የዛሬው ወሬዬ መሠረት የሚያደርገው “The Road Less Travelled” ከተሰኘው መጽሐፍ ያገኘሁትን ትምህርት ነው፡፡ የዚህ መጽሐፍ ደራሲ ስኮት ፔክ የሚባል ሳይኮቴራፒስት ሲሆን ከጻፋቸው መጻሕፍት ውስጥ እንደዚህኛው የተወደደለት የለም ይባላል- 10000000 ቅጂ ተሸጦለታል፡፡
እንደስኮት ፔክ አባባል ብዙዎቻችን ለበጎ ነገር ሰነፎች ነን፡፡ በዚህም የተነሣ በጎ ነገር መሆኑን ብናውቅም እንኳ አዲሱን በጎ ነገር ከማድረግ ይልቅ በለመድነው መጥፎ ነገር ውስጥ መዘፍዘፍ ይመቸናል፡፡ በሱስ ተጠምደን ሱሱ ሥነልቡናዊ ጤንነታችንን፣ አካላዊ በጎነታችንን፣ ቤተሰባችንን፣ ሥራችንን፣ ማኅበራዊ ኑሯችንን ወዘተ. እያቃወሰው፣ እየበጠበጠው እያየንና ጉዳቱም በእጅጉ እየተሰማን፣ ሱሱን ማቆም እንዳለብንም እያወቅን ሱሱን ለማቆም ግን እንሰንፋለን፡፡ ሱሱን ለማቆም ልናደርጋቸው የሚገቡ ነገሮችን ሁሉ ስናስባቸው ዳገት ይሆኑብናል፡፡ ውጤቱ ጥሩ መሆኑን ብናውቅም ልፋቱን ላለመልፋት ድካሙንም ላለመድከም ሳንጀምረው እንዝላለን፡፡ በለውጥ ሒደት ላይ ከመንገላታት ይልቅ እንደደረቀ ግንድ እየበሰበስን፣ ምሥጥ እየበላን ባለንበት መገተርን እንመርጣለን፡፡
ተማሪዎች አምርረን ብናጠና ውጤታችን እንደሚያምር እናውቃለን ግን ያንን ለማድረግ ማጥናት፣ መሞከር፣ መታገል፣ ለረጅም ሰዐት ወረቀት ታቅፎ፣ ብዕር አንቆ መቀመጥ ጭንቅ ይሆንብናል፡፡ ከዚህ ይልቅ ቁጭ ብለን 50 ጊዜ ያየነውን ፊልም ደግመን ለ51ኛ ጊዜ ብናይ ወይም ጌም ብንጫወት ወይም ኤም ቲቪ ላይ የማይመለከቱንን የቴሌቪዥን ሾዎች መከታተል ይቀልለናል፡፡ እርግጥ ነው እናውቃለን፡፡ አሁን ጌም መጫወታችን የወደፊት ሕይወታችንን በመቀየስ ረገድ ላቅ ያለ ሚና የሚጫወተውን ትምህርታችንን እንድንዘነጋው እያደረገን መሆኑን ልቅም አድርገን እናውቃለን፡፡ ዛሬ ፊልም የምናየው ከነገው ሕይወታችን ላይ እየተበደርን መሆኑም ይገባናል፡፡ ለዚህም ነው ኮ የሚገሥጹን ሰዎች ሲመጡብን ውስጣችን ሽምቅቅ የሚለው፡፡
መጻሕፍትን መመለካከት መልካም እንደሆነ እናውቃለን፡፡ ግን ለአንድ ሰዐት ፍቅር እስከ መቃብርን ማንበብ ለአንደኛውን መቃብር መውረድን ያህል የሚጨንቀን ብዙዎች ነን፡፡ ከአድማስ ባሻገርን ከማንበብ አድማስ ተሻግሮ መሰደድ የሚቀናንም ቁጥራችን ቀላል አይመስለኝም፡፡ ኒቼን ከማንበብ ጅብ ቢነጨን የምንመርጥም ለቁጥር የምናታክት ይመስለኛል፡፡
