Thursday, February 23, 2012

የቤተሰብ መርገም


ዛሬ ከግሪክ ሚቶሎጂ አንድ ተረክ እንቆንጥር፡፡

በድሮ ጊዜ አንድ አትሬዉስ የሚባል ሰው የግሪክ አማልክትን በኃይል ለመብለጥ ይገዳደራል፡፡ በዚህም የተነሣ አማልክቱ ተቆጥተው የእርሱ ውላጆች በሙሉ ሕይወት የቀናች እንዳትሆንላቸው “አትሬዉስና ቤቱ የተረገሙ ይሁኑ!” የሚል እርግማን አስተላለፉ፡፡[i] ይህ እርግማን በትዕቢቱ ያስቆጣቸውን አትሬዉስን ብቻ ሳይሆን ልጆቹንና የልጅ ልጆቹን ሁሉ የሚመለከት ነበረ፡፡  

ጊዜ ነጎደ፡፡ እርግማኑም ተረሳና ከአትሬዉስ ልጆች መካከል አንዱ የሆነው አጋሜምኖን ክሊቴምኔስትራ ከምትሰኝ ሴት ጋር በፍቅር ይወድቃል፡፡ በመጨረሻም ያገባትና ኦሬስተስ የተባለ ልጅ ይወልዳሉ፡፡ ይህቺ ክሊቴምኔስትራ ግን በልጇ አባት ላይ ሌላ ሰው ወሸመችበት፡፡[ii]  መወሸሙም ሳይበቃት አጋሜምኖን ከጦርነት ሲመለስ ከውሽማዋ ጋር ተባብራ ገደለችው- የልጇን አባት! እርሷ ለውሽማዋ ፍቅር ብላ አጋሜምኖንን ስትገድል እርግማኑን ወደልጇ ማተላለፏን አላየችም፡፡ የአፍቃሪ ነገር! ያውም የውሽማ ፍቅር ችግር እኮ ነው፡፡ አማልክቱ ይህንን ሁሉ ከኦሊምፐስ ተራራ ላይ ተጎልተው ይመለከታሉ፡፡ እርግማናቸው በመሥራቱም “ቺርስ!” እየተባባሉ አማልክታዊ ጽዋቸውን ይቀባበላሉ፡፡ አባትየው ላይ የወደቀው እርግማን በገዛ ሚስቱ በመገደል ሲጠናቀቅ ያልተባረከ ሕይወት የመመምራት አማልክታዊው እርግማን ግን ወደ ልጁ ወደ ኦሬስተስ ተላለፈ፡፡

ኦሬስተስ እናቱ የፈጸመችውን ይህንን ወንጀል ሲያውቅ ነፍሱ አጣብቂኝ ውስጥ ወደቀች፡፡ ከፊቱም ሁለት አማራጮች ብቻ ቀረቡለት፡፡ አማራጭ አንድ በግሪኮች ባህል ወንድ ልጅ የአባቱን ገዳይ መግደል አለበት፡፡ አማራጭ ሁለት አንድ ግሪካዊ ሊፈጽማቸው ከሚችሉ ኃጢኣቶች ሁሉ እጅግ ከባዱ የገዛ እናቱን መግደል ነው፡፡[iii]

የአባቱን ገዳይ አለመበቀል ከባድ ነውር ነው፡፡ የወለደችውን እናቱን መግደልም ታላቅ ኃጢኣት ነው፡፡ ምን ይሻላል? ኦሬስተስ ብዙ ካወጣና ካወረደ በኋላ የመጀመሪያውን አማራጭ በመውሰድ የአባቱን ደም ለመበቀል የወለደችውን እናቱን ሲጥ አደረጋት፡፡ እርግማኑ ሠራ! አማልክቱ አሁንም ተደስተው “ቺርስ!” ተባባሉ፡፡



