Tuesday, November 11, 2014

ልማትና ባርነት

ልማትና ባርነት አይተዋወቁም፤ ለምን? ዋናውና መሠረታዊው ምንያት ባርያ ለነገ አለመጨነቁ ነው፤ ባርያ ከራሱ ውጭ የሆነ ነገር ምንም የለውም፤ ለራሱም ቢሆን ባለቤት አይደለም፤ ባርያ የጌታው ዕቃ ወይም መሣሪያ ነው፤ ለዕቃ ወይም ለመሣሪያ የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ የሚያስብለት ጌታው ነው፤ ባርያ ለነገ ምን እበላለሁ? ነገ ምን እጠጣለሁ? የት እውላለሁ? የት አድራለሁ? እያለ አይጨነቅም፤ ባርያ ኃላፊነት የለበትም፤ በቅሎ ወይም ፈረስ፤ ወይም ቢላዋ፣ ወይም ማገዶ፣ ወይም ጩቤ፣ ወይም ጠመንጃ ምን ኃላፊነት አለባቸው? ባርያ መብት የለውም፤ ያለው ግዴታ ብቻ ነው፤ ጌታው ለጥቅሙ ሲል ለባርያው ከሚያደርገው ሌላ ግዴታ የለበትም፤ በባርያው ላይ ግን ሙሉ መብት አለው፡፡ በጌታውና በባርያው መሀከል ያለው ግንኙነት በዕቃና በባለቤቱ መሀከል እንዳለው ግንኙነት ነው፡፡ በአጭሩ ባርያ ከሰውነት ደረጃ ወርዶ ዕቃ ሆኖአል፡፡ ለባርያ ትልቁ ነገር ሆዱ ነው፤ በሆዱ ለሆዱ ይገዛል፤ አንዱ ባርያ ለነጻነት እንዳይታገል የሚጠብቀው ሌላው ባርያ ነው፡፡
ልማትና ባርነት አይተዋወቁም ስል ልማት ከሰውነት ባሕርይ የሚመነጭ መሆኑንና ባርነት የሰው ልጅን ከሰውነት ደረጃ የሚወጣ መሆኑን ለመግለጽ ነው፡፡ ልማት የራሱ ባለቤት የሆነን ሰው ይፈልጋል፤ ልማት ለራስ ኑሮና ሁኔታ ኃላፊነትን የሚቀበል ሰውን ይጠይቃል፤ ልማት ማሰብንና ዓላማ መቅረጽን የሚችል ሰውን ዘዴዎች ይፈልጋል፡፡ በአጠቃላይ ልማት ሰው መሆንን ይጠይቃል፡፡ ሰው መሆን ቆሞ ከመሄድ ይበልጣል፡፡

 
መስፍን ወልደ ማርያም፡፡ 2003፡፡ የክሕደት ቁልቁለት፡፡ ንግድ ማተሚያ ድርጅት፣ አዲስ አበባ፡፡   

No comments:

Post a Comment