Tuesday, April 3, 2012

አንድምታ (The Ethiopian way of Interpreting the Holy Bible)

ከቀደሙ ኢትዮጵያውያን አበው መካከል ቅዱሳት መጻሕፍትን እጅግ ከማፍቀራቸው የተነሣ ንባቡ አላጠግብ ቢላቸው ወደ ትርጓሜ ዘልቀው፣ በዓለም የነበረውን የቅዱሳት መጻሕፍት ዕውቀት መሠረት አድርገው እነርሱ ራሳቸው በትርጓሜ እየተራቀቁ፣ እየመጠቁ የሚጓዙ አበው ነበሩ፡፡ ከእነዚህ አበው የትርጓሜ ሥራዎች መካከል አንድምታ በመባል የሚታወቀው የትርጓሜ አካሄድ አንዱ ነው፡፡

ምንም እንኳ አንድምታ ምንጩ በልዩ ልዩ ሀገራት የነበሩ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ቢሆኑና ለኢትዮጵያዊው ትርጓሜ እነርሱን መሠረት ቢያደርጉም ኢትዮጵያውያኑ ሊቃውንት እንዲሁ በመዋስ ብቻ ግን አልተወሰኑም፡፡ ይልቁንም እነርሱም ዕውቀታቸው ያራቀቃቸውን፣ እምነታቸው ያመጠቃቸውን ያህል መሠረቱን አስፋፍተውታል፤ አሳድገውታል፤ አምጥቀውታልም፡፡ ሆኖም ይህ የምጥቀት ጉዞው በአንዳንድ ምክንያቶች የተደናቀፈባቸው፣ የጫጨባቸው እንዲሁም የተገደለባቸው አጋጣሚዎችም ነበሩ፡፡ ከእነዚህም መካከል አንዱ ትርጓሜ በየጊዜው እያደገና እየሰፋ የሚሄድ ነገር ሳይሆን እንደጸሎት የሚደገም የማይሻሻልና የማይታረም እንደዶግማ ፍጹም ተደርጎ መቆጠሩ ነው፡፡ ለምሳሌ፡- እርሳቸው ራሳቸው የትርጓሜ መምህር የነበሩትና ዘመኑን የቀደመ ኢኩሜኒካል አስተሳሰብ የነበራቸው መጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴ የሚከተለውን ጽፈው ነበር፡-


በ17ኛው ምእት የነበሩት አራት ዓይና[1] መምህር ኤስድሮስ የቀደመውን ትርጓሜ ሲያስተምሩ ከኖሩ በኋላ ብዙ መጻሕፍትን አንብበው የመጀመሪያውን ትርጉም በማሻሻል ብዙ አስተያየት ጨምረው የጠመመውን አቅንተው፣ በመምህርነት ተመድበው ያስተምሩ የነበሩት ደቀመዛሙርታቸውን ሁሉ ጠርተው ለማስተማር ቢሞክሩ
“ንሕነሰ ኢተወለድነ እም ዝሙት፡፡”
“እኛስ ከዝሙት አልተወለድንም፡፡”  
በማለት የተሻሻለውንና አስተያየት የተጨመረበትን ትርጓሜ ለመቀበል ፈቃደኞች ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የአንድምታ ትርጓሜ ትምህርት ቤት ለሁለት ተከፍሏል፡፡ (2011፣ 23)[2]     

ይህንንም ለውጥን እምቢኝ ከሚለው ባህላችንና ባህላችን ከፈጠረውና ከሚኖርበት ሰብእናችን ጋር አያይዘን ካየነው ብዙም የሚያስገርም አይሆንም- የተለመደ ስፍናችን ነውና፡፡

