Saturday, November 1, 2014

ቡርኪና ፋሶ፤ የሐቀኞች ምድር


ከቅኝ ግዛት ወደ ነጻነት
ከ1896 ጀምሮ እስከ 1960 ድረስ ለ65 ዓመታት በፈረንሳይ ቅኝግዛት ሥር ስትማቅቅ የኖረች ሀገር ናት፡፡ ፈረንሳውያኑም “የፈረንሳይ የላይኛው ቮልታ” እያሉ ነበር የሚጠሯት- በሀገሪቱ ውስጥ የሚፈሱትን ጥቁሩ ቮልታ፣ ነጩ ቮልታና ቀዩ ቮልታ የሚባሉ የሦስት ወንዞቿን ስም መሠረት አድርገው፡፡ በ1960 ዓ.ም. ከፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ስትላቀቅ ደግሞ ስሟ “የፈረንሳይ” የሚለውን ሸክም አራግፎ “ሰሜናዊ ቮልታ” ተባለ፡፡ የመጀመሪያ ፕሬዚደንቷም ማውሪስ ያሜዖጎ ኾኑላት፡፡
የአምባገነን አዙሪት ፅንስ
ማውሪስ ያሜዖጎ ወደ ሥልጣን በመጡ ማግሥት የቮልታ ዴሞክራሲያዊ ኅብረት ከሚባለው የእርሳቸው ፓርቲ ውጪ ሌሎች የሀገሪቱን ፓርቲዎች በሙሉ ከእንቅስቃሴ አገዱ (ልማቱን ለማቀጠል 60 ዓመት የእኛ ፓርቲ ሥልጣን ላይ መቆየት አለበት፤ ሌሎቹ ፓርቲዎች ፀረ ልማት፣ ፀረ ዴሞክራሲ፣ ፀረ ምንጥስዮ፣ ፀረ ቅብርጥስዮ፣ ወዘተ. ናቸው ብለውም ዲስኩር አሰምተውም ይኾናል፤ እንጃ!)፡፡ በድርጊታቸው ያዘነው ፖለቲካዊ ተሳትፎው የታፈነበት ሕዝብ በ1966 በተማሪዎች፣ የሠራተኛ ማኅበራትና የመንግሥት ሠራተኞች ሀገሪቷን በአድማና በሰልፍ አንቀጠቀጧት፡፡ 
የሀገሪሽ መረበሽን ለማስቆም በሚል ሰበብም ጦር ሠራዊቱ በጉዳዩ ላይ እጁን አስገባና ሕገ መንግሥቱን አገደ፤ ፓርላማውን በተነ፤ ፕሬዚደንት ያሜዖጎንም ከሥልጣናቸው አባረራቸው፡፡ ከዚያ በኋላ ሀገሪቱ ምንም የተረጋጋና ኹሉን ያማከለ መንግሥት ልታገኝ አልቻለችም፡፡ አንዱ ወታደር በሌላው እየተፈነቀለ እስከ 1987 ድረስ ሌተፍናንት ኮሎኔል ሳንጎሌ ላሚዛና፣ ኮሎኔል ሳዬ ዜርቦ፣ ሜጀር ዣንክላውድ ኦዌድራዖጎ፣ ካፒቴን ቶማስ ሳንካራ የሚባሉ አራት ወታደሮችን መሪዎች አድርጋ አፈራርቃለች፡፡ 

ቶማስ ሳንካራ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲኾኑ “ለውጥ ያስፈልጋል!” በሚል መፈክር ነበር፡፡ “ሀገሪቱ ለውጥ ያስፈልጋታል፤ ለውጡ የሚጀምረው ደግሞ ከስሟ ነው፡፡” በማለትም የሀገሪቷን ስም ከሰሜናዊ ቮልታነት ወደ ቡርኪና ፋሶ ቀየሩት፡፡ ስሙን የፈጠሩት ራሳቸው ቶማ ሳንካራ ናቸው፡፡ ቃሉን ለማበጁትም ሙሬ እና ዲዮላ ከሚባሉ የሀገሪቱ ኹለት ዐበይት ቋንቋዎች አንድ፣ አንድ ቃል ተውሰዋል፡፡ በሙሬ ቋንቋ “ቡርኪና” ማለት “ሐቀኛ” ሲኾን፣ “ፋሶ” ደግሞ በዲዮላኛ “አባት ሀገር” ማለት ነው፡፡ እነዚኽን ኹለት ቃላት አገጣጠሙና ቡርኪና ፋሶ አሏት- “የሐቀኞች ምድር”፡፡