ምንም እንኳ ይህ ሁሉ ዕቅዳቸው ቢሆንምና በዕቅዳቸው አፈጻጸምም ቢደሰቱም የአማልክትነት ሥልጣናቸው የተፈጸመውን ኃጢኣት እንዲቀጡ ያስገድዳቸዋልና በግሪክ ውስጥ እናቱን የገደለ ኃጢኣተኛን ለኃጢኣቱ የሚገባውን ፍዳ የሚከፍሉትን ፍዩሪዎች በመባል የሚጠሩ ሦስት አስጠሊታ የስቃይ መናፍስትን ወደ ኦሬስተስ ላኩበት፡፡ እነዚህ መናፍስትም ኦሬስተስን በሔደበት ሁሉ እየተከተሉ የሠራውን ኃጢኣት እያስታወሱ ይወቅሱታል፡፡ በአሰቃቂ ገጽታቸውም ያስፈራሩት ጀመር፡፡ ሕይወቱ ሲዖል ሆነችበት፡፡ ከኃኣቱ ሊያመልጥ ብዙ ሞከረ፤ ግን አልቻለም፡፡ የኃጢኣቱን ሥርየት ለማግኘት ብዙ ማሰነ፡፡ ግን አልሳካልህ አለው፡፡ ከብዙ ዓመታት ስቃይና መፍትሔ ፍለጋ በኋላ አንድ ቀን አንድ ውሳኔ ላይ ደረሰ- አማልክቱን ከእርግማኑ እንዲፈቱት መጠየቅ፡፡ በዚህም መሠረት አማልክቱን በአያቱ ላይ ካስተላለፉትና በእርሱም ላይ ተነግሮ የማያልቅ ስቃይን ካስከተለበት ከዚህ እንደስኳር በሽታ በዘር የሚተላለፍ እርግማን እንዲፈቱት ይጠይቃቸዋል፡፡

አማልክቱም ጉዳዩን በችሎት ለማየት ተስማሙ፡፡ በችሎቱም ላይ አፖሎ የተባለው አምላክ ለኦሬስተስ እንዲህ ሲል ይሟገትለት ጀመር፡፡

“ሁሉንም ነገር ያቀድሁትና ኦሬስተስ እናቱን እንዲገድል ያደረግሁት እኔ ነኝ፡፡ ስለሆነም ኦሬስተስ ስለተፈጸመው ወንጀል ተጠያቂ ሊሆን አይገባም፡፡”
በዚህ ጊዜ ኦሬስተስ ከመቀመጫው ዘልሎ በመነሣት
“ተቃውሞ አለኝ!” አለ፡፡
“ተቃውሞህ ምንድነው?” ዳኞቹ አማልክት ጠየቁት፡፡
“እናቴን የገደለው አፖሎ ሳይሆን እኔ ራሴ መሆኔ እንዲያዝልኝ፡፡” 
አማልክቱ ተገረሙ፡፡ ከአቴሬዉስ ቤተሰብ መካከል አንድም ሰው እንዲህ አማልክቱን ከማማረርና ከመርገም ውጪ ለኃጢኣቱ ራሱን በተጠያቂነት ያስቀመጠ ሰው አይተው አያውቁም፡፡ በዚህም የተነሣ ኦሬስተስ ሙሉበሙሉ ከእርግማኑም ከኃጢኣቱም ነጻ እንዲሆን ወሰኑለት፡፡ እነዚያ ያሰቃዩት የነበሩ መናፍስትም የምክርና የፍቅር መናፍስት ወደመሆን ተቀየሩለት፡፡ በእነርሱ ምክርም ሕይወት የአልጋ ላይ ጉዞ ሁናለት ዓለሙን ሲቀጭ ኖረ፡፡

እና ምን ይጠበስ?

