አምባገነንነት ምሶሶዎች አሉት፡፡ የአምባገነኖች ህልውናም በእነዚኽ ምሶሶዎች ህልውና ላይ ይመሠረታል፡፡ በዚኽ የተነሣም አምባገነኖች ሥልጣናቸውን ለማቆየት እነዚኽን ምሶሶዎች የሙጥኝ ይላሉ፡፡ ይኽ ጽሑፍም እነዚኽን ምሶሶዎች
ለመተንተን ይሞክራል፡፡
1.
ድንቁርና (Ignorance)
የአምባገነኖች ዐቢይ ጠላት የሰው ልጅ የማሰብ ብቃት ነው፡፡አምባገነኖች፡ ተገዢዎቻቸውን ሲጠሯቸው አቤት፣ ሲልኳቸው ወዴት የሚሉ የአምባገነኖቹ ፈቃድ ፈጻሚ መሣሪያዎች እንዲኾኑ እንጂ “ለምን?” እና “እንዴት?” ብለው የሚጠይቁ፣ በነጻ ፈቃዳቸውና በምርጫቸው የሚንቀሳቀሱ፣ ለድርጊቶቻቸውም ሙሉ ኃላፊነት የሚወስዱ ፍጥረታት እንዲኾኑ አይሹም፡፡ አምባገነኖች በነገሡበት ዘመንና ቦታ ኹሉ በልዩ ልዩ ሥውርና ገሃድ መንገዶች የሰው ልጅ ከመሠረታዊ ፍላጎቶቹ (ምግብ፣ ዕረፍትና ርቢ) መሟላት ውጪ እንዳያስብ ይኮላሻል፡፡
አምባገነኖች ሐሳብን የመግለጽ ነጻነትን እጅግ የሚፈሩትም ለዚኽ ነው፡፡ ሰው ሐሳቡን በነጻነት እየገለጸ የሚወያይ ከኾነ የማሰብ ዐቅሙን ይጠቀማል፤ አማራጭ ሐሳቦችን እያቀረበ ይሟገታል፤ ይመዝናል፤ ይመርጣል፡፡ይኽ ደግሞ ተገዢዎቹን ልፍለጥኽ ሲሉት የሚጋደም፣ ልቁረጥኽ ሲሉት የሚገተር ሕይወት አልባ ግንድ ከመኾን ያወጣቸዋል፡፡ ይኼኔ አምባገነንነት ችግር ላይ ትወድቃለች፡፡ እንዲኽም ስለኾነ፣ አምባገነኖች በሚገዟት ሀገር ውስጥ የሚያስቡ ጭንቅላቶች ይቆረጣሉ፤ የሚጠይቁ አንደበቶች ይዘጋሉ፤ የሚያስተባብሩ እጆችም ይታሠራሉ፡፡ የማስተዋል መጨረሻው ስደት ወይም እሥር ወይም ሞት ይኾናል፡፡ የሰው ልጆችን በነጻነት እንዲያስቡ የሚያደርጉ ተቋማትም ኾኑ ግለሰቦች የአምባገነኖቹ በትር ያርፍባቸዋል፡፡ ማኅበረሰቡ ጋዜጠኞች፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፣ ሞጋች ምሁራን፣ ንቁ ፖለቲከኞች፣ ወዘተ. እንዳያበቅል ሥርዓታዊ ማምከን (systematic
sterilization) ይካኼድበታል፡፡
በአምባገነን ሥርዓት በተጠፈረች ሀገር ውስጥ ዩኒቨርሲቲዎች ይኖራሉ፤ የሰውን ልጅ የሰው ልጅነቱን በምልዓት እንዲኖረው የሚያደርግ ትምህርት ግን አይኖርም፡፡ ከ“ፒኤችዲ ፋብሪካዎች” የሚመረቱ በርካታ “ምሩቃን” ይኖራሉ፤ ዐዋቂዎች ግን እፍኝ አይሞሉም፡፡ የብዙኃን መገናኛዎች (ሚዲያ) ይኖራሉ፤ ሥራቸው ግን የሕዝቡን ንቃተ ኅሊና እንዲጫጭ ማድረግ ይኾናል፡፡ ቴሌቪዥኖቹ ከዜና ይልቅ ዘፈንን፣ ከእውነተኛ የማኅበራዊ ጉዳዮች ትንታኔ ይልቅ የጉርምስና ድሪያዎችን፣ ወይም የብዙኃንን ቀልብ በቀላሉ የሚይዙ ስሜታዊ
(sensational) ትእይንቶችን በልዩ ልዩ ቀለምና ስም ይዘው ይቀርባሉ፡፡ ሬዲዮኖቹ ደግሞግባቸው ተገዢዎች ዛሬንም ኾነ ነገን በገዢዎቻቸው ዓይን ብቻ እንዲያዩ፣ በጨቋኞቻቸው ልኬት ብቻ እንዲለኩ ማድረግ ነው፡፡ በሌላ አማርኛ የአድማጮቻቸውን ጆሮ ማስባት ነው፡፡ ጆሮ ሰብቶ ምን ሊኾን?