ልማታዊው ካምፖሬና እንከን የለሽ ምርጫዎቹ 

ይኹን እንጂ፣ የቶማስ ሳንካራ መንግሥት ብዙም አልከረመም፡፡ በ1987 በካፒቴን ብሌይስ ካምፖሬ የተመራ መፈንቅለ መንግሥት ቶማስ ሳንካራን ገድሎ የመፈንቅለ መንግሥቱን መሪ፣ ብሌይስ ካምፖሬን፣ የሀገሪቱ ፕሬዚደንት አደረገ፡፡ ከ1987 ጀምሮም እስከ 2014 ድረስ ካምፖሬ ሀገሪቱን ሕዝቧን እንደ ሰም አቅልጦ እንደ ገል ቀጥቅጦ ገዛቸው፡፡ ምዕራባውያን ወዳጆቹም፣ በተለይም ደግሞ የቀድሞዋ ቅኝ ገዢ ፈረንሳይ፣ ቡርኪና ፋሶ በካምፖሬ ዘመን ፈጣን ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት እንዳሳየች፣ ሰላም እንደሰፈነባት መሰከሩለት፡፡ እርሱም ዴሞክራሲያዊነቱን ለማመስከር በ1990፣ በ1998፣ በ2005፣ በ2010 “እንከን የለሽ” ሀገር ዐቀፍ ምርጫዎችን አካኺዷል፡፡ የምርጫዎቹ ኹሉ አሸናፊም “ልማታዊው ካምፖሬ” ነበር፡፡ 

ሀገሪቱ ፓርላማ ቢኖራትም ፓርላማው ካምፖሬ አፍንጫውን ሲሠረስረው የሚያስነጥስ፣ ካምፖሬ ሲከፋው የሚያለቅስ፣ ካምፖሬ ሲቀልድ የሚስቅ የአሻንጉሊቶች ሸንጎ ኾኖ ነበር፡፡ 



 እንደ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያሉ ዐለምዐቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ካምፖሬን ዐይንኽ ላፈር ካሉት ቆይተዋል፡፡ አገዛዙ በየጊዜው በጋዜጠኞችና የሀገራቸው ዕድል ፈንታ ጽዋ ተርታ ያገባናል በሚሉ ዜጎች ላይ የሚያደርሰው አፈና፣ ወከባ፣ ሥቃይ፣ ግድያና ምንዳቤ ምን ያኽል ከባድ እንደኾነ በየጊዜው ተጽፏል፤ ተነግሯልም- ካምፖሬ የዝኆን ዦሮ ይስጠኝ አለ እንጂ፡፡ ሕዝቡም “ሸጌዋ መቻል ምን ይከፋል፤ ሆድ ካገር ይሰፋል” እያለ ቻለው፡፡

የሕዝብ ቁጣ

ካምፖሬ ሥልጣን ላይ ከወጣ በኋላ እንደቀልድ 27 ዓመታት ነጎዱ፡፡ እርሱ ግን “የልማቱ ጉዳይ በጥብቅ ስላሳሰበው”ና እርሱ ከሌለ ልማቱ እንደሚቋረጥ ስላመነ "የልማቱን ቀጣይነት ለማረጋገጥ" የአሻንጉሊቶቹን ሸንጎ ሰብስቦ የሥልጣን ዘመኑን የሚያራዝም ሕግ እንዲያወጡለት ጠየቃቸው፡፡ 

እነርሱም “ልማታዊው መሪያችን ከሀገራችን ጋር በጥልቅ ፍቅር ወድቀዋል፤ ፍቅርን ማሰናከል ደግሞ አይገባም፡፡” በማለት ሕጉን ሊያጸድቁለት ሽር ጉድ ማለት ጀመሩ፡፡ ሕዝቡ ደግሞ የሰውየው ፍቅር “ከሀገሪቱ ሳይኾን ከአልጋዋ ጋር ነው፡፡” ብሎ አኮረፈ፡፡ ካምፖሬም “እረኛ ቢያኮርፍ ምሳው እራቱ ይኾናል እንጂ ምን ሊያመጣ” ብሎ ኩርፊያውን ችላ አለው፡፡ ይኼኔ ኩርፊያው ወደ ቁጣ ተቀየረ፡፡ የተቆጣው ሕዝብም የአሻንጉሊቶቹ ሸንጎ ድረስ ኼዶ አሻንጉሊቶቹን ቢያጣ በገዛ ገንዘቡ የተሠራውን የሸንጎውን አዳራሽ እሳት ለቀቀበት፡፡ የልማት ዲስኩሩ ያደነቆረውን የቴሌፍጀን ጣቢያውንም በቁጥጥሩ ሥር አዋለ፡፡ ካምፖሬም ነፍሴ አውጭኝ ብሎ ፈረጠጠ- “ለልማቱ ብሎ”፡፡