የማኅበረሰባችን ኑሮ በምጣኔ ሀብትም በሞራልም እየተመሰቃቀለ እንደሆነ እናውቃለን፡፡ የምንመራቸው ወይም የምንመራባቸው አብያተ እምነቶቻችን በዘቀጠ ሕይወት እንደተሞሉ እናውቃለን፡፡ ቤተሰባዊ ሕይወታችን ችግር እንዳለበት እናውቃለን፡፡ ትምህርት ቤቶቻችን ብቁ የዜጎች ማፍሪያ እየሆኑ እንዳልሆነ እናውቃለን፡፡ የትምህርት ፖሊሲያችን
“የተማረ ይግደለኝ ይላል የሀገሬ ሰው
ይኸው ተምሬያለሁ መጣሁ ልጨርሰው፡፡” በማለት የመማሪያ ጠረጴዛቸው ላይ በጽሑፍ የሚፎክሩ “ሀገር አቅኚ ምሁራንን” እያፈራልን መሆኑን እናውቃለን፡፡
ግን የሃይማኖት አስተምህሮዎቻችን፣ የመመሪያ ፖሊሲዎቻችን፣ “ባህላችን” የምንለው የአነዋወር ዘይቤያችን ችግር ይኖርባቸው ይሆን? ብሎ መፍትሔ ከመስጠት ይልቅ ችግሮቹን ማን እንዳመጣቸው መጨቃጨቅ ይቀናናል፡፡ ምእመናን አገልጋዮችን፣ አገልጋዮች አባቶችን፣ አባቶች ሌሎች አባቶቻቸውን ወይም ዘመኑን፣ መንግሥት ሹመኞቹን፣ ሹመኞቹ የበታች ሠራተኞችን፣ ሠራተኞች ፖሊሲውን፣ መንግሥትን፣ ሹመኞችን፣ ወዘተ. ያማርራሉ፡፡ ሁሉም ራሱን የችግሩ ሰለባ እንጂ የችግሩ ፈጣሪ እንዳልሆነ ለማሳየት ይሮጣል፡፡ አንዱ በሌላው ሲያማኻኝ ችግሩ ጭቅጭቅን ይወልዳል፡፡ ጭቅጭቁ ቁስል ይፈጥራል፤ ቁስሉም በጊዜ ብዛት ይበሰብሳል፡፡ የበሰበሰ ደግሞ መጨረሻው አለመኖር ነው፡፡
እርግጥ ነው መነታረካችን መፍትሔ እንደማይሆን እናውቃለን፡፡ እኛ ምን የማናውቀው አለ! እንኳን ይቺን የዝንብ ልጃገረድ እናርፋለን፡፡ እ-ና-ው-ቃ-ለ-ን፡፡ ነገር ግን ሌላው ሰው ትክክል ሆኖ የችግራችን መፍትሔ ከሚገኝ እኛ ትክክል ሆነን መፍትሔ ባይመጣ ይሻለናል፡፡
ውስጣችን መለወጥን ትጠማለች፡፡ ነፍሳችን ከሱስ ነጻ መሆን፣ ከማይጠቅማት መንገድ መውጣት፣ የመኖራችንን ዓላማና የተፈጠርንለትን ግብ እግር እግር በትጋት ማሳደድና ማሳካት ትፈልጋለች፡፡ ደግሞም ትችላለች፡፡ ግን ስንፍናችን ዕንቅ፣ ጥርንቅ አድርጎ ይዟታል፡፡
አዳማዊ የውርስ ኃጢኣት
ስኮት ፔክ “የሰው ልጅ ያለበት ጥንተ አብሶ ወይም አዳማዊ ኃጢኣት (Original Sin) ስንፍና ነው፡፡” ይላል፡፡ ስንፍና ብዙ መልኮች እንዳሉትና አንዱና ትልቁ ከአዳም የወረስነው ኃጢኣት መገለጫው ለለውጥ ያለን ስንፍና እንደሆነ ያስረዳል፡፡