የእነዚህ አበው ሥራዎች የቀረቡበት ቋንቋ ዛሬ ያለው ትውልድ ከሚናገረው በእጅጉ የተለየ በመሆኑ የተነሣ ይህ የእኛ ዘመነኛው ትውልድ በቀላሉ አንብቦ ይረዳቸዋል ብሎ ማሰብ ያዳግታል፡፡ ነገር ግን ትዕግሥትን በእጁ አድርጎ ለማጥናትና ለመመራመር ፈቃደኛ የሆነ ሰው ግን የእኒህን አበው የእምነታቸውን ጽንዓት፣ የዕውቀት ጥልቀት፣ የምናብ ስፋትና የኂሳዊ አስተሳሰባቸውን (Critical thinking) ንቃት እያጤነ ሊደሰት፣ ሊመሰጥ፣ ሊራቀቅ፣ በእነርሱ አንደበትም ሊጸልይ ይችላል፡፡

ለዚህ ምሳሌ ይሆናችሁ ዘንድ ከወንጌል አንድምታ አንዲት ሰበዝ መዝዤ ላሳያችሁ፡፡ ብዙዎቻችን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጻድቃን በበግ ኃጥኣን በፍየል እንደሚመሰሉ አንብበናል፡፡ ወይም ሲነበብ ሰምተናል፡፡ ግን ፍጥረቱን ሁሉ ከፈጠረ በኋላ “መልካም እንደሆነ አየ” ተብሎ በኦሪት ዘፍጥረት ላይ የምናነበው እግዚአብሔር እንዴት አንዱን ፍጥረት መልካም አንደኛውን ደግሞ ክፉ ሊያደርጋቸው ቻለ? ከፈጠረው ፍጥረት መካከል መጥፎ ፍጥረት አለ ማለት ነው? ብለን መጠየቃችን አይቀርም፡፡ አበው ግን ምሳሌውን እንደሚከተለው ይተነትኑታል (እግረ መንገዳችሁን በእንስሳት ጠባያት ጥናት ላይ የነበራቸውን ዕውቀት አስተውሉልኝማ)፡-

በጎች ጻድቃንን በቀኙ ያቆማቸዋል፡፡ ፍየሎች ኃጥኣንንም በግራው ያቆማቸዋል፡፡ (ማቴ 25፡31)
ጻድቃንን በጎች አላቸው፡፡
በግ ትሑት ነው ወደ ምድር እያየ ይሔዳል፡፡ ጻድቃንም ዕለተ ሞታቸውን እያሰቡ ይኖራሉና፡፡ ከርስቱ ከመቃብር ሌላ የሚያስብ ሰነፍ ነው እንዲል፡፡
በግ ኀፍረቷን በላቷ ትሰውራለች፡፡ ጻድቃንም የራሳቸውን ኃጢኣት በንስሐ የወንድማቸውን ኃጢኣት በትዕግስት ይሠውራሉና፡፡
አንድም በግ ጭቃውን አይጸየፈውም ጻድቃንም መከራውን አይሰቀቁትምና፡፡
አንድም በግ ከዋለበት አይታወቅም (ያለበትን አካባቢ በጩኸት በቅብጥብጥነት አያምስም)፤ ጻድቃንም ካሉበት አይታወቁምና፡፡
አንድም ከበግ አውሬ አንዱን የነጠቀለት እንደሆነ ይሸሻል፡፡ ከሸሸም በኋላ አይመለስም- “በግ ከበረረ የሰው ልጅ ከተመረረ” እንዲሉ፡፡ ጻድቃንም ከባልንጀራቸው አንዱ የሞተ እንደሆነ ይመንናሉ ከመነኑም በኋላ አይመለሱምና፡፡
አንድም በግ ኑሮው በደጋ ነው፡፡ ጻድቃንም ኑሯቸው በመንግሥተ ሰማይ ነውና፡፡
በቀኝ ያቆማቸዋል አለ:: የሚመጣው በክበበ ትስብእት[3] (በሰውነቱ) ነውና፡፡
አንድም ቀኝ ኃያል ነው ጻድቃንም ለበጎ ሥራ ኃያላን ናቸውና፡፡
አንድም ቀኝ ፈጣን ነው ፈጣኖች ናቸውና ቅን ነው ቅኖች ናቸውና፡፡
አንድም በክብርም ሲል ነው፡፡