2.ድኽነት
ኹለተኛው የአምባገነኖች መቆሚያ ምሶሶ ድኽነት ነው፡፡ ምሶሶውም ኹለት መልኮች አሉት፡፡
ኹለተኛው የአምባገነኖች መቆሚያ ምሶሶ ድኽነት ነው፡፡ ምሶሶውም ኹለት መልኮች አሉት፡፡
ሀ. የኑሮ ፋታ የሚሰጥ ትርፍ ሀብት
አምባገነኖች ተገዢዎቻቸው እነርሱ የማይቆጣጠሩት ትርፍ ሀብት (surplus) እንዲኖራቸው አይሹም፡፡ ምክንያቱም ትርፍ ሀብት ካለ ሰዎች የዕለት ጉሮሯቸውን ለመድፈን ከሚያደርጉት ሩጫ ፋታ ያገኛሉ፡፡ የሰው ልጅ ፋታ ሲያገኝ ደግሞ ከዕለት ጉሮሮው አለፍ አድርጎ ማሰቡ ታሪካዊ እውነት ነው፡፡ ቅድም እንዳየነው ደግሞ የአምባገነኖች ትልቁ ጠላት የሰው ልጅ የማሰብ ችሎታ ነው፡፡ ለምሳሌ፣ እዚኽ ሀገር የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ መሠረታዊ ፍላጎቶችን እንደምንም ብሎ ከማሟላት ሲዘልል ታይቶ ያውቃል? የመንግሥት ሠራተኞች የኾኑ ሰዎች ጡረታ ሲወጡ እንደሌላ ሀገር ጡረተኞች የማረፊያ ጊዜ አገኘኹ ብለው ደስ የማይላቸው ለምንድነው? የልጆቹን የገንዘብ ድጋፍ የማይሻ የመንግሥት ሠራተኛ የነበረ ጡረተኛ አይታችኹ ታውቃላችኹ? በሠራተኛነታቸው ጊዜ ይከፈላቸው የነበረው ገንዘብ ከእጅ ወደአፍ ብቻ ስለኾነ ለቁጠባ የሚተርፍ የላቸውም፡፡ የመንግሥት ሠራተኞች ለምንድነው እንዲኽ ዝቅተኛ ክፍያ እንዲያገኙ የሚደረገው? እውነት
የሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት ሊከፍል የሚችለው ይኽን ብቻ ነው?