ሁላችን የለመድናትን የምቾት ዞናችንን የሚነካብንን ሰው ፈጽሞ አንወድም፡፡ ከሰው ልጅነት ታሪካችን እንደምንረዳው የምቾት ዞናችንን ለማስጠበቅ ከኩርፊያ እስከ ሐሜት፣ ከዛቻ እስከ ግድያ ያሉ ቴክኒኮችን ስንጠቀም ኖረናል፡፡ የምቾት ዞናችንን ግንብ በጥያቄ መድፍ የተነኮሱብንን ሰዎች በአውሮፓ ኢንኲዚሽን ፍርድቤቶች፣ በአፄ ዘርዓ ያዕቆብ ቋንጃና አፍንጫ ቆረጣዎች፣ በጽንፈኛና ፍርደ ገምድል የፍርድ ቤት ውሳኔዎች ሁሉ ስንፋለም ኖረናል፡፡ በቁማችን የምንበሰብስበትን የምቾት ዞናችንን ከማጣት ውጣ ውረድ ለበዛበት የለውጥ ጎዳና የሚቀሰቅሱንን ሰዎች መርገምና ቁጣችንን በእነርሱ ላይ ማንደድ ይቀልለናል፡፡ ለምን ቢሉ የአዳም ልጆች ነና፡፡ ስንፍናን ከእርሱ ወርሰናታል፡፡
በስኮት ፔክ አስተሳሰብ፣ አዳምና ሔዋን የመጀመሪያው ጥፋታቸው የተከለከሉትን ፍሬ መብላታቸው አይደለም፡፡ እባብ ፍሬዋን እንዲበሉ ሲሰብካቸው እባብን ብቻ ከማመን ይልቅ በግልጽ ያናግሩት የነበረው አምላካቸውን “ለምን ከለከልኸን?” ብለው ጠይቀው ለመረዳት አለመሞከራቸው እንጂ፡፡ ወይም በጋዜጠኝነት ቋንቋ ስለሁኔታው ሚዛናዊ ዘገባ ለአእምሯቸው ለማግኘት (“balance” ለመፍጠር) አልሞከሩም፡፡ የዚህም ምክንያቱ ስንፍና ነው፡፡
አታድርጉ የተባሉትን ለምን አታድርጉ እንደተባሉ ለመረዳት አታድርጉ ያላቸውን ፈጣሪያቸውን ከመጠየቅ ይልቅ የእባብን ምክር እንዲሁ መቀበልን መረጡ፡፡ ለመጠየቅ ሰነፉ፡፡ በመስነፋቸውን እነሆ የሆነው ሁሉ ሆነ፡፡ ለእኛ ለልጆቻቸውም አወረሱን፡፡
ራሱ ስኮት ፔክ እንደሚመሰክረው በርካታ ታካሚዎቹ የጀመሩት ሕክምና ውጤታማ እንደሚሆን ቢያውቁና ቢያምኑም እንኳን የነበራቸውን የኑሮ ዘይቤ እርግፍ አድርጎ መተዉ ስለሚያስፈራቸው ችግሩን አቅፎ መኖርን በመምረጥ ሕክምናውን ያቋርጡታል፡፡ ይህንን እኔም በተማሪዎቼ ላይ አይቻለሁ፡፡ ብዙ መሥራት የሚችሉበት ዐቅም እያላቸው ራሳቸውን ከማሠራት ይልቅ የለመዷትን ስንፍና እያጣጣሙ በውድቀት ጎዳና ላይ በብስጭት መጓዝን የመረጡ ተማሪዎችን በበቂ ሁኔታ አውቃለሁ፡፡ ለነገሩ ወላጆቻቸው “ከማያውቁት መልአክ የሚያውቁት ሰይጣን ይሻላል፡፡” እያሉ አይደል ያሳደጓቸው?
ስለዚህ ሕይወታችን ከቆመችበት የመበስበሻ ስፍራ እንድትመነጠቅ መጀመሪያ ስንፍና ጠላታችን መሆኑን አምነን ልንታገል ይገባናል፡፡ ሕይወት ዓላማዋን አሳክታ መኖሯ ትርጉም እንዲኖረው በትርጉሟም ጠቃሚ እንድትሆን ከታጠረችበት የስንፍና አሽክላ ልትላቀቅ ይገባታል፡፡ አንድ መነኩሴ በአንድ ወቅት እንዳስተማሩኝ “ሕይወት ዓላማ ከሌላት ትርጉም፣ ትርጉም ከሌላት ደግሞ ጥቅም የላትምና፡፡”
No comments:
New comments are not allowed.