁ ቁጥር ሻማ አበራልሃለሁ፤ እሰግድልሃለሁ፤ ወዳንተ እጸልያለሁ፡፡ ከዚህ ቤት ስወጣ ግን የትም ቢሆን ተከትለኸኝ
አትምጣ፡፡ ልኑርበት፡፡”
ሰውየው ከወደቀበት ቀና ሲል ኢየሱስ የለም፡፡ ቅድም ዝግ የነበረው መጽሐፍ ቅዱስ ግን
ተገልጧል፤
“በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፡፡ ነገር ግን አይዟችሁ! እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ፡፡” Based on the books by Fr. Gerard W. Hughes (SJ) entitled "God, Where Are You?" and "God of Surprises".
No comments:
Post a Comment