ለ.ድኽነት=insignificance
ጉስታቮ ጉቲዬሬዝ (Gustavo
Gutiérrez) የሚባሉ አንድ ሊቅ ድኽነትን ሲበይኑት “To be poor means to be
insignificant.” ብለዋል፡፡ (“ድኻ መኾን ማለት ምናምንቴ መኾን ነው፡፡” ብለን እንተረጉመዋለን፡፡) ይኽንን የአምባገነኖችን ጠባይ ስናስተነትንም፣ አምባገነኖች ተገዢዎቻቸውን የሰው ልጅነት ክብር እንዳይሰማቸው፣ የዋጋ ቢስነት፣ የዐቅመ ቢስነት ስሜት እንዲነግሥባቸው ለማድረግ የማይፈነቅሉት ደንጊያ እንደሌለ እናስተውላለን፡፡ለምሳሌ፣ አብዛኛው ሕዝብ በባዶ እግሩ በሚኼድበት ሀገር እነርሱ እጅግ ውድ በኾኑ መኪኖች ይንፈላሰሳሉ፡፡ አብዛኛው ሕዝብ ጭቅቅት በወረሳቸው የአፈር ቤቶች ውስጥ በሚኖርበት ሀገር እነርሱ እጅግ የተቀናጡ ቤቶች ውስጥ ይኖራሉ፡፡ ሲያሻቸው ሊያጠቋቸው የሚፈልጓቸውን አካላት የሚያጠቁበት በልክ የተሰፋ ሕግ ያወጣሉ፡፡ እነርሱ ደግሞ ለማኅበረሰቡ ሕግ የማይገዙ ፍጹም የበላይ ኾነው ይኖራሉ፡፡ የሚሾሟቸውን ሰዎች የሚሾሙበት መስፈርት ለእነርሱ ያለው ታማኝነት ወይም ሲልኩት ወዴት ሲጠሩት አቤት የሚል ብቻ እንዲኾን የሚያደርጉበት፣ ያለብቃታቸው የተሾሙ ተከታዮቻቸው እነርሱን በታማኝነት እስካገለገሉ ድረስ ያሻቸውን ሲያደርጉ ዝም የሚሉበት ሥነ ልቡናዊ ምክንያት አንድ ነው- የሕዝቡን ሥነ ልቡና በዐቅመ ቢስነት ስሜት ለመስለብ፡፡ እያንዳንዱ ራሱን ምንም ማድረግ የማይችል አድርጎ እንዲቆጥር ማድረግ፡፡ ይኽ ወደ ሦስተኛው ምሶሶ ይወስደናል፡፡
3. ፍርኀት
ይኽኛው ምሶሶ 4 መልኮች አሉት፡፡
ሀ. ፍርኀትን የወለደው መዓርግ
ይኽኛው ምሶሶ 4 መልኮች አሉት፡፡
ሀ. ፍርኀትን የወለደው መዓርግ
አምባገነኖች የሥራቸውን ክፋትና ተቋማዊ ዐቅመ ቢስነታቸውን ውስጠ ኅሊናቸው ስለሚያውቅ ኑሯቸው ኹሌም የሥጋት ነው፡፡ አምባገነንነታቸውን ጠብቀውፍርኀታቸውንና ዐቅመ ቢስነታቸውን ለማስወገድምብዙ ጥረት ያደርጋሉ፡፡ ለምሳሌ፣ የአንድ ሀገር መሪ መኾን የሚበቃ መስሎ አይታያቸውም፡፡ እያንዳንዷ የሀገሪቱ ተቋም በእነርሱ ቀጥተኛ እዝ ሥር ካልወደቀ ዕንቅልፍ አያገኙም፡፡ የመዓርግ ስሞቻቸውን ብንመለከት “የተከበሩ ጠቅላይ ሚ/ር አቶ ዶ/ርእገሌ እገሌ፣ የእንትን ፓርቲ አውራ ጸሐፊ፣ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ፣ የዴሞክራሲ ችቦ አቀጣጣይ፣ ወዘተ.” እንደኾነ እናያለን፡፡ እነርሱ ማለት ሀገሪቱ፣ ሀገሪቱ ማለትም እነርሱ ብቻ ይኾኑና ያርፉታል፡፡ በአንድ ወቅት ንጉሠ ነገሥት ኃይለ ሥላሴ ፊታውራሪ ተክለሐዋርያት ተክለማርያምን “ምን ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ ትላለኽ? ኢትዮጵያ ያለ እኛ የለችም!” እንዳሉት፣ ወይም በቅርቡ እንደተጀመረው “ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በመፈቃቀድ ተስማምተው የሚኖሩባት ዐዲሲቱ ኢትዮጵያ ያለእኛ አትኖርም፡፡” የሚል ፉከራ ማለት ነው፡፡ ዳሩ ምን ያደርጋል፣ የጊዜ ጉዳይ እንጂ አምባገነኖች ተንኮታኵተው መውደቃቸው አይቀርም፡፡ እንዳለመታደል ኹኖ ግን አምባገነን ቡድኖችም ኾኑ ግለሰቦች ሲወድቁ ራሳቸውን ማዕከለ-ኵሉ (the center of everything) አድርገው ስለሚቆዩ አጠቃላይ የሀገሪቱ ተቋማት ራሳቸውን ችለው መሥራት ያቅታቸዋል፡፡ “ኹሉን ነገር በቁጥጥራችን ሥር ካላዋልን ያምፅብናል፡፡” በሚል ፍርኀታቸው በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ ተቋማትን በሙሉ አገልጋያቸው ስለሚያደርጉ ተቋማቱ እነርሱ በሌሉበት መሥራት እንዳይችሉ ይኾናሉ፡፡ ዛሬ ማብቂያ ያለው በማይመስል የእርስበርስ ጦርነት የወደመችው የሙአማር ጋዳፊዋ ሊቢያ ጥሩ ምሳሌ ትኾነናለች፡፡
ለ. ፍርኀት የወለደው አምልኮ
ከዚኽም በተጨማሪ፣ አምባገነኖች ተገዢዎቻቸው በፍጹም ፍርኃት እንዲያመልኳቸው ይሻሉ፡፡ የኒኮሎ ማኪያቬሊን “ከመወደድ መፈራት ይሻላል፡፡” (It is better to be feared than
loved.) አቀንቃኞች ናቸው፡፡ ተገዢዎቻቸው የእነርሱን የሐሳብ ጥራትም ኾነ የድርጊቶቻቸውን ትክክለኛነት እንዲጠይቁ፣ እንዲተቹ አይፈቀድላቸውም፡፡ “አለቃ ኹልጊዜም ትክክል ነው!” “Boss is always right.” የሚለውን የጅል ብሂል መቀበል የተገዢዎች ግዴታ ነው፡፡ ለምሳሌ፣ ገዢዎቹ (ፓርቲያቸው) የኾነ ቀን ከዕንቅፋቸው ብንን ብለው “ቢፒአር ከትምህርት ቤት እስከ ፋብሪካ ድረስ ያሉ ተቋማዊ ችግሮቻችንን ይፈታል!” ሲሉ ተገዢዎቹም ያንን ያለምንም ጥርጥር “አሜን!” ማለት ይኖርባቸዋል፡፡ ቢፒአር የተባለው ሲከሽፍ ደግሞ ለክሽፈቱ ኃላፊነትን መውሰድና የገዢዎቻቸውን ስድብ መጠጣትም ይጠበቅባቸዋል- ምስኪን ተገዢዎች!“ቢኤስሲ” ሲሉ “ቢኤስሲ”፣ “ካይዘን” ሲሉ “ካይዘን”፣ ወዘተ.፡፡ አምባገነን ሥርዓት የሰውን ልጅ ከሰው ልጅነት ወደ ሕይወት አልባ የገደል ማሚቶነት ያወርደዋል፡፡
ሐ. አማራጩን ማጨለም
ሌላኛው የአምባገነን ሥርዓት የፍርኀት መልክ ከአምባገነን ሥርዓቱ ውጪ ያሉ አማራጮችን ሕዝቡ እንዲፈራ ማድረግ ነው፡፡ ለምሳሌ፣ በንጉሡ ዘመን ከነበረው ሕዝብ መካከል የማይናቅ ቁጥር የነበረው ንጉሠ ነገሥት ኃይለ ሥላሴ እርሳቸው ከሥልጣን ከወረዱ ሀገሪቱ እንደሚያበቃላት፣ የእርስበርስ ጦርነት እንደሚውጣት ያምን ነበር፡፡ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ሀገር ጥለው ሲጠፉና እርሳቸው “ወንበዴዎቹ” እያሉ ሲያጥላሏቸው የነበሩት ሰዎች በአዲስ አበባ ዙሪያ በደረሱ ጊዜ ሕዝቤ በድንጋጤ በየቤተእምነቱ መሽጎ “እግዚኦ!”