ኃጥኣንን አጣሊ (ፍየሎች) አላቸው ፍየል ትዕቢተኛ ናት ሽቅብ ሽቅብ ትመለከታች፡፡
ኃጥኣንም ትዕቢተኞች ናቸውና፡፡
አንድም ፍየል ኀፍረቷን በላቷ አትሠውርም ኃጥኣንም የወንድማቸውን ኃጢኣት በትዕግሥት የራሳቸውን ኃጢኣት በንስሐ አይሠውሩትምና፡፡
አንድም ፍየል ጭቃውን ይጸየፈዋል፡፡ ኃጥኣንም መከራውን ይሰቀቁታልና፡፡
አንድም ፍየል ከዋለበት ሁሉ ከእህል ከተክል እየገባ ሰው ሲያሳዝን ይውላል፤ ኃጥኣንም ሰው ሲያሳዝኑ ይኖራሉና፡፡ አንድም ፍየል አንዱን አውሬ የነጠቀበት እንደሆነ ለጊዜው ይሸሻል ኋላ ችፍ እያለ ይቀርባል (አውሬውም) እየነጠቀ ይፈጀዋል፡፡ ኃጥኣንም ከወገናቸው አንድ የሞተ እንደሆነ “መነንን” ይላሉ፡፡ ተመልሰው ግን በርስቱ በጉልቱ በቤቱ በንብረቱ ሲሉ ይገኛሉና፡፡
አንድም ፍየል ኑሮው በቆላ ነው፤ ኃጥኣንም ኑሯቸው ቆላ ገሃነም ነውና፡፡
በግራው ያቆማቸዋል አለ፡፡ የሚመጣው በክበበ ትስብእት (በሰውነቱ)[4] ነውና፡፡ አንድም፡፡ ግራ ደካማ ነው ኃጥኣንም ለበጎ ሥራ ደካማ ናቸውና፡፡ ግራ ጠማማ ነው ጠማሞች ናቸውና፡፡[5]



[1] አራት ዓይና የሚለው ሐረግ አራቱን የትርጓሜ ቤቶች ጠንቅቀው ለተማሩ ሊቃውንት የሚሰጥ የኢትዮጵያውያን ሀገረሰባዊ መዓርግ ነው፡፡
[2] ሰይፈ ሥላሴ ዮሐንስ፡፡ 20011፡፡ “የአንድምታ ትርጓሜ በኢትዮጵያ ባህልና ትምህርት፡፡” በውስተ Ethiopian Review of Cultures Vol XIV. Hiruy Abdu and Henok yared (ed.) Addis Ababa, Capucin Franciscan Institute of Philosophy and Theology.
[3] በአምላክነቱማ መምጣት መሔድ የለበትም፤ ግራና ቀኝም የለውም- ቅዳሴ ማርያም “ለመለኮት ወርድና ቁመት፣ ላይና ታች፣ ቀኝና ግራ የለውም፡፡” እንዲል፡፡ እርሱ ከቦታና ከጊዜ መታገጊያ ውጪ ነውና፡፡ ነገርግን በዳግም ምጽአቱ የሚገለጠው በሰውነቱ፣ ከእመቤታችን በነሣው ሥጋ ስለሆነ በቀኙ ያቆማቸዋል ተባለ፡፡
[4] በግርጌ ማስታወሻ ቁጥር ሁለት ላይ የተሰጠውን ማብራሪያ ይመልከቱ፡፡
[5] ወንጌል ቅዱስ፤ ከቀድሞ አባቶች ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው ንባብና ትርጓሜው፡፡ 1995፡፡ አዲስ አበባ፣ ትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት፡፡

No comments:

Post a Comment