 

ያ የመጀመሪያው ፕሬዚደንት ማውሪስ ያሜዖጎ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በማፈንና በማገድ የጀመረው የአምባገነንነት መንገድ እነሆ ሀገሪቱን  ከጭቆና አዙሪት ውስጥ ከትቷት፣ ጭቆናም ድኽነትን በዓይነት በዓይነቱ እየቀፈቀፈ ዛሬም በዓለም ላይ በችጋራምነታቸው ከሚታወቁ ሀገራት አንዷ ኾናለች- የሐቀኞቹ ምድር፡፡ 


አኹን የጦር ሠራዊቱ ሰላምና መረጋትን ለማስፈን በሚል ሰበብ መንግሥት ኾኗል፡፡ ሀገሪቱ ከገባችበት የመፈንቅለ መንግሥት- አምባገነን- መፈንቅለ መንግሥት- አምባገነን አዙሪት ውስጥ ትወጣ ይኾን? ሕዝቡ የበሽታውን ምልክት ነቅሏል፤ በሽታውን መንቀል ይችል ይኾን? እንጃ!

የአምባገነን ሥርዓት አንዱ ክፋቱ በዘመነ መንግሥቱ ሌሎች የፖለቲካ ድምፆች እንዲሰሙና እንዲደራጁ ስለማይፈቅድ አምባገነን ሥርዓቱ ሲወድቅ የሥልጣን ክፍተት (power vacuum) መፍጠሩ ነው፡፡ በሌላ አባባል አምባገነን ሥርዓት ፈጠነም ዘገየም መውደቁ አይቀርምና እርሱ ሲወድቅ እርሱን ተክቶ የሀገሪቱን ምጣኔ ሀብታዊና ፖሊቲካዊ ጉዳዮች የሚከናውን በቅጡ የተደራጀ ኃይል አይኖርም፡፡ ይኽን ክፍተት በመጠቀም ወደ ሥልጣን የሚመጡት ደግሞ ኹሌም ወታደሮች ወይም ታጣቂ ቡድኖች መኾናቸው ታሪካዊ ሐቅ ነው- የተሻለ መደራጀትና የእዝ ሰንሰለት የወታደራዊ ተቋማት ተፈጥሮ ነውና፡፡ ከጥቂት ቆይታ በኋላም ከወታደሮቹ የሥልጣን ፍቅር አናታቸው ላይ የወጣባቸውና ብልጣብልጦች የኾኑ ተቀናቃኞቻቸውን በሙሉ ሙልጭ አድርገው ያስወግዱና ይነግሣሉ፡፡ የ1966ቷንና የ1983ቷን ኢትዮጵያ፣ የ2011ዷን ግብፅ፣ የመን፣ ሊብያን፣ ወዘተ. መመልከት ነው፡፡
በምክንያታዊነት የሚመራና መተማመን የመላበት ዴሞክራሲያዊ መደራጀት ሳይካኼድ አብዮት ማንሣት ጥቂት ቆይቶ “The Beautyful Ones Are Not Yet Born.” እያሰኘ ያስለቅሳል- ቆንጆዎችን ያጨነግፋልና፡፡ ቆንጆዎቹ እንዲወለዱ ዕውቀትና ምክንያታዊነት የሚመሩት፣ መተማመን የሞላበት ዴሞክራሲያዊ መደራጀት ያሻል፡፡ ያሉትን ደካማ መደራጀቶች ከግብታዊነት ወደ ምክንያታዊነት፣ ካለመተማመን ወደ በአንድ ርእዮተ ዓለም ተማምኖ መሰባሰብ ማሳደግ ያሻል፡፡
የሐቀኞች ምድር ሆይ! ሐቀኞችሽ ይወለዱልሽ! ቆንጆዎቹ ልጆችሽ ዛሬ ይወለዱልሽ! አነባኹ!   

The vicious circle of  oppression




   
  

      

No comments:

Post a Comment