ከኦሬስተስ እንማር፡፡ በእኛ ሕይወት ውስጥ ለተፈጠሩ ስሕተቶች የመጀመሪያውን ተጠያቂነት መውሰድ ያለባቸው ወላጆቻችን ወይም ማኅበረሰባችን ወይም ትምህርት ቤታችን አይደሉም፡፡ እርግጥ ነው ሁሉም አነሰም በዛም ድርሻ ይኖራቸዋል፡፡ ነገር ግን ድርጊቶቹን ያደረግነው እኛ መሆናችንን እንመን፡፡ ነጻ ፈቃዳችንን ተጠቅመን የፈጸምናቸው መሆናቸውን እንቀበል፡፡ በንስሐ መታደስ ወይም ዳግም መወለድ ወይም ሕዳሴ (renaissance) እዚያ ላይ ይጀመራል፡፡

ብዙዎቻችን ያደረግናቸውን እኩያን ነገሮች በሰይጣን እናማኻኛለን፡፡ ወይም በጓደኞቻችን እናሳብባለን፡፡ ወይም እግዜርን እንወቅሳለን፡፡ ሰይጣን ዕቅድ ያቅዳል እንጂ አያስፈጽምም፡፡ የሕይወታችን “ሕግ አውጪ”(ፓርላማ) (Legislative Organ) ለመሆን ይሞክራል፤ አንድም ቀን ግን የመፈጸም ዐቅም አግኝቶ አያውቅም፡፡ በሌላ አገላለጽ የሕይወታችን “ሕግ አስፈጻሚዎች” (Executive Organ) ነን፡፡ ምስክርነቱን አምነን ምክሩን ተከትለን የምንፈጽውን የምንፈጽመው እኛና እኛ ብቻ ነን፡፡ ከዚያ በኋላ እርሱ የደስታ ጽዋውን በእኛ የሐዘን እንባ ይሞላና “ቺርስ!” ይለናል፡፡ የታባቱ ይህ ክፉ!

ሰይጣን ያለንበት ሁኔታ እጅግ የሚያስቆጣ መሆኑን አበክሮ ይነግረናል እንጂ እኛን ሆኖ መቆጣት አይችልም፡፡ ስድብ ያቀብለናል እንጂ አፋችንን ከፍቶ የግድ እንድንሳደብ ሊያደርገን አይችልም፡፡ ጉቦ የሚሰጡ ሰዎች ያቀርብልናል እንጂ ጉቦውን ከሰዎቹ እጅ መቀበል አይችልም፡፡ ጾታዊ ስሜቶቻችንን ከሚገባው በላይ እንድናተኩርባቸው ይመክረናል እንጂ ጾታዊ ትንኮሳ መፈጸም አይችልም፡፡ በወጣትነታችን ወሲብ ካልፈጸምን ጤንነታችን እንደሚያጠራጥር፣ ደስታችን አፈር ድቤ እንደሚገባ በቲቪው፣ በሬድዮው፣ በመጽሔቱ አድሮ ይሰብከናል እንጂ የእኛን አካል በመጠቀም ዝሙት መፈጸም አይችልም፡፡ ኃጢኣት መሥራት ምንም ማለት እንዳልሆነ ልዩልዩ ሰብአዊ ምሳሌዎችን እያመጣና የሰዎቹን ደስታ እያመላከተ እንቁልልጬ ይለናል እንጂ ኃጢኣት ሊያሠራን አይቻለውም፡፡ ይህን ሁሉ የምናደርገው እኛ ነን፡፡ ስለዚህም የሰይጣንን ምክርም ሆነ ምስክርነት አለመስማት ከባድ ቢሆንም አለመፈጸም ግን እንደሚቻል አስቡ፡፡ ለዚህ ነው ታላቁ መጽሐፍ “እግዚአብሔርን እሺ በሉት፡፡ ሰይጣንን ግን እንቢ በሉት፡፡” ያለን፡፡ ፈጣሪያችን እንኳ ነጥቆን የማያውቀውን ነጻ ፈቃዳችንን ማንም ሊወስድብን አይችልም፡፡ አይገባምም፡፡

