Saturday, January 1, 2011

ልደተ እግዚእ


ምድረ ፍልስጥኤም እንደ ሌሎቹ የመካከለኛው ምስራቅ፣ የሰሜን አፍሪካና የታናሸ እስያ አገሮች በሮም ቅኝ ግዛት ሥር ነበረች፡፡ በውስጧ ነበሩ ሕዝቦችም የተከፋፈለ የሃይማኖትና የፖለቲካ ቡድን ነበራቸው፡፡ ከነዚህም ዋናዎቹ የፈሪሳውያንና የሰዱቃውያን ቡድኖች ነበሩ፡፡ የሰዱቃውያን ቡድን የሀብታሞችና የካህናት ቡድን ነው፡፡ ይህ ቡድን ለባህል፣ ለሥነ ሥርዓትና ና ለሃይማኖት ግድ የሌለው፣ ክኝ ገዥዎች ጋር ተስማምቶ በነሱ ሥልጣኔ መጠቀምን ብቻ የሚፈልግ ቡድን ነበር፡፡ ከሃይማኖት መጻሕፍትም የሙሴን ሕግ ብቻ እንጂ የነቢያትን ትንቢትና ሌሎችንም የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት አይቀበሉም ነበር፡፡ የሙታንን ትንሣኤና የመሢሕንም መምጣት አያምኑም ነበር፤ ሌላው ቡድን የፈሪሳውያን ቡድን ነው፡፡ ፈሪሳዊ “ፓራሽ” ከሚለው የዕብራይስጥ ቃል የወጣ ነው ትርጉሙም “የተለየ” ማለት ነው፡፡ እነዚህ ፈሪሳውያን ምንም የቅኝ አገዛዝ ቀንበር መላልሶ ቢያደቃቸውም ባህልና ልምዳችን አይነካ፤ በሃይማኖትም የሙሴን ሕግና የነቢያትን መጻሕፍት የምንጠብቅ እኛ ብቻ ነን ባዮች ነበሩ፡፡ ስለዚህ ከአይሁድ ዘር ውጭ ከሆነ ማንኛውም ጎሳና ዘር ጋር በባህልና በሥልጣኔ መቀራረቡን እንደመርከስና ሕግን እንደመተላለፍ ይቆጥሩት ነበር፡፡ የመሲሕንም መምጣ ነቅተውና ተግተው ይጠባበቁ ነበር፡፡ ለዚህም ዋናው ምክንያቸው ሀገራቸው ፍልስጥኤምን ከሮምግዛት ነጻ የማውጣት የቆየ ጉጉት ስላላቸው ነው፡፡