ሲል የከረመው ሀገሪቱ እንደሶማልያ ተበታትና በእርስበርስ ጦርነት አፈር ትበላለች ብሎ ስለፈራ ነበር፡፡ “ወንበዴዎቹ ሀገር ሊመሩ ይደፍራሉ” ብሎ ያመነው ሰው ጥቂት እንደነበር ዘመኑን የኖሩበት ሰዎች ነግረውናል፡፡ አምባገነኖ እነርሱ ከሌሉ ልማቱ ይቆማል፤ ሀገሪቱ ትበታተናለች፤ ብሔር በብሔር ላይ፣ ሃይማኖት በሃይማኖት ላይ ይነሣል፤ ወዘተ. እያልን ምጽአታዊ ጭንቀት (doomsday
anxiety) እንዲውጠን ይመኛሉ፡፡ በዚኽ ሐሳባችን ተነሥተንአምባገነንነታቸውን እንድናመልክ፣ ሙጥኝ እንድንላቸውይፈልጋሉ፡፡
አማራጩ አምባገነኖቹ እንደሚሉት ጨለማ አለመኾኑን ለማሳየት የሚፈልጉትንም ያዳክማሉ፤ ያሳድዳሉ፡፡ በአምባገነኖች ሀገር የተቀናቃኝ ፖለቲካ ፓርቲ አባል፣ ወይም ጋዜጠኛ፣ ወይም የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች፣ ወይም ለኅሊናው ያደረ ሰው መኾን እጅግ የሚያስቸግረው ለዚኽ ነው፡፡ ምክንያቱም ሰዉ አማራጩ ጨለማ እንዳልኾነ ካወቀ ፍርኀቱን አውልቆ ይጥልና አምባገነንነታቸውን ያከትመዋላ!
መ. አድኃሪ ፕሮፓጋንዳ
የሥነ ሰብ (Anthropology) ሊቃውንት አንድ ማኅበረሰብ ከቤተሰብ ወደ አምባገነናዊ ንጉሣዊ ሥርዓት የሚያድግበትን ዝግመተ ለውጥ ቅደም ተከተል ቤተሰብ (family)àነገድ (band)à የጎበዝአለቃ (chieftain) à ንጉሣዊሥርዓት (monarchy)
ብለው ያሰፍራሉ፡፡ ብዙ ቤተሰቦች ነገድን ከመሠረቱ በኋላ የነገዳቸውን ህልውና ከውጪ ጠላቶች ለማስጠበቅ ሲሉ በአንድ የጎበዝ አለቃ ሥር ይሰባሰባሉ፡፡ የጎበዝ አለቃውም በሥልጣኑ ላይ ጥቂት ከቆየና ልጆቹን በእርሱ ቦታ መተካት ከቻለ ሥርወ መንግሥት (dynasty) ይመሠርታል፡፡ ሥርወ መንግሥት ከኾነ በኋላ የተዋጊነት፣ የተከላካይነት ድርሻውን ስለሚወስድ ተገዢዎቹ ያለእርሱ የተጋላጭነት ስሜት
(vulnerability)እንዲሰፍርባቸው ያደርጋል፡፡ ሀገሪቱ በጠላት የተከበበች እንደኾነችና በእርሱ ጥንካሬ ብቻ እንደቆመች እንዲሰማቸው፣ የእርሱ ቤት (የእርሱ ፓርቲ) ከሌለም ሀገሪቱ በውጪ ጥቃት እንደምትወድም እንዲያስቡ ያደርጋል፡፡ የሕዝቡን ጭንቅላት እንዲኽ የሚጫወትበትም የማኅበረሰብን ዕድገት አምባገነንነት ላይ ቸክሎ የሚያስቀር አድኃሪ ሐቲት (discourse)/ፕሮፓጋንዳ ነው፡፡
ለመሰናበቻ ከዮሐንስ አድማሱ “እስኪ ተጠየቁ” የግጥም መድበል ውስጥ “ፍርሃት የኛ ጌታ” ከሚለው ግጥም ጥቂት ስንኞች
እንቀንጭብ፡-
ፍርሃት የኛ ጌታ
ፍርሃት የገዛን እኛ የፍርሃት ሀገር
ዜጋ፣
በፍርሃት ብቻ መቸም መውጫ መግቢያችን
የተዘጋ፣
ያለንበትም ቤቱ ሁሉ መላው አየሩ
ተነፈገ፣
በውስጡ ያለነው እኛ ሰውነታችን
ጠወለገ፡፡
No comments:
Post a Comment