የክፉ ድርጊት ፍጻሜው ደስታ አልባ ሕይወት መግፋት ነው፡፡ መጀመሪያው ግን ክፉ ሐሳብ ነው፡፡ በመሆኑም የትኛውም ሐሳብ ወደአእምሯችን ሲወረወር እንዳለ መቀበል አይገባም- ወርዋሪው ማንም ይሁን፡፡ የመጣውን ሐሳብ ክፉና ደግነቱን ሳንመረምር እንኳን ማድረግ ቀርቶ ልንናገረውም አይገባም፡፡ ሕይወታችን እንዳይመሰቃቀል ዝግ ብለን እናሰላስለው፡፡  

Beware of your thoughts, they become your words.
Beware of your words, they become your actions.
Beware of your actions, they become your habits.
Beware of your habits, they become your character.
Beware of your character, it becomes your destiny.

ተብለናልና::




[i] ልክ አሜሪካ አሁን በቅርቡ ኢራን ላይ “ከኢራን የሚገበያይ የተረገመ ይሁን፡፡” ብላ እንዳወረደችው የኢኮኖሚ እርግማን መሆኑ ነው፡፡ የፕሬዚደንት አሕመዲን ነጃድን በኃይል መገዳደር ለመጨፍለቅ የኢራንን ሕዝብ በጠቅላላው በኢኮኖሚ ማዕቀብ ማድቀቅ ከቤተሰብ ተኮር እርግማን በምን ይለያል? በቀን አንድ ሚሊየን በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ የምታመርተውን ሀገር ገበያ በመከልከል የድኃ ሀገራት ሕዝቦች ኑሮ በነዳጅ ዋጋ ንረት እንዲመሰቃቀል ማድረግ ከትውልድ ተሻጋሪ እርግማን በምን ይለያል?       

[ii] በነገራችን ላይ ስለውሽምነት ሳስብ የዛሬ ስንት ሺህ ዓመት በፊትም ነበረ፡፡ ዛሬ “የሠለጠነ” በሚባለውና ሰው የምድሩን ጨርሶ ሰማይ ላይ መንሳፈፍ በጀመረበት ጊዜያችንም አለ፡፡ እንዴት ነው በሁለትና በሦስት ሺህ ዓመታትም አንለወጥም ማለት ነው? ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊትም ዛሬም ተመሳሳይ ስሕተት የምንሠራ ፍጥረት ከሆንን የሴልም በሉት የትል ስብስብ የሆነችው ሥጋችን ፈቃድም እንደልቡ የሚሠለጥንብን ከሆነ አካባቢያችንን አሠልጥነናል እንጂ እኛ ሠልጥነናል ብሎ ለመናገር የሚቻል አይመስለኝም፡፡

[iii] ያኔ የአማርኛ ሙሾ አውራጅ ከግሪክ ከተሞች በአንዷ ብትኖር ኖሮ
ሟቹ አባትህ
ገዳይዋ እናትህ
ሐዘንህ ቅጥ አጣ
          ከቤትህ አልወጣ፡፡           ብላ ልቡ እስኪፈርጥ ታስለቅሰው ነበረ፡፡

1 comment:

  1. We, humans, are full of choices: we can chose to do either good or evil. In the case of a curse befalling a person (of a choice he has not made)no matter how difficult it may seem, there is, yet, a way to find a way out to restoration and discovery of a descent life than subduing one's self to eternal damnation . We must open our very self to seek wisdom by abstaining ourselves from doing wrong because it's written that:''Wisdom will never enter the soul of a wrong-doer, nor dwell in a body enslaved to sin''Wisdom 1:4. Moreover, through our acts of penance and prayer we may seek eternal salvation. Well, Mr., I have learn something from what you have posted on the Greek Mythology. We must not blame any one for what's going on with our lives. We must face our demons. no doubt we would be able to defeat him with the power bestowed upon us from the Lord. If God is with us who can be against us?
    One more verse from the book of Wisdom :
    Do not court death by the errors of your ways, nor invite destruction through the work of your hands.For God did not make Death, he takes no pleasure in destroying the living.(1:12-13)

    ReplyDelete