እንደነሱ አስተሳሰብ መሲሕ ሲመጣ የጦር ኃል አቋቁሞ ራሱ የጦር መሪ በመሆን የሮማን የቅኝ ግዛት ቀንበር አውልቆ ጥሎ የዳዊትን ቤተ መንግሥት የሚያድስ መሲሕ ይጠባበቁ ነበር ማለት ነው፡፡ ምንም እንኳ ከትንሣኤ በኋላ ሥጋዊ ኑሮ አለ ብለው ቢያምኑም ትንሣኤ ሙትን መኖሩን ያውቁ ነበር፡፡ ፈሪሳውያን በዕለታዊ ኑሯቸው ብዙ ሀብት የሌላቸውና በዕውቀትም መጠነኞች ነበሩ፡፡ መሲሕ መጥቶ የጦር ኃይል አቋቁሞ በጦር ኃይል ፍልስጤምን ነጻ ያወጣል የሚለውን የፈሪሳውያን እምነትና ተስፋ በመቃወም ሌላ ንዑስ ቡድን ከፈሪሳውያን ተከፍለው በሙት ባሕር አካባቢ ገዳም መሥርተው ይኖሩ ነበር፡፡ የእነሱም ዓላማቸው እንደ ፈሪሳውያ መሲሕን መጠበቅ ነው፡፡ ኤሤይ በመባል የሚታወቁት እነዚሁ ክፍሎች ከፈሪሳውያ የሚለዩት ፈሪሳውያን በጦር ኃይል ነጻ እንወጣለን ሲሉ ኤሤይ የሚባሉት ደግሞ በተአምራት በእግዚአብሔር ኃይል ፍልስጥኤም ነጻ ትወጣለች ብለው ያምኑ ነበር፡፡  በቤተልሔም በስተደቡብ ልዩ ሰሙ ኩምራን በሚባል ቦታ የሚኖሩ እነዚህ ሰዎች መጻሕፍትን በመጻፍ ጸሎትን በማድረስ ብዙ ጊዜ ቆይተዋል፡፡ ኤሴዎችና ፈሪሳውያ ባንድ አንድ ሐሳብ ቢለያዩም መሲሕ መምጣቱንና የተወሰኑ ምርጥ ጎሳዎችን ነጻ እንደሚያወጣ ዓለማቀፋዊ መሲሐዊ መንግሥት እንደሚያቋቁምና እነሱም መንግሥቱ ባለሟች እንደሚሆኑ ሁለቱም ቡድኖች ያምኑ ነበር፡፡ በእስራኤል የሃይማኖትና የነገድ ቤተሰብ ውስጥ ይህ ልዩነት ተፈጥሮ መከራቸውን ሲያዩ በፍልስጥኤምና ከፍልስጥኤም ውጭ የነበረው የሮማ መንግሥት ፖለቲካ ደግሞ ከቅኝ ግዛቱ ስፋት የተነሣ ያነገንግ ነበር፡፡ የነጻ አውጭ ግንባሮች በየጊዜው የሚጥሉትን አደጋና ግጭት ለመቆጣጠር እንዲያመች በየጊዜው የሕዝብ ቆጠራ እንዲደረግ ታዞ ነበር፡፡ ሕዝቡ በጠቅላላ ገበሬውም ሆነ ነጋዴው የመንግሥም ባለሥልጣን በሚሠራው ሥራ ሁሉ ባለ ጸጋ ስለነበር የሮም ግዛት ተወዳዳሪ የሌላት ታላቅ አገር ነበረች፡፡ ታዲያ ምን ያደርጋል እነዚህ ሁሉ ሀብታት ለሕዝቡ ደስታንና ውስጣዊ ዕረፍትን ሊያስገኙለት አልቻሉም፡፡ ሁልጊዜ በአካባቢው ከሚሰማው የሽብራ የሁከት ድምጽ የተነሣ ባልታሰበ ቀን እንደመሰሳለን የሚል ቀቢጸ ተስፋ ገዝቶት ነበር፤ ያመልኳቸው ከነበሩ ጣዖታትም አንዳችም የተስፋ ድምጽ አልነበረም፡፡ በቀቢጸ ተስፋ ባሕር ውስጥ ገብቶ የሚማቅቀውና መውጣትም የተሳነው አማኛቸውን ሊያረጋጉት አልቻሉም፡፡ ዳዊት እንደተናገረው ዓይን እያላቸው የማያዩ፣ ጆሮ እያላቸው የማይሰሙ፣ እጅ እያላቸው የማይዳስሱ፣ አፍ እያላቸው የማይናገሩ፣ እግር እያላቸው የማይሄዱ ግዑዛን ናቸውና፡፡ ከዚህም የተነሣ ማለት የሚያመልኳው ጣዖታት ሊረዷውና ሊያረጋጓቸው ስላልቻሉ ሕዝቡ “አማልክቶቻችን የዋኃና ግድ የለሾች ናቸው” እያለ በጣዖታቱ ይዘብት ነበር፡፡ የሰው ልጅ ሥልጣኔም በክፋትና በደግነት መካከል ያለውን ልዩነት ለማመልከት አልቻለም፡፡

በዚህ አኳኋን ስለሰው ልጅ የወደፊት ዕድል ምንም የተስፋ ጭላንጭል አልነበረም፡፡

ሰው በተፈጥሮው ከወዴት መጣሁ? ወዴትስ ነው የምሄደው? ብሎ ራሱን በራሱ የመጠየቅና የመመርመር ስጦታ ያለው ባለ አእምሮ ፍጡር ስለሆነ እነዚህ ጥያቄዎች ሁል ጊዜም ከፊቱ ይደቀኑበታል፡፡ ነገር ግን ለነዚህ ጥያቄዎች ከውስጥ ከራሱም ሆነ ከውጭ ከሌላ አጥጋቢ መልስ ስላላገኘ ከላይ   ንደገለጥነው የደስታን ኑሮ ጣዕሙንና ምሥጢሩን ሊያውቀው አልቻለም፡፡ በሮም ቅኝ ግዛት ውስጥ የሚኖሩ ሁሉ በዚህ ሁኔታ በቀቢጸ ተስፋ ስለተሞሉ እነርሱም ሆኑ ሥርዓተ ማኅበራቸው ጠባቂ እንደሌለው መንጋ ወይም ቀዛፊ ሊቀ ሐመር (ካፒቴን) እንደሌለው መርከብ አቅጣጫው የማይታወቅ ሆነ፡፡ ሕዝቡን ለማስደሰት በሮም የቴያትር ሰገነት ላይ የሚቀርበው የጨዋታ ዓይነትም እንኳ ደም መፋሰስና መደባደብ ሰስለነበር በጨለማ ላይ የዛፍና የገደል ጥላ ሲጨመር ጨለማው እንደሚጸና ሰቀቀኑን አባብሶት ነበር፡፡ ሀብታሙ በሀብቱ ደስታን ለመሸመት አልሆንለት ብሎ ሲጨነቅ፣ ሲጠበብ በዝቅተኛው ሕዝብ ዘንድ ደግሞ ዕጓለማውታንና መበለታትን ወዴት ወደቃችሁ የሚላቸው አልነበረም፡፡ በሽተኞችና ረሃብተኞች ጥርኝ ጥሬ፣ ኩባያ ውኃ የሚላቸው አጥተው በረሀብ ይተላለቁ ነበር፡፡ ሲሞቱም ያውሬ ራት እንጂ የሚቀብራቸው አልነበረም፡፡ ባጠቃላይ ፍርድ ተጓደለ ድሀ ተበደለ የሚል ታዛቢ ተመልካች የሌለበት የአስረሽ ምቺውና የብላ ተባላ  ዘመን ነበር፡፡ “የሰው አውሬው ሰው ነው” (homo homini Lupus est) የሮማውያን ተረት የተፈጸመው በዚህ ጊዜ ነበር፡፡



እነ አውግስጦስ ቄሣር የሰላም እመቤት ብለው የሰየሟት ወይም ራሷን ሰላም ብለው የጠሯት ፓክስ ሮማና ፍቅርና ሰላምን አላስገኘችላቸውምና ይህ ሁሉ የሁከትና የሽብር ጥላ ባንዣበበት ወራት የቤተክርስቲያን መሠረት፣ የአሕዛብ ብርሃን፣ የእስራኤል ዘነፍስ ክብር መድኅነ ዓለም በሮም ቅኝ ግዛት ሥር በነበረች ክፍል ፍልስጥኤም ልዩ ስሟ ቤተልሔም በምትባል በይሁዳ ክፍል ተወለደ፡፡

በተወለደም ጊዜ ትንቢት ያልተነገረላቸው፣ ሱባኤ ያልተቆጠረላቸው ከአሕዛብ ወገን የሆኑ ሰብአሰገል መድኅን መወለዱን አውቀው ከምድረ አሕዛብ ወርቅ፣ ዕጣን፣ ከርቤ ይዘውለት መጡ ገበሩለትም፡፡ የመወለዱም ዓላማ የሰውን ዘር ከጠፋበት ለመፈለግ፣ ወደፊተኛው ክብሩ ለመመለስ፣ ስለ ጽድቅ ለማስተማርና ለመመስከር ነው፡፡ በመድኅን መወለድ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ መላእክትም ተደስተዋል፡፡ “በሰማይ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይገባዋል በምድርም ሰላም” እያሉ ዘምረዋል፡፡ ይህ ሁሉ በአንድ ወገን የነበረው የአቀባበል ሥነ ሥርዓት ሲሆን በሌላ በኩል የነበረው የአቀባበል ሥነ ሥርዓት ደግሞ የሚያሳዝን ነበር፡፡ ለምሳሌ “ሥርዓተ ኦሪትን፣ ትንቢተ ነቢያትን በሚገባ እንከታተላለን፡፡” ይሉ የነበሩ ፈሪሳውያን ክንዱ የሚያደቅ፣ ግርማው የሚንቀጠቅጥ፣ ሮማውያንን አባሮ አገራቸውን ነጻ የሚያወጣ ኃይለኛ መሲሕ ሲጠባበቁ ይኖሩ እንደነበር ተገልጧል፡፡ የኛ መሲሕ ክርስቶስ ግን እነሱ እንደጠበቁት ሁኖ አልመጣም፡፡ እንዲያውም ከላይ እንደተገለጠው ዘመኑ የሁከትና የሽብር ስለነበር አውግስጦስ ቄሣር በየጊዜው ዜጎቹን ያስቆጥር ነበርና ድንግል ማርያም ለመመዝገብ፣ ለመቆጠር አገር ጥላ ስንቋን ቋጥራ በሔደችበት ቦታ መጠጊያ እንኳ በሌለበት በተጨናነቀ አካባቢ ከብቶች በሚያድሩበት ቦታ መሲሕ ተወለደ፡፡ በዚያም የሀብታሞች ነገሥታት ልጆች ሲወለዱ በሚነጠፍላቸው ወርቀ ዘቦ ግምጃ ሳይሆን ሉቃስ እንደ ነገረን እናቱ በጨርቅ ጠቀለለችው፡፡                       
   

ይህን ጽሑፍ የወሰድሁት የሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የነበሩት አቡነ ጎርጎርዮስ “የቤተክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ” ብለው ካሳተሙት መጽሐፍ ላይ ነው፡፡  

በረከታቸው ይደርብን! 

No comments:

Post a Comment